የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | ሚያዝያ 15
    • የአንባብያን ጥያቄዎች

      አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ከሃይማኖታዊ ሕንጻዎችና ንብረቶች ጋር ግንኙነት ያለው ሥራ አግኝተዋል። እንዲህ ዓይነቱን ሥራ በተመለከተ ቅዱስ ጽሑፉ ምን ይላል?

      አንድ ሰው ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር የማሟላት ኃላፊነት እንዳለበት የሚያጎላውን 1 ጢሞቴዎስ 5:​8ን ከልብ በሥራ ለማዋል የሚፈልጉ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው አሳሳቢ ጉዳይ ሊያጋጥማቸው ይችላል። እርግጥ፣ ክርስቲያኖች ከላይ የተጠቀሰውን ምክር በሥራ ማዋል ቢኖርባቸውም የሥራውን ባሕርይ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ የተገኘውን ዓለማዊ ሥራ ሁሉ እንዲይዙ ሰበብ አይሆናቸውም። ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ ለሚጠቁሙ ሌሎች ነገሮች ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ቤተሰቡን ለመርዳት ያለው ፍላጎት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጾታ ብልግና ወይም ስለ ግድያ የሚናገረውን ነገር እንዲጥስ ምክንያት አይሆነውም። (ከዘፍጥረት 39:​4-9፤ ኢሳይያስ 2:​4፤ ዮሐንስ 17:​14, 16 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ክርስቲያኖች ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲወጡ ከተሰጣቸው ትእዛዝ ጋር ተስማምተው መኖር አለባቸው።​—⁠ራእይ 18:​4, 5

      በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች በርካታ የሥራ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። እነዚህን ዓይነት ሥራዎች መሥራት ይቻላል እነዚያን ደግሞ መሥራት አይቻልም እያልን በመዘርዘር ስለ እያንዳንዱ ሥራ ደንብ ለማውጣት መሞከር ትርጉም የለሽ ከመሆኑም ሌላ እንደዚያ የማድረግ ሥልጣን የለንም። (2 ቆሮንቶስ 1:​24) ሆኖም ክርስቲያኖች ሥራን በሚመለከት የግል ውሳኔዎች ሲያደርጉ ግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮችን እስቲ እንመልከት። እነዚህ ነጥቦች በሐምሌ 15, 1982 መጠበቂያ ግንብ ላይ አምላክ በሰጠን ሕሊና መጠቀምን አስመልክቶ በወጣ ርዕስ በአጭሩ ተገልጸው ነበር። ርዕሱ ያካተተው አንድ ሳጥን ሁለት ጥያቄዎች ካነሳ በኋላ ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች ጉዳዮችን ዘርዝሯል።

      የመጀመሪያው ቁልፍ ጥያቄ የሚከተለው ነው:- ሰብዓዊ ሥራው ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ የተወገዘ ነውን? መጠበቂያ ግንቡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ስርቆትን፣ በደም አላግባብ መጠቀምንና የጣዖት አምልኮን እንደሆነ ጠቅሷል። አንድ ክርስቲያን ከላይ የተጠቀሱትን የመሳሰሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ተግባሮች ከሚያስፋፋ ዓለማዊ ሥራ መራቅ አለበት።

      ሁለተኛው ጥያቄ የሚከተለው ነው:- አንድ ክርስቲያን ይህን ሥራ መሥራቱ ከተወገዘ ተግባር ጋር ተባባሪ ያደርገዋልን? ቁማር ቤት፣ በጽንስ ማስወረጃ ክሊኒክ ወይም ዝሙት አዳሪ ቤት ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ተግባር ተባባሪ እንደሆነ ግልጽ ነው። ምንም እንኳ በየዕለቱ በዚያ የሚያከናውነው ሥራ ወለል ማጽዳት ወይም የስልክ ጥሪ መቀበል ብቻ ቢሆንም የአምላክ ቃል ለሚያወግዘው ተግባር የበኩሉን ድርሻ እያበረከተ ነው።

