ጥናት 52
ልብ የሚነካ ምክር
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ‘ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት መምከር’ ይጠበቅባቸዋል። (ቲቶ 1:9) አንዳንድ ጊዜ ከባድ ችግሮችን ለመፍታት ሲሉ ምክር መስጠት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ምክሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ሽማግሌዎች ‘ለመምከር ተጠንቀቅ’ የሚለውን ማሳሰቢያ መከተል ይኖርባቸዋል። (1 ጢሞ. 4:13) ውይይታችን በአብዛኛው የሚያተኩረው በሽማግሌዎች ወይም እዚህ መብት ላይ ለመድረስ በሚጣጣሩት ወንድሞች ላይ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠኑ ደግሞ ተማሪዎቻቸውን መምከር እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው። በእነዚህ አጋጣሚዎችም ቢሆን ምክር ለመስጠት የሚያገለግሉት መመሪያዎች ተመሳሳይ ናቸው።
ምክር መስጠት የሚያስፈልግበት ጊዜ። ምክር መስጠት የሚያስፈልገው መቼ እንደሆነ ለማስተዋል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምክር የተሰጠባቸውን አጋጣሚዎች መመርመሩ ጠቃሚ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ሽማግሌዎች የእግዚአብሔርን መንጋ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክሯል። (1 ጴጥ. 5:1, 2) ጳውሎስ ወጣት ወንዶች ‘ራሳቸውን የሚገዙ’ ይሆኑ ዘንድ ምከራቸው ሲል ለቲቶ ጽፎለታል። (ቲቶ 2:6) ጳውሎስ ክርስቲያኖች ‘አንድ ንግግር እንዲናገሩ’ እንዲሁም በወንድሞች መካከል መለያየትን ከሚፈጥሩ ሰዎች ፈቀቅ እንዲሉ አጥብቆ አሳስቧል። (1 ቆሮ. 1:10፤ ሮሜ 16:17፤ ፊልጵ. 4:2) እንዲሁም በተሰሎንቄ ጉባኤ የነበሩት ክርስቲያኖች ያደርጉት የነበረውን መልካም ነገር አንስቶ ቢያመሰግናቸውም የተሰጣቸውን መመሪያ ይበልጥ እንዲሠሩበት መክሯቸዋል። (1 ተሰ. 4:1, 10) ጴጥሮስ ክርስቲያን ወንድሞቹ ‘ከሥጋ ምኞት እንዲርቁ ለምኗቸዋል።’ (1 ጴጥ. 2:11) ይሁዳ በብልግና የተጠላለፉ ኃጢአተኛ ሰዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እንዳለ በማስተዋል ወንድሞቹ ‘ለእምነት እንዲጋደሉ’ መክሯቸዋል። (ይሁዳ 3, 4) ክርስቲያኖች በአጠቃላይ በኃጢአት መታለል ልባቸው እልከኛ እንዳይሆን እርስ በርሳቸው እንዲመካከሩ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (ዕብ. 3:13) ጴጥሮስ በክርስቶስ የማያምኑትን አይሁዳውያን “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” ሲል መክሯል።—ሥራ 2:40
ልብ የሚነካ ምክር ለመስጠት የሚያስፈልጉት ባሕርያት ምንድን ናቸው? አንድ ሰው ሌሎችን ሳይጫን ወይም ሳይቆጣ ለሥራ የሚያነሳሳ ምክር መስጠት የሚችለው እንዴት ነው?
“በፍቅር።” ምክር የምንሰጠው “በፍቅር” ካልሆነ ምክር ተቀባዩ እያወገዝነው እንዳለ ሊሰማው ይችላል። (ፊልሞ. 9) እርግጥ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚጠይቅ ነገር ሲኖር አነጋገራችን ያንን ስሜት የሚያንጸባርቅ መሆን ይኖርበታል። ለስለስ ያለ አነጋገር የመልእክቱን ኃይል ሊያዳክም ይችላል። በተጨማሪም ከልብ በተቆርቋሪነት ስሜት መናገር አስፈላጊ ነው። በፍቅር መናገር አድማጮች እርምጃ እንዲወስዱ እንደሚያነሳሳ የታወቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱና አብረውት ስለሚያገለግሉት ባልንጀሮቹ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሲናገር ‘እየመከርን አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁ’ ብሏል። (1 ተሰ. 2:11) እነዚህ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ወንድሞችን ይረዱና ያበረታቱ የነበረው በፍቅር ነው። ለአድማጮችህ የምትናገረው ነገር ለእነርሱ ካለህ ልባዊ አሳቢነት የመነጨ መሆን ይኖርበታል።
ዘዴኛ ሁን። ዓላማህ ምክር የምትሰጣቸውን ሰዎች ለተግባር ማነሳሳት ስለሆነ አነጋገርህ ምክሩን እንዳይቀበሉ የሚያደርጋቸው መሆን የለበትም። ሆኖም “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” ከመንገር ወደኋላ ማለት የለብህም። (ሥራ 20:27) ምክር ሲሰጣቸው የሚያደንቁ ሰዎች ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉ በደግነት ስላሳሰብካቸው ብቻ አይከፉም ወይም ለአንተ ያላቸው ፍቅር አይቀንስም።—መዝ. 141:5
