መጥፎ ድርጊትን እምቢ ለማለትየሚያስችል ጥንካሬ ማግኘት
“ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በነበርኩበት ጊዜ” ይላል ጢሞቴዎስ “በአንድ ሱቅ ውስጥ ተቀጥሬ እሠራ ስለነበር አንድ አብሮኝ የሚሠራ ልጅ ወደ ቤቱ እንድሄድ ጋበዘኝ። ወላጆቹ ራቅ ወዳለ ቦታ ስለሚሄዱ ሴቶችን እንደሚያመጣና ከእነርሱ ጋር የጾታ ግንኙነት ማድረግ እንደምንችል ነገረኝ።” ዛሬ ያሉ ብዙ ወጣቶች እንዲህ ያለውን ግብዣ ዓይናቸውን ሳያሹ ይቀበሉታል። ይሁን እንጂ የጢሞቴዎስ ምላሽ ምን ነበር? “ቤቱ እንደማልሄድና ክርስቲያናዊ ሕሊናዬ ስለማይፈቅድልኝ ካላገባኋት ሴት ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም እንደማልፈልግ ያለ አንዳች ማመንታት ገለጽሁለት።”
ጢሞቴዎስ እንቢተኝነቱን ሲገልጽ እዚያው የምትሠራ አንዲት ወጣት ሴት እያዳመጠችው እንደነበር አላስተዋለም። ከዚህ በኋላም በቅንነቱ የተማረከችው ይህቺ ወጣት በተደጋጋሚ ያቀረበችለትንም ግብዣ እምቢ ለማለት ተገድዷል። ይህንን በኋላ እንመለስበታለን።
ዛሬ በፈታኝ ሁኔታዎች መታጠራችን አዲስ ነገር አይደለም። ከ3,000 ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጄ ሆይ፣ ኃጢአተኞች ቢያባብሉህ እሺ አትበል። . . . ከጎዳናቸውም እግርህን ፈቀቅ አድርግ።” (ምሳሌ 1:10, 15) ይሖዋ ራሱ “ክፉውን ለማድረግ ብዙዎችን አትከተል” የሚል ትእዛዝ ለእስራኤል ብሔር ሰጥቶ ነበር። (ዘጸአት 23:2) አዎን፣ ለሌሎች ሰዎች የማይዋጥላቸው ቢሆንም መጥፎ የሆነ ነገር እንድንፈጽም የሚገጥመንን ፈተና ተቋቁመን እምቢ ማለት ይኖርብናል።
በተለይ ዛሬ እምቢ ማለት በጣም አስፈላጊ ነው
መጥፎ ድርጊት ላለመፈጸም እምቢ ማለት ቀላል ሆኖ ባያውቅም በተለይ ዛሬ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻ ቀን’ ብሎ በሚጠራው በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በመሆኑ ይበልጥ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በሚናገረው መሠረት ሰዎች በአጠቃላይ ተድላን የሚወዱና ዓመፀኞች እንዲሁም መንፈሳዊ ፍላጎትም ሆነ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና የሌላቸው ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አንድ የጄዝዊት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እንዲህ ብለዋል:- “በአንድ ወቅት የምንመራባቸው ባሕላዊ ደንቦች ነበሩን። ይሁን እንጂ እነርሱም ጥያቄ ተነሥቶባቸው ደካማ ወይም ዘመን ያለፈባቸው እንደሆኑ ተደርገው ተቆጥረዋል። ዛሬ ግን ጨርሶ የሥነ ምግባር መመሪያ ያለ አይመስልም።” በተመሳሳይም አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንዲህ ብለዋል:- “ነገሮች ጥቁርና ነጭ ሆነው መታየታቸው ቀርቷል። ሁሉም ነገር ግራጫ ሆኗል። . . . ትክክልና ስህተት በሆነው ነገር መካከል ያለውን ልዩነት የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸው። ዛሬ እንደ ኃጢአት የሚታየው ጥፋት ሲሠሩ መያዝ እንጂ ሕግ ማፍረስ አይደለም።”
ሐዋርያው ጳውሎስ እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ስላላቸው ሰዎች ጽፏል:- “እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።” (ኤፌሶን 4:18, 19) ይሁን እንጂ መከራ ይጠብቃቸዋል። ኢሳይያስ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፣ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፣ . . . ወዮላቸው!” (ኢሳይያስ 5:20) እነዚህ ሰዎች የዘሩትን ማጨዳቸው ባይቀርም በቅርቡ ደግሞ ታላቅ ‘ወዮታ’ ይኸውም ከይሖዋ የሚመጣ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።—ገላትያ 6:7
