የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • be ጥናት 50 ገጽ 258-ገጽ 262 አን. 3
  • ልብ ለመንካት መጣር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልብ ለመንካት መጣር
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአድማጮችን ልብ ለመንካት መጣር
    ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ
  • የአድማጮችህን ልብ መንካት
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • የምናስተምራቸውን ሰዎች ልብ መንካት የምንችለው እንዴት ነው?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2015
  • የማስተማር ችሎታህን አዳብር
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
ለተጨማሪ መረጃ
በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
be ጥናት 50 ገጽ 258-ገጽ 262 አን. 3

ጥናት 50

ልብ ለመንካት መጣር

ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ስለምትወያዩበት ጉዳይ ሰዎቹ ምን እንደሚሰማቸው አስብ። ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲቀርቡና ከእርሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ የሚረዳቸውን የልብ ዝንባሌና ስሜት እንዲያዳብሩ እርዳቸው።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሰዎች ይሖዋን ማስደሰት እንዲችሉ የአምላክ ቃል በልባቸው ውስጥ ሊተከል ይገባል።

ለሰዎች መመሥከር ብቻ ሳይሆን ልባቸውን ለመንካት መጣር ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ከውጭ የሚታየውን የአንድ ሰው ሁኔታ ከልብ ጋር እያነጻጸረ ይገልጻል። ምሳሌያዊው ልብ የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት የሚያመለክት ሲሆን ስሜቱን፣ ሐሳቡን፣ እንደዚያ የሚያስብበትን ምክንያትና የሚያስበው ነገር በድርጊቱ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ሁሉ ይጨምራል። የእውነት ዘር የሚዘራው በዚህ ምሳሌያዊ ልብ ውስጥ ነው። (ማቴ. 13:​19) አምላክን የመታዘዝ ፍላጎትም ከልብ የሚመነጭ መሆን ይኖርበታል።​—⁠ምሳሌ 3:​1፤ ሮሜ 6:​17

የምታስተምረው ነገር ወደ ልብ ጠልቆ እንዲገባ የሚከተሉትን ነገሮች ልታስብባቸው ይገባል:- (1) በአድማጭህ ልብ ውስጥ ምን እንደተተከለ ለማስተዋል ሞክር። (2) እንደ ፍቅርና አምላካዊ ፍርሃት ያሉትን ግሩም ባሕርያት ይበልጥ እንዲያዳብር እርዳው። (3) ይሖዋን በሚገባ ማስደሰት ይችል ዘንድ የልቡን ዝንባሌ እንዲመረምር አበረታታው።

ማስተዋል። ሰዎች እውነትን የማይቀበሉበት ምክንያት ይለያያል። መጽሐፍ ቅዱስ በምታስጠናበት ጊዜ ተማሪው ያለውን የተዛባ አመለካከት ቀይሮ ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲይዝ መርዳት ሊኖርብህ ይችላል። ወይም ለሚያውቀው ነገር ማስረጃ ማቅረብ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ግለሰቡ፣ ሰው በተፈጥሮው መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልገው ይገነዘባል? ስለ ጉዳዩ ምን ያህል እምነት አለው? የማያምንበትስ ነገር ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት አመለካከት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? እውነትን ማወቁ የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ከመቀበል ወደኋላ እንዲል የሚያደርጉትን ፍላጎቶችና ምኞቶች ማሸነፍ እንዲችል እርዳታ ያስፈልገው ይሆን?’

ሰዎች በአንድ ነገር እንዴት ሊያምኑ እንደቻሉ መረዳት ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ምሳሌ 20:​5 “ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው [“አስተዋይ፣” አ.መ.ት ] ሰው ግን ይቀዳዋል” ይላል። ማስተዋል ፊት ለፊት የማይታየውን ነገር መረዳት መቻል ነው። ይህ ሥራዬ ብሎ በትኩረት መከታተልን ይጠይቃል።

ስሜት የሚገለጸው በቃል ብቻ አይደለም። ስለ አንዳንድ ርዕሶች ስትወያዩ በተማሪው ፊት ላይ ለየት ያለ ስሜት ልታነብብ ወይም የድምፁ ቃና ሲቀየር ልታስተውል ትችላለህ። ወላጅ ከሆንክ ደግሞ የልጅህ ባሕርይ እየተለወጠ እንዳለ ስታስተውል አንዳንድ ተጽዕኖዎች እየገጠሙት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብህ አይቀርም። እነዚህ ምልክቶች በልጅህ ልብ ውስጥ ያለው ሐሳብና ስሜት ነጸብራቅ ስለሆኑ ቸል ብለህ ልታልፋቸው አይገባም።

