የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—መስከረም 2017
ከመስከረም 4-10
it-2-E 1082 አን. 2
ቤተ መቅደስ
ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ። በ593 ዓ.ዓ. ይኸውም ኢየሩሳሌምና በዚያ የነበረው የሰለሞን ቤተ መቅደስ በጠፉ በ14ኛው ዓመት፣ ካህንና ነቢይ ሆኖ ያገለግል የነበረው ሕዝቅኤል በራእይ አማካኝነት ወደ አንድ ትልቅ ተራራ ተወሰደ፤ በተራራው አናት ላይ ሆኖም የይሖዋን ታላቅ ቤተ መቅደስ ተመለከተ። (ሕዝ 40:1, 2) ሕዝቅኤል ያየውን ነገር ሁሉ “ለእስራኤል ቤት” በዝርዝር እንዲናገር ታዝዞ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት መመሪያ የተሰጠው በግዞት የተወሰዱት አይሁዳውያን ኀፍረት ተሰምቷቸው ንስሐ ለመግባት እንዲነሳሱ ለማድረግ እንዲሁም ታማኝ የሆኑትን አይሁዳውያን ለማጽናናት ሲባል ነው። (ሕዝ 40:4፤ 43:10, 11) በራእዩ ላይ ለመለኪያዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር። በራእዩ ላይ የተጠቀሱት መለኪያዎች “ዘንግ” ወይም “ሸምበቆ” (ረጅም ሸምበቆ 3.11 ሜትር) እና “ክንድ” (ረጅም ክንድ 51.8 ሴንቲ ሜትር) ናቸው። (ሕዝ 40:5 ግርጌ) ለመለኪያዎቹ የዚህን ያህል ትኩረት በመሰጠቱ፣ አንዳንዶች ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ይህ ቤተ መቅደስ ከጊዜ በኋላ አይሁዳውያን ከግዞት ሲመለሱ ዘሩባቤል ለሠራው ቤተ መቅደስ እንደ ናሙና የሚያገለግል እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። ይሁንና እንዲህ ብሎ ለመደምደም የሚያበቃ ማስረጃ የለም።
it-2-E 467 አን. 4
ስም
የአምላክን ስም የተሸከሙት እስራኤላውያን፣ የእሱን የጽድቅ መመሪያዎች ሳይከተሉ በመቅረታቸው የአምላክን ስም አርክሰዋል። (ሕዝ 43:8፤ አሞጽ 2:7) እስራኤላውያን ታማኝ ባለመሆናቸው አምላክ ቀጥቷቸዋል፤ ይህም ሌሎች ብሔራት የይሖዋን ስም እንዲያቃልሉ መንገድ ከፍቷል። (ከመዝ 74:10, 18 እና ከኢሳ 52:5 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ብሔራት፣ ይህን ቅጣት ያመጣው ይሖዋ እንደሆነ ስላልተገነዘቡ እስራኤላውያን መቅሰፍቶቹ የደረሱባቸው ይሖዋ ሕዝቡን መጠበቅ ሳይችል በመቅረቱ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ተረድተውታል። ይሖዋ፣ ስሙን እንዲህ ካለው ነቀፋ ለማንጻት ስለፈለገ ለስሙ ሲል እርምጃ በመውሰድ እስራኤላውያን ቀሪዎችን ከግዞት ወደ አገራቸው መልሷቸዋል።—ሕዝ 36:22-24
it-2-E 140
ፍትሕ
በመሆኑም ይሖዋ፣ የእሱን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ከፍትሕ ጋር በተያያዘ ያወጣቸውን መሥፈርቶች እንዲያውቁና በተግባር እንዲያውሉ ምንጊዜም ይጠብቅባቸዋል፤ ይህን መጠበቁም ምክንያታዊ ነው። (ኢሳ 1:17, 18፤ 10:1, 2፤ ኤር 7:5-7፤ 21:12፤ 22:3, 4፤ ሕዝ 45:9, 10፤ አሞጽ 5:15፤ ሚክ 3:9-12፤ 6:8፤ ዘካ 7:9-12)
ከመስከረም 11-17
it-2 1001
የሰው ልጅ
