ጥናት 48
የምታስረዳበት መንገድ
በአምላክ ቃል አማካኝነት በአኗኗራችን ለውጥ ማድረግ በመቻላችን ደስ ብሎናል። ሌሎች ሰዎችም እንደኛው ለውጥ በማድረግ እንዲጠቀሙ እንሻለን። ከዚህም በላይ ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ የወደፊቱን ሕይወታቸውንም እንደሚነካው እንገነዘባለን። (ማቴ. 7:13, 14፤ ዮሐ. 12:48) እውነትን እንዲቀበሉ እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ማስተዋል ካልታከለበት የእኛ ልባዊ ፍላጎትና ቅንዓት ብቻውን በቂ አይሆንም።
ሰዎች ከልብ የሚያምኑበት ነገር ሐሰት እንደሆነ ፊት ለፊት የምንናገር ከሆነ ብዙ የጥቅስ ማስረጃ ብናቀርብ እንኳ በአብዛኛው መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ሰዎች የሚያከብሯቸውን በዓላት አመጣጣቸው አረማዊ እንደሆነ በመናገር ማውገዝ ብቻ ሰዎቹ ለበዓላቱ ያላቸውን አመለካከት ላይለውጥ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት የሚኖረው ምክንያታዊ ሆኖ መቅረብ ነው። ምክንያታዊ መሆን ምንን ይጨምራል?
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ላይኛይቱ ጥበብ ሰላም ወዳድና ምክንያታዊ’ እንደሆነች ይነግረናል። (ያዕ. 3:17 NW ) “ምክንያታዊ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ፍቺ “ግትር አለመሆን” የሚል ነው። አንዳንድ ተርጓሚዎች “አሳቢ፣” “ገር” ወይም “ታጋሽ” እያሉ ተርጉመውታል። ምክንያታዊ መሆን ከሰላም ወዳድነት ጋር ተያይዞ እንደቀረበ ልብ በል። በቲቶ 3:2 ላይ ደግሞ የተከራካሪነት ባሕርይ ተቃራኒ ተደርጎ ከየዋህነት ጋር ተያይዞ ተጠቅሷል። ፊልጵስዩስ 4:5 [NW ] “ምክንያታዊ” የሚል ስም ማትረፍ እንዳለብን ያሳስበናል። ምክንያታዊ የሆነ ሰው የሚያነጋግራቸውን ሰዎች አስተዳደግ፣ ሁኔታና ስሜት ግምት ውስጥ ያስገባል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ራሱን ከሁኔታው ጋር ለማስተካከል ፈቃደኛ ይሆናል። ለሰዎች እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀስን ስናስረዳቸው ልባቸውንና አእምሮአቸውን ከፍተው እንዲያዳምጡን ሊያደርግ ይችላል።
ከየት እንጀምር? ታሪክ ጸሐፊው ሉቃስ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ሳለ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ ‘ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና ከሙታን እንደሚነሳ’ ያስረዳ እንደነበር ዘግቧል። (ሥራ 17:2, 3) ጳውሎስ ይህንን ያደረገው በአይሁድ ምኩራብ ውስጥ መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ነው። ያነጋግራቸው የነበሩት ሰዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚያምኑ ነበሩ። አድማጮቹ የሚያምኑበትን ነገር በመጥቀስ ንግግሩን መጀመሩ ተገቢ ነበር።
ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ከግሪካውያን ጋር ሲወያይ ግን ንግግሩን የጀመረው ከቅዱሳን ጽሑፎች በመጥቀስ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በመግቢያው ላይ የጠቀሰው እነርሱ የሚያውቁትንና የሚያምኑበትን ነገር ሲሆን ከዚሁ ጋር አያይዞ ስለ ፈጣሪና ስለ ዓላማዎቹ አስረድቷቸዋል።—ሥራ 17:22-31
በዛሬውም ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምኑና ለሕይወታቸው መመሪያ እንደሆነ አድርገው የማይመለከቱት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ይሁንና ዛሬ ያለው ክፉ ሥርዓት ተጽዕኖ ያላሳደረበት ሰው የለም ለማለት ይቻላል። ሁሉም ሰው ከዚህ መጥፎ ሁኔታ ለመገላገል ይናፍቃል። በመጀመሪያ እነርሱን የሚያሳስባቸው ነገር አንተንም እንደሚያሳስብህ ከገለጽህ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል አስረዳቸው። እንዲህ ያለውን አሳማኝ አቀራረብ ከተጠቀምህ አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን መልእክት ለመስማት ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ።