ተስማሚ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ እንድታስተውል ሊረዱህ ይችላሉ። እንደሚከተለው ያሉትን ጥያቄዎች ልትጠይቅ ትችላለህ:- “ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?” “እንዲህ ብለህ እንድታመን ያደረገህ ምንድን ነው?” “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?” ይሁንና ሰዎችን በጥያቄ ልታፋጥጥ አይገባም። “አንድ ነገር ብጠይቅህ ደስ ይለኛል” ብለህ ጥያቄህን በዘዴ ልትጀምር ትችላለህ። በሌላው ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ማግኘት ትዕግሥትና ጥንቃቄ ይጠይቃል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው በሌላው ላይ እምነት ኖሮት የልቡን አውጥቶ ለመናገር ጊዜ ይወስድበታል። በዚህ ጊዜም ቢሆን እንኳ ግለሰቡ በግል ጉዳዩ እንደገባህ እንዲሰማው የሚያደርግ ጥያቄ ከማንሳት መቆጠብ ይኖርብሃል።​—⁠1 ጴጥ. 4:​15

ሰውዬው ለሚነግርህ ነገር በምላሹ የምታሳየው ስሜትም ቢሆን አስተዋይ መሆንን ይጠይቃል። ዓላማህ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ሊረዳው እንደሚችል መገንዘብ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብህም። አመለካከቱን ለማረም አትቸኩል። ከዚህ ይልቅ ከሚናገራቸው ቃላት በስተጀርባ ያለውን ስሜት ለማስተዋል ሞክር። እንዲህ ካደረግህ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለብህ ታውቃለህ። ተማሪውም ስሜቱን እንደተረዳህለት ስለሚሰማው አንተ የምትናገረውን ነገር በቁም ነገር ለማዳመጥ መነሳሳቱ አይቀርም።​—⁠ምሳሌ 16:​23

ለብዙ ሰዎች ንግግር በምትሰጥበትም ጊዜ በአድማጮች መካከል ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ስሜታቸውን እንዲገልጹ ማድረግ ትችል ይሆናል። አድማጮችህን በደንብ የምታይ፣ ፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት በንቃት የምትከታተል እንዲሁም ለራሳቸው መልስ የሚሰጡባቸውን አመራማሪ ጥያቄዎች የምታቀርብ ከሆነ ስለምትናገረው ነገር ምን ስሜት እንዳደረባቸው ፍንጭ ማግኘት ትችላለህ። አድማጮችህን በደንብ የምታውቃቸው ከሆነ ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገባ። ከአምላክ ቃል እየጠቀስህ ስታስረዳ የጉባኤውን አጠቃላይ መንፈስ ማሰብ ይኖርብሃል።​—⁠ገላ. 6:​18

የአድማጮችን ስሜት መቀስቀስ። ሰውዬው ምን እንደሚያምንና እንደማያምን እንዲሁም እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ ከተገነዘብህ በኋላ ያንን መሠረት በማድረግ ልትቀጥል ትችላለህ። ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በወቅቱ ከተከናወኑት ነገሮች ጋር እያገናዘበ ‘ቅዱሳት መጻሕፍትን ገልጦ በማስረዳት’ የአድማጮቹን ልብ ነክቷል። (ሉቃስ 24:​32) አንተም ሰውዬው ያጋጠመውን ሁኔታ ወይም የሚጓጓለትን ነገር ከአምላክ ቃል ጋር አዛምደህ ለማቅረብ ልትጥር ይገባል። ልቡ ተነክቷል ማለት የሚቻለው የተማረው ነገር “እውነት” መሆኑን ሙሉ በሙሉ ሲያምን ብቻ ነው።

