እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
ብዙ ሰዎች ቁሳዊ ሀብት በማካበት ደስታ ማግኘት የሚቻል ይመስላቸዋል። አንተስ ምን ይመስልሃል? ቁሳዊ ነገሮች ደስታ እንድናገኝ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ባይካድም ለደስታ ዋስትና አይሆኑም፤ ደግሞም ተንደላቆ መኖር እምነታችን እንዲጠናከር ወይም በመንፈሳዊ የጎደሉን ነገሮች እንዲሟሉልን አያደርግም።
ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሏል:- “በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው። መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና።” (ማቴዎስ 5:3 NW ) በተጨማሪም ኢየሱስ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና፤ ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ብሏል።— ሉቃስ 12:15
ብዙዎች በጾታ ብልግና እና በሌሎች ‘የሥጋ ሥራዎች’ በመሳተፍ ደስታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ገላትያ 5:19-21) ሆኖም ለሥጋዊ ተድላ መሯሯጥ እውነተኛና ዘላቂ ደስታ አያስገኝም። እንዲያውም እንዲህ ያሉትን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ሰዎች የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።— 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10
ሌሎች ደግሞ ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከፍ ለማድረግ በመጣር ደስታ ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ በውስጣዊ ማንነታቸው ላይ አተኩረዋል። ቤተ መጻሕፍትና የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች ራስን በራስ ማስተማር በሚቻልባቸው መጻሕፍት የተሞሉ ቢሆንም እነዚህ ጽሑፎች ለሰዎች ዘላቂ ደስታ አላመጡላቸውም። ታዲያ እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?
እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ከፈለግን በተፈጥሯችን ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን ፍላጎት መገንዘብ አለብን። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው” ብሏል። እርግጥ ይህን ፍላጎታችንን ተረድተን ምንም ሳናደርግ ብንቀር የምናገኘው ጥቅም አይኖርም። ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ የማራቶን ሯጭ ከውድድሩ በኋላ የውኃ ጥማቱን ሳያረካ ቢቀር ምን ይደርስበታል? ወዲያውኑ በሰውነቱ ውስጥ ያለው ፈሳሽ አልቆ ሌሎች ከባድ ችግሮች አያጋጥሙትም? በተመሳሳይም የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎታችንን ሳናሟላ ብንቀር የኋላ ኋላ በመንፈሳዊ እንዳከማለን። ይህ ደግሞ ደስታ ማጣት ያስከትላል።
ኢየሱስ በመንፈሳዊ የጎደለውን ነገር ሙሉ በሙሉ በመገንዘቡ ዘወትር የአምላክ ቃልን ያጠና እና በእሱ ላይ ያሰላስል ነበር። በቀላሉ ከቅዱሳን ጽሑፎች አንዳንድ ክፍሎችን ፈልጎ ማግኘትና ማንበብ ይችል የነበረ ሲሆን ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ አስተምሯል። (ሉቃስ 4:16-21፤ ከኤፌሶን 4:20, 21 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ኢየሱስ የሰማይ አባቱን ፈቃድ ማድረግ ምግብ ከመብላት ጋር እንደሚመሳሰል ተናግሯል። የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከፍተኛ ደስታ አምጥቶለታል።— ዮሐንስ 4:34
አዎን፣ ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት እውነተኛ ደስታ መጨበጥ አይቻልም፤ የውዳቂውን ሥጋ ፍላጎት ማስተናገድም ቢሆን ደስታ አያስገኝም። እውነተኛ ደስታ የልብ ሁኔታ ነው፤ በእውነተኛ እምነትና ከይሖዋ አምላክ ጋር ባለን ጥሩ ዝምድና ላይ የተመሠረተ ነው። እንግዲያውስ መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው” ብሎ መዘመሩ የተገባ ነው።— መዝሙር 144:15ለ NW
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እምነት እና ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረትህ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልሃል