የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች፣ መስከረም-ጥቅምት 2021
ከመስከረም 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘዳግም 33-34
“የይሖዋን ‘ዘላለማዊ ክንዶች’ መሸሸጊያ አድርጉ”
it-2 51
የሹሩን
ለእስራኤል የተሰጠ የማዕረግ ስም ነው። በግሪክኛ ሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥ “የሹሩን” የፍቅር መጠሪያ ሆኗል፤ “ተወዳጅ” ተብሎ ተተርጉሟል። “የሹሩን” የሚለው መጠሪያ እስራኤላውያን የይሖዋ የቃል ኪዳን ሕዝብ ሆነው መመረጣቸውን ሊያስታውሳቸው ይገባ ነበር፤ ይህ ደግሞ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኖ የመኖር ግዴታ እንደሚያስከትልባቸው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። (ዘዳ 33:5, 26፤ ኢሳ 44:2) ዘዳግም 32:15 ላይ የሹሩን የሚለው ስም የተሠራበት በምጸት አነጋገር ነው። እስራኤል የሹሩን እንደተባለው ስሙ ከመሆን ይልቅ ዓመፀኛ ሆነ፤ የሠራውን አምላክ ተወ፤ እንዲሁም አዳኙን ናቀ።
rr 120፣ ሣጥን
ተመልሰን በእግራችን እንድንቆም የሚያስችል እርዳታ
ሕዝቅኤል ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የኖረው ነቢዩ ሙሴ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ለመርዳት የሚያስችል ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም እንዳለው ተናግሮ ነበር። ሙሴ “አምላክ ከጥንት ጀምሮ መሸሸጊያ ነው፤ ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው” ሲል ጽፏል። (ዘዳ. 33:27) በእርግጥም አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን እርዳታ ለማግኘት አምላክን የምንጠይቀው ከሆነ በክንዶቹ አንስቶ በእግራችን እንደሚያቆመን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሕዝ. 37:10
ሩጫውን በጽናት ሩጡ
16 ልክ እንደ አብርሃም ሙሴም አምላክ የሰጠው ተስፋ በሕይወት ዘመኑ ሲፈጸም አልተመለከተም። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ በተቃረቡበት ወቅት ይሖዋ ለሙሴ “ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም” ብሎት ነበር። ይህ የሆነው ሙሴና አሮን ዓመፀኛ በሆነው ሕዝብ ተበሳጭተው ‘በመሪባ ውሃ አጠገብ በአምላክ ላይ መታመናቸውን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደሉ’ ነበር። (ዘዳ. 32:51, 52) ታዲያ ሙሴ በሐዘን ተውጦ ወይም ተማርሮ ነበር? በፍጹም። ሙሴ፣ እስራኤላውያንን የባረካቸው ሲሆን በንግግሩ መደምደሚያ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “እስራኤል ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ እግዚአብሔር ያዳነው ሕዝብ፣ እንዳንተ ያለ ማን አለ? እርሱ ጋሻህና ረዳትህ፣ የክብርህም ሰይፍ ነው።”—ዘዳ. 33:29
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 439 አን. 3
ሙሴ
ሙሴ በሞተበት ወቅት 120 ዓመቱ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ በወቅቱ ስለነበረው ጥንካሬ ሲናገር “ዓይኖቹ አልፈዘዙም፤ ጉልበቱም አልደከመም ነበር” ይላል። ይሖዋ የቀበረው ሲሆን መቃብሩ የት እንዳለ አይታወቅም። (ዘዳ 34:5-7) ይሖዋ ይህን ያደረገው እስራኤላውያን መቃብሩን እንደ ቅዱስ ስፍራ በመቁጠር በሐሰት አምልኮ ወጥመድ እንዳይያዙ ብሎ ሊሆን ይችላል። ዲያብሎስም የሙሴን ሥጋ ለእንዲህ ዓይነት ዓላማ ሊጠቀምበት ፈልጎ እንደነበር ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርና ወንድም የሆነው ይሁዳ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል የሙሴን ሥጋ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃል በመናገር ሊፈርድበት አልደፈረም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ይሖዋ ይገሥጽህ’ አለው።” (ይሁዳ 9) እስራኤላውያን በኢያሱ አመራር ሥር ሆነው ወደ ከነአን ምድር ከመግባታቸው በፊት ለሙሴ 30 ቀን አልቅሰውለታል።—ዘዳ 34:8
ከመስከረም 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 1-2
“መንገድህን ማቃናት የምትችለው እንዴት ነው?”
ደፋር ሁኑ—ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው!
7 የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ድፍረት እንዲኖረን ከፈለግን ቃሉን ማጥናትና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ኢያሱ ሙሴን በተካበት ወቅት እንዲህ እንዲያደርግ ተነግሮት ነበር፦ “ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አገልጋዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም። . . . ይህ የሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ በውስጡ የተጻፈውንም በጥንቃቄ መፈጸም እንድትችል ቀንም ሆነ ሌሊት እያነበብክ አሰላስል፤ እንዲህ ካደረክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።” (ኢያሱ 1:7, 8 NW) ኢያሱ ይህን ምክር ስለተከተለ ‘መንገዱ የተቃና’ ሆኖለታል። እኛም እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይበልጥ ደፋሮች ስለምንሆን በአምላክ አገልግሎት መንገዳችን የተቃና ይሆናል።
ደፋር ሁኑ—ይሖዋ ከእናንተ ጋር ነው!
