የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • rs ገጽ 130-ገጽ 133
  • እምነት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እምነት
  • ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላችሁ በተግባር አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • እምነት—በመንፈሳዊ የሚያጠነክር ባሕርይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • “እምነት ጨምርልን”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
  • በእውነት ላይ የተመሠረተ እምነት አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
ለተጨማሪ መረጃ
ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
rs ገጽ 130-ገጽ 133

እምነት

ፍቺ:- “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብ. 11:1) እውነተኛ እምነት ተላላነት ማለት አይደለም፤ አንድን ነገር ያለ ማስረጃ በጭፍን መቀበል ወይም እንዲሆን ስለፈለግን ብቻ መቀበል ማለት አይደለም። እውነተኛ እምነት መሠረታዊ እውቀት ማግኘትን፣ ከመረጃዎች ጋር መተዋወቅን፣ እንዲሁም መረጃው ለሚያሳየው ነገር ከልብ የመነጨ አድናቆት ማሳየትን ይጠይቃል። እንግዲያውስ ያለ ትክክለኛ እውቀት እውነተኛ እምነት ሊኖር ባይችልም፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው የሚያምነው “በልቡ” እንደሆነ ይናገራል።—ሮሜ 10:10

ብዙ ሰዎች እምነት የሌላቸው ለምንድን ነው?

እምነት የአምላክ መንፈስ ፍሬ ነው። አምላክም መንፈሱን ለማግኘት ለሚጥሩ ሁሉ በደስታ ይሰጣቸዋል። (ገላ. 5:22፤ ሉቃስ 11:13) ስለዚህ እምነት የሌላቸው ሰዎች ይህንን መንፈስ ለማግኘት አይጥሩም፣ ቢጥሩም እንኳ ለተሳሳተ ዓላማ ነው፤ ወይም መንፈሱ በሕይወታቸው ውስጥ እንዳይሠራ ያሰናክሉታል ማለት ነው። ለዚህም ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ:-

ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የላቸውም:- መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ስለሆነ የአምላክ መንፈስ ውጤት ነው። (2 ጢሞ. 3:16, 17፤ 2 ሳሙ. 23:2) መጽሐፍ ቅዱስን አለማጥናት ማናቸውንም የእውነተኛ እምነት እድገት ያደናቅፋል። የአብያተ ክርስቲያናት አባሎች መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖራቸው ቢችልም የአምላክን ቃል ሳይሆን የሰዎችን ሐሳቦች የሚማሩ ከሆነ ስለ አምላክና ስለ ዓላማው ትክክለኛ እምነት አይኖራቸውም። በራሳቸውና በሌሎች ሰዎች ሐሳብ ላይ በመንተራስ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ይሞክራሉ።—ከ⁠ማቴዎስ 15:3–9 ጋር አወዳድር።

በሃይማኖታዊ ሁኔታዎች ግራ ተጋብተዋል:- ብዙ ሰዎች የአምላክን ቃል እናስተምራለን ብለው እየተናገሩ ከቃሉ ጋር ተስማምተው በማይኖሩት ግብዝ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ግራ ተጋብተዋል። ሌሎች ደግሞ ከክርስትና እምነት ውጪ የሆኑ የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች የነበሩ ቢሆንም አባል የነበሩባቸው ሃይማኖቶች ያፈሯቸውን መጥፎ ፍሬዎች ተመልክተዋል ወይም ሃይማኖታቸው በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመቋቋም እንዳልጠቀማቸው ተረድተዋል። ስለ እውነተኛው አምላክ ትክክለኛ እውቀት ስለሌላቸው ከሃይማኖት ጋር ከተያያዘ ከማናቸውም ነገር ይርቃሉ።—ከ⁠ሮሜ 3:3, 4፤ ከ⁠ማቴዎስ 7:21–23 ጋር አወዳድር።

