ይሖዋን ከልብ እየፈለግኸው ነውን?
አንድ የይሖዋ ምሥክር በየዕለቱ አብረውት በባቡር ለሚጓዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማካፈል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። (ማርቆስ 13:10) ሆኖም ፍርሃት አፉን ያዘው። ታዲያ ተስፋ ቆርጦ ትቶት ይሆን? በፍጹም። ይሖዋ እንዲረዳው አዘውትሮ ይጸልይ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከሰዎች ጋር እንዴት ውይይት እንደሚጀምር ይለማመድ ነበር። ይሖዋ አምላክ የዚህን ወንድም ጸሎት ሰምቶ ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችል ድፍረት ሰጥቶታል።
ይሖዋንና ሞገሱን ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ እንዲህ ያለ ልባዊ ጥረት ማድረጋችን የግድ አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት” ብሏል። (ዕብራውያን 11:6 አ.መ.ት) ይሖዋን መፈለጋችን ብቻ በቂ አይደለም። ‘ከልብ መሻት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ በትጋትና በሙሉ ልብ የሚደረግ ጥረትን ያመለክታል። ይህም በሙሉ ልብ፣ ሐሳብ፣ ነፍስና ኃይል ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ነው። ይሖዋን ከልብ የምንፈልግ ከሆነ ግዴለሾች፣ ራሳችንን የምንቆጥብ ወይም ሰነፎች መሆን አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ከልብ በመነጨ ቅንዓት እንፈልገዋለን።—ሥራ 15:17
ይሖዋን ከልብ የፈለጉ ሰዎች
ቅዱሳን ጽሑፎች ይሖዋን ከልብ ስለፈለጉ ሰዎች የሚናገሩ በርካታ ምሳሌዎችን ይዘዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ያዕቆብ ሲሆን ሥጋ ከለበሰ የአምላክ መልአክ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ሲታገል አድሯል። ከአምላክ ጋር ‘ስለታገለ’ ማለትም ስለ ጸና፣ ከፍተኛ ጥረት ስላደረገ ወይም ሳይታክት ስለታገለ እስራኤል (ከአምላክ ጋር የታገለ) የሚል ስም ተሰጥቶታል። ያዕቆብ ከፍተኛ ጥረት በማድረጉ መልአኩ ባርኮታል።—ዘፍጥረት 32:24-30
ሌላዋ ምሳሌ ደግሞ ስሟ ያልተጠቀሰ አንዲት የገሊላ ሴት ስትሆን ይህች ሴት ለ12 ዓመታት ያህል ደም ይፈስሳት ስለነበር ‘ብዙ ተሰቃይታለች።’ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ እያለች ማንንም መንካት አይኖርባትም ነበር። ሆኖም “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ” የሚል እምነት ስለነበራት እንደምንም ብላ ኢየሱስ ወዳለበት ሄደች። ‘ይከተለውና ይጋፋው በነበረው ብዙ ሕዝብ’ መሃል እየተሽሎከለከች ወደ ኢየሱስ ስትቀርብ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይህቺ ሴት የኢየሱስን ልብስ እንደዳሰሰች “የደምዋ ምንጭ ደረቀ” ማለትም ከህመሟ ተፈወሰች። ኢየሱስ “ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ፍርሃት ተሰማት። ቢሆንም ኢየሱስ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ” በማለት አረጋጋት። ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ ክሷታል።—ማርቆስ 5:24-34፤ ዘሌዋውያን 15:25-27
በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንዲት ከነዓናዊት ሴት ልጅዋን እንዲፈውስላት ኢየሱስን አጥብቃ ለመነችው። ኢየሱስ የልጆችን ምግብ ለቡችሎች መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ነገራት። ተልኮ የመጣው ለአይሁዳውያን ስለሆነ እስራኤላውያን ላልሆኑ ሰዎች ምንም ማድረግ እንደማይችል መናገሩ ነበር። ምሳሌው የገባት ይህች ሴት ግን “አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት ተማጸነችው። ኢየሱስ የነበራትን ጠንካራ እምነትና ቅንነት ተመልክቶ “አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደ ወደድሽ ይሁንልሽ” አላት።—ማቴዎስ 15:22-28
