ጥናት 53
አድማጮችን የሚያበረታታ ንግግር
የአምላክ አገልጋዮች የሚገጥማቸው ችግር ምንም ይሁን ምን ከክርስቲያን ጉባኤ ማበረታቻ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ በተለይ ሽማግሌዎች የሚያቀርቧቸው ንግግሮችና የሚሰጧቸው ምክሮች የሚያበረታቱ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል።—ኢሳ. 32:2
ሽማግሌ ከሆንክ የምታቀርባቸው ንግግሮች መንፈስን የሚያድሱና የሚያጽናኑ ናቸው? ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል የሚጥሩትን ይበልጥ የሚያበረታቱ ናቸው? ብዙ ሰዎች ግድየለሽና ተቃዋሚዎች ቢሆኑም እንኳ ክርስቲያኖች የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም እንዲጸኑ ኃይል የሚሰጡ ናቸው? ከአድማጮችህ መካከል የመንፈስ ጭንቀትና ከባድ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ያለባቸው ወይም መድኃኒት ባልተገኘለት ከባድ ሕመም የሚሰቃዩ ቢኖሩስ? ወንድሞችህን ‘በአፍህ ቃል ማበረታታት’ ትችላለህ።—ኢዮብ 16:5
ንግግር ስትሰጥ አድማጮችህ ከይሖዋና ከዝግጅቶቹ ተስፋና ብርታት እንዲያገኙ መርዳት የምትችልበት አጋጣሚ አለህ።—ሮሜ 15:13፤ ኤፌ. 6:10
ይሖዋ ያደረጋቸውን ነገሮች መለስ ብለው እንዲያስቡ አድርግ። ሌሎችን ማበረታታት የሚቻልበት አንዱ ትልቁ መንገድ ጥንት ይሖዋ ሕዝቦቹን እንዴት እንደረዳቸው መግለጽ ነው።—ሮሜ 15:4
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ ኢያሱን ‘እንዲያደፋፍረው’ እና ‘እንዲያጸናው’ ይሖዋ ነግሮት ነበር። በወቅቱ ተስፋይቱ ምድር ገና በጠላቶቻቸው እጅ ነበረች። ታዲያ ሙሴ ኢያሱን ያበረታታው እንዴት ነበር? ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ይሖዋ ያደረገላቸውን ነገር ሁሉ ለመላው የእስራኤል ብሔር ተርኳል። በዚህ ጊዜ ኢያሱም ያዳምጥ ነበር። (ዘዳ. 3:28፤ 7:18) ይሖዋ በአሞራውያን ላይ ድል እንዲቀዳጁ እንደረዳቸውም ገልጾላቸዋል። ከዚያም ሙሴ ኢያሱን “ጽና፣ አይዞህ” ሲል አበረታቶታል። (ዘዳ. 31:1-8) አንተስ ወንድሞችህን በምታበረታታበት ጊዜ ይሖዋ ያደረገላቸውን መለስ ብለው እንዲያስቡ በማድረግ እምነታቸው እንዲታደስ ትረዳቸዋለህ?