አምላክ ክፋት እንዲቀጥል የፈቀደበትን ምክንያት አልተረዱም:- ብዙ ሰዎች አምላክ ክፋት እንዲቀጥል ለምን እንደፈቀደ ባለመረዳታቸው ምክንያት ለሚፈጸሙት መጥፎ ነገሮች ሁሉ እርሱን ይወቅሱታል። ሰው ወደ መጥፎ ነገር የሚያዘነብለው የአምላክ ፈቃድ ስለሆነ ሳይሆን በአዳም ኃጢአት የተነሣ መሆኑን አይረዱም። (ሮሜ 5:12) የሰይጣን ዲያብሎስን መኖርና በዓለም ጉዳዮች ላይ ያለውን ተጽዕኖ ስላልተገነዘቡ በሰይጣን የተፈጸሙትን አሳፋሪ ነገሮች ሁሉ በአምላክ ላይ ያላክካሉ። (1 ዮሐ. 5:19፤ ራእይ 12:12) ስለ እነዚህ ነገሮች በመጠኑ የሚያውቁ ቢሆንም እንኳ አምላክ እርምጃ ከመውሰድ የዘገየ ይመስላቸዋል። ምክንያቱም ስለ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የተነሣውን ክርክር በግልጽ አያስተውሉም፤ እንዲሁም አምላክ እስከ ዛሬ ድረስ ያሳየው ትዕግሥት የማይገባቸውን የመዳን አጋጣሚ እንደሰጣቸው አይረዱም። (ሮሜ 2:4፤ 2 ጴጥ. 3:9) አምላክ ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ለዘላለም ለማጥፋት ጊዜ እንደቀጠረ አያስተውሉም።—ራእይ 22:10–12፤ 11:18፤ ዕን. 2:3

ኑሯቸው በሥጋዊ ፍላጎቶችና አመለካከቶች የተዋጠ በመሆኑ:- በአጠቃላይ ሲታይ እውነተኛ መሠረት ያለው እምነት የሚጐድላቸው ሰዎች ሌሎች ፍላጎቶችን ለማሳደድ ራሳቸውን አስገዝተዋል። አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ አምናለሁ ይሉ ይሆናል። ነገር ግን በጥልቀት አያጠኑት ወይም ያነበቡትን ነገር በዕለታዊ ሕይወታቸው ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ አያሰላስሉ ይሆናል። (ከ⁠1 ዜና መዋዕል 28:9 ጋር አወዳድር።) አንዳንድ ጊዜ እምነታቸውን በማሳደግ ፋንታ ከጽድቅ ጋር ለሚቃረኑ ነገሮች ያላቸው ፍላጎት የልባቸውን ዝንባሌ እንዲቆጣጠር ስለሚፈቅዱ ከአምላክና ከመንገዶቹ ይወጣሉ።—ዕብ. 3:12

አንድ ሰው እንዴት እምነት ሊያገኝ ይችላል?

ሮሜ 10:17:- “እምነት ከመስማት ነው።” (ከ⁠ሥራ 17:11, 12፤ ዮሐ. 4:39–42፤ 2 ዜና 9:5–8 ጋር አወዳድር። አንድ ሰው በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል መመርመር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ ትምክህት የሚጣልበት መሆኑን ለመረዳትና ለመቀበል በጥንቃቄ ቢመረምር እምነቱ ይጠነክርለታል።)

ሮሜ 10:10:- “ሰው በልቡ [ያምናል።]” (አንድ ሰው አምላካዊ ለሆኑ ነገሮች ያለውን አድናቆት ከፍ ለማድረግ ሲያሰላስል እነዚህን ያሰላሰላቸውን ነገሮች በምሳሌያዊ ልቡ ውስጥ እንዲቀረጹ ያደርጋል።)

አንድ ሰው አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ የተመሠረቱ እርምጃዎችን ሲወስድና ያደረጋቸውን ነገሮች አምላክ እንደባረከለት ሲመለከት እምነቱ ሊጠናከርለት ይችላል።—መዝሙር 106:9–12⁠ን ተመልከት።