እነዚህ ሰዎች ከልብ ጥረት ባያደርጉና ገና ከጅምሩ እንቅፋት ሲገጥማቸው ተስፋ ቆርጠው ቢሆን ኖሮ የፈለጉትን ነገር ማግኘት ይችሉ ነበር? አይችሉም! እነዚህ ምሳሌዎች ይሖዋን ስንፈልግ ኢየሱስ እንዳስተማረው ‘መነዝነዝ’ ማለትም ሳንታክት ጥረት ማድረጋችን ተገቢ እንዲያውም አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝቡናል።—ሉቃስ 11:5-13
እንደ ፈቃዱ መለመን
ተአምራዊ ፈውስ ስላገኙ ሰዎች በሚናገሩት ከላይ በተጠቀሱት ታሪኮች ውስጥ ሰዎቹ የፈለጉትን ነገር ያገኙት ሳይታክቱ በመጣራቸው ብቻ ነውን? አይደለም። ጥረታቸው ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን ነበረበት። ኢየሱስ ተአምር ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል የተሰጠው የአምላክ ልጅና ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ማሳየት እንዲችል ነበር። (ዮሐንስ 6:14፤ 9:33፤ ሥራ 2:22) ከዚህም በላይ ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት ይሖዋ በክርስቶስ የሺህ ዓመት አገዛዝ ወቅት ለሰው ልጆች የሚያደርገውን የሚያሳዩ ናሙናዎች ነበሩ።—ራእይ 21:4፤ 22:2
በአሁኑ ወቅት እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች መፈወስንና በልሳን መናገርን የመሰሉ ተአምራቶች መፈጸም የሚያስችል ኃይል እንዲኖራቸው የአምላክ ፈቃድ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 13:8, 13) የእርሱ ፈቃድ የመንግሥቱ ምሥራች በምድር ዙሪያ እንዲሰበክና ‘ሰዎች ሁሉ እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የአምላክ አገልጋዮች ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ ልባዊ ጥረት ካደረጉ ጸሎታቸው እንደሚሰማላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።
አንዳንዶች ‘የአምላክ ዓላማ መፈጸሙ የማይቀር ከሆነ እኛ ጥረት ማድረጋችን ለምን አስፈለገ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይሖዋ ያለ ሰዎች እርዳታ ዓላማውን ከግብ ማድረስ እንደማያቅተው የታወቀ ቢሆንም ሰዎች ፈቃዱን ለመፈጸም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መመልከት ያስደስተዋል። ይሖዋ ቤት ከሚሠራ ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውዬው ቤቱን ለመሥራት ፕላኑን በጥብቅ የሚከተል ቢሆንም በአካባቢው የሚገኙ የግንባታ ቁሳቁሶችን ለመጠቀም ይመርጣል። በተመሳሳይም ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚያከናውነው ሥራ ያለው ሲሆን ለዚህ ሥራ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ አገልጋዮቹን መጠቀም ያስደስተዋል።—መዝሙር 110:3 አ.መ.ት፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16, 17
ቶሺዮ የተባለን አንድ ወጣት ተሞክሮ ተመልከት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ ትምህርት ቤቱን እንደ ልዩ የአገልግሎት መስክ በመቁጠር የቻለውን ያህል ምሥክርነት ለመስጠት አሰበ። ምንጊዜም መጽሐፍ ቅዱስ የማይለየው ሲሆን በጠባዩም ምሳሌ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። በመጀመሪያው የትምህርት ዓመት መገባደጃ ላይ ለክፍሉ ተማሪዎች ንግግር ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ አገኘ። ቶሺዮ ይሖዋ እንዲረዳው ጸለየ። “አቅኚ ለመሆን ያለኝ ግብ” በሚል ርዕስ ያቀረበውን ንግግር የክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ በጥሞና ስላዳመጡለት በጣም ተደሰተ። በንግግሩ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር። ከክፍሉ ተማሪዎች መካከል አንዱ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማ ሲሆን ከጊዜ በኋላ እድገት አድርጎ ተጠመቀ። ቶሺዮ ከጸሎቱ ጋር በሚስማማ መንገድ ያደረገው ልባዊ ጥረት ከፍተኛ በረከት አስገኝቶለታል።
አንተስ ልባዊ ጥረት ታደርጋለህ?