      የሥራ ምርጫን በሚመለከት ውሳኔ ማድረግ የነበረባቸው በርካታ ክርስቲያኖች እነዚህን ጥያቄዎች መመርመራቸው የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል።

      ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች በመነሳት በእውነተኛ አምልኮ የሚካፈል አንድ ሰው በቀጥታ የአንድ የሐሰት ሃይማኖታዊ ድርጅት ተቀጣሪ በመሆን በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማይሠራበትን ምክንያት መረዳት ይችላል። ራእይ 18:​4 “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” የሚል ትእዛዝ ይዟል። አንድ ሰው የሐሰት አምልኮን የሚያስተምር የአንድ ሃይማኖት ቋሚ ተቀጣሪ ከሆነ በታላቂቱ ባቢሎን ተግባሮችና ኃጢአቶች ተካፋይ ይሆናል። ተቀጣሪው አትክልተኛ፣ የጽዳት፣ የጥገና ወይም የሒሳብ ሠራተኛ ቢሆንም የሚያከናውነው ሥራ እውነተኛውን አምልኮ የሚቃረን አምልኮን ለማራመድ የሚያገለግል ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ተቀጣሪ ቤተ ክርስቲያኑን ለማስዋብ፣ ለማደስ ወይም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴውን ማካሄድ እንዲችል በዚያ ሲሠራ የሚያዩ ሰዎች ግለሰቡ የሃይማኖቱ አባል እንደሆነ አድርገው ማሰባቸው አይቀርም።

      ሆኖም የአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም ሃይማኖታዊ ድርጅት ቋሚ ተቀጣሪ ስላልሆነ ሰው ምን ለማለት ይቻላል? ምናልባት በቤተ ክርስቲያኑ ምድር ቤት ውስጥ የተሰበረ የውኃ ቧንቧ በአፋጣኝ እንዲጠግን ተጠርቶ ይሆናል። ይህ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኑን ጣሪያ ቁርጥ ክዳን ለማልበስ ወይም ቅዝቃዜ መከላከያ ለማስገባት የወጣ ኮንትራትን በጨረታ ለማሸነፍ ከመወዳደር የተለየ አይደለም?

      አሁንም በርካታ የተለያዩ ሁኔታዎችን ማሰብ ይቻላል። በመሆኑም መጠበቂያ ግንቡ የገለጻቸውን አምስት ተጨማሪ ነጥቦች እስቲ እንመልከት:-

      1. ሥራው ከቅዱስ ጽሑፉ አንጻር ሲታይ ምንም አጠያያቂነት የሌለው ሰብዓዊ አገልግሎት ነውን? አንድን ፖስተኛ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ደብዳቤ በሚያደርስበት አካባቢ አገልግሎት ከሚሰጣቸው ሕንጻዎች አንዱ ቤተ ክርስቲያን ወይም ጽንስ ማስወረጃ ክሊኒክ ቢሆን በዚህ ሥራ መሰማራቱ አንድን የተወገዘ ተግባር ደግፏል ሊያሰኘው አይችልም። አምላክ ያዘጋጀው የፀሐይ ብርሃን አንድን ቤተ ክርስቲያን ወይም ጽንስ ማስወረጃ ክሊኒክን ጨምሮ ሁሉም ሕንጻዎች ብርሃን እንዲያገኙ ያስችላል። (ሥራ 14:​16, 17) ፖስተኛ የሆነ አንድ ክርስቲያን በየዕለቱ ለሁሉም ሰዎች ሰብዓዊ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ሊያስብ ይችላል። ድንገተኛ አደጋ ተፈጥሮ አገልግሎት እንዲሰጥ የተጠራ የአንድ ወንድም ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያክል ቧንቧ ሠራተኛ የሆነ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የፈነዳ ቧንቧ እንዲጠግን ሊጠራ ወይም የአንቡላንስ አገልግሎት የሚሰጥ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቅዳሴ በሚካሄድበት ወቅት ድንገት የታመመ ሰው እንዲረዳ ሊጠራ ይችላል። ይህን ተግባር ድንገተኛ እንደሆነ ሰብአዊ እርዳታ አድርጎ ሊቆጥረው ይችል ይሆናል።

