የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 43 ገጽ 234-ገጽ 235 አን. 3
  • የተመደበልህን ጽሑፍ መጠቀም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የተመደበልህን ጽሑፍ መጠቀም
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በትምህርት ቤቱ የሚሰጡህን የተማሪ ክፍሎች መዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • የመዘጋጀት አስፈላጊነት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ለጉባኤ የሚቀርቡ ንግግሮችን መዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • አስተዋጽኦ ማዘጋጀት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 43 ገጽ 234-ገጽ 235 አን. 3

ጥናት 43

የተመደበልህን ጽሑፍ መጠቀም

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ንግግርህ ከተሰጠህ ርዕሰ ጉዳይ መውጣት የለበትም። ትምህርቱን የምታቀርብበት ጽሑፍ ከተመደበልህ ደግሞ እዚያ ያሉትን ጥቅሶችና ዋና ዋና ነጥቦች ልትጠቀም ይገባል።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ንግግራችንን የምናዳብረው በተመደበልን ጽሑፍ ላይ ተመርኩዘን ከሆነ ታማኝና ልባም ባሪያ መንፈሳዊ ምግብ ለሚያቀርብበት ዝግጅት አክብሮት እንዳለን እናሳያለን።

መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያን ጉባኤን ከሰው አካል ጋር በማመሳሰል ይናገራል። ‘እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ያለው ድርሻ የተለያየ’ ቢሆንም ሁሉም አስፈላጊ ናቸው። እንደዚሁ ሁሉ እኛም የተሰጠንን ማንኛውንም መብት በአድናቆት ተቀብለን ልንሠራ ይገባል። ይህም እኛ ደስ የሚለን ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ስላለ ብቻ አንዳንዱን ትምህርት ብዙም አስፈላጊ እንዳልሆነ አድርገን ከማሰብ ይልቅ የሚሰጠንን ማንኛውንም ክፍል በደንብ ተዘጋጅተን ማቅረብ ይኖርብናል ማለት ነው። (ሮሜ 12:​4-8) ታማኝና ልባም ባሪያ “በጊዜው” መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። (ማቴ. 24:​45) የተሰጠንን መመሪያ ተከትለን ንግግሩን ጥሩ አድርገን ማቅረባችን ለዚህ ዝግጅት ያለንን አክብሮት የሚያሳይ ይሆናል። ይህ ደግሞ መላው ጉባኤ ተግባሩን በተቃና መንገድ እንዲያከናውን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

በንግግርህ ውስጥ የምታካትታቸው ነጥቦች። በትምህርት ቤቱ ክፍል እንድታቀርብ ስትመደብ ርዕሰ ጉዳዩ ብቻ ከተሰጠህ ከዚያ መውጣት የለብህም። አብዛኛውን ጊዜ ግን ርዕሰ ጉዳዩ ብቻ ሳይሆን ትምህርቱን የምታቀርብበትም ጽሑፍ ይጠቀሳል። ንግግሩን ከየትኛው ጽሑፍ እንደምታቀርብ ካልተገለጸ ከተለያዩ ጽሑፎች ሐሳብ ማሰባሰብ ትችላለህ። ይሁን እንጂ ንግግርህን ስትዘጋጅ ጠቅላላው የትምህርቱ ይዘት ከተሰጠህ ርዕሰ ጉዳይ መውጣት እንደሌለበት መዘንጋት አይኖርብህም። በተጨማሪም በንግግርህ የምታካትታቸውን ነጥቦች ስትመርጥ አድማጮችህን ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልግሃል።

ንግግሩን የምታቀርብበትን ጽሑፍ በደንብ አጥና። ጥቅሶቹንም አንድ በአንድ ከትምህርቱ ጋር ለማገናዘብ ሞክር። ከዚያም አድማጮችን በሚጠቅም መንገድ እንዴት ልታቀርበው እንደምትችል አስብ። በንግግርህ ውስጥ እንደ ዋና ነጥብ የምትጠቀምባቸውን ሁለት ወይም ሦስት ነጥቦች ምረጥ። እንዲሁም ጽሑፉ ላይ ካሉት ጥቅሶች መካከል ልታነብባቸውና ልታብራራቸው የምትፈልጋቸውን ጥቅሶች ምረጥ።