20 በዚህ በክፋት በተሞላ ዓለም ውስጥ ችግሮች ሲጋረጡብን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ተፈታታኝ ነው። ያም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም። አምላክ ከእኛ ጋር ነው። የጉባኤው ራስ የሆነው ልጁ ኢየሱስም ከእኛ ጋር ነው። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ከ7,000,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች አሉልን። ከእነሱ ጋር በመሆን እምነት ማሳየታችንንና ምሥራቹን ማወጃችንን እንቀጥል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ ‘ደፋርና ብርቱ ሁን፤ አምላክህ ይሖዋ ከአንተ ጋር ነው’ የሚለውን የ2013ን የዓመት ጥቅስ ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ኢያሱ 1:9 NW
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
2:4, 5—ረዓብ ሰላዮቹን እንዲይዙ ንጉሡ የላካቸውን ሰዎች በተሳሳተ መንገድ የመራቻቸው ለምንድን ነው? ረዓብ ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላ ሰላዮቹን የደበቀቻቸው በይሖዋ ላይ እምነት እያዳበረች በመምጣቷ ነው። ስለዚህ የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ይፈልጉ ለነበሩ ሰዎች ሰላዮቹን አሳልፎ የመስጠት ግዴታ የለባትም። (ማቴዎስ 7:6፤ 21:23-27፤ ዮሐንስ 7:3-10) እንዲያውም፣ ረዓብ ‘የጸደቀችው’ የንጉሡን መልእክተኞች በተሳሳተ አቅጣጫ በመምራቷ ጭምር ነው።—ያዕቆብ 2:24-26
ከመስከረም 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 3-5
“ይሖዋ በእምነት የምናከናውናቸውን ሥራዎች ይባርካል”
it-2 105
ዮርዳኖስ
የዮርዳኖስ ወንዝ ከገሊላ ባሕር በታች ሲደርስ፣ ጥልቀቱ በአማካይ ከ1 እስከ 3 ሜትር ይደርሳል፤ ስፋቱ ደግሞ ከ27 እስከ 30 ሜትር ገደማ ይሆናል። በጸደይ ወቅት ግን የዮርዳኖስ ወንዝ ሞልቶ ዳርቻውን ሁሉ ያጥለቀልቃል፤ በዚህ ጊዜ ስፋቱም ሆነ ጥልቀቱ ይጨምራል። (ኢያሱ 3:15) የዮርዳኖስ ወንዝ እንዲህ በሞላበት ወቅት ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን ላቀፈው የእስራኤል ብሔር ወንዙን መሻገር (በተለይ ኢያሪኮ አቅራቢያ) አደገኛ ነበር። በዚህ አካባቢ የውኃው ፍሰት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ቅርብ ጊዜ እንኳ ወንዙ ውስጥ የሚታጠቡ ሰዎች በውኃ ተወስደው ያውቃሉ። ይሖዋ ግን በተአምር የዮርዳኖስ ወንዝ እንደ ግድብ ተቆልሎ እንዲቆም አደረገ፤ በመሆኑም እስራኤላውያን በደረቅ ምድር መሻገር ቻሉ። (ኢያሱ 3:14-17) ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ ኤልያስ ከኤልሳዕ ጋር ሆኖ ተመሳሳይ ተአምር ሲፈጸም ተመልክቷል፤ በኋላ ላይ ደግሞ ኤልሳዕ ብቻውን ይህ ተአምር ሲፈጸም አይቷል።—2ነገ 2:7, 8, 13, 14
ልባችሁ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ሐሴት ያድርግ
17 ታዲያ መንፈሳዊ ሥራዎችን ማከናወን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለመገንባት የሚረዳን እንዴት ነው? እስቲ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ሲሉ የሆነውን ነገር ለማየት እንሞክር። ይሖዋ የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናት የዮርዳኖስን ወንዝ እንዲያቋርጡ መመሪያ ሰጣቸው። ይሁንና ወደ ወንዙ ሲደርሱ በጸደይ ወቅት በጣለው ዝናብ ምክንያት ወንዙ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። ታዲያ እስራኤላውያን ምን ያደርጉ ይሆን? ወንዙ አጠገብ በመስፈር ውኃው እስኪጎድል ለሳምንታት አሊያም ከዚያ በላይ ይጠብቁ ይሆን? በጭራሽ፤ ከዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመን መመሪያውን ተከተሉ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ታቦቱን የተሸከሙት ካህናት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በደረሱ ጊዜ እግራቸው ውሃውን እንደ ነካ፣ ከላይ የሚወርደው ውሃ ቆመ፤ . . . የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ካህናትም፣ ሕዝቡ ሁሉ ማለት እስራኤል በሙሉ ፈጽመው እስኪሻገሩ ድረስ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል በደረቁ ምድር ላይ ቀጥ ብለው ቆመው ነበር።” (ኢያሱ 3:12-17) እየተንደረደረ ሲመጣ የነበረው ውኃ ቀጥ ሲል እስራኤላውያኑ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ገምት! እስራኤላውያን ይሖዋ በሰጣቸው መመሪያ በመታመናቸው በእሱ ላይ ያላቸው እምነት ተጠናክሮ እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው።
