ምዕራፍ አራት
ቤተሰባችሁን ማስተዳደር የምትችሉት እንዴት ነው?
1. በዘመናችን ቤተሰብን ማስተዳደር በጣም ከባድ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?
“የዚህ ዓለም መልክ ተለዋዋጭ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 7:31 NW) ከ1,900 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የተጻፉት እነዚህ ቃላት በዘመናችን በሚያስደንቅ ሁኔታ እየተፈጸሙ ነው! የዓለም ሁኔታ፣ በተለይ ደግሞ የቤተሰብን ሕይወት በተመለከተ ያሉት ሁኔታዎች እየተለወጡ ነው። ከ40 ወይም ከ50 ዓመት በፊት ተቀባይነት የነበራቸው ወይም ደግሞ ባሕላዊ የነበሩ ነገሮች በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው ተቀባይነት የላቸውም። በዚህም ምክንያት ቤተሰብን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር እጅግ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሰጡትን ምክር ከተከተላችሁ ይህን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም ትችላላችሁ።
እንደ አቅማችሁ ኑሩ
2. በቤተሰብ ውስጥ ውጥረት ሊፈጥሩ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
2 በዛሬው ጊዜ ብዙዎቹ ሰዎች ቀላል በሆነ የቤተሰብ ኑሮ ረክተው የሚኖሩ አይደሉም። የንግዱ ዓለም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የሚሄዱ በርካታ ምርቶችን እያመረተ በማስታወቂያ ዘዴዎቹ በመጠቀም ሕዝቡን ለመማረክ እየጣረ በመሆኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ አባቶችና እናቶች እነዚህን ምርቶች ለመግዛት ሲሉ ለብዙ ሰዓታት ይሠራሉ። ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ወላጆች ደግሞ ለቤተሰባቸው የዕለት ጉርስ የሚሆን ነገር ለማግኘት በየቀኑ ላይ ታች ይዋትታሉ። የግድ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ለማሟላት ሲሉ ብቻ ቀደም ሲል በሥራ ያሳልፉት ከነበረው በጣም የበለጠ ጊዜ ለመሥራት ምናልባትም ሁለት የተለያዩ ሥራዎች ለመያዝ ይገደዳሉ። ሌሎች ደግሞ ሥራ አጥነት በጣም የተስፋፋ ችግር በመሆኑ አንድ ሥራ ቢያገኙ እንኳ ይደሰታሉ። አዎ፣ በአሁኑ ጊዜ ላሉት ቤተሰቦች ኑሮው ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም፤ ቢሆንም ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቤተሰቦች ሁኔታቸው የፈቀደላቸውን ያህል የቻሉትን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
3. ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸው መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? አንድ ሰው ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ ማዋሉ ቤተሰቡን በተሳካ ሁኔታ እንዲያስተዳድር ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ የኢኮኖሚ ተጽዕኖዎች ደርሰውበት ነበር። እነዚህን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም ባደረገው ጥረት አንድ ጠቃሚ ትምህርት ተምሯል፤ ይህንንም ለጓደኛው ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጾታል። “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) እርግጥ ነው፣ አንድ ቤተሰብ የሚያስፈልገው ምግብና ልብስ ብቻ አይደለም። የሚኖርበትም ቤት ያስፈልገዋል። ልጆቹም መማር ያስፈልጋቸዋል። የሕክምናና ሌሎች ወጪዎችም ይኖራሉ። ያም ሆኖ ግን ጳውሎስ በጻፋቸው ቃላት ላይ የተንጸባረቀው መሠረታዊ ሥርዓት ይሠራል። የምንፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለማሟላት ከመጣር ይልቅ በሚያስፈልጉን ነገሮች ብቻ የምንረካ ከሆነ ሕይወት አስቸጋሪ አይሆንብንም።
4, 5. አስቀድሞ ዕቅድ ማውጣት ቤተሰብን በማስተዳደር ረገድ ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?