አንዳንዶች ባሉባቸው ችግሮች ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ የይሖዋ መንግሥት የሚያመጣቸውን በረከቶች የሚያገኙ መስሎ አይታያቸው ይሆናል። ይሖዋ የሰጠው ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር ልታስገነዝባቸው ይገባል።—ኢያሱ 23:14
በአንዳንድ አገሮች ወንድሞቻችን ምሥራቹን እንዳይሰብኩ ታግደዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ያጋጠማቸውን ተሞክሮ በመጠቀም ወንድሞቻቸውን ማበረታታት ይችላሉ። (ሥራ 4:1–5:42) እንዲሁም አምላክ በሕዝቡ ጉዳይ እጁን እንዴት ጣልቃ እንዳስገባ የሚገልጸውን የአስቴር መጽሐፍ ታሪክ መናገር ወንድሞች ድፍረት እንዲያገኙ ሊረዳቸው ይችላል።
አንዳንድ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ነገር ግን ምንም ለውጥ የማያደርጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የቀድሞ አኗኗራቸው በጣም መጥፎ ከመሆኑ የተነሳ አምላክ ፈጽሞ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ይሰማቸው ይሆናል። ይሖዋ ለንጉሥ ምናሴ ምን እንዳደረገለት ልትነግራቸው ትችላለህ። (2 ዜና 33:1-16) ወይም ደግሞ አኗኗራቸውን በማስተካከል ክርስቲያን ስለሆኑትና በአምላክ ፊት እንደ ጻድቅ ስለተቆጠሩት የቆሮንቶስ ሰዎች ልትገልጽላቸው ትችል ይሆናል።—1 ቆሮ. 6:9-11
ችግር የሚደርስባቸው የአምላክን ሞገስ ስላጡ እንደሆነ የሚሰማቸው ሰዎች ይኖራሉ? ኢዮብ የደረሰበትን መከራና ለአምላክ ያለውን ታማኝነት እስከ መጨረሻ ድረስ በመጠበቁ ያገኛቸውን በረከቶች መለስ ብለው እንዲያስቡ ልታደርግ ትችላለህ። (ኢዮብ 1:1-22፤ 10:1፤ 42:12, 13፤ መዝ. 34:19) ወደ ኢዮብ የመጡት የሐሰት አጽናኞች ኢዮብ አንድ ኃጢአት ሠርቶ መሆን አለበት የሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደርሰው ነበር። (ኢዮብ 4:7, 8፤ 8:5, 6) በሌላ በኩል ደግሞ ጳውሎስና በርናባስ ደቀ መዛሙርቱ ‘በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ ሲመክሩና ሲያበረታቱ’ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” ብለዋል። (ሥራ 14:21, 22) ዛሬም በተመሳሳይ ሁሉም ክርስቲያኖች በመከራ መጽናታቸው ግድ እንደሆነና ይህም በአምላክ ዘንድ ትልቅ ዋጋ እንዳለው በመግለጽ መከራ የሚደርስባቸውን ማጽናናት ትችላለህ።—ምሳሌ 27:11፤ ማቴ. 24:13፤ ሮሜ 5:3, 4፤ 2 ጢሞ. 3:12
አድማጮችህ ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም በራሳቸው ሕይወት ሳይቀር ያዩትን ነገር መለስ ብለው እንዲያስቡ በማድረግ አበረታታቸው። አንተ ትንሽ ብቻ ከመራሃቸው ይሖዋ በግል ያደረገላቸው ብዙ ነገር ወደ አእምሮአቸው ሊመጣ ይችላል። መዝሙር 32:8 [አ.መ.ት ] እንዲህ ይላል:- “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” ይሖዋ ከዚህ ቀደም እንዴት እንደመራቸው ወይም ኃይል እንደሰጣቸው እንዲያስቡ በማድረግ እንደሚንከባከባቸውና ወደፊትም ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥማቸው እንዲወጡት እንደሚረዳቸው ከራሳቸው ተሞክሮ እንዲያስተውሉ ልታደርጋቸው ትችላለህ።—ኢሳ. 41:10, 13፤ 1 ጴጥ. 5:7
