ለትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች የቀረበ መመሪያ
በእያንዳንዱ ጉባኤ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚሾም አንድ ሽማግሌ ይኖራል። ይህ ኃላፊነት ከተሰጠህ በትጋት መሥራትህና እያንዳንዱ ተማሪ እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት መጣርህ ትምህርት ቤቱ ለጉባኤው ትልቅ ድርሻ እንዲያበረክት አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ዋናው ተግባርህ በጉባኤያችሁ በየሳምንቱ የሚካሄደውን ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መምራት ይሆናል። ክፍል ወስደው ከሚያቀርቡት ተማሪዎች በተጨማሪ ስብሰባውን የሚከታተሉ ሌሎች አድማጮችም እንዳሉ አትዘንጋ። ትምህርት ቤቱን የምትመራበት መንገድ በመማሪያ መጽሐፉ ከገጽ 5 እስከ 8 ላይ ከተጠቀሱት ዓላማዎች ቢያንስ አንዱን የሚያስጨብጥ መሆን ይኖርበታል።
ተማሪው ክፍሉን የሚያቀርበው በንባብም ይሁን በሠርቶ ማሳያ ወይም በንግግር እያንዳንዱን ተማሪ ለመርዳት ልባዊ ጥረት አድርግ። ትምህርት ቤቱ እንዲሁ ክፍል የሚያቀርቡበት ብቻ ሳይሆን ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱት እርዳቸው። እርግጥ እድገት ማድረግ እንዲችሉ የግል ጥረታቸው ሊታከልበት ይገባል። ያም ሆኖ አንተም አሳቢነት ማሳየትህ፣ የምክሩን ነጥብ እንዲያስተውሉት መርዳትህና ምክሩን እንዴት ሊሠሩበት እንደሚችሉ ማብራራትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ለማድረግ እያንዳንዱ ክፍል ሲቀርብ በጥሞና ተከታትለህ ገንቢ ሐሳብ መስጠት መቻል ይኖርብሃል።
ትምህርት ቤቱ በሰዓቱ ተጀምሮ በሰዓቱ እንዲያልቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። የምትሰጠው ምክር ከተመደበልህ ሰዓት እንዳያልፍ በመጣር ምሳሌ ሆነህ መገኘት አለብህ። አንድ ተማሪ ሰዓት ካሳለፈ አንተ ራስህ ወይም ሌላ የመደብከው ሰው ምልክት ሊሰጠው ይገባል። ተማሪው የጀመረውን ዓረፍተ ነገር ጨርሶ ከመድረክ መውረድ ይኖርበታል። ሌሎች የትምህርት ቤቱ ክፍሎች ሲቀርቡ ሰዓት ካለፈ ደግሞ አንተ የምትሰጠውን ምክር አጠር አጠር በማድረግ ሰዓቱን ለማካካስ ሞክር። ከዚያም ስብሰባው ሲያልቅ ሰዓት ያሳለፈውን ወንድም አነጋግረው።
አንተ ካለህ ትምህርት ቤቱን መምራት ያለብህ አንተ ነህ። የማትኖርበት አጋጣሚ ቢፈጠር ግን የሽማግሌዎች አካል አስቀድሞ የመረጠው ሽማግሌ ትምህርት ቤቱን ሊመራ ይገባል። ፕሮግራም በማውጣት፣ የክፍል መስጫ ቅጾቹን በመሙላትና በማደል ወይም በሚቀሩት ምትክ ክፍል የሚያቀርቡ ተማሪዎችን በመመደብ ረገድ የሚረዳህ ሰው ካስፈለገህ የሽማግሌዎች አካል የመረጠው አንድ የጉባኤ አገልጋይ ሊያግዝህ ይችላል።
ተማሪዎችን መመዝገብ። አስፋፊዎች በሙሉ በትምህርት ቤቱ እንዲመዘገቡ አበረታታ። ከጉባኤው ጋር በትጋት የሚተባበሩ ሌሎችም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር እስከተስማሙና አኗኗራቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጣጣም እስከሆነ ድረስ በትምህርት ቤቱ መመዝገብ ይችላሉ። አንድ ሰው በትምህርት ቤቱ ለመመዝገብ ፍላጎት እንዳለው ሲገልጽ ከልብ አመስግነው። ግለሰቡ አስፋፊ ካልሆነ በትምህርት ቤቱ ለመመዝገብ ሊያሟላው የሚገባውን ብቃት በተመለከተ ልታነጋግረው