4 ሌላው ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ የሚገኘው ነው። ኢየሱስ “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ኪሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 14:28) እዚህ ላይ ኢየሱስ አስቀድሞ ዕቅድ ስለ ማውጣት መናገሩ ነበር። ቀደም ሲል ባየነው አንድ ምዕራፍ ውስጥ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለመጋባት ያሰቡ ወጣት ወንዶችና ሴቶችን እንዴት እንደሚረዳቸው ተመልክተናል። ከጋብቻም በኋላ ቢሆን ቤተሰብን በማስተዳደር ረገድ ይህን ማድረጉ ጠቃሚ ነው። በዚህ ረገድ ዕቅድ ማውጣት ሲባል ያለውን ገቢ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም አስቀድሞ በማሰብ በጀት ማውጣትን ይጠይቃል። በዚህ መንገድ አንድ ቤተሰብ በየቀኑ ወይም ደግሞ በየሳምንቱ ለሚያስፈልጉ ነገሮች ገንዘብ በመመደብና እንደ አቅም በመኖር ወጪዎቹን መቆጣጠር ይችላል።
5 በአንዳንድ አገሮች እንዲህ ዓይነት በጀት ማውጣት ማለት የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮች ለመግዛት ሲባል በከፍተኛ ወለድ ገንዘብ ለመበደር ከመነሳሳት መቆጠብ ማለት ሊሆን ይችላል። በሌሎች አገሮች ደግሞ በክሬዲት ካርዶች አጠቃቀም ረገድ ራስን መግዛት ማለት ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 22:7) አንድን ዕቃ አስፈላጊነቱንና ዕቃውን መግዛታችን ሊያስከትለው የሚችለውን መዘዝ ሳናወጣና ሳናወርድ እንዲሁ ስላየነውና ስላማረን ብቻ ከመግዛት መቆጠብ ማለትም ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በጀት ማውጣት ገንዘብን በራስ ወዳድነት መንፈስ በቁማር፣ ትምባሆ በማጨስና ከልክ በላይ በመጠጣት ማባከን የቤተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሊጎዳው እንደሚችል በግልጽ ያሳያል። ከዚህም በላይ እነዚህ ድርጊቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይጋጫሉ።—ምሳሌ 23:20, 21, 29-35፤ ሮሜ 6:19፤ ኤፌሶን 5:3-5
6. በድህነት ለመኖር የተገደዱ ሰዎችን የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶች ሊረዷቸው ይችላሉ?
6 በድህነት ተቆራምደው ለመኖር የተገደዱ ሰዎችስ? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይህ ዓለም አቀፋዊ ችግር ጊዜያዊ መሆኑን ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል። ይሖዋ በፍጥነት እየተቃረበ ባለው አዲስ ዓለም ውስጥ ድህነትን፣ የሰውን ዘር እያሠቃዩ ካሉ ሌሎች መጥፎ ነገሮች ጋር በአንድነት ያስወግደዋል። (መዝሙር 72:1, 12-16) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ቢሆን እንኳ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በማለት ይሖዋ በገባው ቃል ስለሚያምኑ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አይቆርጡም። በመሆኑም አንድ አማኝ “ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም” በማለት በሙሉ ትምክህት መናገር ይችላል። (ዕብራውያን 13:5, 6) በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በዕለታዊ ኑሯቸው የተረጎሙና በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን ያስቀደሙ አምላኪዎቹን በብዙ መንገዶች ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:33) ከእነዚህም መካከል በርካታዎቹ የሚከተሉትን የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት በመናገር ለዚህ ምሥክርነት ሊሰጡ ይችላሉ:- “በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጒደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።”—ፊልጵስዩስ 4:12, 13
ሸክሙን መጋራት
ለቤተሰብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማሟላት ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ነው
7. በሥራ ላይ ከዋሉ፣ ቤተሰብን በተሳካ ሁኔታ በማስተዳደር ረገድ ሊጠቅሙ የሚችሉት የትኞቹ የኢየሱስ ቃላት ናቸው?