ልባችሁ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ሐሴት ያድርግ
18 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ሕዝቦቹ እንዲህ ዓይነት ተአምር አይሠራም፤ ይሁንና ሕዝቦቹ የሚያከናውኗቸውን መንፈሳዊ ሥራዎች ይባርካል። በሥራ ላይ ያለው የአምላክ ኃይል የመንግሥቱን መልእክት በዓለም ዙሪያ ማዳረስ እንዲችሉ ኃይል ይሰጣቸዋል። ከሁሉ የላቀ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ምንጊዜም ከጎናቸው እንደሚሆን ማረጋገጫ ሲሰጣቸው እንዲህ ብሏል፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ . . . እነሆም እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ. 28:19, 20) የማፈር ወይም የመፍራት ባሕርይ የነበራቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በአገልግሎት ለሚያገኟቸው ሰዎች ምሥራቹን እንዲናገሩ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድፍረት እንደሰጣቸው ተሰምቷቸዋል።—መዝሙር 119:46ን እና 2 ቆሮንቶስ 4:7ን አንብብ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
5:14, 15—“የእግዚአብሔር ሰራዊት አለቃ” ማን ነው? ኢያሱ የተስፋይቱን ምድር ነዋሪዎች ድል እያደረገ አካባቢውን መቆጣጠር በጀመረበት ጊዜ እርሱን ለማበረታታት የመጣው አለቃ፣ ሰው ከመሆኑ በፊት “ቃል” ይባል ከነበረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 1:1፤ ዳንኤል 10:13) ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች በሚያደርጉት መንፈሳዊ ውጊያ እንደሚያግዛቸው ማወቁ እንዴት ያበረታታል!
ከመስከረም 27–ጥቅምት 3
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 6-7
“ከንቱ ከሆኑ ነገሮች ራቁ”
ከንቱ ነገር ከማየት ዓይናችሁን መልሱ!
5 ይህ ከሆነ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ አካን የተባለው እስራኤላዊ በምርኮ በተያዘችው በኢያሪኮ ከተማ ውስጥ ያያቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማግኘት ዓይኑ በመቋመጡ ለመስረቅ ተነሳስቷል። ወደ ይሖዋ ግምጃ ቤት ከሚገቡት አንዳንድ ነገሮች ውጪ በዚያች ከተማ ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ መጥፋት እንዳለባቸው አምላክ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። እስራኤላውያን በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን ነገሮች እንዳይመኙና እንዳይወስዱ ሲባል “እርም ከሆኑት ነገሮች” እንዲርቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር። አካን ይህን ትእዛዝ በመጣሱ እስራኤላውያን በጋይ ከተማ ሽንፈት ያጋጠማቸው ሲሆን አንዳንዶቹም ሕይወታቸውን አጥተዋል። አካን ጉዳዩ በግልጽ እስኪታወቅ ድረስ ጥፋቱን አላመነም ነበር። አካን በተጋለጠ ጊዜ “[ዕቃዎቹን] አይቼ ጐመጀሁ፤ ወሰድኋቸውም” በማለት ተናገረ። አካን በዓይን አምሮት መሸነፉ እሱም ሆነ ‘የእሱ የሆነው ሁሉ’ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። (ኢያሱ 6:18, 19፤ 7:1-26) አካን እንዳይወስድ የተከለከለውን ነገር በልቡ ተመኘ።
ኃጢአትን መግለጥ ለምን አስፈለገ?
አንድን ኃጢአት መግለጥ አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ ነው። ይሖዋ ንጹሕና ቅዱስ የሆነ አምላክ ነው። እሱን የሚያመልኩ ሁሉ በመንፈሳዊና በሥነ ምግባር ንጹሕ እንዲሆኑ ይፈልጋል። በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ። ዳሩ ግን፦ እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 1:14-16) ርኩስ የሆኑ ድርጊቶችን ወይም ኃጢአትን የሚፈጽሙ ግለሰቦች እንዲታረሙ አለዚያም እንዲወገዱ ካልተደረገ መላውን ጉባኤ ሊያረክሱና የይሖዋን ሞገስ እንዲያጣ ሊያደርጉ ይችላሉ።—ከኢያሱ ምዕራፍ 7 ጋር አወዳድር።
ከንቱ ነገር ከማየት ዓይናችሁን መልሱ!
