የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ጥቅምት 2017
ከጥቅምት 2-8
it-2-E 902 አን. 2
ሰባ ሳምንታት
መተላለፍንና ኃጢአትን ማስቆም። የመሲሑ መቆረጥ ወይም መሞት፣ ከሞት መነሳትና ወደ ሰማይ መሄድ ‘መተላለፍን ለማስቆም፣ ኃጢአትን ለመደምሰስ እንዲሁም በደልን ለማስተሰረይ’ አስችሏል። (ዳን 9:24) የሕጉ ቃል ኪዳን አይሁዳውያኑ ኃጢአተኞች መሆናቸውን በማጋለጥ ውግዘት አስከትሎባቸዋል፤ በተጨማሪም ቃል ኪዳኑን በሚያፈርሱ ሰዎች ላይ እንደሚመጣ የተነገረው እርግማን እንዲደርስባቸው አድርጓል። የሙሴ ሕግ ሰዎች “ብዙ” በደል እንደሚፈጽሙ ያጋለጠ ቢሆንም ይህ ሁኔታ አምላክ በመሲሑ አማካኝነት ታላቅ ምሕረትና ጸጋ የሚያሳይበት አጋጣሚ ፈጥሯል። (ሮም 5:20) የመሲሑ መሥዋዕት ንስሐ የገቡ ሰዎች መተላለፍና ኃጢአት እንዲሰረዝ ያስቻለ ከመሆኑም ሌላ እነዚህ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣባቸው ቅጣት ነፃ እንዲሆኑ አድርጓል።
it-2-E 900 አን. 7
ሰባ ሳምንታት
‘ከስልሳ ዘጠኝ ሳምንታት’ በኋላ መሲሑ ይገለጣል። የ70ዎቹ ሳምንታት ክፍል የሆኑትና በሁለተኛ ደረጃ የተጠቀሱት ‘62ቱ ሳምንታት’ (ዳን 9:25) የሚጀምሩት ልክ ‘7ቱ ሳምንታት’ እንዳበቁ ነው። በመሆኑም ኢየሩሳሌምን መልሶ ለመገንባት “ትእዛዝ [ከወጣበት] ጊዜ አንስቶ መሪ የሆነው መሲሕ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ” 7 ሲደመር 62 “ሳምንታት” ማለትም 69 “ሳምንታት” ይሆናል ማለት ነው። እነዚህ 69 ሳምንታት የ483 ዓመታት ርዝማኔ ያላቸው ሲሆን ይህም ከ455 ዓ.ዓ. እስከ 29 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። ከላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ በውኃ የተጠመቀው፣ በመንፈስ ቅዱስ የተቀባውና “መሪ የሆነው መሲሕ” በመሆን አገልግሎቱን የጀመረው በ29 ዓ.ም. የመከር ወራት ላይ ነው።—ሉቃስ 3:1, 2, 21, 22
it-2-E 901 አን. 2
ሰባ ሳምንታት
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ “ይቆረጣል።” በመቀጠልም ገብርኤል ለዳንኤል “ከ62ቱ ሳምንታት በኋላ መሲሑ ይቆረጣል፤ ትቶት የሚያልፈው ምንም ነገር አይኖርም” ብሎታል። (ዳን 9:26) ‘7ቱ ሳምንታት ሲደመር 62ቱ ሳምንታት’ ካበቁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማለትም ከሦስት ዓመት ተኩል ገደማ በኋላ ክርስቶስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞት የተቆረጠ ሲሆን ያለውን ሁሉ ለሰው ልጆች በመስጠት ቤዛ ሆኗል። (ኢሳ 53:8) ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢየሱስ ‘የሳምንቱን’ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፈው በአገልግሎት ነው። በአንድ ወቅት (በ32 ዓ.ም. የበልግ ወራት ሳይሆን አይቀርም) ኢየሱስ “ሦስት ዓመት ሙሉ” ፍሬ ስላላፈራች የበለስ ዛፍ የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሮ ነበር፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የበለስ ዛፏን ምሳሌ የተናገረው የአይሁድን ብሔር በአእምሮው ይዞ ነው። (ከማቴ 17:15-20፤ 21:18, 19, 43 ጋር አወዳድር።) በምሳሌው ላይ ኢየሱስ የወይን አትክልት ሠራተኛው ለወይን እርሻው ባለቤት እንደሚከተለው እንዳለው ገልጿል፦ “ጌታዬ፣ ዙሪያዋን ቆፍሬ ፍግ ላድርግባትና እስቲ ለአንድ ዓመት ደግሞ እንያት። ወደፊት ፍሬ ካፈራች ጥሩ፤ ካልሆነ ግን ትቆርጣታለህ።” (ሉቃስ 13:6-9) ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ልበ ደንዳና ለሆነው ብሔር በመስበክ ያሳለፈውን ጊዜ ለማመልከት ሊሆን ይችላል፤ ይህን ምሳሌ የተናገረው አገልግሎቱን ለሦስት ዓመት ገደማ ያህል ሲያከናውን ቆይቶ አራተኛ ዓመቱን ሊይዝ ባለበት ወቅት ላይ ነበር።
it-2-E 901 አን. 5
ሰባ ሳምንታት
‘የሳምንቱ አጋማሽ’ የሚያርፈው በሰባቱ ዓመታት አጋማሽ ላይ ወይም አንዱ የዓመታት “ሳምንት” ከጀመረ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ነው። ሰባኛው “ሳምንት” የጀመረው በ29 ዓ.ም. የበልግ ወራት ላይ ማለትም ኢየሱስ በተጠመቀበትና ክርስቶስ እንዲሆን በተቀባበት ጊዜ ላይ ስለሆነ የሳምንቱ አጋማሽ (የሦስት ዓመት ተኩሉ ጊዜ) እስከ 33 ዓ.ም. የጸደይ ወራት ወይም በዚያ ዓመት ፋሲካ እስከሚከበርበት ጊዜ (ኒሳን 14) ድረስ ይዘልቃል። በጎርጎርዮስ የቀን አቆጣጠር መሠረት ይህ ዕለት የዋለው ሚያዝያ 1, 33 ዓ.ም. ላይ ይመስላል። (LORD’S EVENING MEAL [Time of Its Institution] የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ የመጣው ‘የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ’ እንደሆነና የአምላክ ፈቃድ ደግሞ ‘የመጀመሪያውን [ሕጉ የሚያዛቸውን መሥዋዕቶችና መባዎች] አስወግዶ ሁለተኛውን ማቋቋም’ እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ የራሱን አካል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የአምላክን ፈቃድ ፈጽሟል።—ዕብ 10:1-10