7 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መገባደጃ ላይ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:39) ይህን ምክር በቤተሰብ ውስጥ በሥራ ላይ ማዋል ቤተሰብን በማስተዳደር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ለመሆኑ ከማንም ይበልጥ የሚቀርቡን ውድ ባልንጀሮቻችን እነማን ናቸው? በቤተሰባችን ውስጥ ያሉት ባሎችና ሚስቶች፣ ወላጆችና ልጆች አይደሉምን? የቤተሰብ አባሎች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
8. ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ ሊገለጽ የሚችለው እንዴት ነው?
8 እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ይህን ማድረግ የሚችልበት አንዱ መንገድ የአቅሙን ያህል የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመሥራት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ነው። በመሆኑም ልጆች እንደ ልብሶችና አሻንጉሊቶች ያሉ ነገሮችን ከተጠቀሙባቸው በኋላ ወደየቦታቸው መመለስን መማር ይኖርባቸዋል። በየቀኑ ጠዋት ጠዋት አልጋን ማንጠፉ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ ሊሆን ቢችልም የቤተሰቡን ሥራ በማቃለል ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጥቃቅንና ጊዜያዊ የሆኑ ያልተስተካከሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ቤቱን ንጹሕ አድርጎ ለመያዝና ከምግብ በኋላ ዕቃዎቹን አንስቶ ለማጠብና ለማጽዳት ሁሉም በጋራ ተባብረው ሊሠሩ ይችላሉ። ስንፍናና ለራስ ጥቅም ብቻ ማሰብ፣ እንዲሁም ልግመኝነትና በፈቃደኝነት ተነሳስቶ አለመሥራት በሁሉም ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ምሳሌ 26:14-16) በሌላ በኩል ግን የእሺ ባይነትና የፈቃደኝነት መንፈስ የቤተሰቡን ሕይወት አስደሳች ያደርገዋል። “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል።”—2 ቆሮንቶስ 9:7
9, 10. (ሀ) ብዙውን ጊዜ ትዳር በያዘች ሴት ጫንቃ ላይ ምን ሸክም ይወድቃል? ይህን ሸክም ማቅለል የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) የቤት ውስጥ ሥራን በተመለከተ ምን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
9 አሳቢነትና ፍቅር በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥረውን ሁኔታ ለማስወገድ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ሲወርድ ሲዋረድ በቆየው ባህል መሠረት እናቶች የቤተሰብ ሕይወት ምሰሶዎች ሆነው ቆይተዋል። ልጆችን ይንከባከባሉ፣ ቤታቸውን ያጸዳሉ፣ የቤተሰባቸውን ልብስ ያጥባሉ፣ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ይሸምታሉ፣ እንዲሁም ምግብ ያበስላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ አገሮች ባለው ባህል ሴቶች እርሻ ላይ ተሠማርተው ይሠራሉ፣ ምርቱን ገበያ ሄደው ይሸጣሉ፣ ወይም ደግሞ የቤተሰቡን በጀት በሌሎች መንገዶች ይደጉማሉ። ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዲህ ዓይነት ልማድ በሌለባቸው አገሮችም እንኳ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ትዳር የያዙ ሴቶች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ሲሉ ተቀጥረው ለመሥራት ይገደዳሉ። በእነዚህ የተለያዩ መስኮች ተሠማርታ በትጋት የምትሠራ ሚስትና እናት ልትመሰገን ይገባታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰችው ‘ባለሙያ ሚስት’ [የ1980 ትርጉም] ትጉህና ታታሪ ናት። “የሀኬትንም እንጀራ አትበላም።” (ምሳሌ 31:10, 27) ይህ ማለት ግን በቤት ውስጥ ያለውን ሥራ መሥራት ያለባት እሷ ብቻ ነች ማለት አይደለም። ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ ከቤት ውጪ በየሥራ ቦታቸው ተሠማርተው ቀኑን ሙሉ ሲሠሩ ከዋሉ በኋላ ባልየውና የተቀሩት የቤተሰብ አባላት ሲያርፉና ሲዝናኑ በቤት ውስጥ ያለውን ሥራ ሚስትየዋ ብቻዋን መሸከም ይኖርባታልን? በፍጹም እንዲህ መሆን የለበትም። (ከ2 ቆሮንቶስ 8:13, 14 ጋር አወዳድር።) ከዚህ ይልቅ፣ ለምሳሌ እናትየዋ ምግብ እያዘጋጀች ከሆነ ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት ማዕዱን በማቀራረብ፣ መገዛት ያለበት ነገር ካለ ሄደው በመግዛት ወይም ደግሞ አንዳንድ ነገሮችን በማጽዳት ቢረዷት ደስ ሊላት ይችላል። አዎ፣ ሁሉም ሸክሙን ሊጋሩ ይችላሉ።—ከገላትያ 6:2 ጋር አወዳድር።
