የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 11/1 ገጽ 9-14
  • ለአምላክ ቃል ያላችሁ ፍቅር ምን ያህል ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለአምላክ ቃል ያላችሁ ፍቅር ምን ያህል ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክን ቃል ‘መመኘት’
  • ለአምላክ ቃል ፍቅር የነበረው መዝሙራዊ
  • የተለየ ለመሆን ድፍረት የነበረው መስፍን
  • የአምላክ ቃል ኢየሱስን አጽንቶታል
  • የክርስቶስን ምሳሌ የኮረጁ ሌሎች ሰዎች
  • በይሖዋ ቃል ታመኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • የአምላክ ቃል መንገዳችሁን እንዲያበራላችሁ ፍቀዱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ‘ከይሖዋ ጋር ተጣበቀ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • ጠቃሚና አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 11/1 ገጽ 9-14

ለአምላክ ቃል ያላችሁ ፍቅር ምን ያህል ነው?

“አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።”​—⁠መዝሙር 119:​97

1. አምላክን የሚፈሩ ሰዎች የአምላክን ቃል እንደሚወድዱ ማሳየት የሚችሉበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?

በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች የራሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ አላቸው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘትና የአምላክን ቃል መውደድ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ከስንት አንድ ጊዜ ብቻ እያነበበ ለአምላክ ቃል ፍቅር አለኝ ብሎ ሊናገር ይችላል? በፍጹም እንደዚያ ሊል አይችልም! በተቃራኒው ደግሞ በአንድ ወቅት ለመጽሐፍ ቅዱስ እምብዛም ግድ ያልነበራቸው ሰዎች ዛሬ ይህን መጽሐፍ በየዕለቱ ያነብቡታል። ለአምላክ ቃል ፍቅር አዳብረዋል፤ እንዲሁም እንደ መዝሙራዊው የአምላክ ቃል “ቀኑን ሁሉ” ትዝታቸው ሆኗል።​—⁠መዝሙር 119:​97

2. አንድ የይሖዋ ምሥክር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር እምነቱን ጠብቆ መቆየት የቻለው እንዴት ነው?

2 ለአምላክ ቃል የጠበቀ ፍቅር ካላቸው ሰዎች መካከል ናሾ ዶሪ ይገኝበታል። ከሌሎች የእምነት አጋሮቹ ጋር በትውልድ አገሩ በአልባንያ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በጽናት አገልግሏል። በአብዛኛዎቹ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በእገዳ ሥር ስለነበሩ እነዚህ የታመኑ ክርስቲያኖች ይደርሳቸው የነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ እጅግ ጥቂት ነበር። ይሁንና የወንድም ዶሪ እምነት ጠንካራ ነበር። እንዴት? “መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት የማንበብ ግብ የነበረኝ ሲሆን የማየት ችሎታዬ እስከ ደከመበት ጊዜ ድረስ ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት እንደዚያ ሳደርግ ኖሬያለሁ” ሲል ተናግሯል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መላው መጽሐፍ ቅዱስ በአልባኒያ ቋንቋ አልተዘጋጀም ነበር። ይሁንና ወንድም ዶሪ በልጅነቱ ግሪክኛ ተምሮ ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነበው በዚህ ቋንቋ ነበር። ወንድም ዶሪ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማንበቡ የተለያዩ መከራዎችን ተቋቁሞ እንዲያልፍ እንደረዳው ሁሉ እኛንም እንዲሁ ሊረዳን ይላል።

የአምላክን ቃል ‘መመኘት’

3. ክርስቲያኖች ለአምላክ ቃል ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ “አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:​3) አንድ ሕፃን የእናቱን ጡት ለመጥባት እንደሚጓጓ ሁሉ ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖችም የአምላክን ቃል በማንበብ ትልቅ ደስታ ያገኛሉ። አንተስ እንደዚያ ይሰማሃል? እንደዚያ የማይሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። አንተም ለአምላክ ቃል ያለህን ጉጉት ማሳደግ ትችላለህ።

4. መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ ማዳበር ምን ነገር ይጠይቃል?