የይሖዋን ጥሩነት፣ ፍቅሩን፣ ይገባናል የማንለውን ደግነቱን እንዲሁም መንገዱ የቀና መሆኑን ጎላ አድርገህ በመግለጽ የምታስተምራቸው ሰዎች ለአምላክ ፍቅር እንዲያድርባቸው ማድረግ ትችላለህ። በግለሰብ ደረጃ የሚያሳዩአቸውን ግሩም ባሕርያት ይሖዋ በቅርብ እንደሚከታተል ካስረዳሃቸው አድማጮችህ ከእርሱ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት እንደሚቻል እንዲያምኑ ልታደርጋቸው ትችላለህ። ለዚህ ሊረዳህ የሚችለው እንደ መዝሙር 139:​1-3፣ ሉቃስ 21:​1-4 እና ዮሐንስ 6:​44 ባሉት ጥቅሶች ላይ እንዲያሰላስሉ ማድረግ እንዲሁም ይሖዋ ከታመኑ አገልጋዮቹ ጋር ያለው ትስስር ምን ያህል የጠበቀ እንደሆነ እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። (ሮሜ 8:​38, 39) ይሖዋ ስህተታችንን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ አኗኗራችንን፣ ለንጹሕ አምልኮ ያለንን ቅንዓት እንዲሁም ለስሙ የምናሳየውን ፍቅር እንደሚመለከት አስረዳቸው። (2 ዜና 19:​2, 3፤ ዕብ. 6:​10) ስለ እያንዳንዳችን ተፈጥሮ ጥቃቅኗን ነገር እንኳ ሳይቀር ስለሚያስታውስ ‘በመታሰቢያ መቃብር ላሉት ሁሉ’ በቀላሉ ሕይወትን መልሶ ይሰጣቸዋል። (ዮሐ. 5:​28, 29፤ ሉቃስ 12:​6, 7) የሰው ልጅ የተፈጠረው በአምላክ መልክና ምሳሌ ስለሆነ ስለ ይሖዋ ባሕርያት የምናደርገው ውይይት ሰዎች ከልባቸው ጥሩ ምላሽ እንዲሰጡ እንደሚያነሳሳቸው የታወቀ ነው።​—⁠ዘፍ. 1:​27

በተጨማሪም አንድ ሰው ይሖዋ ለሰዎች ያለውን ዓይነት አመለካከት ማዳበርን ሲማር ልቡ ሊነካ ይችላል። አምላክ ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ይህን ያህል የሚጨነቅልን ከሆነ አስተዳደጋቸው፣ ብሔራቸው ወይም ዘራቸው ምንም ይሁን ምን ለሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ አሳቢነት እንደሚያሳይ የታወቀ ነው። (ሥራ 10:​34, 35) ግለሰቡ ይህንን ካስተዋለ ጥላቻንና ወገናዊነትን ከልቡ ነቅሎ ለማውጣት የሚያስችል ጠንካራ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት ይኖረዋል። ይህም በክርስቲያናዊ ሕይወቱ ከሌሎች ጋር በሰላም እንዲኖር ያስችለዋል።

በሌላ በኩል ሰዎች ፈሪሃ አምላክ እንዲያዳብሩ ለመርዳትም ልትጥር ይገባል። (መዝ. 111:​10፤ ራእይ 14:​6, 7) እንዲህ ያለው አምላካዊ ፍርሃት አንድ ሰው በራሱ ጥንካሬ ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ነገሮች ማድረግ እንዲችል ብርታት ይሰጠዋል። ሰዎች ይሖዋን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት እንዲያድርባቸው ለመርዳት ስለ ድንቅ ሥራዎቹና ስላሳየው ይህ ነው የማይባል ፍቅራዊ ደግነት ልትገልጽላቸው ትችላለህ።​—⁠መዝ. 66:​5፤ ኤር. 32:​40

ይሖዋ ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ሊያዝንም ሊደሰትም እንደሚችል አድማጮችህ እንዲገነዘቡ መርዳት ይኖርብሃል። (መዝ. 78:​40-42) ሰይጣን በአምላክ ፊት ላነሳው ግድድር መልስ በመስጠት ረገድ አኗኗራቸው ምን ድርሻ እንዳለው እንዲገነዘቡ እርዳቸው።​—⁠ምሳሌ 27:​11

