አሞናውያን—ለተደረገላቸው ደግነት ጥላቻ የመለሱ ሰዎች
የሀሽማይቷ መንግሥት የዮርዳኖስ ዋና ከተማ የሆነችው ዘመናዊቷ አማን ከምድረ ገጽ የጠፋ አንድ ሕዝብ ታስታውሰናለች። እነዚህ ሰዎች አሞናውያን ይባሉ ነበር። አሞናውያን እነማን ነበሩ? ከእነርሱ ውድቀት ምን እንማራለን?
አሞናውያን የጻድቁ ሎጥ ዘር ነበሩ። (ዘፍጥረት 19:35–38) ሎጥ የአብርሃም የወንድም ልጅ ስለሆነ አሞናውያን የእስራኤላውያን ዘመዶች ነበሩ ማለት ትችላለህ። ቢሆንም የሎጥ ዝርያዎች የሐሰት አማልክት ማምለክ ጀመሩ። ይሖዋ አምላክ ግን ደግነት ማሳየቱን ቀጠለ። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲቃረቡ አምላክ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር፦ “ለሎጥም ልጆች ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከአሞን ልጆች ምድር ርስት አልሰጥህምና በአሞን ልጆች አቅራቢያ ስትደርስ አትጣላቸው አትውጋቸውም።”—ዘዳግም 2:19
አሞናውያን ይህንን ደግነት አድንቀውት ነበርን? አላደነቁም፣ እንዲያውም ይሖዋ ምንም አላደረገልንም አሉ። አምላክ ላሳያቸው ደግነት የሰጡት ምላሽ የአምላክ ሕዝብ በነበሩት እስራኤላውያን ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ማሳደር ነበር። ምንም እንኳ እስራኤላውያን የይሖዋን ትእዛዝ በማክበር በአሞናውያን ላይ ጦርነት ባይከፍቱም አሞናውያንም ሆኑ ወንድሞቻቸው ሞዓባውያን ስጋት ላይ ወደቁ። እውነት ነው፣ አሞናውያን ወታደራዊ ጥቃት አልሰነዘሩም፤ ሆኖም በለዓም የተባለ ነቢይ በገንዘብ ገዝተው እስራኤላውያንን እንዲረግምላቸው ጠየቁት!—ዘኁልቁ 22:1–6፤ ዘዳግም 23:3–6
በዚያን ጊዜ አንድ እንግዳ ነገር ተከሰተ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በለዓም መራገም አልቻለም ነበር። መናገር የቻለው እስራኤላውያንን የሚባርኩ ቃላት ብቻ ነበር፤ እንዲህ አላቸው፦ “የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፣ የሚረግምህም ሁሉ የተረገመ ይሁን።” (ዘኁልቁ 24:9) አሞናውያንን ጨምሮ በነገሩ እጃቸው የነበረበት ሕዝቦች ከዚህ ኃይለኛ ትምህርት ማግኘት ነበረባቸው። አምላክ ሕዝቦቹ ከተነኩ ለእነርሱ ሲል ጣልቃ ከመግባት ወደ ኋላ አይልም!