4 ይህንን ማድረግ ትችል ዘንድ በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የዘወትር ልማድህ ለማድረግ ከተቻለም በየዕለቱ ለማንበብ ራስህን ገስጽ። (ሥራ 17:​11) ናሾ ዶሪ ያደርግ እንደነበረው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለአንድ ሰዓት ማንበብ አትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ በየዕለቱ የአምላክን ቃል ለመመርመር የሚያስችል የተወሰነ ጊዜ መመደብ ትችላለህ። ብዙ ክርስቲያኖች በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ለማሰላሰል ሲሉ ጠዋት ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብለው ይነሣሉ። ዕለቱን ከዚህ በተሻለ በምን ነገር መጀመር ይቻላል? ሌሎች ደግሞ ከመተኛታቸው በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ቀኑን መደምደም ይመርጣሉ። አንዳንዶች ደግሞ አመቺ ሆኖ ባገኙት ሌላ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስ ያነብባሉ። ዋናው ቁም ነገር መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማንበቡ ነው። ከዚያ ደግሞ ባነበብከው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጥቂት ጊዜ መድብ። እስቲ የአምላክን ቃል በማንበብና በዚያ ላይ በማሰላሰል የተጠቀሙ የአንዳንድ ግለሰቦችን ምሳሌ እንመርምር።

ለአምላክ ቃል ፍቅር የነበረው መዝሙራዊ

5, 6. የመዝሙር 119 ጸሐፊን በስም ባናውቀውም የጻፈውን መዝሙር በማንበብና በዚያ ላይ በማሰላሰል ስለ ጸሐፊው ምን መማር እንችላለን?

5 የመዝሙር 119 ጸሐፊ ለአምላክ ቃል ጥልቅ አድናቆት እንደነበረው ግልጽ ነው። ይህንን መዝሙር የጻፈው ማን ነው? ጸሐፊው ማን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተገለጸም። ይሁን እንጂ ከመዝሙሩ ይዘት ስለ ጸሐፊው አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ እንችላለን። ጸሐፊው ያሳለፈው ሕይወት ችግር የሞላበት እንደነበር እናውቃለን። የይሖዋ አገልጋዮች ነን ይሉ የነበሩት አንዳንድ የሚያውቃቸው ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የእርሱ ዓይነት ፍቅር አልነበራቸውም። የሆነ ሆኖ መዝሙራዊው የእነርሱ አመለካከት ትክክለኛ የሆነውን ነገር ከማድረግ እንዲገታው አልፈቀደም። (መዝሙር 119:​23) አንተም ለመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች አክብሮት ከሌላቸው ሰዎች ጋር የምትኖር ወይም የምትሠራ ከሆነ ሁኔታህ ከመዝሙራዊው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል።

6 መዝሙራዊው አምላካዊ አክብሮት የነበረው ሰው ቢሆንም ፈጽሞ ራሱን የሚያመጻድቅ ሰው አልነበረም። አለፍጽምና እንዳለበት አልሸሸገም። (መዝሙር 119:​5, 6, 67) ይሁንና ኃጢአት እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም። “ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል?” ሲል ጠይቋል። መልሶም “ቃልህን በመጠበቅ ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 119:9) የአምላክ ቃል በጎ ተጽዕኖ በማሳደር በኩል ያለውን ኃይል ጎላ አድርጎ ሲገልጽ “አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (መዝሙር 119:11) በአምላክ ላይ ኃጢአት እንዳንሠራ ሊጠብቀን የሚችል ኃይል በመሆኑ በእርግጥም ብርቱ ነው!

7. በተለይ ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ለማንበብ ንቁ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

