የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ማርያም “የሚሻለውን” መረጠች
በኢየሱስ ዘመን የነበሩትን አይሁዳውያን ሴቶች የረቢዎች ወግ እስርስር አድርጓቸው ነበር። በመሆኑም ሕጉን እንዲማሩ የሚያበረታታ ነገር አልነበረም። እንዲያውም ሚሽና ላይ “አንድ ሰው ሴት ልጁን ስለ ሕጉ ቢያስተምር ዘማዊ እንድትሆን ያስተማራት ያህል ይቆጠራል” የሚል ሐሳብ ይገኛል።—ሶታህ 3:4
ከዚህ የተነሳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ የነበሩት አብዛኞቹ ሴቶች ጥሩ ትምህርት ሳያገኙ ቀርተዋል። “ከኢየሱስ አገልግሎት በፊት አይሁዳውያን ሴቶች የአንድ ታላቅ አስተማሪ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ይፈቀድላቸው እንደነበር የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። እንዲህ ካለው ታላቅ አስተማሪ ጋር መጓዝና ከሕፃናት በቀር ሌሎችን ማስተማርማ ፈጽሞ የማይታሰብ ነበር” ሲል ዚ አንከር ባይብል ዲክሽነሪ ዘግቧል። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች የበለጠ ሴቶችን ሲያንቋሽሹ አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር በአደባባይ መነጋገር የለበትም የሚል ሕግ ሳይቀር አውጥተው ነበር!
ኢየሱስ ይህን አምላካዊ ያልሆነ አስተሳሰብ አልተከተለም። ሴት ወንድ ሳይል ስላስተማረ ተከታዮቹ ከሁለቱም ጾታዎች የተውጣጡ ነበሩ። (ሉቃስ 8:1-3) በአንድ ወቅት ኢየሱስ የማርታና የማርያም እንግዳ እንዲሆን ግብዣ ቀርቦለት ነበር። (ሉቃስ 10:38) እነዚህ ሁለት ሴቶች የአልዓዛር እህቶች ሲሆኑ ሦስቱም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትና ጥሩ ወዳጆች ነበሩ። (ዮሐንስ 11:5) አልዓዛር በሞተበት ወቅት ማርታንና ማርያምን ሊያጽናኗቸው የመጡት ሰዎች ብዙ ከመሆናቸው አንፃር ሲታይ ይህ ቤተሰብ ታዋቂ የነበረ ይመስላል። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ በቤታቸው በተስተናገደበት ጊዜ ከተፈጸመው ነገር ጠቃሚ ትምህርት እንዳገኙ ሁሉ እኛም የምናገኘው ትልቅ ትምህርት ይኖራል።
በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ መማር
ማርታና ማርያም ለኢየሱስ ታላቅ ድግስ ለማዘጋጀት ጓጉተው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ለማድረግ ደግሞ አቅሙ የነበራቸው ይመስላል። (ከዮሐንስ 12:1-3 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እንግዳቸው ሲመጣ ማርያም ‘ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀመጠች።’ (ሉቃስ 10:39) ኢየሱስ ለመማር ፍላጎት የነበራትን አንዲት ቅን ሴት ከማስተማር ወደ ኋላ እንዲል የሚያደርገው ምንም ዓይነት ሰው ሠራሽ ሕግ አልነበረም! ማርያም ልክ እንደ አንድ ተማሪ ኢየሱስ ፊት ተቀምጣ የጌታዋን ትምህርት በጥሞና ስታዳምጥ በዓይነ ሕሊናችን ልንስላት እንችላለን።—ከዘዳግም 33:3፤ ሥራ 22:3 ጋር አወዳድር።
ከማርያም በተለየ ሁኔታ ማርታ ‘አገልግሎት ስለ በዛባት ባክናለች።’ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ምግብ በማዘጋጀት ላይ ስለነበረች በቤት ውስጥ ሥራ ተወጥራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ማርታ እርሷ ሁሉንም ሥራ እየሠራች እህቷ ግን በኢየሱስ እግር አጠገብ በመቀመጧ ተናደደች! ስለዚህ ማርታ ኢየሱስ ለማርያም ይናገራቸው የነበሩትን ቃላት በድንገት አቋርጣ:- “ጌታ ሆይ፣ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አያገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው።”—ሉቃስ 10:40