10 አንዳንዶች “በአገራችን ወንድ ልጅ እንዲህ ዓይነት ሥራ አይሠራም፤ ነውር ነው” ይሉ ይሆናል። ይህ እውነት ሊሆን ይችላል፤ ግን ሁኔታውን ትንሽ ቆም ብለን ብናስብበት ጥሩ አይሆንምን? ይሖዋ አምላክ ቤተሰብን ባቋቋመ ጊዜ ሴቶች ብቻ ሊሠሯቸው የሚገቡ ሥራዎች አሉ የሚል መመሪያ አልሰጠም። በአንድ ወቅት ታማኙ አብርሃም ከይሖዋ የተላኩ ልዩ መልእክተኞች ወደ ቤቱ በመጡ ጊዜ ለእነርሱ የሚሆን ምግብ በማዘጋጀትና በማቅረብ ራሱም በቀጥታ በሥራው ተሳትፎ ነበር። (ዘፍጥረት 18:1-8) መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኤፌሶን 5:28) ባልየው ሥራ ውሎ ሲመጣ የሚደክመውና ማረፍ የሚፈልግ ከሆነ ሚስትየዋስ ልክ እንደሱ፣ እንዲያውም ከእሱ ይበልጥ ሊደክማትና ዕረፍት ሊያስፈልጋት አይችልምን? (1 ጴጥሮስ 3:7) እንግዲያው ባልየው በቤት ውስጥ ሥራ ቢያግዛት ተገቢና ፍቅራዊ ድርጊት አይሆንምን?—ፊልጵስዩስ 2:3, 4
11. ኢየሱስ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ጥሩ ምሳሌ የተወው በምን መንገድ ነው?
11 ኢየሱስ አምላክንም ሆነ አብረውት የነበሩትን አጋሮቹን በማስደሰት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ምንም እንኳ ትዳር መሥርቶ የማያውቅ ቢሆንም ለባሎች፣ እንዲሁም ለሚስቶችና ለልጆች ጥሩ ምሳሌ ነው። ስለ ራሱ ሲናገር “የሰው ልጅ [ሌሎችን] ሊያገለግል . . . እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ብሏል። (ማቴዎስ 20:28) ሁሉም የቤተሰብ አባሎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካዳበሩ ቤተሰቡ ምንኛ ደስተኛ እንደሚሆን አስቡት!
ንጽሕና—እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12. ይሖዋ፣ የሚያገለግሉት ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል?
12 ቤተሰብን በማስተዳደር ረገድ ጥሩ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት በ2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ የሚገኘው ነው። ጥቅሱ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ይላል። እነዚህን በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ቃላት የሚታዘዙ ሰዎች “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ” በሚፈልገው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያገኛሉ። (ያዕቆብ 1:27) ቤተሰባቸውም ከዚህ ጋር የተያያዙ ጥቅሞችን ያገኛል።
13. ቤተሰብን በማስተዳደር ረገድ ንጽሕና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በሽታና ሕመም የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ያረጋግጥልናል። ያ ጊዜ ሲደርስ “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።” (ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:4, 5) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን እያንዳንዱ ቤተሰብ በየጊዜው ከበሽታ ጋር መታገል ይኖርበታል። ጳውሎስና ጢሞቴዎስም እንኳ ታመው ነበር። (ገላትያ 4:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ይሁን እንጂ የሕክምና ጠበብት ብዙ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል ይናገራሉ። ጥበበኛ የሆኑ ቤተሰቦች ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ርኩሰትን ካስወገዱ ልንከላከላቸው ከምንችላቸው አንዳንድ በሽታዎች መጠበቅ ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።—ከምሳሌ 22:3 ጋር አወዳድር።
14. የሥነ ምግባር ንጽሕና ቤተሰብን ከበሽታ ሊጠብቅ የሚችለው በምን መንገድ ነው?