መዝሙር 92:7 “ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ፣ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፣ ለዘላለም ዓለም እንደሚጠፉ ነው” ይላል። በሌላ አባባል ይህ አለቅጥ የተንዠረገገው የዓመፃ ሰብል የሰዎችን ሕይወት እንዳመሰ እንዲሁ አይቀጥልም። እንዲያውም ኢየሱስ ይህንን ክፋት የሚፈጽመውን “ትውልድ” አምላክ ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት እንደሚያጠፋው ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 21, 34) እንግዲያው ከዚህ መከራ መትረፍ የምንፈልግ ከሆነ ከአምላክ የአቋም ደረጃ አንጻር ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ደግሞም ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ድርጊት ላለመፈጸም እምቢ ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ ሊኖረን ይገባል። ይህንን ማድረግ ቀላል ነገር ባይሆንም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ ዛሬ አንዳንድ የሚያበረታቱ ምሳሌዎችን ሰጥቶናል።
እምቢ ካለ አንድ ወጣት ምሳሌ መማር
በተለይ ምንዝርና ዝሙት እንዲፈጽሙ የሚቀርብላቸውን ግብዣ እምቢ ማለት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላሉ ለአንዳንዶች እንኳ ሳይቀር አስቸጋሪ የሆነባቸው ይመስላል። በመግቢያው አንቀጽ ላይ የጠቀስነው ጢሞቴዎስ በዘፍጥረት 39:1-12 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የወጣቱን የዮሴፍን ምሳሌ አስታውሷል። ዮሴፍ የግብጻዊው ባለ ሥልጣን የጲጥፋራ ሚስት ከእርሷ ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽም ደግማ ደጋግማ በጠየቀችው ጊዜ ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬውን አሳይቷል። ዘገባው ዮሴፍ “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” በማለት ‘እምቢ እንዳለ’ ይገልጻል።
ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት ነጋ ጠባ ስትነዘንዘው አይሆንም ለማለት ያስቻለውን የሥነ ምግባር ጥንካሬ ያገኘው እንዴት ነበር? በመጀመሪያ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ከጊዜያዊ ደስታ አስበልጦ ተመልክቶታል። ከዚህም ሌላ ዮሴፍ የሚመራበት መለኮታዊ ሕግ የተሰጠው ሰው ባይሆንም (የሙሴ ሕግም ገና አልነበረም) የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። የወረት ፍቅር ከያዛት ከጲጥፋራ ሚስት ጋር ዝሙት መፈጸም በባሏ ላይ ብቻ ሳይሆን በአምላክም ላይ ኃጢአት መሥራት ማለት እንደሚሆን ተገንዝቦ ነበር።—ዘፍጥረት 39:8, 9
ዮሴፍ የኋላ ኋላ ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የጦፈ ስሜት የሚያመራውን የመጀመሪያ እርምጃ እንኳ አለመውሰዱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የተገነዘበ ይመስላል። አንድ ክርስቲያን የዮሴፍን ምሳሌ መከተሉ ጥበብ ይሆናል። የሐምሌ 1, 1957 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ሥጋዊ ድክመት እንዳለበት መገንዘብ አለበት እንጂ ስሜቴ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተገለጸው ድንበር ላይ ሲደርስ ልገታው እችላለሁ ብሎ ማሰብ አይኖርበትም። ለተወሰነ ጊዜ ይህን ለማድረግ ቢሳካለት እንኳ ቀስ በቀስ ይህን ድንበር አልፎ በኃጢአት ሊወድቅ ይችላል። በየጊዜው የሚጨማመሩ የብልግና ሐሳቦች አይለው አንድ ቀን ግለሰቡን ስለሚቆጣጠሩት የመጨረሻው ውጤት ኃጢአት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህ በኋላ አእምሮውን እንደነዚህ ካሉ ነገሮች ማላቀቅ ይከብደዋል። ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ገና ከጅምሩ መከላከል ነው።”