7 ክርስቲያን ወጣቶች የመዝሙራዊውን ቃላት መመርመራቸው ተገቢ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ክርስቲያኖች የጥቃት ዒላማ ሆነዋል። ዲያብሎስ አዲሱን የይሖዋ አምላኪዎች ትውልድ ለማበላሸት ይፈልጋል። የሰይጣን ግብ ወጣት ክርስቲያኖችን በማባበል ለሥጋዊ ምኞታቸው ተሸንፈው የአምላክን ሕግ እንዲያፈርሱ ማድረግ ነው። ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ብዙውን ጊዜ የዲያብሎስን አስተሳሰብ ያንጸባርቃሉ። በፕሮግራሞቹ ውስጥ የሚታዩት ተዋናዮች ማራኪና ተወዳጅ መስለው ይታያሉ። የሚፈጽሙት ብልግና ምንም ስህተት እንደሌለው ሆኖ ይቀርባል። መልእክቱ ምንድን ነው? ‘ያልተጋቡ ሰዎች ከልባቸው እስከተዋደዱ ድረስ የፆታ ግንኙነት ቢፈጽሙ ምንም ስህተት የለበትም’ የሚል ነው። የሚያሳዝነው በየዓመቱ በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች ለእንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ይሸነፋሉ። አንዳንዶች የእምነት መርከባቸው ተሰብሮባቸዋል። ስለዚህ ተጽዕኖ አለ! ይሁን እንጂ ይህ ተጽዕኖ እናንተ ወጣቶች መቋቋም እስከማትችሉት ድረስ እጅግ ከባድ ነው ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ፣ ወጣት ክርስቲያኖች ጤናማ ያልሆኑ ምኞቶችን ማሸነፍ የሚችሉበትን መንገድ አዘጋጅቷል። ‘የአምላክን ቃል በመጠበቅና ቃሉን በልባቸው በመሰወር’ ሰይጣን የሚጠቀምበትን ማንኛውንም መሣሪያ መመከት ይችላሉ። የአምላክን ቃል በግል አዘውትረህ ለማንበብና በዚያ ላይ ለማሰላሰል ምን ያህል ጊዜ ታጠፋለህ?

8. በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ለሙሴ ሕግ ያለህን አድናቆት እንዳታሳድግ ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?

8 የመዝሙር 119 ጸሐፊ “ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ!” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 119:97) የትኛውን ሕግ ማለቱ ነው? የሙሴን ሕግ ጨምሮ ይሖዋ የገለጸውን ቃል ማለቱ ነው። አንዳንዶች ሕጉ ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ በማሰብ አንድ ሰው እነዚህን ሕጎች እንዴት ሊወድድ ይችላል ብለው ይገረሙ ይሆናል። ይሁን እንጂ መዝሙራዊው እንዳደረገው የሙሴ ሕግ በያዛቸው የተለያዩ ገጽታዎች ላይ ስናሰላስል ከሕጉ በስተጀርባ ያለውን ጥበብ ልናስተውል እንችላለን። ሕጉ በርካታ ትንቢታዊ ዘርፎችን ከመያዙም በላይ ለንጽህናና ለጥሩ ጤንነት የሚረዱ የንጽህና አጠባበቅና የአመጋገብ መመሪያዎችን ይዟል። (ዘሌዋውያን 7:​23, 24, 26፤ 11:​2-8) ሕጉ በንግድ ሥራዎች ሐቀኛ መሆንን የሚያበረታታ ሲሆን እስራኤላውያንም ለተቸገሩ የእምነት አጋሮቻቸው አሳቢነትን እንዲያሳዩ ይመክራል። (ዘጸአት 22:​26, 27፤ 23:​6፤ ዘሌዋውያን 19:​35, 36፤ ዘዳግም 24:​17-21) የፍርድ ውሳኔዎች ያለ አድልዎ መከናወን ነበረባቸው። (ዘዳግም 16:​19፤ 19:​15) የመዝሙር 119 ጸሐፊ የሕይወት ተሞክሮ እያገኘ ሲሄድ የአምላክን ሕግ ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች መጨረሻቸው ያማረ ሲሆንላቸው እንደተመለከተና በዚህም የተነሣ ለሕጉ ያለው ፍቅር እያደገ እንደሄደ ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬም በተመሳሳይ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ ስኬት ሲያገኙ ለአምላክ ቃል ያላቸው ፍቅርና አድናቆት ይበልጥ እያደገ ይሄዳል።