ብዙውን ጊዜ ምክር ከመስጠትህ በፊት አንዳንድ ነገሮችን ለይተህ በመጥቀስ ከልብ ማመስገንህ ጠቃሚ ነው። ወንድሞችህ የሚያደርጓቸውን ይሖዋን የሚያስደስቱ ብዙ መልካም ነገሮች አስብ። በሥራ የሚገለጠው እምነታቸው፣ በሙሉ ልብ እንዲያገለግሉ የሚያነሳሳቸው ፍቅር እና መከራን ተቋቁመው መጽናታቸው ካሏቸው መልካም ጎኖች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። (1 ተሰ. 1:2-8፤ 2 ተሰ. 1:3-5) ይህም ወንድሞችህ እንደምታደንቃቸውና ስሜታቸውን እንደምትረዳላቸው እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ ከዚያ ቀጥሎ የምትሰጣቸውን ምክር በደስታ ይቀበላሉ።
‘በትዕግሥት።’ ምክር መሰጠት ያለበት ‘በትዕግሥት’ ነው። (2 ጢሞ. 4:2) ይህ ምን ማድረግን ይጠይቃል? ትዕግሥት ስህተትን ወይም የሚያስቆጣን ነገር መቻልን ይጨምራል። ትዕግሥተኛ ሰው አድማጮቹ የሰጣቸውን ምክር እንደሚሠሩበት ተስፋ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት መንፈስ ይዘህ ምክር የምትሰጥ ከሆነ አድማጮችህ ስለ እነርሱ አሉታዊ አመለካከት እንዳለህ አድርገው አያስቡም። ወንድሞችህና እህቶችህ ይሖዋን ለማገልገል አቅማቸው የፈቀደላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ በእነርሱ ላይ እምነት ካለህ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ይበልጥ ይበረታታሉ።—ዕብ. 6:9
“ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት።” አንድ ሽማግሌ “ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት” ሊመክር የሚችለው እንዴት ነው? ‘በሚያስተምርበት ጊዜ በታመነው ቃል በመጽናት’ ነው። (ቲቶ 1:9) የግል አስተያየትን ከመሰንዘር ይልቅ የአምላክን ቃል ተጠቅመህ ልባቸውን ለመንካት ሞክር። የምትሰጠውን ምክር በተመለከተ ማስተዋል ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አድርገህ ተጠቀም። ምክር የምትሰጥበትን ጉዳይ በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ ሥራ ላይ ማዋል ምን ጥቅም እንዳለው በዝርዝር ያዝ። በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ምክር ሳይቀበሉ መቅረት አሁንም ሆነ ወደፊት ምን መዘዝ እንደሚያስከትል በአእምሮህ በመያዝ ምክር የምትሰጠው ሰው ተገቢውን እርምጃ መውሰዱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳመን ተጠቀምበት።
አድማጮችህ ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንዴት ሊያደርጉት እንደሚገባ በግልጽ ማስረዳት መቻል ይኖርብሃል። ምክሩ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑንም ግልጽ አድርግላቸው። ውሳኔ በማድረግ ረገድ ጥቅሱ የሚሰጠው የተወሰነ ነፃነት ካለ እስከ ምን ድረስ እንደሆነ አብራራ። በመጨረሻ አድማጮችህ ምክሩን ሥራ ላይ ለማዋል ቁርጥ ያለ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያበረታታ ሐሳብ ተናግረህ ደምድም።
‘የመናገር ድፍረት’ ይኑርህ። አንድ ሰው ልብ የሚነካ ምክር መስጠት እንዲችል ‘በእምነት የመናገር ድፍረት’ ሊኖረው ይገባል። (1 ጢሞ. 3:13 የ1980 ትርጉም ) አንድ ሰው የመናገር ድፍረት እንዲያገኝ የሚያስችለው ምንድን ነው? ወንድሞቹ እንዲያደርጉት የሚመክረውን ነገር በተመለከተ ራሱ ‘መልካም ምሳሌ’ ሆኖ መገኘቱ ነው። (ቲቶ 2:6, 7፤ 1 ጴጥ. 5:3) ይህ ከሆነ አድማጮች ምክር ሰጪው ራሱ የማይሠራበትን ነገር እነርሱ እንዲያደርጉት እየገፋፋቸው እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። እርሱ ክርስቶስን ለመምሰል እንደሚጥር ሁሉ እነርሱም እርሱን መኮረጅ እንደሚችሉ ይገነዘባሉ።—1 ቆሮ. 11:1፤ ፊልጵ. 3:17
በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተና በፍቅር የተሰጠ ምክር ውጤቱ ያማረ እንደሚሆን የታወቀ ነው። የመምከር ኃላፊነት የተጣለባቸው ሁሉ ይህን ኃላፊነት በትጋት መወጣት ይኖርባቸዋል።—ሮሜ 12:8