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከወላጆቹ የወረሳቸው ሃይማኖታዊ እምነቶችና ልማዶች ይኖሩ ይሆናል። እነዚህን እምነቶችና ልማዶች አምላክ እንደማይደሰትባቸው ሲማር ከመጽሐፍ ቅዱስ ካገኘው እውቀት ጋር ለመስማማት ሲል እነዚህን ነገሮች ለመተው ይወስናል። ተማሪው ይህንን ውሳኔውን ለወላጆቹ ሊያስረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? ከእነርሱ የወረሳቸውን ሃይማኖታዊ እምነቶችና ልማዶች እርግፍ አድርጎ መተዉ እነርሱንም እንዳቃለላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ለምን ይህንን ውሳኔ እንዳደረገ ለወላጆቹ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ ከማስረዳቱ በፊት እነርሱን እንደሚወድዳቸውና እንደሚያከብራቸው መግለጽ እንደሚያስፈልገው ይሰማው ይሆናል።
ምክንያታዊ መሆን የሚያስፈልግበት ጊዜ። ይሖዋ አንድ ነገር እንዲደረግ የማዘዝ ሙሉ ሥልጣን ቢኖረውም ምክንያታዊ በመሆን ረገድ አቻ አይገኝለትም። የይሖዋ መላእክት ሎጥንና ቤተሰቡን በሰዶም ላይ ከሚመጣው ጥፋት ለማዳን በመጡ ጊዜ “እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ” ብለውት ነበር። ይሁንና ሎጥ “እንዲህስ አይሁን” ሲል ይሖዋን ተማጽኗል። ከዚያ ይልቅ ወደ ዞዓር ሸሽቶ ያመልጥ ዘንድ እንዲፈቀድለት ለመነ። ይሖዋ የሎጥን ልመና በመስማት አሳቢነት ያሳየው ሲሆን ሌሎቹ ከተሞች ሁሉ ሲጠፉ ዞዓር ሳትጠፋ ቀረች። ከጊዜ በኋላ ግን ሎጥ ይሖዋ እንዳለው ወደ ተራራ ሸሽቷል። (ዘፍ. 19:17-30) ይሖዋ መጀመሪያም ቢሆን እርሱ ያለው ነገር ትክክል እንደሆነ ያውቅ ነበር። ሆኖም ሎጥ ራሱ ይህንን ሐቅ እስኪያስተውል ድረስ በአሳቢነት ታግሶታል።
እኛም ከሌሎች ጋር በምናደርገው ውይይት ጥሩ ውጤት ማግኘት እንድንችል ምክንያታዊ መሆን ይኖርብናል። ሌላኛው ሰው እንደተሳሳተ እርግጠኛ ልንሆንና ለዚህም በቂ ማስረጃ ሊኖረን ይችላል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ መሳሳቱን በግድ ለማሳመን ከመጣር መቆጠብ ጥሩ ይሆናል። ምክንያታዊ እንሆናለን ሲባል በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ከመናገር ወደኋላ እንላለን ማለት አይደለም። ግለሰቡ አመለካከቱን ስለገለጸልህ ማመስገን ወይም የተሳሳቱ አስተያየቶችን ሁሉ ለማረም ከመሞከር ይልቅ በሚያስማሟችሁ ነጥቦች ላይ ማተኮር የተሻለ ሊሆን ይችላል። እምነትህን አንቋሽሾ ቢናገር እንኳ ስሜታዊ አትሁን። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ ልትጠይቀው ትችል ይሆናል። ከዚያም መልስ ሲሰጥ በጥሞና አዳምጠው። እንዲህ ማድረግህ ስለ ሰውዬው አስተሳሰብ ይበልጥ እንድታስተውል ሊረዳህና ወደፊት ጥሩ ውይይት ማድረግ የምትችሉበትን አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል።—ምሳሌ 16:23፤ 19:11
ይሖዋ ለሰዎች የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። በአግባቡ ላይጠቀሙበት እንደሚችሉ ቢያውቅም እንኳ ይህን ነፃነታቸውን አልገፈፋቸውም። ኢያሱ የይሖዋ ቃል አቀባይ ሆኖ ለእስራኤል ሕዝብ ሲናገር አምላክ ያደረገላቸውን ከዘረዘረ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፣ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፣ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ፣ እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” (ኢያሱ 24:15) ዛሬ ለእኛ የተሰጠን ተልዕኮ ምሥራቹን ‘መስበክ’ ነው። ይህንን ምሥራች በእርግጠኝነት ብንናገርም ሰዎች እንዲያምኑበት ለማስገደድ አንሞክርም። (ማቴ. 24:14) የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ ይችላሉ። ይህን መብታቸውን ልንነፍጋቸው አንችልም።