      2. ሰውየው በሥራው ላይ ያለው የመወሰን ሥልጣኑ ምን ያህል ነው? ባለሱቅ የሆነ አንድ ክርስቲያን ምስሎች፣ መናፍስታዊ ክታቦች፣ ሲጋራ ወይም ከደም የተሠራ ቋሊማ ሱቁ ውስጥ አስገብቶ ለመሸጥ እንደማይስማማ የታወቀ ነው። ባለቤት እንደመሆኑ መጠን ሁሉ በእሱ ቁጥጥር ሥር ነው። ሰዎች ሲጋራ ወይም ምስሎች በመሸጥ እንዲያተርፍ ሊገፋፉት ቢችሉም እሱ ከቅዱስ ጽሑፋዊ እምነቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳል። በሌላ በኩል በአንድ ትልቅ ግሮሰሪ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ አንድ ክርስቲያን ገንዘብ ተቀባይ፣ የጽዳት ሠራተኛ ወይም ሒሳብ ያዥ ሆኖ እንዲሠራ ሊመደብ ይችላል። በግሮሰሪ ውስጥ ከሚሸጡት ነገሮች መካከል እርሱ የማይስማማባቸው ሸቀጦች (ሲጋራ ወይም ለሃይማኖታዊ በዓል የሚውሉ ነገሮች) ሊኖሩ ቢችሉም ግሮሰሪው የሚያስገባቸውንና የሚሸጣቸውን ዕቃዎች በተመለከተ የመወሰን ሥልጣን የለውም።a (ከሉቃስ 7:​8፤ 17:​7, 8 ጋር አወዳድር።) ይህ ጉዳይ ቀጥሎ ከተጠቀሰው ነጥብ ጋር ይዛመዳል።

      3. ሰውየው የሚያበረክተው ድርሻ ምን ያህል ነው? ስለ ሱቅ ወዳነሳነው ምሳሌ እስቲ እንመለስ። ምናልባት በገንዘብ ተቀባይነት ወይም ዕቃዎችን በመደርደር እንዲሠራ የተመደበ አንድ ተቀጣሪ ሲጋራ ወይም ሃይማኖታዊ ዕቃዎች የሚያጋጥሙት አልፎ አልፎ ብቻ ይሆናል፤ ማለትም ይህ የአጠቃላይ ሥራው አነስተኛ ክፍል ነው። ሆኖም ይህ ጉዳይ በዚያው ሱቅ ውስጥ ተቀጥሮ ከሚሠራ ሲጋራ እንዲሸጥ ከተመደበ ሰው ሁኔታ ፍጹም የተለየ ነው! ሲጋራ የሚሸጠው ሰው ነጋ ጠባ የሚሠራው ሥራ ክርስቲያናዊ እምነትን በሚጻረር ነገር ላይ ያተኮረ ነው። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) ይህ ምሳሌ ሥራን በሚመለከት የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሰውዬው በሥራው ውስጥ የሚያበረክተውን ድርሻ ወይም ከሥራው ጋር ያለውን ቁርኝት ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈለገበትን ምክንያት ያሳያል።