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ይህ መጠሪያ በብዛት የተሠራበት በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ ነው፤ አምላክ ነቢዩ ሕዝቅኤልን “የሰው ልጅ” በማለት ከ90 ጊዜ በላይ ጠርቶታል። (ሕዝ 2:1, 3, 6, 8) ይሖዋ ይህንን መጠሪያ በዚህ መንገድ የተጠቀመበት ነቢዩ ሕዝቅኤል ተራ ሰው መሆኑን ለመግለጽ ሊሆን ይችላል፤ ይህ አጠራር፣ የመልእክቱ ምንጭ በሆነው ሉዓላዊ አምላክና መልእክቱን በሚያደርሰው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ያጎላል። ይኸው መጠሪያ በዳንኤል 8:17 ላይ ነቢዩ ዳንኤልን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ከመስከረም 18-24
it-2-E 382
ሚሳቅ
ዳንኤልና ጓደኞቹ፣ ንጉሡ ያቀረበላቸውን ምርጥ ምግብ መብላት ‘እንደሚያረክሳቸው’ የተሰማቸው በሦስት ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል፦ (1) ባቢሎናውያን በሙሴ ሕግ መሠረት ርኩስ እንደሆኑ የሚቆጠሩ እንስሳትን ይበሉ ነበር፤ (2) ባቢሎናውያን የሚበሏቸውን እንስሳት ደም በሚገባ ላያፈስሱት ምናልባትም አንዳንዶቹን እንስሳት አንቀው ሊገድሏቸው ይችላሉ፤ (3) አረማውያን በአብዛኛው እንስሳቱን መጀመሪያ ለአማልክቶቻቸው መሥዋዕት አድርገው የማቅረብ ልማድ ነበራቸው፤ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ሥጋ መብላትን፣ ለአማልክቶቹ የሚቀርበው አምልኮ ክፍል እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩት ነበር።—ዳን 1:8፤ ከ1ቆሮ 10:18-20, 28 ጋር አወዳድር።
w88 10/1 30 ¶3-5
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በመጨረሻም ዳንኤል የተባለውን ዕብራዊ፣ ንጉሥ ቤልሻዛር ፊት አቀረቡት፤ ንጉሡም ለሌሎቹ ያቀረበውን ሽልማት ለዳንኤልም እንደሚሰጠው ማለትም ሐምራዊ ልብስ እንደሚያለብሰው፣ አንገቱ ላይ የወርቅ ሐብል እንደሚያደርግለትና በመንግሥቱ ላይ ሦስተኛ ገዢ እንደሚሆን ቃል ገባለት። ነቢዩም እንደሚከተለው በማለት በአክብሮት መልስ ሰጠ፦ “ስጦታህ ለራስህ ይሁን፤ ገጸ በረከቶችህንም ለሌሎች ስጥ። ይሁንና ጽሑፉን ለንጉሡ አነባለሁ፤ ትርጉሙንም አሳውቀዋለሁ።”—ዳንኤል 5:17
ከዚህ ማየት እንደሚቻለው ዳንኤል፣ የጽሑፉን ትርጉም ለማሳወቅ ክፍያ ወይም ጉቦ አልጠየቀም። ንጉሡ ስጦታውን ለራሱ ማስቀረት አሊያም ለሌሎች መስጠት ይችላል። ዳንኤል ትርጓሜውን የሚናገረው ስጦታ ለማግኘት ፈልጎ ሳይሆን በባቢሎን ላይ የጥፋት ፍርድ ያስተላለፈው እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ ስለሰጠው ነው፤ ደግሞም ይህ ፍርድ የሚፈጸምበት ጊዜ ቀርቦ ነበር።
ዳንኤል ልክ እንደተናገረው ጽሑፉን አንብቦ ትርጉሙን ካብራራ በኋላ ንጉሡ ስጦታው ለነቢዩ እንዲሰጠው ትእዛዝ እንዳስተላለፈ ዳንኤል 5:29 ላይ ተገልጿል። ሐምራዊውን ልብስ የለበሰውና የወርቅ ሐብሉን ያጠለቀው ዳንኤል ራሱ አይደለም። ስጦታው ለዳንኤል የተሰጠው የአገሪቱ የመጨረሻ ባለሥልጣን ማለትም ንጉሥ ቤልሻዛር ይህ እንዲደረግ ትእዛዝ ስላስተላለፈ ነው። ነቢዩ ስጦታውን መቀበሉ፣ ጥቅም የማግኘት ፍላጎት እንደሌለው በዳንኤል 5:17 ላይ በግልጽ ከተናገረው ሐሳብ ጋር አይጋጭም።