ትክክል ለሆነ ነገር ያለን ፍቅርና ስህተት ለሆነው ነገር ያለን ጥላቻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ ስለሚሄድ የሚቀልለው ሐሳቡን ገና ከጅምሩ መቋቋሙ ነው። (መዝሙር 37:27) ይሁን እንጂ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግና መጽናት ያስፈልገናል። እንደዚያ የምናደርግ ከሆነ በይሖዋ እርዳታ ትክክል ለሆነ ነገር ያለን ፍቅርና ስህተት ለሆነ ነገር ያለን ጥላቻ እያደገ ይሄዳል። ከዚሁ ጋር ግን ኢየሱስ እንደተናገረው ከፈተና በመራቅና ከክፉው እንዲያድነን አዘውትረን በመጸለይ መትጋት ይኖርብናል።—ማቴዎስ 6:13፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17
ለእኩዮች ተጽዕኖ ላለመሸነፍ እምቢ ማለት
ሌላው ስህተት እንድንሠራ ተጽዕኖ የሚያሳድረው ነገር የእኩዮች ተጽእኖ ነው። አንድ ወጣት እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “ሁለት ዓይነት ኑሮ እኖራለሁ። ትምህርት ቤት ሌላ ሰው፣ ቤት ውስጥ ደግሞ ሌላ ሰው ነኝ። በትምህርት ቤት የብልግና ንግግር ከአፋቸው ከማይለያቸው ልጆች ጋር ስንገዋለል እውላለሁ። አሁን እኔም እንደ እነርሱ እየሆንሁ ነው። ምን ባደርግ ይሻለኛል?” በዚህ ጊዜ የተለየ አቋም ለመውሰድ ድፍረት ያስፈልጋል። ይህንን ድፍረት ማግኘት የሚቻልበት አንዱ መንገድ ደግሞ እንደ ዮሴፍ ስለመሳሰሉት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ማንበብና በእነዚያ ላይ ማሰላሰል ነው። ሌሎች እንደ ዳንኤል፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የመሰሉ ግሩም ምሳሌዎችም አሉ። እነዚህ አራት ወጣቶች ከእኩዮቻቸው የተለየ አቋም ለመውሰድ የሚያስችል ድፍረት ነበራቸው።
እነዚህ አራት ወጣት እስራኤላውያን በባቢሎን ቤተ መንግሥት ውስጥ ከነበሩ ሌሎች ወጣቶች ጋር ትምህርት ይሰጣቸው በነበረበት ጊዜ ‘ከንጉሡ መብል በየዕለቱ የሚመጣላቸው ድርጎ መመገብ’ ይጠበቅባቸው ነበር። ስለ አመጋገብ የተሰጠውን የሙሴ ሕግ ላለመጣስ ሲሉ ይህን ምግብ ለመመገብ እምቢ አሉ። ይህ ጥንካሬ የሚጠይቅ ውሳኔ ነበር። በተለይ ምግቡ ‘የንጉሡ መብል’ ስለነበር በጣም የሚያጓጓ ዓይነት እንደሚሆን መገመት እንችላለን። እነዚህ ወጣቶች በዛሬው ጊዜ ያለ ልክ አልኮል ለመጠጣት፣ አደገኛ ዕፆችን ለመውሰድ እንዲሁም ትንባሆ ለማጨስ ለሚፈተኑ አልፎ ተርፎም በዚህ ረገድ ሌሎች ተጽዕኖ ለሚያደርጉባቸው ክርስቲያኖች እንዴት ግሩም ምሳሌ ናቸው!—ዳንኤል 1:3-17
ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው” ሲል የተናገረው ነገር እውነት መሆኑንም አሳይተዋል። (ሉቃስ 16:10) በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላል በነበረው የምግብ ጉዳይ የወሰዱት ድፍረት የተሞላበት አቋምና ከይሖዋ ያገኙት በረከት ይበልጥ ከባድ የሆነውን የኋለኛውን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንደሰጣቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (ዳንኤል 1:18-20) ይህ ፈተና የመጣው በጣዖት አምልኮ እንዲካፈሉ አለዚያ ግን በእሳት ተቃጥለው እንደሚሞቱ በተነገራቸው ጊዜ ነበር። እነዚህ ሦስት ወጣቶች ምንም ይምጣ ምን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመን እርሱን ብቻ ለማምለክ ድፍረት የተሞላበት ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ የሚንቀለቀል እሳት ካለበት እቶን ውስጥ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ በማውጣት እነዚህ ወጣቶች ላሳዩት እምነትና ድፍረት ባርኳቸዋል።—ዳንኤል 3:1-30