      4. የክፍያው ምንጭ ከየት ነው? ወይም ሥራው የሚካሄድበት ቦታ የት ነው? ሁለት ሁኔታዎችን ተመልከት። አንድ የጽንስ ማስወረጃ ክሊኒክ አካባቢው ለዓይን ማራኪ እንዲሆን በማሰብ በደጁ አጠገብ ያሉትን መንገዶች ለማጽዳት አንድ ሰው ከፍሎ ለማሠራት ይወስናል። ይህ ተከፍሎት የሚያጸዳ ሰው ምንም እንኳ ገንዘብ የሚከፍለው ጽንስ ማስወረጃው ክሊኒክ ቢሆንም የእርሱ ሥራ ክሊኒኩ ውስጥ አይደለም። ደግሞ ሌሎች ሰዎችም ቢሆኑ ቀኑን ሙሉ እዚያ አያዩትም። ከዚህ ይልቅ ከፋዩ ማንም ይሁን ማን ሰዎች የሚያዩት ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ምንም የማይጋጭ ሕዝባዊ አገልግሎት ሲሰጥ ነው። አሁን ደግሞ የዚህን ተቃራኒ እንመልከት። ዝሙት አዳሪነት በሕግ በተፈቀደበት አገር ውስጥ አንዲት ነርስ በየዝሙት አዳሪ ቤቶች እየሄደች በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመቀነስ የታቀደ የጤና ምርመራ እንድታካሂድ ጤና ጣቢያው ከፍሎ ያሠራታል። የጤና ጣቢያው ደሞዝተኛ ብትሆንም እንኳ የምታከናውነው ሥራ የጾታ ብልግናው ይበልጥ አስተማማኝና ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ በዝሙት አዳሪ ቤቶች ውስጥ የሚካሄድ ነው። እነዚህ ምሳሌዎች የክፍያው ምንጭና የሥራው ቦታ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ለምን እንደሆነ ያሳያሉ።

      5. በዚህ ሥራ መሠማራቱ ምን ተጽእኖ አለው፤ ሥራው የሰውየውን ሕሊና ያጎድፋል ወይም ሌሎችን ያደናቅፋል? የራሳችንንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ሕሊና ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን። ምንም እንኳ አንድ ሥራ (የሥራውን ቦታና የክፍያውን ምንጭ ጨምሮ) በአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም አንድ ግለሰብ ግን ሕሊናውን የሚረብሽ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የተወልን ሐዋርያው ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፣ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና” ሲል ተናግሯል። (ዕብራውያን 13:​18) ሕሊናችንን የሚረብሽ ሥራ ከመሥራት መራቅ አለብን፤ ይሁን እንጂ ከእኛ የተለየ ሕሊና ያላቸውን ሰዎች መንቀፍም የለብንም። በተቃራኒው ደግሞ አንድ ክርስቲያን አንድን ዓይነት ሥራ መሥራቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደማይቃረን ቢያውቅም እንኳ በጉባኤውም ሆነ በአካባቢው ያሉ የብዙ ሰዎችን ሕሊና እንደሚረብሽ ይገነዘብ ይሆናል። የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ትክክለኛውን ዝንባሌ ያንጸባርቃሉ:- “አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም። ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​3, 4

      አሁን ለአንድ የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ አዲስ መስተዋቶችን መግጠም፣ ምንጣፎቹን ማጽዳት ወይም እሳት ማንደጃውን መጠገን የመሳሰሉትን ሥራዎች ወደሚመለከተው ዋነኛ ጥያቄ እስቲ እንመለስ። ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ከጉዳዩ ጋር ምን ዝምድና አላቸው?

      የውሳኔ ሰጪውን አካል ጉዳይ አስታውስ። ክርስቲያኑ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚያከናውነውን ይህ ዓይነቱን ሥራ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል መወሰን የሚችል ባለቤት ወይም ሥራ አስኪያጅ ነው? እንዲህ ዓይነት ሥልጣን ያለው ክርስቲያን አንድ ሃይማኖት የሐሰት አምልኮን እንዲያስፋፋ ለመርዳት ለአንድ ዓይነት ሥራ በመጫረት ወይም ኮንትራት በመውሰድ ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር ተካፋይ መሆን ይፈልጋል? ይህ ነገር አንድ ሰው በራሱ ሱቅ ውስጥ ሲጋራ ወይም ምስሎች ለመሸጥ ከመወሰኑ ጋር ሊመሳሰል አይችልምን?​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​14-16