ጥያቄ መጠየቅ። አሳማኝ በሆነ መንገድ በማስረዳት ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። የሰዎቹን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባና በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። ጥያቄዎችንም በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሟል። ይህም አመለካከታቸውን እንዲገልጹ እንዲሁም በልባቸው የሚያስቡት ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ እንዲታይ በር ከፍቷል። ከዚህም በተጨማሪ ስለሚወያዩበት ጉዳይ እንዲያመዛዝኑ አድርጓቸዋል።
ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ ሰው “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ሲል ኢየሱስን ጠይቆት ነበር። ኢየሱስ በቀላሉ መልሱን ሊነግረው ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ “በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?” ሲል በመጠየቅ ሰውዬው የራሱን አመለካከት እንዲገልጽ አድርጓል። ሰውዬው በትክክል መለሰ። ትክክለኛውን መልስ ስለሰጠ ውይይታቸው በዚያው አበቃ ማለት ነው? አላበቃም። ኢየሱስ እንዲናገር አጋጣሚ ስለሰጠው ሰውዬው ራሱን ሊያጸድቅ የሚፈልግ መሆኑን የሚጠቁም አንድ ጥያቄ አነሳ። “ባልንጀራዬስ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስ ባልንጀራ የሚለውን ቃል ፍቺ በቀጥታ ቢነግረው አይሁዳውያን ለአሕዛብና ለሳምራውያን ከነበራቸው አመለካከት የተነሣ ሰውዬው ወደ ክርክር ሊያመራ ስለሚችል አንድ ምሳሌ በመንገር ስለ ጉዳዩ እንዲያስብ አድርጎታል። ምሳሌው በወንበዴዎች ንብረቱ ተዘርፎና ተደብድቦ የወደቀን ሰው አንድ ካህንና አንድ ሌዋዊ አይተው እንዳላዩ ሲያልፉት ሌላ ደግ ሳምራዊ ግን እንደረዳው የሚገልጽ ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ሰውዬው የምሳሌውን ቁም ነገር መረዳቱን ለማረጋገጥ ቀላል ጥያቄ አቀረበለት። ኢየሱስ ያስረዳበት መንገድ ሰውዬው ‘ባልንጀራ’ የሚለውን ቃል ከዚያ በፊት አስቦት በማያውቀው አቅጣጫ እንዲያስተውል አስችሎታል። (ሉቃስ 10:25-37) ይህ ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም የማስተማር ዘዴ ነው! አንተ ብቻ ከምትናገር ይልቅ ጥያቄዎችንና ምሳሌዎችን በዘዴ ተጠቅመህ ስለ ጉዳዩ እንዲያስብ ማበረታታትን ልመድ።
በምክንያት ማስረዳት። ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ በሚገኝ ምኩራብ ገብቶ ሲናገር አድማጮቹ ከሚያምኑበት መጽሐፍ በመጥቀስ ብቻ አልተወሰነም። ነጥቡን ያብራራ፣ በማስረጃ አስደግፎ ያቀርብ እንዲሁም የትምህርቱን ጠቀሜታ ያስረዳ እንደነበር ሉቃስ ዘግቧል። ከዚህ የተነሳ ‘አንዳንዶቹ አማኞች ሆነው ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባብረዋል።’—ሥራ 17:1-4
የምትናገረው ለማንም ይሁን ለማን እንዲህ ዓይነት አሳማኝ ማብራሪያ ጥሩ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ለዘመዶችህ ስትመሠክር፣ ከሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ ከሚማሩት ጋር ስትነጋገር፣ አገልግሎት ላይ ካገኘኸው ሰው ጋር ስትወያይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ወይም በጉባኤ ንግግር ስትሰጥ ይህንን ዘዴ ልትጠቀም ትችላለህ። ጥቅስ ስታነብብ መልእክቱ ለአንተ ግልጽ የሆነልህን ያህል ለሌላው ሰው ግልጽ ላይሆን ይችላል። የምትሰጠው ማብራሪያ ወይም ነጥቡን ከአድማጮችህ ሁኔታ ጋር የምታዛምድበት መንገድ ግትር አቋም ያለህ ሊያስመስልብህ ይችላል። ከጥቅሱ መካከል ቁልፍ የሆኑትን ቃላት መርጦ ማብራራቱ ይሻል ይሆን? በዙሪያው ያለውን ሐሳብ በመጥቀስ ወይም ከጉዳዩ ጋር የሚያያዝ ሌላ ጥቅስ በመጠቀም ተጨማሪ ማስረጃ ማቅረብ ትችል ይሆን? የተናገርከው ሐሳብ ምክንያታዊ መሆኑን እንዲያስተውሉ የሚረዳ አንድ ምሳሌ መናገር ትችል ይሆን? ወይስ አድማጮችህ ስለ ጉዳዩ እንዲያስቡ የሚያደርግ ጥያቄ መጠቀም ይሻላል? እንዲህ ያለው አሳማኝ አቀራረብ ጥሩ አመለካከት እንዲኖራቸውና ሰፋ አድርገው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።