አድማጮችህ የይሖዋን ትእዛዛት መጠበቃቸው ለራሳቸው ጥቅም እንደሆነ እንዲያስተውሉ አድርግ። (ኢሳ. 48:​17) ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ ለአፍታም እንኳ ቢሆን የአምላክን ትእዛዛት ቸል ማለት በስሜትና በአካል ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ መጠቆም ነው። ኃጢአት መፈጸም እንዴት ከአምላክ እንደሚያርቀን እንዲሁም ሌሎች እውነትን ከእኛ እንዳይማሩ እንቅፋት እንደሚፈጥር አልፎ ተርፎም የሰዎችን መብት መጋፋት እንደሚሆን አስረዳ። (1 ተሰ. 4:​6 NW ) አድማጮችህ የአምላክን ትእዛዛት በመጠበቅ ላገኟቸው በረከቶች አመስጋኝ እንዲሆኑ አበረታታ። በይሖዋ የጽድቅ ጎዳና መመላለስ ከብዙ መከራ እንደሚጠብቀን በማሰብ ለጽድቅ ትእዛዛቱ ያላቸው አድናቆት እንዲጨምር አድርግ። አንድ ሰው ይሖዋ የሚናገረውን መስማት ጥበብ እንደሆነ ከልብ ካመነ ከዚያ ተቃራኒ የሆኑትን ነገሮች ሁሉ ይጸየፋል። (መዝ. 119:​104) የአምላክን ትእዛዛት መጠበቅ ለይሖዋ ያደረ መሆኑን የሚያሳይበት አጋጣሚ እንጂ ሸክም እንደሆነ አይሰማውም።

ራሳቸውን እንዲመረምሩ መርዳት። ሰዎች በመንፈሳዊ ማደጋቸውን እንዲቀጥሉ በልባቸው ያለውን በቁም ነገር መመርመር ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊረዳቸው እንደሚችል ግልጽ አድርግላቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕጎችን፣ ምክሮችን፣ ታሪኮችንና ትንቢቶችን ብቻ የያዘ መጽሐፍ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡ እርዳቸው። የአምላክንም አስተሳሰብ እንድናስተውል ይረዳናል። በያዕቆብ 1:​22-25 ላይ የአምላክ ቃል ከመስተዋት ጋር ተነጻጽሯል። ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የምንሰጠው ምላሽ የልባችንን ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። ይህም ‘ልብን የሚፈትነው’ አምላክ እንዴት እንደሚመለከተን የሚጠቁም ነው። (ምሳሌ 17:​3) አድማጮችህ ይህን ነገር ዘወትር እንዲያስታውሱ አበረታታቸው። አምላክ በቃሉ ውስጥ ባሰፈረልን ትምህርት ላይ እንዲያሰላስሉና እርሱን ደስ ለማሰኘት በሕይወታቸው ምን ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲያስተውሉ አጥብቀህ አሳስባቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ‘የልባቸውን ስሜትና አሳብ’ በይሖዋ አመለካከት ለመመዘን የሚያስችል ጥሩ ዘዴ እንደሆነ አድርገው እንዲያዩት እርዳቸው። ይህም አምላክ የሚፈልግባቸውን ማንኛውንም ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኛ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።​—⁠ዕብ. 4:​12፤ ሮሜ 15:​4

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በተማሩት መሠረት ለውጥ ለማድረግ ቢፈልጉም ይሉኝታ ይይዛቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ ሥር ከሰደዱ ሥጋዊ ፍላጎቶቻቸው ጋር ይታገሉ አሊያም ከአንዳንድ ዓለማዊ ልማዶች ሳይላቀቁ አምላክን ማገልገል የሚችሉበትን መንገድ ይፈልጉ ይሆናል። በሁለት ሐሳብ መወላወል ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ግለጽላቸው። (1 ነገ. 18:​21) አምላክ ልባቸውን ይመረምርና ያጠራላቸው ዘንድ እንዲጸልዩ አሳስባቸው።​—⁠መዝ. 26:​2፤ 139:​23, 24

ይሖዋ የሚያደርጉትን ትግል እንደሚረዳላቸውና መጽሐፍ ቅዱስም ስለዚሁ ጉዳይ የሚናገረው ነገር እንዳለ ግለጽላቸው። (ሮሜ 7:​22, 23) በኃጢአተኛ ልባቸው ዝንባሌ እንዳይሸነፉ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስባቸው።​—⁠ምሳሌ 3:​5, 6፤ 28:​26፤ ኤር. 17:​9, 10