የተለየ ለመሆን ድፍረት የነበረው መስፍን

9. ንጉሥ ሕዝቅያስ ለአምላክ ቃል ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

9 የመዝሙር 119 ይዘት ሕዝቅያስ ወጣት መስፍን በነበረበት ጊዜ ካሳለፈው ታሪክ ጋር የሚጣጣም ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የዚህ መዝሙር ጸሐፊ ሕዝቅያስ ነው የሚል ሐሳብ ይሰነዝራሉ። እንደዚያ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ሕዝቅያስ ለአምላክ ቃል ትልቅ አክብሮት የነበረው ሰው ነበር። ከመዝሙር 119:​97 ጋር ፍጹም በሚስማማ መንገድ ተመላልሷል። መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝቅያስን በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣበቀ፣ እርሱንም ከመከተል አልራቀም፣ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዘውን ትእዛዝ ጠበቀ።”​—⁠2 ነገሥት 18:​6

10. የሕዝቅያስ ምሳሌ ለአምላክ አክብሮት በሌላቸው ወላጆች ላደጉ ክርስቲያኖች ምን ማበረታቻ ይዟል?

10 ከዘገባዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ሕዝቅያስ አምላካዊ አክብሮት በነበረው ቤተሰብ መካከል አልነበረም። አባቱ ንጉሥ አካዝ እምነት የለሽ ጣዖት አምላኪ የነበረ ሲሆን ወንድ ልጁን ማለትም የሕዝቅያስን ወንድም በእሳት በማቃጠል ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል! (2 ነገሥት 16:​3) አባቱ እንዲህ ዓይነት መጥፎ ምሳሌ ቢሆንም ሕዝቅያስ ከአምላክ ቃል ጋር ጥሩ ትውውቅ ስለነበረው ‘መንገዱን’ ከማንኛውም አረማዊ ተጽዕኖ ‘ማንጻት’ ችሏል።​—⁠2 ዜና መዋዕል 29:​2

11. ሕዝቅያስ ያልታመነው አባቱ ምን ዓይነት ሁኔታ ሲገጥመው ተመልክቷል?

11 ሕዝቅያስ እያደገ ሲሄድ ጣዖት አምላኪ የነበረው አባቱ የአስተዳደር ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ይመለከት ነበር። ይሁዳ በጠላት ተከብባ ነበር። የሶርያው ንጉሥ ረአሶን ከእስራኤሉ ንጉሥ ከፋቁሔ ጋር በማበር ኢየሩሳሌምን ከብበው ነበር። (2 ነገሥት 16:​5, 6) ኤዶማውያንና ፍልስጤማውያንም የተሳካ ወረራ በማካሄድ ወደ ይሁዳ ዘልቀው ገብተው አንዳንድ የይሁዳ ከተሞችን ሳይቀር ተቆጣጥረው ነበር። (2 ዜና መዋዕል 28:​16-19) አካዝ ይህን ሁሉ ችግር ለመወጣት ምን አደረገ? አካዝ ከሶርያውያን ጥቃት እንዲያድነው ይሖዋን ከመለመን ይልቅ ወርቅና ብር እንዲሁም የቤተ መቅደሱን ንብረት ሳይቀር በጉቦ መልክ በመስጠት የአሦር ንጉሥ እንዲረዳው ተማጽኗል። ይሁን እንጂ ይህ ለይሁዳ ዘላቂ ሰላም አላመጣላትም።​—⁠2 ነገሥት 16:​6, 8

12. ሕዝቅያስ አባቱ የፈጸማቸውን ስህተቶች ከመድገም እንዲርቅ ምን ሊረዳው ይችል ነበር?

12 በመጨረሻም አካዝ ሞተና ሕዝቅያስ በ25 ዓመቱ ነገሠ። (2 ዜና መዋዕል 29:​1) በአንጻራዊ ሁኔታ ዕድሜው ትንሽ ቢሆንም ይህ የተሳካለት ንጉሥ እንዳይሆን አላገደውም። ከሃዲ የነበረውን አባቱን ከመከተል ይልቅ የይሖዋን ሕግ ሙጥኝ ብሏል። ይህም ለነገሥታት የተሰጠውን ልዩ ትእዛዝ መጠበቅን የሚጨምር ነበር:- “[አንድ ንጉሥ] በመንግሥቱ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ ከሌዋውያን ካህናት ወስዶ ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፤ . . . መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፣ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።” (ዘዳግም 17:​18, 19) ሕዝቅያስ የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብ ይሖዋን መፍራትን ሊማርና አምላካዊ አክብሮት ያልነበረው አባቱ የሠራቸውን ስህተቶች ከመድገም ሊርቅ ይችላል።

13. በመንፈሳዊ አነጋገር አንድ ክርስቲያን የሚያደርገው ነገር ሁሉ እንደሚከናወንለት እንዴት እርግጠኛ መሆን ይችላል?

