የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ኅዳር 2017
ከኅዳር 6-12
jd 90-91 ¶16-17
የይሖዋን የላቁ መሥፈርቶች በመከተል እሱን ማገልገል
16 የመጀመሪያው ሰው አዳም ‘መልካምና ክፉ የሆነውን በተመለከተ ከሁሉ የተሻለው የማን መሥፈርት ነው?’ በሚለው ጉዳይ ረገድ ያደረገው ምርጫ ሞኝነት የተንጸባረቀበት ነው። እኛስ ከእሱ የተሻለ ምርጫ እናደርግ ይሆን? ይህ ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል፤ አሞጽ “ክፉ የሆነውን ጥሉ፤ መልካም የሆነውንም ውደዱ” ሲል አሳስቦናል። (አሞጽ 5:15) በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምሥራቅ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች ፕሮፌሰር የነበሩት ዊልያም ሬኒ ሃርፐር ይህን ጥቅስ አስመልክተው ሲናገሩ “[በአሞጽ] አመለካከት፣ መልካምና ክፉ ለሆነው ነገር መሥፈርቱ (መለኪያው) የያህዌህ ፈቃድ ነው” ብለዋል። አሥራ ሁለቱ ነቢያት በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ጎልቶ የሚታየው ጭብጥም ይህ ነው። መልካምና ክፉ ስለሆኑት ነገሮች ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ለመቀበል ፈቃደኞች ነን? እነዚህ የላቁ መሥፈርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በቡድን ደረጃ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተብለው የሚጠሩት ተሞክሮ ያላቸው የጎለመሱ ክርስቲያኖች መሥፈርቶቹን ያብራሩልናል።—ማቴዎስ 24:45-47
17 ክፉ የሆነውን መጥላታችን አምላክን ከሚያሳዝኑ ነገሮች እንድንርቅ ያነሳሳናል። ለምሳሌ አንድ ሰው፣ በኢንተርኔት የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ማየት ወይም ማንበብ ጎጂ እንደሆነ ስለሚያውቅ ይህን ከማድረግ ይቆጠብ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያሉ ድረ ገጾችን ስለ መመልከት ‘በውስጡ’ ምን ይሰማዋል? (ኤፌሶን 3:16) በአሞጽ 5:15 ላይ የሚገኘውን መለኮታዊ ምክር ተግባራዊ ሲያደርግ፣ ክፉ ለሆነው ነገር ጥላቻ ማዳበር ቀላል ይሆንለታል። ይህም መንፈሳዊ ሰው ለመሆን በሚያደርገው ትግል አሸናፊ እንዲሆን ይረዳዋል።
ከኅዳር 13-19
jd 112 ¶4-5
አምላክ በሚፈልገው መንገድ ሌሎችን መያዝ
4 አምላክ፣ በእስራኤል አቅራቢያ የምትገኘውን ኤዶምን በማውገዝ ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፦ “በወንድምህ ቀን ይኸውም ወንድምህ ክፉ ነገር በደረሰበት ቀን መፈንደቅ አይገባህም ነበር፤ የይሁዳ ሕዝብ በጠፋበት ቀን ሐሴት ማድረግ አልነበረብህም።” (አብድዩ 12) የጢሮስ ሰዎች ከአይሁዳውያን ጋር ከነበራቸው የንግድ ግንኙነት አንጻር እንደ ወንድሞቻቸው ሊቆጠሩ ይችሉ ይሆናል፤ ኤዶማውያን ግን የያዕቆብ መንትያ ወንድም የሆነው የኤሳው ዘሮች በመሆናቸው ለእስራኤላውያን ቃል በቃል ወንድሞቻቸው ነበሩ። ይሖዋም እንኳ ኤዶማውያንን የእስራኤላውያን ‘ወንድሞች’ እንደሆኑ ተናግሯል። (ዘዳግም 2:1-4) በመሆኑም ባቢሎናውያን አይሁዳውያንን ሲያጠፏቸው ኤዶማውያን መደሰታቸው ለእነሱ የመረረ ጥላቻ እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው።
5 ኤዶማውያን፣ ወንድሞቻቸው ለሆኑት አይሁዳውያን የነበራቸው አመለካከት አምላክን እንዳላስደሰተው ግልጽ ነው። ይሁንና ‘እኔስ ወንድሞቼን የምይዝበትን መንገድ በተመለከተ አምላክ ምን ይሰማዋል?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። በዚህ ረገድ ልናስብባቸው ከሚገቡ አቅጣጫዎች አንዱ፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲከሰት ለወንድሞቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ይኖረናል የሚለው ነው። ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን፣ አንተን ወይም የቅርብ ዘመድህን የሚጎዳ ነገር አደረገ እንበል። ‘ቅር የተሰኘህበት ነገር’ ቢኖር ጉዳዩን ችላ ብለህ ከማለፍ ወይም ለማስተካከል ጥረት ከማድረግ ይልቅ ቂም ትይዛለህ? (ቆላስይስ 3:13፤ ኢያሱ 22:9-30፤ ማቴዎስ 5:23, 24) እንዲህ ዓይነት ስሜት ካለህ ወንድምህን በምትይዝበት መንገድ ላይ መታየቱ አይቀርም፤ ለምሳሌ ወንድምህን ፊት ትነሳው፣ ትርቀው ወይም ስለ እሱ መጥፎ ነገር ትናገር ይሆናል። እስቲ ሌላም ነጥብ እናንሳ፤ ከጊዜ በኋላ ይህ ወንድም አንድ ጥፋት በመሥራቱ የጉባኤ ሽማግሌዎች ምክር ወይም እርማት ሰጡት እንበል። (ገላትያ 6:1) ታዲያ በዚህ ወቅት የኤዶማውያን ዓይነት መንፈስ ታሳያለህ? በሌላ አባባል ይህ ወንድም ችግር ውስጥ በመውደቁ ትደሰታለህ? አምላክ የሚፈልገው ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖርህ ነው?