      አንድ ክርስቲያን ተቀባይነት ያላቸውን የሥራ ዓይነቶች የመወሰን መብት የሌለው ተራ ተቀጣሪ ከሆነ የሥራው ቦታና በሥራው ላይ ያለው ተሳትፎ መጠን የመሳሰሉ ሌሎች ጉዳዮች ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው። ተቀጣሪው የታዘዘው ወንበሮችን እንዲያደርስ ወይም ለአንድ ልዩ ዝግጅት አዳዲስ ወንበሮችን በቦታ በቦታቸው እንዲያስቀምጥ አሊያም በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሳ እሳት ወደ ሌላ ከመዛመቱ በፊት ማጥፋትን የመሰለ የእሳት አደጋ ሠራተኞች የሚያከናውኑት ዓይነት ሰብዓዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ብቻ ነውን? ይህ ሥራ በአንድ የንግድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ቤተ ክርስቲያኑን ቀለም በመቀባት ረጅም ጊዜ ከሚያሳልፍ ወይም ቤተ ክርስቲያኑን ለማሳመር በቋሚነት በአትክልተኝነት ከሚሠራ ሰው የተለየ እንደሆነ ብዙዎች ይገነዘባሉ። አንድ ክርስቲያን በዚህ መልኩ በቋሚነት ወይም ለረጅም ጊዜ መታየቱ ሌሎች ሰዎች ይህ ክርስቲያን አልደግፈውም ከሚለው ሃይማኖት ጋር ቁርኝት እንዳለው አድርገው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው አልፎ ተርፎም ሊያሰናክላቸው ይችላል።​—⁠ማቴዎስ 13:​41፤ 18:​6, 7

      ሥራን በሚመለከት አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ጉዳዮችን ተመልክተናል። እነዚህ ጉዳዮች የሐሰት ሃይማኖትን በሚመለከት በአንድ የተወሰነ ጥያቄ ዙሪያ የቀረቡ ናቸው። ይሁን እንጂ ነጥቦቹ ከሌሎች ዓይነት ሥራዎችም ጋር በተያያዘ በተመሳሳይ መንገድ ሊጤኑ ይችላሉ። በማንኛውም ሁኔታ ሥር ጉዳዩን የሚመለከቱ የተወሰኑ ምናልባትም ለየት ያሉ ነገሮችን ግምት ውስጥ በማስገባት በጸሎት ሊታሰብበት ይገባል። ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች በርካታ ቅን ክርስቲያኖች በይሖዋ ፊት ትክክልና ቀና በሆነ መንገድ ለመሄድ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳዩ በእውቀት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን እንዲያደርጉ ረድተዋቸዋል።​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6፤ ኢሳይያስ 2:​3፤ ዕብራውያን 12:​12-14

      [የግርጌ ማስታወሻ]

      a ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነቱን ሥልጣን ማጤን አስፈልጓቸዋል። አንድ ታካሚ ሊወስዳቸው የሚገቡ መድኃኒቶችን ወይም ሊከተል የሚገባውን የሕክምና ሂደት በተመለከተ አንድ ሐኪም የመወሰን መብት ሊኖረው ይችል ይሆናል። ምንም እንኳ ታካሚው ባይቃወምም የመወሰን ሥልጣን ያለው ዶክተር የሆነ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እያወቀ ታካሚው ደም እንዲሰጠው ወይም ውርጃ እንዲፈጸም እንዴት ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል? በአንጻሩ ደግሞ ሆስፒታሉ ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራ አንዲት ነርስ ይህ ዓይነቱ ሥልጣን ላይኖራት ይችላል። የተለመደውን ተግባሯን ስታከናውን አንድ ዶክተር ለሆነ ዓላማ የደም ምርመራ እንድታደርግ ወይም ጽንስ ለማስወረድ የመጣችን ታካሚ እንድትረዳ ያዝዛት ይሆናል። በ2 ነገሥት 5:​17-19 ላይ ሰፍሮ ከሚገኘው ምሳሌ ጋር በሚስማማ መንገድ ደም እንዲሰጥ የማዘዝ ሥልጣን እስከሌላት ወይም ጽንስ ማስወረዱ እንዲፈጸም እስካላደረገች ድረስ ለታካሚው ሰብዓዊ አገልግሎቶችን መስጠት እንደምትችል ይሰማት ይሆናል። እርግጥ፣ አሁንም ቢሆን ‘በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መኖር’ እንድትችል ሕሊናዋን ግምት ውስጥ ማስገባት አለባት።​—⁠ሥራ 23:​1