14 መንፈሳዊ ንጽሕና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናንም ይጨምራል። በሰፊው እንደሚታወቀው መጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ያሉት ከመሆኑም በላይ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት ያወግዛል። “ሴሰኞች ቢሆኑ . . . ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) በሥነ ምግባር ባዘቀጠው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች እነዚህን ጥብቅ መሥፈርቶች መከተላቸው በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋቸው አምላክን ከማስደሰቱም በተጨማሪ ቤተሰባቸው እንደ ኤድስ፣ ቂጥኝና ጨብጥ ከመሳሰሉት የአባለዘር በሽታዎች እንዲጠበቅ ያደርጋል።—ምሳሌ 7:10-23
15. የአካላዊ ንጽሕና ጉድለት ለበሽታ ሊያጋልጥ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ስጡ።
15 ‘ሥጋን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራስን ማንጻት’ ቤተሰቡ ከሌሎች በሽታዎች እንዲጠበቅ ያደርገዋል። ብዙ በሽታዎች የሚከሰቱት በአካላዊ ንጽሕና ጉድለት ነው። የማጨስ ልማድ ለዚህ አንዱ ዋነኛ ምሳሌ ነው። ማጨስ ሳንባን፣ ልብስንና አየርን መበከል ብቻ ሳይሆን ሰዎች እንዲታመሙም ያደርጋል። በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ትምባሆ በማጨሳቸው ምክንያት ይሞታሉ። እስቲ አስቡት:- ‘ሥጋን የሚያረክስ’ ነገር ቢያስወግዱ ኖሮ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ ባልታመሙና ያለ ጊዜያቸው በሞት ባልተቀጩ ነበር!
16, 17. (ሀ) እስራኤላውያን ከአንዳንድ በሽታዎች እንዲጠበቁ የረዳቸው የትኛው የይሖዋ ሕግ ነው? (ለ) ከዘዳግም 23:12, 13 በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት በሁሉም ቤተሰቦች ውስጥ ሥራ ላይ ሊውል የሚችለው እንዴት ነው?
16 አንድ ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። ወደ 3,500 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት አምላክ ለእስራኤል ሕዝብ የአምልኮ ሥርዓታቸውንና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን ማደራጀት እንዲችሉ ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። ይህ ሕግ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ የንጽሕና አጠባበቅ መመሪያዎችን የያዘ ስለነበር ሕዝቡ ከበሽታ እንዲጠበቁ ረድቷቸዋል። ከእነዚህ ሕጎች አንዱ እንዴት መጸዳዳት እንዳለባቸው የሚገልጽ ነበር፤ በሕጉ መሠረት ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ እንዳይበከል ከሰፈሩ ውጪ ባለ ሥፍራ ጉድጓድ ቆፍረው መጸዳዳትና አፈሩን መልሰው መሸፈን ነበረባቸው። (ዘዳግም 23:12, 13) ይህ ጥንታዊ ሕግ በዛሬው ጊዜም የሚሠራ ጥሩ ምክር ነው። በአሁኑ ዘመንም እንኳ ሰዎች ይህን ሥርዓት ባለመከተላቸው ይታመማሉ፣ ከዚያም አልፎ ይሞታሉ።a