13 ለአምላክ ቃል ያልተቋረጠ ትኩረት እንዲሰጡ ማበረታቻ የተሰጠው ለእስራኤል ነገሥታት ብቻ ሳይሆን አምላክን ለሚፈሩ ለመላው እስራኤላውያን ጭምር ነበር። እውነተኛ ደስታ የሚያገኘው ‘በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለው ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ’ ሰው እንደሆነ የመጀመሪያው መዝሙር ይገልጻል። (መዝሙር 1:​1, 2) መዝሙራዊው እንዲህ ዓይነቱ ሰው “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ብሏል። (መዝሙር 1:3) በተቃራኒው ደግሞ በይሖዋ አምላክ ላይ እምነት የሌለውን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመንገዱ ሁሉ የሚወላውል’ በማለት ይገልጸዋል። (ያዕቆብ 1:​8) ሁላችንም ደስተኛና የተሳካልን ሰዎች መሆን እንፈልጋለን። ዘወትር የሚደረግ ትርጉም ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ደስተኞች እንድንሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

የአምላክ ቃል ኢየሱስን አጽንቶታል

14. ኢየሱስ ለአምላክ ቃል ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

14 በአንድ ወቅት ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ከአስተማሪዎች መሀል ቁጭ ብሎ ወላጆቹ አገኙት። እነዚህ በአምላክ ሕግ የተካኑ ሰዎች “በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ!” (ሉቃስ 2:​46, 47) ይህ የሆነው ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። አዎን፣ ገና በለጋ እድሜው ሳይቀር ለአምላክ ቃል ፍቅር ነበረው። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ከቅዱሳን ጽሑፎች በመጥቀስ ሰይጣንን “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ገስጾታል። (ማቴዎስ 4:3-10) ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በሚኖርባት ከተማ በናዝሬት ላሉ ሰዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም መስበክ ጀመረ።​—⁠ሉቃስ 4:​16-21

15. ኢየሱስ ለሌሎች በሚሰብክበት ጊዜ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ ትምህርቱን ለመደገፍ ከአምላክ ቃል በተደጋጋሚ ይጠቅስ ነበር። አድማጮቹ ‘በትምህርቱ እጅግ ተገርመዋል።’ (ማቴዎስ 7:​28) የኢየሱስ ትምህርቶች ከይሖዋ ከራሱ የመነጩ መሆናቸው ምንም አያስደንቅም! ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም።”​—⁠ዮሐንስ 7:16, 18

16. ኢየሱስ ለአምላክ ቃል የነበረው ፍቅር እስከ ምን ድረስ ነው?

16 ከመዝሙር 119 ጸሐፊ በተለየ መልኩ ኢየሱስ ‘ዓመፅ አልነበረበትም።’ ከኃጢአት ነፃ የሆነና ‘ራሱን አዋርዶ ለሞት የታዘዘ’ የአምላክ ልጅ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:​8፤ ዕብራውያን 7:​26) ይሁንና ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም የአምላክን ቃል ያጠናና ይታዘዝ ነበር። በአቋሙ እንዲጸና የረዳው ቁልፍ ነገርም ይኸው ነበር። ጴጥሮስ ሰይፉን መዝዞ ጌታው አልፎ እንዳይሰጥ ለመከላከል በሞከረ ጊዜ ኢየሱስ ይህን ሐዋርያ ከገሰጸው በኋላ እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? እንዲህ ከሆነስ:- እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” (ማቴዎስ 26:53, 54) አዎን፣ ኢየሱስን ይበልጥ ያሳሰበው ከመከራና ከሚያዋርድ ሞት ማምለጡ ሳይሆን ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሉት ነገር ፍጻሜውን ማግኘቱ ነበር። ለአምላክ ቃል የነበረው ፍቅር እንዴት የሚያስደንቅ ነው!