8 እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓይን አምሮትና በሥጋ ምኞት እንዳይሸነፉ የሚከላከል ክትባት አልወሰዱም። በመሆኑም የአምላክ ቃል በምናያቸውና በምንመኛቸው ነገሮች ረገድ ራሳችንን እንድንገዛ ማበረታቻ ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 9:25, 27፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።) ቅን ሰው የነበረው ኢዮብ፣ ዓይናችን አንድን ነገር እንድንመኝ የማድረግ ኃይል እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:1) ኢዮብ ሴትን ሥነ ምግባር በጎደለው መንገድ መንካት ይቅርና እንዲህ ዓይነቱን ሐሳብ በአእምሮው እንኳ ላለማውጠንጠን ቆርጦ ነበር። ኢየሱስ አእምሯችን ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ሐሳቦች የጸዳ መሆን እንዳለበት ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።”—ማቴ. 5:28
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በጥንት ዘመን ወራሪዎች በግንብ የታጠረችን ከተማ ለማጥቃት ዙሪያዋን መክበባቸው የተለመደ ነበር። ወራሪዎቹ የከበቧትን ከተማ ድል አድርገው ለመቆጣጠር የሚፈጅባቸው ጊዜ ምንም ያህል ይሁን፣ በከተማዋ ውስጥ የተረፈውን እህል ጨምሮ የከተማዋን ሀብት በሙሉ ይመዘብራሉ። ይሁን እንጂ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች የኢያሪኮን ፍርስራሽ ሲመረምሩ ከፍተኛ የእህል ክምችት አግኝተዋል። ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተሰኘ መጽሔት ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፦ “በከተማዋ ፍርስራሽ ውስጥ ከሸክላ ዕቃዎች ሌላ በብዛት የተገኘው ነገር እህል ነው። . . . በፓለስቲና ምድር በተደረገው አርኪኦሎጂያዊ ምርምር ይህ ያልተለመደ ነገር ነው። [በቁፋሮ ወቅት] አንድ ወይም ሁለት ጎታ እህል ይገኝ ይሆናል፤ ይህን ያህል ብዛት ያለው እህል ማግኘት ግን አዲስ ነገር ነው።”
ቅዱስ ጽሑፋዊው ዘገባ በሚናገረው መሠረት እስራኤላውያን የኢያሪኮን እህል ያልዘረፉበት በቂ ምክንያት ነበራቸው። ይሖዋ ምንም ነገር እንዳይወስዱ አዟቸው ነበር። (ኢያሱ 6:17, 18) እስራኤላውያን ኢያሪኮን የወረሯት የመከር ወቅት እንዳለፈ በመሆኑ ከተማዋ ከፍተኛ የእህል ክምችት ነበራት። (ኢያሱ 3:15-17፤ 5:10) በኢያሪኮ ውስጥ ብዙ እህል መገኘቱ፣ እስራኤላውያን ከተማዋን የከበቧት ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ለአጭር ጊዜ እንደሆነ ይጠቁማል።
ከጥቅምት 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 8-9
“ስለ ገባኦናውያን ከሚናገረው ታሪክ የምናገኛቸው ትምህርቶች”
it-1 930-931
ገባኦን
ከኢያሱ ጋር ያደረጉት ስምምነት። በኢያሱ ዘመን የገባኦን ነዋሪዎች ሂዋውያን ነበሩ፤ ሂዋውያን ለጥፋት ከተወሰኑት ሰባት ከነአናውያን ብሔራት አንዱ ናቸው። (ዘዳ 7:1, 2፤ ኢያሱ 9:3-7) ገባኦናውያን አሞራውያን ተብለውም ተጠርተዋል፤ ይህ መጠሪያ ከነአናውያንን በአጠቃላይ ለማመልከት የተሠራበት ጊዜም አለ። (2ሳሙ 21:2፤ ከዘፍ 10:15-18፤ 15:16 ጋር አወዳድር።) ከሌሎቹ ከነአናውያን በተቃራኒ ገባኦናውያን ይሖዋ ለእስራኤል እየተዋጋ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር፤ በመሆኑም በወታደራዊ ኃይላቸውና በከተማቸው ታላቅነት መታመናቸው እንደማያዋጣ ገብቷቸው ነበር። ኢያሪኮና ጋይ ከጠፉ በኋላ የገባኦን ሰዎች (ከፊራ፣ በኤሮት እና ቂርያትየአሪም የተባሉትን ሦስት የሂዋውያን ከተሞች ነዋሪዎችም በመወከል ሳይሆን አይቀርም) ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም ለመፍጠር በጊልጋል ወዳለው ወደ ኢያሱ መልእክተኞች ላኩ። (ኢያሱ 9:17) የገባኦናውያን መልእክተኞች ወደ ኢያሱ የሄዱት ያረጀ ልብስ ለብሰውና ያለቀ ጫማ አድርገው እንዲሁም የተቀዳደዱ የወይን ጠጅ አቁማዳዎች፣ ያረጁ ከረጢቶች፣ ደረቅና የተፈረፈረ ዳቦ ይዘው ነበር፤ ይህን ያደረጉት እስራኤላውያን ድል ከሚያደርጓቸው ከተሞች ከአንዱ ሳይሆን ከሩቅ አገር እንደመጡ ለማስመሰል ነው። ይሖዋ በግብፅ እንዲሁም ሲሖንና ኦግ በተባሉት ሁለት የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ያደረገውን እንደሰሙ ገለጹ። በኢያሪኮና በጋይ ላይ የደረሰውን ነገር አለመጥቀሳቸው ግን ብልህነታቸውን ያሳያል፤ ምክንያቱም እንዳሉት “ከሩቅ አገር” ከመጡ ለጉዞ ከመነሳታቸው በፊት ይህ ዜና ሊደርሳቸው አይችልም። የእስራኤል ተወካዮች ማስረጃውን ከመረመሩ በኋላ አመኗቸው፤ እንደማያጠፏቸውም ቃል ኪዳን ገቡላቸው።—ኢያሱ 9:3-15