  • ታስታውሳለህን?
    መጠበቂያ ግንብ—1999 | ሚያዝያ 15
    • ታስታውሳለህን?

      በቅርብ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? ከሆነ፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መመለስ ትችል እንደሆነ ተመልከት:-

      ◻ ጳውሎስ “ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች [“አምባሳደሮች፣” የ1980 ትርጉም] ነን” ሲል የተጠቀመበት መግለጫ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው? (2 ቆሮንቶስ 5:​20)

      በጥንት ዘመን አብዛኛውን ጊዜ አምባሳደሮች ይላኩ የነበረው ግጭት በሚፈጠርባቸው ወቅቶች ሲሆን በግጭቱ ምክንያት ጦርነት እንዳይነሳ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ይደራደሩ ነበር። (ሉቃስ 14:​31, 32) ኃጢአተኛው የሰው ዘር ዓለም ከአምላክ የራቀ በመሆኑ አምላክ ያቀረበውን የማስታረቂያ ሐሳብ ለሰዎች እያስታወቁ ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲመሠርቱ ለማሳሰብ የተቀቡ አምባሳደሮቹን ልኳል።​—⁠12/15 ገጽ 18

      ◻ የአብርሃምን እምነት ያጠናከሩለት አራት ነገሮች ምንድን ናቸው?

      አንደኛ፣ አምላክ የተናገረውን በመከተል በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት አሳይቷል (ዕብራውያን 11:​8)፤ ሁለተኛ፣ እምነቱ ከተስፋው ጋር በጣም የተቆራኘ ነበር (ሮሜ 4:​18)፤ ሦስተኛ፣ አብርሃም አዘውትሮ ከአምላክ ጋር ይነጋገር ነበር፤ እንዲሁም አራተኛ፣ አብርሃም የአምላክን መመሪያ በተከተለ ጊዜ ይሖዋ ድጋፍ ሰጥቶታል። ዛሬ እነዚሁ ነገሮች እምነታችንን ሊያጠናክሩልን ይችላሉ።​—⁠1/1 ገጽ 17, 18

      ◻ “ወደ ፈተናም አታግባን” የሚለው አባባል ምን ትርጉም ይዟል? (ማቴዎስ 6:​13)

      የእርሱን ትእዛዝ እንድንጥስ በምንፈተንበት ጊዜ አምላክ እንድንወድቅ እንዳይፈቅድ መለመናችን ነው። ይሖዋ ተሸንፈን ‘ለክፉው’ ለሰይጣን እጃችንን እንዳንሰጥ ሊመራን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 10:​13)—⁠1/15 ገጽ 14

      ◻ አንድ ሰው ለሠራው ኃጢአት የአምላክን ምሕረት ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?

      ለአምላክ ከመናዘዝ በተጨማሪ መጸጸትና “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ” ማፍራት ያስፈልጋል። (ሉቃስ 3:​8) የንስሐ መንፈስና የሠራነውን ስህተት ለማስተካከል ያለን ፍላጎት የክርስቲያን ሽማግሌዎችን መንፈሳዊ እርዳታ እንድንሻ ይገፋፋናል። (ያዕቆብ 5:​13-15)—⁠1/15 ገጽ 19

      ◻ ትሑት ለመሆን መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

      ትሑት ሰው ትዕግሥተኛና ቻይ ነው፤ እንዲሁም ከመጠን በላይ ስለ ራሱ አያስብም። ትሕትና እውነተኛ ወዳጆችን እንድታፈራ ያስችልሃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን በረከት ያስገኝልሃል። (ምሳሌ 22:​4)​—⁠2/1 ገጽ 7

      ◻ በኢየሱስ ሞትና በአዳም ሞት መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት ምንድን ነው?