ምሳሌ:- ምናልባት ‘በእርግጥ አምነዋለሁ’ የምትለው ጓደኛ ይኖርሃል፤ ‘ይህን ሰው አምነዋለሁ። ቃሉን እንደሚጠብቅ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፤ ችግር ሲያጋጥመኝ እንደሚረዳኝ አውቃለሁ’ ትል ይሆናል። ገና ትናንት ስላገኘኸው ሰው እንዲህ ብለህ ለመናገር ትችላለህ እንዴ? አትችልም። እንዲህ በማለት የምትናገርለት ሰው ለረጅም ጊዜ የምታውቀውና ትምክህት የሚጣልበት መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜያት ያረጋገጠልህ መሆን ይኖርበታል። ሃይማኖታዊ እምነትም ከዚህ የተለየ አይደለም። እምነት እንዲኖርህ ከፈለግህ ጊዜ ወስነህ ይሖዋንና የይሖዋን አሠራር ማጥናት ያስፈልግሃል።

አምላክ እንዳለ ማመን

በገጽ 146–152 ላይ “አምላክ” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ተመልከት።

ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ የነገሮች ሥርዓት እንደሚመጣ ማመን

አንድ ሰው ይሖዋ ለባሪያዎቹ ያደረጋቸውን ነገሮች በሚገባ ካወቀ እንደሚከተለው ሲል የተናገረውን የኢያሱን የመሰለ አመለካከት ያድርበታል:- “እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁ ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።”—ኢያሱ 23:14

የሰዎች ጤንነት እንደሚታደስ፣ የሙታን ትንሣኤ እንደሚኖር የተነገረውና ሌሎቹም የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረጋቸውና በጽሑፍ ተመዝግበው በሚገኙት ተአምራት ተጠናክረዋል። እነዚህ ታሪኮች ተረቶች አይደሉም። የወንጌልን ታሪኮች አንብብና እውነተኛ ታሪኮች መሆናቸውን የሚያረጋግጡትን ማስረጃዎች ተመልከት። የቦታ ስሞች ተጠቅሰዋል፤ በዘመኑ ይኖሩ የነበሩ የዓለማዊ ገዥዎች ስም ተመዝግቧል፤ ከአንድ በላይ የሆኑ የዓይን ምሥክሮች የጻፉት ይህ ታሪክ እስከ አሁን ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል። በእነዚህ መረጃዎች ላይ ማሰላሰል በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ ያለህን እምነት ያጠነክርልሃል።

ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾችና ትላልቅ ስብሰባዎች በመሄድ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ሕይወትን እንደሚለውጥ፣ ሰዎችን ሐቀኞችና ንጹሕ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ እንዲሁም ሁሉም የሰው ዘሮችና ብሔረሰቦች በእውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ ተስማምተው እንዲኖሩና እንዲሠሩ ሊያደርጋቸው እንደሚችል የሚያረጋግጠውን ማስረጃ ራስህ መመልከት ትችላለህ።

አንድ ሰው እምነት ካለው እምነቱን በሥራ መግለጽ የግድ ያስፈልገዋልን?

ያዕ. 2:17, 18, 21, 22, 26:- “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው:- አንተ እምነት አለህ፣ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፣ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያድግ እንደ ነበረ፣ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ [“ፍጹም ሆኖ እንደተቆጠረለት” አዓት ] ትመለከታለህ። ከነፍስ [“ከመንፈስ” አዓት ] የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።”

ምሳሌ:- አንድ ወጣት አንዲትን ወጣት ሴት ለጋብቻ በማሰብ ሊያጠናት ይቀርባትና እንደሚያፈቅራት ይነግራት ይሆናል። ነገር ግን ለጋብቻ ካልጠያቃት ከልብ ያፈቅራታል ለማለት ይቻላል? በተመሳሳይም ሥራ የእምነታችንንና የፍቅራችንን እውነተኛነት የምናሳይበት መንገድ ነው። አምላክን የማንታዘዝ ከሆነ እርሱን በእውነት አንወደውም፣ በመንገዶቹ ትክክለኛነትም እምነት የለንም ማለት ነው። (1 ዮሐ. 5:3, 4) ይሁን እንጂ ምንም ያህል ብንሠራ መዳን የድካማችን ዋጋ ሆኖ ሊከፈለን አይችልም። የዘላለም ሕይወት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከአምላክ የሚሰጥ ስጦታ እንጂ ለሥራችን ዋጋ ሆኖ የሚከፈል አይደለም።—ኤፌ. 2:8, 9

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