17 ለእስራኤላውያን ተሰጥቶ ከነበረው ከዚህ ሕግ በስተጀርባ ካለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መንገድ የአንድ ቤተሰብ መታጠቢያ ቤትና መጸዳጃ መኖሪያው ውስጥ ሆነም አልሆነ ንጹሕ መሆንና በጀርም ማጥፊያ ኬሚካሎች መጽዳት ይኖርበታል። መጸዳጃው በንጹሕ ሁኔታ ካልተያዘና የማይሸፈን ከሆነ ዝንቦች ሊሰፍሩበትና ጀርሞቹን በቤት ውስጥ ወዳሉ ሌሎች ቦታዎች አልፎ ተርፎም በምንበላው ምግብ ላይ ሊያዛምቱ ይችላሉ! ከዚህም በተጨማሪ ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ከተጸዳዱ በኋላ እጆቻቸውን መታጠብ ይኖርባቸዋል። አለዚያ ጀርሞቹን በእጆቻቸው ይዘው ሊመለሱ ይችላሉ። አንዲት ፈረንሳዊት ዶክተር እንደገለጹት እጅን መታጠብ “አሁንም ቢሆን ከምግብ መፈጨት፣ ከመተንፈሻ አካሎች ወይም ደግሞ ከቆዳ ጋር የተያያዙ አንዳንድ በሽታዎችን መከላከል ከሚቻልባቸው ከሁሉ የተሻሉ አስተማማኝ መንገዶች አንዱ ነው።”
ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚወጣው ወጪ ለመድኃኒት ከሚውለው ገንዘብ ያነሰ ነው
18, 19. ድህነት ባለባቸው አካባቢዎች ሳይቀር ቤትን በንጽሕና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምን ሐሳቦች ቀርበዋል?
18 ድህነት ባለባቸው አካባቢዎች ንጽሕናን መጠበቅ ከባድ እንደሆነ እሙን ነው። በእንዲህ ዓይነት አካባቢዎች የኖረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የሐሩሩ የአየር ንብረት ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚደረገውን ትግል በጣም አድካሚ ያደርገዋል። ንፋሱ አቧራውን እያነሳ ቤት ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ያለብሰዋል። . . . በከተሞችና በአንዳንድ ገጠራማ ቦታዎች በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለው የሕዝብ ቁጥር ለጤንነት አደገኛ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ክፍት የሆኑ የቆሻሻ መውረጃዎች፣ የሚያነሳው ያጣ የቆሻሻ ክምር፣ የቆሸሹ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ በሽታ የሚያዛምቱ አይጦች፣ በረሮዎችና ዝንቦች በየቦታው የሚታዩ ነገሮች ናቸው።”
19 በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች መካከል ሆኖ ንጽሕናን መጠበቅ ከባድ ነው። ቢሆንም ንጽሕና ሊደከምለት የሚገባው ነገር ነው። ሳሙናና ውኃ እንዲሁም ትንሽ ተጨማሪ ጥረት ለመድኃኒትና ለሆስፒታል የምናወጣውን ገንዘብ ያህል ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ነገሮች አይደሉም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለበት አካባቢ የምትኖሩ ከሆነ የራሳችሁን ቤትና ግቢ ንጹሕና ከእንስሳት እዳሪ የጠራ እንዲሆን የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። ወደ ቤታችሁ የሚወስደው መንገድ በክረምት ወራት በጣም የሚጨቀይ ከሆነ ወደ ቤታችሁ ጭቃ ይዛችሁ እንዳትገቡ መንገዱ ላይ ጠጠር ወይም ድንጋይ ማፍሰስ ትችላላችሁን? ወደ ቤት የመጣችሁት በእግራችሁ ከሆነ ጫማችሁን አውልቃችሁ ብትገቡ ጥሩ አይሆንምን? የምትጠቀሙበትም ውኃ እንዳይበከል መጠንቀቅ አለባችሁ። በየዓመቱ ከሚሞቱት ሰዎች መካከል ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ሚልዮን የሚሆኑት የሚሞቱት በቆሻሻ ውኃና በንጽሕና አጠባበቅ ጉድለት ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች እንደሆነ ይገመታል።
20. ቤቱ ንጹሕ እንዲሆን ከተፈለገ ኃላፊነቱን እነማን መጋራት አለባቸው?