      አዳም በፈጣሪው ላይ ያመፀው ሆን ብሎ ስለሆነ መሞቱ የሚገባው ነበር። (ዘፍጥረት 2:​16, 17) በአንጻሩ ግን ኢየሱስ ‘ምንም ኃጢአት ስላላደረገ’ በፍጹም ሞት አይገባውም ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:​22) ስለዚህ ኢየሱስ ሲሞት ኃጢአተኛው አዳም በሞተበት ጊዜ ያልነበረው ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ማለትም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ይዞ የመቀጠል መብት ነበረው። ይህም በመሆኑ የኢየሱስ ሞት የሰው ልጆችን በመቤዥት ረገድ መሥዋዕታዊ ዋጋ አለው።​—⁠2/15 ገጽ 15, 16

      ◻ በሕዝቅኤል ትንቢታዊ ራእይ ላይ የታየው ከተማ ምን ያመለክታል?

      ከተማው ቅዱስ ባልሆነ ሥፍራ መካከል የሚገኝ ስለሆነ ምድራዊ ነገር መሆን አለበት። ስለዚህ ከተማው ጻድቅ የሆነውን ምድራዊ ኅብረተሰብ የሚጠቅም ምድራዊ አስተዳደር የሚያመለክት ይመስላል።​—⁠3/1 ገጽ 18

      ◻ ኢየሱስ በ33 እዘአ የማለፍ በዓልን ሲያከብሩ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበው ለምንድን ነበር?

      ኢየሱስ እግር የማጠብ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መደንገጉ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያቱ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወንድሞቻቸውን ለማገልገል የትሕትናና የፈቃደኝነት መንፈስ እንዲያዳብሩ እየረዳቸው ነበር።​—⁠3/1 ገጽ 30

      ◻ ሌሎችን በምናስተምርበት ጊዜ ከተፈጥሮ ችሎታችን ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው?

      ተማሪዎቹ ሊኮርጁ የሚችሉት ያዳበርናቸውን ባሕርያትና መንፈሳዊ ልማዶቻችን ናቸው። (ሉቃስ 6:​40፤ 2 ጴጥሮስ 3:​11)—⁠3/15 ገጽ 11, 12

      ◻ የሕዝብ ተናጋሪዎች ጥቅስ የማንበብ ችሎታቸውን ማሻሻል የሚችሉት እንዴት ነው?

      በመለማመድ ነው። አዎን፣ ምንም ሳይደነቃቀፉ ማንበብ እስኪችሉ ድረስ ከፍ ባለ ድምፅ ደጋግሞ በማንበብ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡ በቴፕ ክር የሚገኝ ከሆነ አንባቢው የሚያጠብቅበትንና ድምፁን የሚለዋውጥበትን ቦታዎች ማዳመጡ እንዲሁም የስሞችና ያልተለመዱ ቃላት አጠራር እንዴት እንደሆነ ልብ ማለቱ ጥበብ ነው።​—⁠3/15 ገጽ 20

      ◻ አንድ ሰው ሲሞት ‘መንፈሱ ወደ አምላክ የሚመለሰው’ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? (መክብብ 12:​7 NW)

      መንፈሱ የሕይወት ኃይል ስለሆነ ‘ወደ እውነተኛው አምላክ ይመለሳል’ ሊባል የሚችለው ግለሰቡ ወደፊት በሕይወት ለመኖር ያለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ በአምላክ እጅ መሆኑን ነው። አንድ ሰው ወደ ሕይወት እንዲመለስ ለማድረግ መንፈሱን ወይም የሕይወት ኃይሉን መልሶ መስጠት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (መዝሙር 104:​30)—⁠4/1 ገጽ 17

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