ይገባል። የምትወያዩት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናው ሰው (ወይም አማኝ የሆነ ወላጁ) በተገኘበት ቢሆን ይመረጣል። በትምህርት ቤቱ ለመመዝገብ የሚያስፈልጉት ብቃቶች አንድ ሰው ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ከሚያሟላቸው ብቃቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እነዚህም አገልግሎታችንን ለመፈጸም መደራጀት በተባለው መጽሐፍ ገጽ 97 እስከ 99 ድረስ ተዘርዝረው ይገኛሉ። በየጊዜው የሚመዘገቡትን አዲስ ተማሪዎች ያካተተ የተማሪዎች ስም ዝርዝር ሊኖርህ ይገባል።
የምክር መስጫው ቅጽ አጠቃቀም። የእያንዳንዱ ተማሪ ምክር መስጫ ቅጽ በመማሪያ መጽሐፉ ገጽ 79 እስከ 81 ላይ ይገኛል። በተለያዩ ቀለማት ከተሰጠው ምልክት መረዳት እንደሚቻለው ከ1 እስከ 17 ያሉት ምክር መስጫ ነጥቦች ተማሪው በንባብ የሚቀርብ ክፍል ሲሰጠው ሊሠራባቸው የሚችሉ ናቸው። ከ7፣ 52 እና ከ53 በቀር ሁሉም የምክር መስጫ ነጥቦች በሠርቶ ማሳያ መልክ ለሚቀርቡ ክፍሎች ሊሠራባቸው ይችላል። ከ7፣ 18 እና 30 በቀር ደግሞ ሁሉም የምክር መስጫ ነጥቦች በንግግር ለሚቀርቡ ክፍሎች ሊሠራባቸው ይችላል።
ለአንድ ተማሪ የምክር መስጫ ነጥብ ሲመደብ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች በተማሪው መጽሐፍ ላይ በሚገኘው ምክር መስጫ ቅጽ ላይ “የተመደበበት ዕለት” በሚለው ቦታ ቀኑን በእርሳስ መጻፍ ይኖርበታል። ተማሪው ክፍሉን ካቀረበ በኋላ በምክር መስጫው ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን መልመጃ ሠርቶበት እንደሆነ በግል ጠይቀው። ሠርቶበት ከሆነ ቅጹ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ ምልክት አድርግ። ተማሪው በምክር መስጫው ነጥብ መሥራቱን ሊቀጥል ይገባል ብለህ ካሰብህ ቅጹ ላይ ሌላ ምንም ማስታወሻ መጻፍ አያስፈልግም። “ሠርቶ ያጠናቀቀበት ዕለት” የሚለውን ቦታ ክፍት መተዉ ብቻ በቂ ይሆናል። እዚህ ቦታ ላይ መጻፍ የሚኖርብህ ተማሪው ወደ ሌላ የምክር መስጫ ነጥብ መሸጋገር ሲችል ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በተማሪው መጽሐፍ ገጽ 82 ላይ ከተዘረዘሩት መቼቶች በስተግራ በኩል ባለው ክፍት ቦታ ላይ ክፍሉ ከቀረበ በኋላ በመቼቱ የተጠቀመበት ቀን ሊጻፍ ይገባል። በእያንዳንዱ ምክር መስጫ ነጥብም ሆነ መቼት ሁለት ጊዜ ለመሥራት የሚያስችል ክፍት ቦታ ተዘጋጅቷል። በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ወቅት ተማሪዎቹ መጽሐፋቸውን ይዘው መገኘት ይኖርባቸዋል።
በአንድ ጊዜ ለአንድ ተማሪ ሊሰጠው የሚገባው አንድ የምክር መስጫ ነጥብ ብቻ ነው። በአብዛኛው ምክር መስጫ ነጥቦቹን በተዘረዘሩበት ቅደም ተከተል እንዲሠሩባቸው ማድረግ የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ካሉ አንዳንዶቹን ነጥቦች በግላቸው በማጥናት እንዲሠሩባቸው ልታበረታታቸው ትችል ይሆናል። ከዚያም የተዋጣላቸው ተናጋሪዎችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ይረዷቸዋል ብለህ በምታስባቸው በእነዚያ ነጥቦች እንዲሠሩባቸው ልትረዳቸው ትችላለህ።
ተማሪው ለብዙ ዓመታት በትምህርት ቤቱ የቆየ እንኳ ቢሆን እያንዳንዱን ምዕራፍ አጥንቶ ሥራ ላይ ለማዋል ቢጥር ብዙ ይጠቀማል። በተወሰነ መስክ ማሻሻያ ማድረግ የሚገባቸው ተማሪዎች ሲኖሩ እነርሱን ለመርዳት የምክር መስጫ ቅጹን ቅደም ተከተል ከመከተል ይልቅ ተፈላጊውን ነጥብ እየመረጥህ ልትሰጣቸው ትችላለህ።