በአምላክ ቃል ውስጥ ስህተት የሆነውን ነገር ለመፈጸም እምቢ ስላሉ ሰዎች የሚገልጹ ብዙ ምሳሌዎች ይገኛሉ። ሙሴ ግብፅ ውስጥ ‘በኃጢአት በሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ ለመፈንጠዝ የሚያስችል አጋጣሚ ያስገኝለት የነበረ ቢሆንም ‘የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን’ እምቢ ብሏል። (ዕብራውያን 11:24-26) ነቢዩ ሳሙኤል ጉቦ በመቀበል ሥልጣኑን አላግባብ ከመጠቀም እምቢ ብሏል። (1 ሳሙኤል 12:3, 4) የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ስብከታቸውን እንዲያቆሙ በታዘዙበት ጊዜ በድፍረት እምቢ ብለዋል። (ሥራ 5:27-29) ኢየሱስም ራሱ ወታደሮቹ “ከርቤ የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ” እንዲጠጣ ያቀረቡለትን ግብዣ ጨምሮ እስከ መጨረሻዋ ትንፋሹ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ድርጊት ለመፈጸም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። የወታደሮቹን ግብዣ መቀበል በዚያ ወሳኝ ወቅት ቁርጠኛ አቋሙን ማዳከም ሊሆንበት ይችል ነበር።—ማርቆስ 15:23፤ ማቴዎስ 4:1-10
እምቢ ማለት—የሕይወትና የሞት ጉዳይ
ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፣ መንገዱም ትልቅ ነውና፣ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ነውና፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”—ማቴዎስ 7:13, 14
ሰፊው መንገድ ለመጓዝ ቀላል ስለሆነ ብዙዎቹ ይመርጡታል። በዚህ መንገድ የሚጓዙት ሰዎች የራሳቸውን ስሜት ስለማርካት ብቻ የሚያስቡ፣ ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸውና ከሰይጣን ዓለም ለመለየት ሳይሆን ተመሳስለው ለመኖር የሚፈልጉ ናቸው። የአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥነ ምግባር መፈናፈኛ እንዳሳጧቸው አድርገው ያስባሉ። (ኤፌሶን 4:17-19) ይሁንና ኢየሱስ ሰፊው መንገድ “ወደ ጥፋት” እንደሚመራ በግልጽ ተናግሯል።
ይሁንና ኢየሱስ በጠባቡ ጎዳና ላይ ለመጓዝ የሚመርጡት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ የተናገረው ለምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት ሕይወታቸውን በአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመምራት እንዲሁም በእነዚሁ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅመው በዙሪያቸው ያሉትን ወደ ኃጢአት የሚመሩ ማባበያዎችና ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚፈልጉት ጥቂቶች በመሆናቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ፍላጎቶችንና የእኩዮችን ተጽእኖ ለመታገል እንዲሁም በመረጡት ጎዳና ምክንያት ሊገጥማቸው የሚችለውን የሌሎች ፌዝ ለመቋቋም የተዘጋጁት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂቶች ብቻ ናቸው።—1 ጴጥሮስ 3:16፤ 4:4