ከጥቅምት 16-22
g05-E 9/8 12 አን. 2
ዓለም አቀፋዊ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ
እንዲያውም በዚያን ጊዜ በምድር ላይ በሚኖሩ ፍጥረታት መካከል አዲስ ዓይነት ሰላማዊ ግንኙነት ይፈጠራል፤ እንዲህ ያለው ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖር የሚችለው አምላክ ታማኝ ለሆኑ ተገዢዎቹ መኖሪያቸው የሆነችውን ምድርን በጥሩ ሁኔታ መያዝ የሚችሉበትን መንገድ ስለሚያስተምራቸው ነው። አምላክ አደገኛ ከሆኑ አራዊትም ጋር ጭምር በምሳሌያዊ ሁኔታ “ቃል ኪዳን” በመግባት ሰላማዊ ሆነው ለሰው ልጆች እንዲገዙ ያደርጋቸዋል።—ሆሴዕ 2:18፤ ዘፍ 1:26-28፤ ኢሳ 11:6-8
ከጥቅምት 23-29
jd-E 87 አን. 11
ላቅ ያሉ መሥፈርቶቹን በመጠበቅ ይሖዋን አገልግሉት
11 ሆሴዕ 14:9 ቀና የሆነውን መንገድ መከተል የሚያስገኘውን ጥቅም ልብ እንድንል ይረዳናል። የአምላክን መሥፈርቶች መጠበቅ ብዙ በረከት ያስገኛል። አምላክ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን አፈጣጠራችንን ያውቃል። የምንመራባቸውን መመሪያዎች የሰጠን ለእኛው ጥቅም በማሰብ ነው። በእኛና በአምላክ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስረዳት አንድን መኪናና መኪናውን የሠራውን ፋብሪካ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። መኪናውን የሠራው ፋብሪካ የመኪናውን ንድፍና አሠራር ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም የመኪናው ዘይት በየተወሰነ ጊዜው መቀየር እንዳለበት መመሪያ ሊሰጥ ይችላል። አንድ ሰው፣ ምናልባትም መኪናው ያለምንም ችግር እየሠራ እንዳለ በማሰብ ይህን መመሪያ ችላ ቢል ምን ይከሰታል? በመመሪያው መሠረት ዘይት ቢቀየርለት ኖሮ ለረጅም ጊዜ ሊያገለግል ይችል የነበረው መኪና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሞተሩ ሊበላሽና መሥራቱን ሊያቆም ይችላል። ከሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ፈጣሪያችን ልንመራባቸው የሚገቡ ትእዛዛት ሰጥቶናል። እነዚህን ትእዛዛት ማክበራችን የሚጠቅመው እኛኑ ነው። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ይህን ሐቅ መገንዘባችን በይሖዋ መሥፈርቶች ለመመራትና ትእዛዛቱን ለመጠበቅ የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ይሆነናል።—መዝሙር 112:1
ከጥቅምት 30-ኅዳር 5
jd-E 167 አን. 4
“በብሔራት መካከል ይህን አውጁ”
4 እስቲ ጉዳዩን ከሌላ አቅጣጫ ለመመልከት እንሞክር። ይሖዋ አምላክ ሁሉም ዓይነት ሰዎች ትንቢት የሚናገሩበትን ጊዜ አስመልክቶ ለነቢዩ ኢዩኤል እንደሚከተለው በማለት ነግሮት ነበር፦ “ከዚያ በኋላ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤ ወጣቶቻችሁም ራእዮችን ያያሉ።” (ኢዩኤል 2:28-32) በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ውስጥ በአንድ ደርብ ላይ ተሰብስበው በነበሩት ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸውና “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” መናገር በጀመሩበት ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እንዳገኘ ተናግሯል። (ሥራ 1:12-14፤ 2:1-4, 11, 14-21) እኛ ስላለንበት ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል? ኢዩኤል የተናገረው ትንቢት ከ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አንስቶ ዋነኛ ፍጻሜውን ማግኘት ጀምሯል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ወንድ ሴት፣ ወጣት አረጋዊ ሳይል እያንዳንዱ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን ‘ትንቢት በመናገር’ ላይ ማለትም “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” በማወጅ ላይ ይገኛል፤ ይህም በሰማይ ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ለሌሎች መናገርን ይጨምራል።