የክርስቶስን ምሳሌ የኮረጁ ሌሎች ሰዎች

17. ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ቃል ምን ያህል የላቀ ግምት ሰጥቶት ነበር?

17 ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:1) ጳውሎስም እንደ ጌታው ለቅዱሳን ጽሑፎች ፍቅር ነበረው። “በውስጥ ሰውነቴ የእግዚአብሔርን ቃል በጣም እወድዳለሁ” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 7:​22 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ጳውሎስ በተደጋጋሚ ከአምላክ ቃል ይጠቅስ ነበር። (ሥራ 13:​32-41፤ 17:​2, 3፤ 28:​23) ጳውሎስ ለተወደደው የአገልግሎት ጓደኛው ለጢሞቴዎስ የመጨረሻ መመሪያ በሰጠበት ጊዜ የአምላክ ቃል በእያንዳንዱ ‘የእግዚአብሔር ሰው’ ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ሊጫወት የሚገባውን ጉልህ ሚና ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​15-17

18. በዘመናችን ለአምላክ ቃል አክብሮት የነበረው አንድ ምሳሌ ጥቀስ።

18 በዚህ በኋለኛው ዘመን የኖሩ ብዙ የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮችም ኢየሱስ ለአምላክ ቃል የነበረውን ፍቅር ኮርጀዋል። በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አንድ ወጣት ከጓደኛው መጽሐፍ ቅዱስ በስጦታ ያገኛል። ይህ ውድ ስጦታ በእርሱ ላይ ያመጣውን ለውጥ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በእያንዳንዷ ዕለት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነ ምዕራፍ ማንበብ የሕይወቴ ክፍል እንዲሆን ወሰንኩ።” ይህ ወጣት ፍሬድሪክ ፍራንዝ ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ የነበረው ፍቅር በይሖዋ አገልግሎት ረጅምና ስኬታማ ሕይወት እንዲያሳልፍ አስችሎታል። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን በቃሉ በመወጣት ችሎታው ይታወሳል።

19. አንዳንዶች ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ምን ፕሮግራም ያወጣሉ?

19 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ለማንበቡ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ይሰጡታል። በየሳምንቱ ከሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አንዱ ለሆነው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ዝግጅት ሲያደርጉ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎችን ያነብባሉ። ለሳምንቱ የተመደበው የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የያዛቸው ጎላ ያሉ ነጥቦችም በስብሰባው ላይ ማብራሪያ ይሰጥባቸዋል። አንዳንድ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቡን ለሰባት ትናንሽ ክፍሎች ከፋፍለው እያንዳንዱን ክፍል በየዕለቱ ማንበቡን ይበልጥ አመቺ ሆኖ አግኝተውታል። ባነበቡት ነገር ላይም ያሰላስላሉ። የሚቻል ሲሆንም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ተመሥርተው ተጨማሪ ምርምር ያደርጋሉ።

20. ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ የሚያስችል ጊዜ ለመዋጀት ምን ያስፈልጋል?

20 መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ለማንበብ ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ‘ጊዜ መዋጀት’ ያስፈልግህ ይሆናል። (ኤፌሶን 5:​16) ይሁን እንጂ ምንም ያህል መሥዋዕትነት ብትከፍል ከምታገኘው ጥቅም ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ እያዳበርክ ስትሄድ ለአምላክ ቃል ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ብዙም ሳይቆይ አንተም እንደ መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” ለማለት ትገፋፋለህ። (መዝሙር 119:97) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደምናየው እንዲህ ያለው አመለካከት አሁንም ሆነ ወደፊት ታላቅ በረከት ያስገኝልሃል።

ታስታውሳለህን?

◻ የመዝሙር 119 ጸሐፊ ለአምላክ ቃል ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

◻ ከኢየሱስና ከጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

◻ በግላችን ለአምላክ ቃል ያለንን ፍቅር ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የታመኑ ነገሥታት የአምላክን ቃል ዘወትር ማንበብ ነበረባቸው። አንተስ?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ገና ትንሽ ልጅ እያለ ሳይቀር ለአምላክ ቃል ፍቅር ነበረው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