እነዚህ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ኃጢአትን ለማሸነፍ ስለሚያደርገው ትግል ሲገልጽ የተሰማው ስሜት በቀላሉ ይገባቸዋል። በዛሬው ጊዜ እንዳለው ዓለም ሁሉ በጳውሎስ ዘመን የነበረው የሮማውያንና የግሪካውያን ዓለምም ወደ መጥፎ ድርጊቶች የሚመራ ሰፊ ጎዳና ነበረው። ጳውሎስ ትክክል የሆነው ነገር ምን እንደሆነ የሚያውቀው አእምሮው ወደ ኃጢአት ከሚያዘነብለው ሥጋው ጋር የማያቋርጥ ‘ውጊያ’ እንደገጠመ ገልጿል። (ሮሜ 7:21-24) አዎን፣ ጳውሎስ ሥጋው ጥሩ አገልጋይ እንደሆነ ቢያውቅም ጨካኝ ጌታ እንደሆነም ስለተገነዘበ ሥጋውን እምቢ ማለትን ተምሯል። “ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) እንዲህ ያለውን የበላይነት ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነበር? የአምላክን መንፈስ እርዳታ ባያገኝ ኖሮ ይህን ለማድረግ የሚያስችል በቂ ጥንካሬ ባልኖረው ነበር።—ሮሜ 8:9-11
በዚህም ምክንያት ጳውሎስ ፍጽምና የነበረው ሰው ባይሆንም እስከ መጨረሻው ድረስ ለይሖዋ ያለውን የጸና አቋም ጠብቆ መኖር ችሏል። ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደሚከተለው ብሎ ለመጻፍ ችሎ ነበር:- “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል።”—2 ጢሞቴዎስ 4:7, 8
እኛም ካለፍጽምናችን ጋር የምንዋጋ ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ጳውሎስና ለእርሱም ጭምር ምሳሌ የሆኑት እንደ ዮሴፍ፣ ሙሴ፣ ዳንኤል፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅ፣ አብደናጎ ያሉትና ሌሎችም ብዙ ታማኝ ሰዎች ትልቅ የማበረታቻ ምሳሌ ይሆኑናል። እነዚህ የእምነት ሰዎች ፍጽምና ያልነበራቸው ቢሆኑም እንኳ በየግላቸው መጥፎ የሆነውን ነገር ለማድረግ እምቢ ብለዋል። ይህን ያደረጉት ደግሞ እኔ ያልኩት ይሁን ባዮች ወይም እብሪተኛ ሰዎች ስለነበሩ ሳይሆን በይሖዋ መንፈስ እርዳታ የሥነ ምግባር ጥንካሬ ስላገኙ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) መንፈሳዊ ሰዎች ነበሩ። ከይሖዋ አፍ የሚወጣውን ቃል የሚጠሙ ሰዎች ነበሩ። (ዘዳግም 8:3) ቃሉ ሕይወታቸው ነበር። (ዘዳግም 32:47) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ይወዱትም ይፈሩትም ነበር። ከእርሱ በሚያገኙትም እርዳታ ክፉ ለሆነው ነገር ጥላቻ ማዳበር የሚያስችል ትዕግሥት አግኝተዋል።—መዝሙር 97:10፤ ምሳሌ 1:7
እኛም የእነርሱን ምሳሌ እንከተል። እርግጥ ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ድርጊት እምቢ በማለት ለመጽናት ልክ እንደነዚህ ሰዎች የይሖዋን መንፈስ ማግኘት ያስፈልገናል። እኛ ከልባችን ከጠየቅነው፣ ቃሉን ካጠናንና አዘውትረን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከተገኘን ይሖዋ መንፈሱን በልግስና ይሰጠናል።—መዝሙር 119:105፤ ሉቃስ 11:13፤ ዕብራውያን 10:24, 25
በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ፍላጎቶቹን ቸል ባለማለቱ ደስተኛ ነው። ከሥራ ባልደረባው ጋር ያደርግ የነበረው ውይይት ጆሮዋ ውስጥ ጥልቅ ያለው አብራው የምትሠራው ወጣት ሴት በጢሞቴዎስ ቅንነት ተማርካ ስለነበር ቆየት ብላ ባሏ በሌለበት እቤቷ እንዲመጣ ጋበዘችው። ጢሞቴዎስ ግብዣውን አልተቀበለም። በቀላሉ ተስፋ ባለመቁረጥ እንደ ጲጥፋራ ሚስት በተለያዩ ጊዜያት ደጋግማ ጠየቀችው። ይሁን እንጂ ጢሞቴዎስ በደግነት ቁርጥ አቋሙን ደጋግሞ አሳወቃት። ለዚህች ሴት ከአምላክ ቃል ግሩም ምሥክርነትም ሰጥቷታል። ይሖዋ እምቢ ለማለት የሚያስችል የሥነ ምግባር ጥንካሬ ስለሰጠው አመስጋኝ የሆነው ጢሞቴዎስ ዛሬ አንዲት ጥሩ ክርስቲያን በማግባቱ ደስተኛ ሆኗል። በእርግጥም ይሖዋ መጥፎ የሆነውን ድርጊት ለመፈጸም እምቢ በማለት ጽኑ ክርስቲያናዊ አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚፈልጉትን ሁሉ አብዝቶ ይባርካቸዋል፤ ጥንካሬውንም ይሰጣቸዋል።—መዝሙር 1:1-3