“በራስህ ማስተዋል አትደገፍ”
14 ልምድ ያካበቱ ሽማግሌዎችም እንኳ ሳይቀሩ ሁላችንም ፍጽምና የሚጎድለን በመሆኑ ውሳኔ ስናደርግ መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዘወር ማለት እንዳለብን መርሳት አይኖርብንም። ብልሃተኞቹ ገባዖናውያን ራሳቸውን በመለወጥ ከሩቅ ቦታ እንደመጡ ለማስመሰል በሞከሩ ጊዜ የሙሴ ተተኪ የሆነው ኢያሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች ምን እንዳደረጉ ተመልከት። ኢያሱም ሆነ ሽማግሌዎቹ ይሖዋን ሳይጠይቁ ከገባዖናውያን ጋር በሰላም ለመኖር ቃል ኪዳን አደረጉ። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ የተደረገውን ስምምነት ደግፎታል፤ ያም ቢሆን መመሪያ አለመጠየቃቸው ትክክል ባለመሆኑ ዘገባው ለእኛ ትምህርት እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል።—ኢያሱ 9:3-6, 14, 15
‘ምድሪቱን ተመላለስባት’
14 የገባዖናውያን ወኪሎች “እኛ ባሪያዎችህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ዝና ሰምተን፣ እጅግ ሩቅ ከሆነ አገር መጥተናል” በማለት አስረዱ። (ኢያሱ 9:3-9) ደግሞም ልብሳቸውና የያዙት ምግብ ሲታይ ከጌልገላ 30 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ ቦታ ሳይሆን በእርግጥም ከሩቅ አገር የመጡ የሚያስመስል ነበር። ኢያሱና የሕዝቡ አለቆች ምንም ስላልተጠራጠሩ ከገባዖናውያንና በአቅራቢያቸው ካሉት ሌሎች ከተሞች ጋር የሰላም ስምምነት ተዋዋሉ። ገባዖናውያን ይህን መላ የዘየዱት እንዳይጠፉ ስለፈሩ ብቻ ነው? በፍጹም፤ የእስራኤላውያንን አምላክ ሞገስ ለማግኘት ይፈልጉ እንደነበር ከሁኔታቸው መረዳት ይቻላል። ይሖዋም ገባዖናውያን ‘ለማኅበረሰቡና ለእግዚአብሔር መሠዊያ ዕንጨት ቈራጮችና ውሃ ቀጂዎች’ እንዲሆኑ ፈቀደላቸው። (ኢያሱ 9:11-27) ገባዖናውያንም ቢሆኑ በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ይህን ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ለማከናወን ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲያውም ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው በቤተ መቅደሱ ግንባታ ከተካፈሉት ናታኒሞች መካከል አንዳንዶቹ ገባዖናውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። (ዕዝራ 2:1, 2, 43-54፤ 8:20) እኛም ከአምላክ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት በመመሥረትና በእርሱ አገልግሎት ውስጥ ትሕትና የሚጠይቁ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቃደኛ በመሆን የእነርሱን ምሳሌ መኮረጅ እንችላለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1030
ስቅላት
ይሖዋ ለእስራኤል በሰጠው ሕግ መሠረት አንዳንድ ወንጀለኞች ከተገደሉ በኋላ በእንጨት ላይ እንዲሰቀሉ ይደረግ ነበር፤ እንዲህ ዓይነቱ ወንጀለኛ ‘በአምላክ እንደተረገመ’ የሚቆጠር ሲሆን ተሰቅሎ ሕዝብ እንዲያየው የሚደረገው መቀጣጫ እንዲሆን ነው። የተሰቀለው ሰው በድን፣ ከመምሸቱ በፊት እንዲወርድና እንዲቀበር ሕጉ ያዝዝ ነበር፤ በድኑን ውጪ ማሳደር አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ምድር ያረክሳል። (ዘዳ 21:22, 23) የተሰቀለው ሰው እስራኤላዊ ባይሆንም እንኳ እስራኤላውያን ይህን መመሪያ ተግባራዊ ያደርጉ ነበር።—ኢያሱ 8:29፤ 10:26, 27
ከጥቅምት 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 10-11
“ይሖዋ ለእስራኤል ተዋጋ”
it-1 50
አዶኒጼዴቅ
እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር በያዙበት ወቅት የኢየሩሳሌም ንጉሥ ነበር። ኢያሱ የሚያደርገውን የድል ግስጋሴ ለመግታት አዶኒጼዴቅ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ካሉ ትናንሽ መንግሥታት ጋር አበረ። (ኢያሱ 9:1-3) በገባኦን የሚኖሩት ሂዋውያን ግን ከኢያሱ ጋር ሰላም ፈጠሩ። አዶኒጼዴቅ ሌሎችም ወደ ጠላት ሰራዊት ከድተው እንዳይገቡ ሲል የበቀለ እርምጃ ለመውሰድ አሴረ፤ ከቀሩት አራት አሞራውያን ነገሥታት ጋር ግንባር በመፍጠር ገባኦንን ከበቧት። ኢያሱ ገባኦናውያንን ለመታደግ በወሰደው አስደናቂ እርምጃ ጥምር ኃይሉ ከባድ ሽንፈት ስለደረሰበት አምስቱ ነገሥታት ወደ መቄዳ ሸሹ፤ በዚያም ዋሻው ውስጥ ዘጉባቸው። ኢያሱ ሠራዊቱ እያየ፣ አዶኒጼዴቅንና አራቱን ነገሥታት በሰይፍ ገደላቸው፤ ከዚያም በእንጨት ላይ ሰቀላቸው። አስከሬናቸው፣ የተደበቁበት ዋሻ ውስጥ ተጣለ፤ መቃብራቸውም እዚያው ሆነ።—ኢያሱ 10:1-27
it-1 1020
በረዶ
ይሖዋ እንዴት ተጠቅሞበታል? በረዶ፣ ይሖዋ ቃሉን ለመፈጸምና ታላቅ ኃይሉን ለማሳየት ከሚጠቀምባቸው ኃይሎች አንዱ ነው። (መዝ 148:1, 8፤ ኢሳ 30:30) ይህን የሚያሳየው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው ዘገባ በጥንቷ ግብፅ ላይ ስለወረደው ሰባተኛ መቅሰፍት የሚናገረው ታሪክ ነው፤ በዚህ ወቅት የወረደው በረዶ ሜዳ ላይ ያለውን ተክልና ዛፍ በሙሉ አውድሟል፤ መስክ ላይ ያሉትን ሰዎችና እንስሳት ገድሏል፤ በጎሸን ምድር የሚኖሩትን እስራኤላውያንን ግን አልነካቸውም። (ዘፀ 9:18-26፤ መዝ 78:47, 48፤ 105:32, 33) በኋላ ላይ እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ሲቆጣጠሩ ጥምረት የፈጠሩ አምስት አሞራውያን ነገሥታት ገባኦናውያንን ለውጊያ ከበቡ፤ በዚህ ጊዜ ኢያሱና ሠራዊቱ እነሱን ለመርዳት ዘመቱ፤ ይሖዋም ጥቃት በሰነዘሩት አሞራውያን ላይ ትላልቅ የበረዶ ድንጋዮችን አወረደባቸው። በዚህ ውጊያ ላይ በእስራኤላውያን ሰይፍ ከሞቱት ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት ይበልጣሉ።—ኢያሱ 10:3-7, 11
የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
10:13—ይህ ያልተለመደ ክስተት እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የሰማይና የምድር ፈጣሪ ለሆነው “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?” (ዘፍጥረት 18:14) ይሖዋ ከፈለገ ምድር እንዳትንቀሳቀስ በማድረግ ከምድር ሆኖ ለሚመለከት ሰው ፀሐይና ጨረቃ የቆሙ መስለው እንዲታዩት ማድረግ ይችላል። ወይም ደግሞ የምድርና የጨረቃ እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል ከፀሐይና ከጨረቃ የሚመጣውን ብርሃን አቅጣጫ በማስቀየር ምድር ብርሃን እንድታገኝ ማድረግ ይችላል። ፀሐይ እንድትቆም የተደረገበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ “እንደዚያ ያለ ዕለት . . . አልነበረም።”—ኢያሱ 10:14
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
አንዳንድ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሳቸውና ለመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች መነሻ ሆነው ማገልገላቸው በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው ብለን እንድንደመድም ሊያደርገን አይገባም። ይሖዋ አምላክ ‘የአምላካችንን ቃል’ የያዙት መጻሕፍት በሙሉ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደረገ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት ‘ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።’ (ኢሳ. 40:8) አዎን፣ ይሖዋ “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” ሆነን ለመገኘት የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ አሁን ባሉን 66 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተት አድርጓል።—2 ጢሞ. 3:16, 17
ከጥቅምት 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 12-14
“ይሖዋን በሙሉ ልብ ተከተሉ”
የኢያሱ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
14:10-13፦ ካሌብ 85 ዓመት የሞላው ቢሆንም እንኳ የኬብሮንን ነዋሪዎች ከከተማው የማስወጣት ከባድ ሥራ እንዲሰጠው ጠየቀ። በዚህ ስፍራ በጣም ረጃጅም የሆኑት ዔናቃውያን ይኖሩ ነበር። ይህ ልምድ ያለው ተዋጊ በይሖዋ እርዳታ ተሳክቶለት ኬብሮንን በእጁ ያስገባ ሲሆን በኋላም ቦታው የመማጸኛ ከተማ ሆነ። (ኢያሱ 15:13-19፤ 21:11-13) ይህ የካሌብ ታሪክ ከባድ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን እንዳንሸሽ ያበረታታናል።