ምክር መስጠት። ምክር በምትሰጥበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ምሳሌዎችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጥሩ አድርገህ ተጠቀም። ተማሪዎቹ የምትሰጠው ምክርም ሆነ ምክሩን የምትሰጥበት መንገድ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙት የላቀ ደረጃ ያላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጣጣም እንደሆነ ሊሰማቸው ይገባል።
ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ‘አብረህ የምትሠራ’ መሆንህን አትርሳ። (2 ቆሮ. 1:24) አንተም እንደ እነርሱ የመናገርና የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለውን መጽሐፍ ልታጠና፣ ምክሩን ሥራ ላይ ልታውልና በዚህ ረገድ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ሆነህ ልትገኝ ይገባል።
ይህን ስታደርግ ሌሎች ተማሪዎች ጥሩ አንባቢዎች፣ የተዋጣላቸው ተናጋሪዎችና ጎበዝ አስተማሪዎች እንዲሆኑ የመርዳት ግብ ሊኖርህ ይገባል። ይህንንም ለማድረግ ተማሪዎቹ የተለያዩትን የንግግር ባሕርያት በደንብ እንዲረዷቸው፣ ለምን አስፈላጊ እንደሆኑ እንዲገነዘቡና እነዚህን የንግግር ባሕርያት እንዴት ማዳበር እንደሚችሉ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ከልብ መጣር ይኖርብሃል። ይህ የመማሪያ መጽሐፍ የተዘጋጀው እንዲህ ያለውን እርዳታ ለመስጠት በሚያስችል መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ መጽሐፉ ላይ ያለውን ሐሳብ በቀጥታ ማንበብህ ብቻ በቂ አይሆንም። የመጽሐፉ ሐሳብ ምን ማለት እንደሆነና እንዴት ሊሠሩበት እንደሚችሉ አብራራ።
አንድ ተማሪ በነጥቡ በደንብ ከሠራበት አመስግነው። ጥሩ ሠርቶበታል ያሰኘው ምን እንደሆነ በአጭሩ ጥቀስ። ሊያሻሽለው የሚገባ ጉዳይ ካለ ደግሞ ለምን ማሻሻል እንደሚያስፈልገው ግልጽ ሊሆንለት ይገባል። እንዴት ሊያሻሽል እንደሚችል አስረዳው። ምክርህ ቀጥተኛ ሆኖም በደግነት የቀረበ መሆን ይኖርበታል።
ብዙዎች ሰው ፊት ቀርበው መናገር እንደሚያስፈራቸው መዘንጋት አይኖርብህም። አንድ ሰው ክፍሉን በደንብ እንዳላቀረበ ከተሰማው ማሻሻል እንደማይችል አድርጎ ሊያስብ ይችላል። “የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም” የተባለለትን የኢየሱስን ምሳሌ ለመኮረጅ ሞክር። (ማቴ. 12:20) ተማሪው ያለውን ስሜት ግምት ውስጥ አስገባ። ምክር በምትሰጥበት ጊዜ ተማሪው አዲስ ነው ወይስ ልምድ ያለው አስፋፊ የሚለውን ጉዳይ ልታስብበት ይገባል። በወዳጅነት መንፈስ ከልብ የቀረበ ምስጋና ሰዎች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ጥረት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ሊያበረታታ ይችላል።