ጽሑፉ ላይ ካለው ሐሳብ ለአድማጮችህ የምታቀርበው ምን ያህሉን ነው? ጥሩ አድርገህ ልታብራራው የምትችለውን የተወሰነ ነጥብ ብቻ መሆን አለበት። ብዙ ነጥብ ለማካተት ስትል ንግግርህ እንዲበላሽ መፍቀድ የለብህም። ከንግግሩ ዓላማ ጋር የማይሄድ ሐሳብ ካለ ያንን ትተህ ግብህን ለማሳካት በሚረዱህ ነጥቦች ላይ ብቻ አተኩር። ለአድማጮችህ ይበልጥ ግንዛቤ የሚያሰፉና ጠቃሚ ይሆናሉ የምትላቸውን ነጥቦች ብቻ ተጠቀም። የተመደበልህን ጽሑፍ መጠቀም ሲባል እዚያ ላይ ያለውን ሐሳብ ሁሉ ማቅረብ ማለት ሳይሆን ከዚያ ሳይወጡ መናገር ማለት ነው።

ንግግርህን ስታቀርብ ዓላማህ ጽሑፉን መከለስ አይደለም። የተወሰኑ ነጥቦችን መርጠህ ማብራራት፣ በምሳሌ ማስረዳትና እንዴት ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማስረጃ አስደግፈህ ማቅረብ ማለት ነው። ተጨማሪ ሐሳብ ከተጠቀምህ ጽሑፉ ላይ ያሉትን አስፈላጊ ነጥቦች ለማዳበር እንጂ ለመተካት መሆን የለበትም።

የማስተማር ብቃቱ ያላቸው ወንድሞች በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ክፍል እንዲያቀርቡ ይመደቡ ይሆናል። እነዚህ ወንድሞች ጽሑፉ ላይ ያለውን ጥሩ አድርገው ማቅረብ እንጂ ሌላ ሐሳብ መተካት እንደሌለባቸው ይገነዘባሉ። የሕዝብ ንግግር የሚያቀርቡ ወንድሞችም ቢሆኑ የንግግር አስተዋጽኦ ይሰጣቸዋል። እነዚህ አስተዋጽኦዎች ለተናጋሪው የተወሰነ ነፃነት የሚሰጡ ቢሆንም ሊዳብሩ የሚገባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች፣ እነርሱን የሚደግፉትን ተጨማሪ ሐሳቦች እንዲሁም ለንግግሩ መሠረት የሆኑትን ጥቅሶች ቁልጭ አድርገው ያስቀምጣሉ። ለንግግሩ ከተመደበው ጽሑፍ ሳይወጡ ማስተማር መቻል ተጨማሪ የማስተማር መብቶች እንድታገኝ በር ሊከፍትልህ ይችላል።

ይህ ሥልጠና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችህ እድገት እንዲያደርጉ በሚያስችል መንገድ ለማስጠናትም ይጠቅምሃል። በተጨማሪም ጥሩ ናቸው ብለህ የምታስባቸውን ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ምንም ዝምድና የሌላቸውን ነጥቦች በማጉላት ከርዕሰ ጉዳዩ ከመራቅ ይልቅ በሚጠናው ትምህርት ላይ ብቻ እንድታተኩር ይረዳሃል። ይሁን እንጂ የዚህ ምክር መንፈስ ከገባህ ለተማሪው የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠብ እንዳለብህ አይሰማህም።

ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

  • ከተሰጠህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ የሚዛመዱ ነጥቦችን ብቻ ተጠቀም።

  • ንግግሩን የምታቀርብበት ጽሑፍ ከተመደበልህ ዋና ዋና ነጥቦችህንና ቁልፍ ጥቅሶችን መምረጥ ያለብህ ከዚያው ጽሑፍ እንጂ ከሌላ መሆን የለበትም።

መልመጃ፦ በሦስት የተለያዩ ቀናት የዕለት ጥቅስ ስታነብብ እየተብራራ ያለውን ርዕሰ ጉዳይ የሚያጎላውን ቃል ወይም ሐረግ አክብብ። ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በቀጥታ በሚያያዙት አንድ ወይም ሁለት አጫጭር ሐሳቦች ላይ አስምር። ጥቅሱንና ምልክት ያደረግህባቸውን ነጥቦች በመመርኮዝ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ በራስህ አባባል አስረዳ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