የማርታ ጥያቄ በራሱ ምንም ስህተት አልነበረውም። ደግሞም በርከት ላሉ ሰዎች ምግብ ማዘጋጀት ከባድ ሥራ ነው። ይህ ኃላፊነት በአንድ ሰው ላይ ብቻ መጫን የለበትም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህ አነጋገሯ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ እንደከፈተ ተመልክቶ ነበር። ስለሆነም “ማርታ፣ ማርታ፣ በብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ ትታወኪማለሽ፣ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን [“የሚሻለውን ነገር፣” የ1980 ትርጉም] መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።”—ሉቃስ 10:41, 42
ኢየሱስ ማርታ ለመንፈሳዊ ነገር አድናቆት ይጎድላታል ማለቱ አልነበረም። እንዲያውም ጥልቅ የሆነ ለአምላክ የማደር ባሕርይ ያላት ሴት እንደሆነች ያውቅ ነበር።a ቀድሞውንም ቢሆን ኢየሱስን ቤቷ እንድትጋብዘው ያነሳሳት ይኸው እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም። ነገር ግን ኢየሱስ በለዘበ መንፈስ በሰጠው ተግሣጽ ማርታ ምግቡን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ስትል ብርቅ የሆነው ከአምላክ ልጅ በግል ትምህርት የማግኘት አጋጣሚ እያመለጣት እንደነበር አመልክቷል።
እርግጥ ነው በወቅቱ የነበረው ባሕል የአንዲት ሴት ማንነት የሚለካው በቤት ውስጥ ሙያዋ ነው የሚለውን አመለካከት የሚደግፍ ነበር። ይሁን እንጂ የኢየሱስ አነጋገር እንደሚያመለክተው ሴቶችም ልክ እንደ ወንዶች በአምላክ ልጅ እግር አጠገብ ተቀምጠው የሕይወትን ቃል ሊሰሙ ይችላሉ! (ዮሐንስ 4:7-15፤ ሥራ 5:14) ከዚህ አንጻር ሲታይ በጌታ እግር አጠገብ ተቀምጣ ከእርሱ ለመማር የሚያስችል አጋጣሚ ለማግኘት ስትል ማርታ ጥቂት ወይም አንድ ዓይነት ምግብ ብቻ ብታዘጋጅ የተሻለ ይሆን ነበር።—ከማቴዎስ 6:25 ጋር አወዳድር።
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ዛሬ ኢየሱስ ‘የሕይወትን ውኃ እንዲያው እንዲወስዱ’ ላቀረበው ግብዣ ምላሽ ከሚሰጡት ሰዎች መካከል ወንዶችም ሴቶችም ይገኙበታል። (ራዕይ 22:17) አንዳንዶች ልክ ማርታ እንዳደረገችው በፍቅር በመነሳሳት መሰል አማኞችን ለማገልገል የአቅማቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። ጠቃሚ ሐሳቦችን ያፈልቃሉ፤ እንዲሁም እርምጃ ለመውሰድ ፈጣኖች ናቸው። በመሆኑም ይሖዋ ለፍቅር ሲሉ የሚደክሙትን ድካም እንደሚባርክላቸው ቃል ገብቷል። (ዕብራውያን 6:10፤ 13:16) ሌሎች ደግሞ የበለጠ ማርያምን ይመስሉ ይሆናል። ጭምቶችና በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። በአምላክ ቃል ላይ ለማሰላሰል ያላቸው ጉጉት በእምነት ሥር ሰድደው እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል።—ኤፌሶን 3:16-19
ሁለቱም ዓይነት ግለሰቦች ለክርስቲያን ጉባኤ በጣም ጠቃሚ ናቸው። ያም ሆነ ይህ ሁላችንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ‘የሚሻለውን መምረጥ’ ይገባናል። ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ትኩረት በመስጠት የይሖዋን ሞገስና በረከት እናገኛለን።—ፊልጵስዩስ 1:9-11 NW
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ማርታ ትልቅ እምነት የነበራት መንፈሳዊ ሴት መሆኗን ወንድሟ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ከኢየሱስ ጋር ካደረገችው ውይይት ማየት ይቻላል። በዚህ ወቅት ኢየሱስን ለማግኘት ትልቅ ጉጉት ያሳየችው ማርታ ነበረች።—ዮሐንስ 11:19-29