ለእያንዳንዱ ተማሪ አክብሮት ሊኖርህ ይገባል። ሮሜ 12:10 [የ1980 ትርጉም ] “እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ” በማለት ይመክረናል። ይህ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ምክር ለሚሰጥ ሰው እንዴት ተስማሚ ማሳሰቢያ ነው! ተማሪው በእድሜ የሚበልጥህ ከሆነ በ1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2 ላይ የተሰጠውን ምክር ልትሠራበት ይገባል። የሰውዬው ዕድሜ ምንም ያህል ይሁን ምን ማስተካከል ስለሚገባው ነገር የሚሰጠው ምክር በደግነት የቀረበ ከሆነ በቀላሉ ሊቀበለው ይችላል።—ምሳሌ 25:11
ምክር በምትሰጥበት ጊዜ የሥልጠናው ዓላማ ምን እንደሆነ ለተማሪው ግልጽ ልታደርግለት ይገባል። ዓላማው በዚያ ነጥብ ጥሩ ሠርቶ መመስገንና ወደሚቀጥለው ምክር መስጫ ነጥብ ማለፍ አይደለም። በንግግርና በማስተማር ችሎታው የሌሎችን አድናቆት ማትረፍም አይደለም። (ምሳሌ 25:27) ፍላጎታችን የንግግር ችሎታችንን ተጠቅመን ይሖዋን ማወደስና ሌሎች ሰዎች እርሱን እንዲያውቁና እንዲወዱ መርዳት ነው። የሥልጠናው ዓላማ በማቴዎስ 24:14 እና 28:19, 20 ላይ የተገለጹትን ሥራዎች በተሳካ መንገድ እንድናከናውን ማገዝ ነው። ብቃቱ ያላቸው የተጠመቁ ወንድሞች ደግሞ ከጊዜ በኋላ የሕዝብ ተናጋሪዎችና አስተማሪዎች በመሆን ‘የአምላክን መንጋ’ የመጠበቅ ኃላፊነት ሊሸከሙ ይችላሉ።—1 ጴጥ. 5:2, 3
ተማሪዎቹ የምክር መስጫው ነጥብ ከተመደበላቸው በኋላ ወዲያውኑ ምዕራፉን ማንበብ እንዲጀምሩ አሳስባቸው። ለክፍላቸው ሲዘጋጁ ከመማሪያ መጽሐፉ ያገኟቸውን ነጥቦች በዕለት ተዕለት ውይይታቸው፣ በጉባኤ ሐሳብ ሲሰጡ እንዲሁም በመስክ አገልግሎት ሲካፈሉ እንዲሠሩባቸው አበረታታቸው።
ክፍል መደልደል። ክፍሉ ቢያንስ ሦስት ሳምንት ቀደም ብሎ ለተማሪዎች ሊሰጥ ይገባል። በተቻለ መጠን ክፍል ያላቸውን በሙሉ ማሳወቅ ያለብህ በጽሑፍ ነው።
ጉባኤውን ለማስተማር ታስበው የተዘጋጁት ክፍሎች በሚገባ ሊያቀርቧቸው ለሚችሉ ሽማግሌዎች እንዲሁም ጥሩ የማስተማር ችሎታ ላላቸው የጉባኤ አገልጋዮች ሊሰጡ ይገባል።
በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ ያለው መመሪያ የትኞቹን ክፍሎች ለወንድሞች የትኞቹን ደግሞ ለእህቶች እንደምትሰጥ ለመወሰን ይረዳሃል። አብዛኞቹ ተማሪዎች እህቶች በሚሆኑበት ጊዜ ወንድሞች በንባብ ከሚቀርቡት ክፍሎች በተጨማሪ ሌሎች ክፍሎችን የማቅረብ አጋጣሚ እንዲያገኙ ለማድረግ ጣር።
ክፍል በምትደለድልበት ጊዜ የእያንዳንዱን ተማሪ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገባ። በተመሳሳይ ዕለት በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ሌላ ክፍል ላለው ወይም በዚያ ሳምንት የሕዝብ ንግግር እንዲያቀርብ ለተመደበ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ክፍል መስጠት ይኖርብሃልን? አንዲት እህት የእርሷ እርዳታ የሚያስፈልገው ትንሽ ልጅዋ ክፍል እንዲያቀርብ በተመደበበት ዕለት እርሷም ክፍል እንድታቀርብ መመደብ ይኖርብሃልን? በተለይ ተማሪው ገና ወጣት ወይም ያልተጠመቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሆነ ርዕሰ ጉዳዩ ከእርሱ ሁኔታ ጋር ይስማማልን? ትምህርቱ በተመደበው የምክር መስጫ ነጥብ ለመሥራት የሚያመች መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል።
ክፍሉ ለእህቶች በሚሰጥበት ጊዜ ተማሪዋ በገጽ 78 እና 82 ላይ በሚገኘው መመሪያ መሠረት የራሷን መቼት ትመርጣለች። አንድ ረዳት ይመደብላታል፤ ሆኖም ተጨማሪ ረዳት መጠቀም ይቻላል። ተማሪዋ ለአንድ የተወሰነ መቼት ይበልጥ የሚስማማ ሰው እንዲመደብላት ከጠየቀች ጥያቄዋን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