እምነትና አምላካዊ ፍርሃት የሚያስገኘው ድፍረት
11 እንዲህ ዓይነቱ እምነት ባለበት የሚቆም አይደለም። እውነትን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ባደረግን፣ የዚህንም ጥቅም ‘በቀመስን’ እንዲሁም ለምናቀርባቸው ጸሎቶች የሚሰጡንን ምላሾች ‘ባየን’ ቁጥር በሌላ አነጋገር በእርግጥ ይሖዋ እየመራን መሆኑን በተገነዘብን መጠን እምነታችን እያደገ ይሄዳል። (መዝሙር 34:8፤ 1 ዮሐንስ 5:14, 15) ኢያሱና ካሌብ የአምላክን ጥሩነት መቅመሳቸው ጥልቅ እምነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እንዳደረገ እሙን ነው። (ኢያሱ 23:14) የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦ አምላክ ቃል በገባላቸው መሠረት ከ40 ዓመቱ የምድረ በዳ ጉዞ በሕይወት ተርፈዋል። (ዘኍልቍ 14:27-30፤ 32:11, 12) ከነዓንን ለመያዝ በተደረገው የስድስት ዓመት ጦርነት በትጋት ተካፍለዋል። በመጨረሻም ረጅም ዕድሜና ጥሩ ጤንነት እንዲሁም የራሳቸው ርስት አግኝተዋል። በእርግጥም ይሖዋ በታማኝነትና በድፍረት የሚያገለግሉትን አብዝቶ ይባርካቸዋል!—ኢያሱ 14:6, 9-14፤ 19:49, 50፤ 24:29
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 902-903
ጌባል
ይሖዋ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጎ ከሰጣቸው፣ ሆኖም በኢያሱ ጊዜ ገና ካልተቆጣጠሯቸው ክልሎች መካከል “የጌባላውያን ምድር” ይገኝበታል። (ኢያሱ 13:1-5) መጽሐፍ ቅዱስን የሚተቹ ሰዎች ይህን ሐሳብ እንደ ስህተት አድርገው ይጠቅሱታል፤ ምክንያቱም የጌባል ከተማ የምትገኘው ከእስራኤል ሰሜናዊ ወሰን (ይኸውም ከዳን በስተ ሰሜን 100 ኪሎ ሜትር ገደማ) በጣም ርቃ ነው፤ በኋላ ላይም ቢሆን ይህች ከተማ በእስራኤላውያን ቁጥጥር ሥር የወደቀች አይመስልም። አንዳንድ ምሁራን የዕብራይስጡ ጽሑፍ እዚህ ጥቅስ ላይ ጉዳት ደርሶበት ሊሆን እንደሚችል ሐሳብ ይሰጣሉ፤ ጥቅሱ በጥንታዊ ቅጂዎች ላይ “ከሊባኖስ ቀጥሎ ያለው ምድር” ወይም “እስከ ጌባላውያን ወሰን ድረስ” እንደሚል ይገምታሉ። ሌላው ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ነገር ግን ይሖዋ በኢያሱ 13:2-7 ላይ የገባው ቃል በእስራኤላውያን ሁኔታ ላይ የተመካ መሆኑን ነው። ከዚህ አንጻር እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸው የተነሳ የጌባልን ምድር ሳይቆጣጠሩ ቀርተው ሊሆን ይችላል።—ከኢያሱ 23:12, 13 ጋር አወዳድር።
ከጥቅምት 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ኢያሱ 15-17
“ውድ የሆነውን ውርሻችሁን ጠብቁ”
it-1 1083 አን. 3
ኬብሮን
እስራኤላውያን በደቡባዊ ከነአን የሚያደርጉትን ዘመቻ ሲቀጥሉ የኬብሮንን ንጉሥና (የሆሐም ተተኪ ሳይሆን አይቀርም) ነዋሪዎቿን አጥፍተዋል። (ኢያሱ 10:36, 37) እርግጥ ነው፣ እስራኤላውያን በኢያሱ አመራር ሥር ሆነው የከነአናውያንን ሰራዊት ማሽመድመድ ችለዋል፤ ይሁንና የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች የሚጠብቁ ወታደሮች ያሰፍሩ የነበረ አይመስልም። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው እስራኤላውያን ወደ ሌላ ጦርነት ሲሄዱ ኤናቃውያን መልሰው በኬብሮን የሰፈሩ ይመስላል፤ በኋላ ላይ ካሌብ (ወይም በእሱ አመራር ሥር ያሉ የይሁዳ ወንዶች) ኤናቃውያንን ከከተማይቱ ማባረር ያስፈለገው ለዚህ ነው። (ኢያሱ 11:21-23፤ 14:12-15፤ 15:13, 14፤ መሳ 1:10) መጀመሪያ ላይ ከይሁዳ ነገድ ለሆነው ለካሌብ ተሰጥታ የነበረችው ኬብሮን በኋላ ላይ መማጸኛ ከተማ እንድትሆን ተለይታለች። የካህናት ከተማ በመሆንም አገልግላለች። “[የኬብሮን ከተማ] እርሻና መንደሮቿ” ግን ለካሌብ ዘሮች ርስት ሆነው የተሰጡ ነበሩ።—ኢያሱ 14:13, 14፤ 20:7፤ 21:9-13
it-1 848
የግዳጅ ሥራ
ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው፣ በጥንት ዘመን “የግዳጅ ሥራ” (በዕብራይስጥ፣ ማስ) የተለመደ ነገር ነበር፤ ድል የተደረጉ ሕዝቦች ብዙውን ጊዜ ባሪያዎች ይደረጉ ነበር። (ዘዳ 20:11፤ ኢያሱ 16:10፤ 17:13፤ አስ 10:1፤ ኢሳ 31:8፤ ሰቆ 1:1) እስራኤላውያን ግብፅ ሳሉ የግዳጅ ሥራ የሚያከናውኑ ባሪያዎች ነበሩ፤ ጨቋኝ የነበሩት ግብፃውያን አለቆቻቸው ጲቶም እና ራምሴስ የተባሉ የማከማቻ ከተሞችን አሠርተዋቸዋል። (ዘፀ 1:11-14) ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ ከነአናውያንን ከምድሪቱ ላይ እንዲያባርሩና እንዲያጠፉ ይሖዋ የሰጣቸውን ትእዛዝ ከመከተል ይልቅ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው። እንዲህ ማድረጋቸው እስራኤላውያን በጣዖት አምልኮ እንዲያዙ ወጥመድ ሆኖባቸዋል። (ኢያሱ 16:10፤ መሳ 1:28፤ 2:3, 11, 12) በኋላ ላይም ንጉሥ ሰለሞን የከነአናውያንን ዝርያዎች ማለትም አሞራውያንን፣ ሂታውያንን፣ ፈሪዛውያንን፣ ሂዋውያንንና ኢያቡሳውያን ለግዳጅ ሥራ መልምሏቸዋል።—1ነገ 9:20, 21
it-1 402 አን. 3
ከነአን
ከእስራኤላውያን የጦርነት ግስጋሴ የተረፉና በእነሱ ቁጥጥር ስር ያልወደቁ ብዙ ከነአናውያን ቢኖሩም ይሖዋ ለእስራኤላውያን “ለአባቶቻቸው ለመስጠት የማለላቸውን ምድር በሙሉ” ሰጥቷቸዋል እንዲሁም “በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ እረፍት” ሰጥቷቸዋል ቢባል ስህተት አይደለም፤ “ይሖዋ ለእስራኤል ቤት ከገባው መልካም ቃል ሁሉ ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም፤ ሁሉም ተፈጽሟል።” (ኢያሱ 21:43-45) በእስራኤላውያን ዙሪያ ያሉት ጠላት ሕዝቦች በፍርሃት ተሽመድምደው ስለነበር ለእስራኤላውያን ደህንነት ስጋት የሚፈጥር ምንም ዓይነት አቅም አልነበራቸውም። ቀደም ሲል አምላክ ከነአናውያንን የሚያስወጣቸው “ጥቂት በጥቂት” እንደሆነ ተናግሮ ነበር፤ ይህን ያደረገው ባድማ በሆነው ምድር ላይ የዱር አራዊት እንዳይበዙ ነው። (ዘፀ 23:29, 30፤ ዘዳ 7:22) እርግጥ ነው፣ ከነአናውያን የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው የጦር ሠረገሎችን ጨምሮ ከእስራኤላውያን የተሻለ የጦር መሣሪያ ነበራቸው፤ ይሁንና እስራኤላውያን አንዳንድ አካባቢዎችን መቆጣጠር ያልቻሉት ይሖዋ ቃሉን መጠበቅ ስላቃተው አይደለም። (ኢያሱ 17:16-18፤ መሳ 4:13) ከዚህ ይልቅ ዘገባው እንደሚጠቁመው፣ እስራኤላውያን አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሽንፈት የደረሰባቸው ባለመታዘዛቸው ነው።—ዘኁ 14:44, 45፤ ኢያሱ 7:1-12
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ይህን ያውቁ ኖሯል?
የጥንቷ እስራኤል መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን ያህል በደን የተሸፈነች ነበረች?
የተስፋይቱ ምድር አንዳንድ አካባቢዎች በደን የተሸፈኑና ዛፎች ‘በብዛት’ የሚገኙባቸው እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ነገ. 10:27፤ ኢያሱ 17:15, 18) ሆኖም በዛሬው ጊዜ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የተመነጠረ ከመሆኑ አንጻር አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው ሐሳብ እውነት መሆኑን ይጠራጠሩ ይሆናል።
ላይፍ ኢን ቢብሊካል ኢዝሬል የተሰኘው መጽሐፍ “በጥንቷ እስራኤል፣ በዛሬው ጊዜ ካለው እጅግ የሚበልጥ ሰፊ ቦታ የሚሸፍኑ ደኖች ነበሩ” ይላል። በደጋ አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ደን በዋነኝነት ጥድን (Pinus halepensis)፣ ባሉጥን (Quercus calliprinos) እና ቴረቢንዝን (Pistacia palaestina) ያካትት ነበር። በማዕከላዊው የተራራ ሰንሰለትና በሜድትራንያን የባሕር ዳርቻ መካከል ያለውን አካባቢ በሚጨምረው በሸፌላ ደግሞ የሾላ ዛፎችም (Ficus sycomorus) በብዛት ይገኙ ነበር።
ፕላንትስ ኦቭ ዘ ባይብል የተሰኘው መጽሐፍ በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል አንዳንድ አካባቢዎች ዛፍ የሚባል ነገር እንደሌለባቸው ይናገራል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ይህ ቀስ በቀስ የተከሰተ ነገር እንደሆነ መጽሐፉ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች በዋነኝነት የእርሻና የግጦሽ ቦታቸውን ለማስፋት እንዲሁም ለግንባታ ቁሳቁሶችና ለማገዶ የሚሆን እንጨት ለማግኘት ሲሉ የተፈጥሮውን ደን ለረጅም ጊዜ ሲጨፈጭፉት ቆይተዋል።”