20 ቤታችሁ ንጹሕ ሊሆን የሚችለው ሁሉም ሰው ማለትም እናት፣ አባት፣ ልጆችና ሊጠይቋችሁ የሚመጡ ሌሎች ሰዎች የየበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ነው። በኬንያ የምትኖር አንዲት የስምንት ልጆች እናት “ሁሉም የበኩላቸውን ድርሻ መወጣትን ተምረዋል” ብላለች። ንጹሕና የጸዳ ቤት ለመላው ቤተሰብ ጥሩ ስም ያተርፋል። “ድህነት ንጽሕናን ላለመጠበቅ ምክንያት አይሆንም” የሚል አንድ የስፓኝ አባባል አለ። አንድ ቤተሰብ የሚኖረው በትልቅ ቤት፣ በአፓርታማ፣ በትንሽ ቤትም ሆነ በደሳሳ ጎጆ ጥሩ ጤና እንዲኖረው የግድ ንጽሕናውን መጠበቅ አለበት።
ማበረታቻ የበለጠ ለመሥራት ያነሳሳል
21. ከምሳሌ 31:28 ጋር በሚስማማ መንገድ፣ ቤተሰብን ደስተኛ ለማድረግ የሚረዳው ነገር ምንድን ነው?
21 የምሳሌ መጽሐፍ ስለ ባለሙያ ሚስት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ልጆችዋ አድናቆታቸውን ይገልጡላታል፤ ባልዋም ያመሰግናታል።” (ምሳሌ 31:28 የ1980 ትርጉም) አንድን የቤተሰባችሁ አባል ካመሰገናችሁ ምን ያህል ጊዜ ሆኗችኋል? የጸደይ አበቦችና ተክሎች ሙቀትና ርጥበት ሲያገኙ እንደሚፈኩ ሁሉ እኛም እንደዚሁ ነን። ተክሎቹ በቂ ሙቀት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ እኛም ምስጋና ያስፈልገናል። አንዲት ሚስት ባልዋ ትጋት የተሞላበት ሥራዋንና ፍቅራዊ እንክብካቤዋን እንደሚያደንቅና አቅልሎ እንደማይመለከተው ማወቋ ያበረታታል። (ምሳሌ 15:23፤ 25:11) ሚስትም እንደዚሁ ባልዋ ከቤት ውጪም ሆነ በቤት ውስጥ ለሚያከናውነው ሥራ ብታመሰግነው ያስደስተዋል። ልጆችም በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤትና በክርስቲያናዊ ጉባኤዎች ላከናወኗቸው ሥራዎች ወላጆቻቸው ሲያመሰግኗቸው ይበረታታሉ። ትንሽ ምስጋና ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል! “አመሰግናለሁ” ብሎ መናገር ምንም የሚጠይቀው ወጪ የለም፤ የቤተሰቡን ሞራል በመገንባት ረገድ የሚያስገኘው ጥቅም ግን በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
22. ቤተሰብ ‘መጽናት’ እንዲችል ምን ያስፈልጋል? ይህን ማግኘት የሚቻለውስ እንዴት ነው?
22 ቤተሰብን ማስተዳደር ቀላል አይደለም፤ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉ። ያም ሆኖ ግን ቤተሰብን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር ይቻላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል” ይላል። (ምሳሌ 24:3) የቤተሰብ አባላት በሙሉ የአምላክን ፈቃድ ለመማርና በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ ለመተርጎም የሚጥሩ ከሆነ ጥበብና ማስተዋል ማግኘት ይችላሉ። በእርግጥም ደስተኛ ቤተሰብ ሊደከምለት የሚገባው ነው!
a የዓለም የጤና ድርጅት ለብዙ ጨቅላ ሕፃናት ሞት ምክንያት የሆነውንና በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘውን የተቅማጥ በሽታ ማስወገድ የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ባወጣው መመሪያ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሏል:- “መጸዳጃ ቤት ከሌለ ከቤት ራቅ ባለና ልጆች በማይጫወቱበት እንዲሁም ደግሞ ውኃ ከምትቀዱበት ቦታ ቢያንስ 10 ሜትር ያህል ርቀት ላይ በሚገኝ ሥፍራ ከተጸዳዳችሁ በኋላ ዓይነ ምድሩን በአፈር ሸፍኑት።”