አምላክ እያደረገልን ባለው ነገር እንደምትደሰት አሳይ። ወንድሞችህን ለማበረታታት ስትፈልግ ይሖዋ ዛሬ እያደረገልን ስላሉት ነገሮች እንዲያስቡ አድርግ። አንተ ራስህ በእነዚህ ነገሮች እንደምትደሰት በሚያሳይ መንገድ የምትናገር ከሆነ እነርሱም ተመሳሳይ ስሜት ያድርባቸዋል።
ይሖዋ የኑሮ ጭንቀቶችን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት እንደሆነ አስረዳ። ሕይወታችንን መምራት የምንችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ያስተምረናል። (ኢሳ. 30:21) የወንጀል፣ የፍትሕ መጓደል፣ የድህነት፣ የበሽታና የሞት መንስኤያቸው ምን እንደሆነና እነዚህን ነገሮች እንዴት እንደሚያስወግድልን ይነግረናል። ፍቅር ባለበት የወንድማማች ማኅበር ውስጥ እንድንታቀፍ አድርጓል። ውድ የሆነ የጸሎት መብት ሰጥቶናል። የእርሱ ምሥክሮች የመሆንም ታላቅ መብት አግኝተናል። ክርስቶስ በሰማይ ንጉሣዊ ሥልጣኑን እንደጨበጠና የዚህ አሮጌ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች በፍጥነት ወደ ፍጻሜያቸው እየገሰገሱ እንዳሉ እንድናስተውል ረድቶናል።—ራእይ 12:1-12
ከእነዚህ ሁሉ በረከቶች በተጨማሪ የጉባኤ፣ የወረዳና የልዩ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎቻችንን ጥቀስ። ለእነዚህ ዝግጅቶች ልባዊ አድናቆት እንዳለህ በሚያሳይ መንገድ በመናገር ሌሎችም ከወንድሞቻቸው ጋር መሰብሰብን በቁም ነገር እንዲያዩት ማበረታታት ትችላለህ።—ዕብ. 10:23-25
ይሖዋ በአገልግሎት የምናደርገውን ጥረት እንደባረከው የሚያሳዩ ሪፖርቶችም የብርታት ምንጭ ይሆናሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ በመንገዳቸው ላይ ላገኟቸው ወንድሞች ስለ አሕዛብ መለወጥ የሚገልጹ ሪፖርቶችን በመንገር ‘እጅግ ደስ አሰኝተዋቸው ነበር።’ (ሥራ 15:3) አንተም ገንቢ ተሞክሮዎችን በመናገር ወንድሞችህን ልታስደስታቸው ትችላለህ።
በተጨማሪም ወንድሞች የሚያደርጉትን ነገር ስናደንቅላቸው ይበረታታሉ። በአገልግሎት ለሚያደርጉት ተሳትፎ አመስግናቸው። በዕድሜ መግፋት ወይም በሕመም ምክንያት ብዙ እንቅስቃሴ ማድረግ የማይችሉትን ሆኖም በታማኝነት የጸኑትን አመስግናቸው። ይሖዋ ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር እንደማይረሳ እንዲያስቡ አድርግ። (ዕብ. 6:10) የተፈተነ እምነት በዋጋ የማይተመን ውድ ሀብት ነው። (1 ጴጥ. 1:6, 7) ወንድሞች ይህን እንዲያስታውሱ ማድረግ ያስፈልጋል።
ስለ ወደፊቱ ተስፋ ከልብ በመነጨ ስሜት ተናገር። በአምላክ መንፈስ አማካኝነት የተነገሩት ተስፋዎች ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ ትልቅ የብርታት ምንጭ ናቸው። አብዛኞቹ አድማጮችህ ስለ እነዚህ ተስፋዎች በተደጋጋሚ ሰምተው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በአድናቆት የምትናገር ከሆነ እነዚህ ተስፋዎች ለአድማጮችህ ሕያው ሊሆኑላቸው፣ እንደሚፈጸሙ ትምክህት ሊያድርባቸውና ልባቸው በአድናቆት ሊሞላ ይችላል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ያገኘኸውን ትምህርት ሥራ ላይ ማዋልህ በዚህ መንገድ እንድትናገር ሊረዳህ ይችላል።
ይሖዋ ሕዝቡን በማጽናናትና በማበረታታት ረገድ አቻ የሌለው አምላክ ነው። ይሁን እንጂ አንተም የእርሱን ምሳሌ በመኮረጅ ሌሎችን ማበረታታትና ማጽናናት ትችላለህ። ለጉባኤው ንግግር የምትሰጥበት አጋጣሚ ስታገኝ ይህን ለማድረግ ጣር።