በተጨማሪ አዳራሾች የሚቀርቡ ክፍሎች። በትምህርት ቤቱ ከ50 በላይ ተማሪዎች ካሉ የተማሪ ክፍሎች የሚቀርቡበት ተጨማሪ ቦታ ማዘጋጀት ትፈልግ ይሆናል። በዚህ ተጨማሪ አዳራሽ እንደ ጉባኤው ሁኔታ ሁሉም የተማሪ ክፍሎች ወይም የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ብቻ የሚቀርቡበትን ዝግጅት ማድረግ ይቻላል።
በእነዚህ አዳራሾች ጥሩ ችሎታ ያለው ምክር ሰጪ ሊመደብ ይገባል። ሽማግሌ ቢሆን ይመረጣል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ብቃት ያለው የጉባኤ አገልጋይ መጠቀም ይቻላል። እነዚህን ወንድሞች የሚመርጠው የሽማግሌዎች አካል ነው። ተማሪዎቹ የሚቀጥለውን ክፍላቸውን የሚያቀርቡት በየትኛውም አዳራሽ ይሁን ተከታትሎ ለመርዳት እንዲቻል ከእነዚህ ምክር ሰጪዎች ጋር በቅርብ ተባብረህ ልትሠራ ይገባል።
ንባብን ለማሻሻል የሚረዳ ልዩ ዝግጅት። የሽማግሌዎች አካል ጉባኤው በሚጠቀምበት ቋንቋ መሠረታዊ የንባብ ትምህርት ማግኘት የሚያስፈልጋቸው በርከት ያሉ ግለሰቦች እንዳሉ ካመነበት ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ዝግጅቶች ማድረግ ትችል ይሆናል። የሚሰጠው ትምህርት ፊደል ማስቆጠርን የሚጨምር ወይም የንባብ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት የታሰበ ሊሆን ይችላል።
ይህ ትምህርት የሚካሄደው የግድ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍሎች እየቀረቡ ሳለ መሆን የለበትም። ሰዎቹን በሚገባ መርዳት እንዲቻል ከዚያ ይበልጥ ሰፋ ያለ ጊዜ ሊያስፈልግ ይችላል። የጉባኤው ሽማግሌዎች ምን እንደሚያስፈልግና ትምህርቱ መቼ እንደሚሰጥ ሊወስኑ ይችላሉ። እንደ አስፈላጊነቱ አንድ ላይ ለማስተማር ወይም በተናጠል ለመርዳት የሚያስችሉ ዝግጅቶች ሊደረጉ ይችላሉ።
ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ ሊመደብ ይገባል። ጥሩ የማንበብ ችሎታ ያለውና ቋንቋውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ወንድም ቢሆን ይመረጣል። ወንድም ማግኘት የማይቻል ከሆነ ሽማግሌዎች ብቃት ያላትና ምሳሌ የምትሆን አንዲት እህት ሊመድቡ ይችላሉ። በምታስተምርበት ጊዜ ራሷን መሸፈን ይኖርባታል።—1 ቆሮ. 11:3-10፤ 1 ጢሞ. 2:11, 12
ማንበብና መጻፍ ተማር የተባለ ቡክሌት በብዙ ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል። ይህ ቡክሌት መሠረተ ትምህርት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። እንደ ተማሪዎቹ የንባብ ችሎታ ሌሎች የማስተማሪያ ጽሑፎችን መጠቀም ይቻላል። ተማሪዎቹ በቂ መሻሻል ካደረጉ በኋላ በመደበኛው የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም እንዲካፈሉ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል።
የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የበላይ ተመልካች ሆነህ ስታገለግል ጉባኤው እንዲጠቀም ብዙ ልታደርገው የምትችለው ነገር ይኖራል። ጥሩ አድርገህ በመዘጋጀት በሮሜ 12:6-8 ላይ በተሰጠው ምክር መሠረት ኃላፊነትህን ከአምላክ እንደተሰጠህ ውድ አደራ አድርገህ ልትመለከተው ይገባል።