አንተም ይሖዋንና የእርሱን ሞገስ ከልብ እንደምትፈልግ በተለያዩ መንገዶች ማሳየት ትችላለህ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በደንብ መዘጋጀትን የመሰሉ ልታደርጋቸው የምትችላቸው መሠረታዊ ነገሮች አሉ። ጥሩ ዝግጅት የተደረገባቸው መልሶች በመስጠት፣ ለተግባር የሚያንቀሳቅሱ ንግግሮችንና ውጤታማ ሠርቶ ማሳያዎችን በማቅረብ ይሖዋን ከልብ እንደምትፈልግ ማሳየት ትችላለህ። የአገልግሎትህን ጥራት ማሻሻልም ሌላው ልታደርገው የምትችለው ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል አቀራረብህን ወዳጃዊ ለማድረግና ለአገልግሎት ክልልህ የሚስማማ መግቢያ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ ትችላለህ። (ቆላስይስ 3:23) አንድ ወንድም ጊዜውንና ጉልበቱን ሳይቆጥብ ራሱን በማቅረብ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ማገልገልን የመሳሰሉ ኃላፊነቶችን መቀበል ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2, 12, 13) ራስህን በፈቃደኝነት በማቅረብ መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ትችላለህ። በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ ወይም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለማገልገል ማመልከት ትችላለህ። እንዲሁም ያላገባህ ወንድም ከሆንህና ብቃቱን የምታሟላ ከሆነ መንፈሳዊ ወንዶች ጥሩ እረኞች እንዲሆኑ በሚሰለጥኑበት በአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መካፈል ትችላለህ። ያገባህ ከሆንክ ደግሞ ሚስዮናዊ በመሆን ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል ያለህን ፍላጎት ማሳየት ትችላለህ። የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዶ ማገልገልም ሌላው አማራጭ ነው።—1 ቆሮንቶስ 16:9
ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው ኃላፊነትህን የምትወጣበት መንፈስ ነው። ምንም ዓይነት ኃላፊነት ቢሰጥህ በትጋት፣ በከፍተኛ ፍላጎት እንዲሁም “በጥሩ ልብ” አከናውነው። (ሥራ 2:46፤ ሮሜ 12:8) የሚሰጥህን እያንዳንዱን ኃላፊነት ይሖዋን ለማስከበር ያለህን ልባዊ ፍላጎት ለማሳየት እንደሚያስችልህ አጋጣሚ አድርገህ ተመልከተው። ይሖዋ እንዲረዳህ አዘውትረህ ጸልይ፤ እንዲሁም አቅምህ የፈቀደልህን ሁሉ አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የተትረፈረፈ በረከት ታገኛለህ።
ልባዊ ጥረት ያስገኘው በረከት
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ፍርሃቱን ለማሸነፍ ይሖዋ እንዲረዳው የጸለየውን ወንድም ታስታውሰዋለህ? ይሖዋ ልባዊ ጥረቱን ባርኮለታል። አቀራረቡን ማራኪ ለማድረግና ውይይት ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን ለመጠቀም ጥረት አደረገ። ከዚያም ውጥረት የነገሠበት የሰዎች ግንኙነት ለሚያሳስበው አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም መሰከረለት። እዚያው ባቡር ላይ ለበርካታ ጊዜያት ተመላልሶ መጠየቅ ካደረገለት በኋላ ሰውዬው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። በእርግጥም ልባዊ ጥረት በማድረጉ ይሖዋ ባርኮታል።
አንተም ይሖዋን ከልብ የምትፈልግ ከሆነ ተመሳሳይ ውጤት ታገኛለህ። ያለመታከት ጥረት ማድረግህን ከቀጠልክና በማንኛውም ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ላይ አቅምህ የፈቀደልህን ካደረግህ ይሖዋ ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምብህ ከመሆኑም በላይ አብዝቶ ይባርክሃል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህች ሴት በቀላሉ ተስፋ ቆርጣ ቢሆን ኖሮ የፈለገችውን ማግኘት ትችል ነበር?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋን በረከት ለማግኘት ሳትታክት ትለምነዋለህ?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋን ከልብ እንደምትፈልግ እንዴት ማሳየት ትችላለህ?