አንድ ነገር ለማድረግ ሲነሱ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን የመመርመር ልማድ እንዲኖራቸው አበረታታ። ተማሪህ እንዲህ እያለ ራሱን የመጠየቅ ልማድ እንዲያዳብር እርዳው:- ‘ይህን ማድረግ የፈለግሁበት ምክንያት ምንድን ነው? ይሖዋ እስከዛሬ ላደረገልኝ ነገር ሁሉ አድናቆት እንዳለኝ የሚያሳይ ነውን?’ ከይሖዋ ጋር ያለው ጥሩ ዝምድና ከምንም ነገር የሚበልጥ ውድ ሃብት ስለመሆኑ ያለውን እምነት ይበልጥ ልታጠናክርለት ይገባል።

አድማጮችህ ይሖዋን ‘በሙሉ ልብ’ ማገልገል ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዳቸው። (ሉቃስ 10:​27) ይህም ስሜታቸውን፣ ፍላጎታቸውን እንዲሁም ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን ሁሉ ከአምላክ መንገድ ጋር ማስማማት ይኖርባቸዋል ማለት ነው። አድማጮችህ የሚያደርጉትን ነገር ብቻ ሳይሆን ስለ አምላክ ትእዛዛት ምን እንደሚሰማቸውና እርሱን የሚያገለግሉበት ውስጣዊ ዝንባሌ ምን እንደሆነ ጭምር መመርመር እንዳለባቸው አስተምራቸው። (መዝ. 37:​4) ማስተካከል ያለባቸው ነገር እንዳለ ካስተዋሉ ደግሞ “ስምህን ለመፍራት ልቤን አንድ አድርግልኝ” ብለው ወደ ይሖዋ እንዲጸልዩ አበረታታቸው።​—⁠መዝ. 86:​11 NW 

ተማሪው ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና ከመሠረተ አንተ ስለገፋፋኸው ሳይሆን በእምነት ተነሳስቶ አምላክን ይታዘዛል። በራሱ ተነሳስቶም ‘ለጌታ ደስ የሚያሰኘው ምን እንደሆነ’ ይመረምራል። (ኤፌ. 5:​10፤ ፊልጵ. 2:​12) እንዲህ ባለው ከልብ የመነጨ ታዛዥነት ይሖዋ ይደሰታል።​—⁠ምሳሌ 23:​15

የሰዎችን ልብ በመመርመር ከእርሱ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ የሚስባቸው ይሖዋ እንደሆነ አትዘንጋ። (ምሳሌ 21:​2፤ ዮሐ. 6:​44) እኛ የሚጠበቅብን ከእርሱ ጋር መተባበር ብቻ ነው። (1 ቆሮ. 3:​9) ይሖዋ ‘በእኛ አማካኝነት እንደሚማልድ’ ያህል ነው። (2 ቆሮ. 5:​20፤ ሥራ 16:​14) መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመን ስናስተምር ይሖዋ አድማጮቻችን የሚሰሙት ነገር የጥያቄያቸው ወይም የጸሎታቸው መልስ መሆኑን እንዲገነዘቡ ልባቸውን ይከፍትላቸዋል እንጂ እውነትን እንዲቀበሉ አያስገድድም። ምን ጊዜም ስታስተምር ይህንን ሐቅ በማስታወስ ይሖዋ እንዲመራህና እንዲረዳህ ከልብህ ተማጸነው።​—⁠1 ዜና 29:​18, 19፤ ኤፌ. 1:​16-18

በዚህ ረገድ ማሻሻል የምትችለው እንዴት ነው?

  • ሰዎችን ከልብህ ውደድ።

  • በአድማጮችህ ልብ ውስጥ ምን እንደተተከለ ለማስተዋል ሞክር።

  • የይሖዋን ግሩም ባሕርያት ጎላ አድርገህ ግለጽ።

  • አድማጮችህ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን መመርመርና ማጥራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ እርዳቸው።

መልመጃ፦ (1) ማቴዎስ 6:​21⁠ን አንብብና እንዴት ልትሠራበት እንደምትችል አሰላስል። ቁጥር 19 እና 20ን አንብብና ልብህ ምን ማስተካከያ እንድታደርግ እንደሚገፋፋህ ቆም ብለህ አስብ። (2) ይሖዋን ለማገልግል የተነሳሳኸው ለምን እንደሆነ ለማጤን ሞክር። አሁንስ ይሖዋን እንድታገለግል የሚገፋፋህ ነገር ምንድን ነው? ይበልጥ ልታጠናክረው የምትፈልገው ይሖዋን የሚያስደስት የልብ ዝንባሌ የትኛው ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