ያም ሆነ ይህ አሞናውያን እስራኤላውያንን ለማጥቃት አጋጣሚ ከመፈለግ አልታቀቡም። በመሳፍንት ዘመን አሞናውያን ከሞዓብና ከአማሌቅ ጋር በማበር የተስፋይቱን ምድር እስከ ኢያሪኮ ድረስ ወረሩ። ነገር ግን እስራኤላዊው መስፍን ናዖድ ወራሪዎችን አስለቅቆ ስለነበረ ድሉ ዘላቂ አልነበረም። (መሳፍንት 3:12–15, 27–30) እስከ መስፍኑ ዮፍታሔ ዘመን ሰላም ሰፍኖ ነበር። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ብሔር በጣዖት አምልኮ ስለተዘፈቀ ይሖዋ ጥበቃውን ከላያቸው አንስቶ ነበር። አምላክ ለ18 ዓመታት “በአሞን ልጆች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።” (መሳፍንት 10:6–9) እስራኤላውያን የጣዖት አምልኮን አስወግደው በዮፍታሔ መሪነት ሥር ሲሰባሰቡ አሞናውያን እንደገና ክፉኛ ተሸነፉ።—መሳፍንት 10:16 እስከ 11:33
የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል ሲነግሥ እስራኤላውያን በመሳፍንት የሚገዙበት ጊዜ አበቃ። ሳኦል መግዛት እንደ ጀመረ የአሞን ጥላቻ እንደገና አገረሸ። ንጉሥ ናዖስ የእስራኤል ከተማ በሆነችው በኢያቢስ ገለዓድ ላይ ያልታሰበ ጥቃት ሰነዘረ። ሰዎቹ ሰላም እንዲሰጣቸው በለመኑት ጊዜ አሞናዊው ናዖስ “ቀኝ ዓይናችሁን ሁሉ በማውጣት ቃል ኪዳን አደርግላችኋለሁ” በማለት በጣም የሚያስደነግጥ ጥያቄ አቀረበላቸው። ታሪክ ጸሐፊው ፍላቪየስ ጆሴፈስ እንደተናገረው “የግራ ዓይናቸው በጋሻ ስለሚከለል ቀኝ ዓይናቸው መጥፋቱ በጦርነት ውስጥ ምንም የማይጠቅሙ ሊያደርጋቸው ይችል ስለነበር” ይህ ጥያቄ በከፊል የማሸነፊያ ዘዴ ነበር። ቢሆንም የዚህ ጭካኔ የተሞላበት ጥያቄ ዋና ዓላማ እስራኤላውያንን መሳለቂያ ማድረግ ነበር።—1 ሳሙኤል 11:1, 2
አሁንም አሞናውያን ይሖዋ ላደረገላቸው ደግነት ጥላቻ መለሱ። ይሖዋ ይህንን ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እንዳላየ ሆኖ አላለፈውም። “ይህን [የናዖስን] ነገር በሰማው ጊዜ በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ፣ ቁጣውም እጅግ ነደደ።” ሳኦል በአምላክ መንፈስ መሪነት 330,000 ወታደሮችን የያዘ ሠራዊት አሰባሰበና ‘ከእልቂት የተረፉት ለየብቻቸው በመሮጥ እስኪበታተኑ’ ድረስ አሞናውያንን ድል አደረጋቸው።—1 ሳሙኤል 11:6, 11 የ1980 ትርጉም
አሞናውያን በራስ ወዳድነት ስለራሳቸው ጥቅም ብቻ ማሰባቸው፣ ጭካኔያቸውና ስግብግብነታቸው ድምጥማጣቸው እንዲጠፋ አድርጓቸዋል። የይሖዋ ነቢይ የነበረው ሶፎንያስ እንዲህ በማለት እንደተነበየው ሆነዋል፦ “እንደ ገሞራ . . . ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ፤ . . . በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፣ እየታበዩም ተናግረዋልና።”—ሶፎንያስ 2:9, 10
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የዓለም መሪዎች በአሞን ላይ የደረሰውን ነገር ልብ ሊሉት ይገባል። አምላክ የእግሩ መረገጫ በሆነችው ምድር ላይ እንዲኖሩ በመፍቀድ ለመንግሥታት ደግነት አሳይቷቸዋል። ቢሆንም ራስ ወዳድ የሆኑት መንግሥታት ምድርን ከመንከባከብ ይልቅ እያጠፏት ነው፤ እንዲያውም ፕላኔታችን በኑክሌር ትጠፋለች የሚል ስጋት ፈጥረዋል። በምድር ላይ ለሚኖሩ የይሖዋ አምላኪዎች ደግነት ከማሳየት ይልቅ በአምላኪዎቹ ላይ ከባድ ስደት በማድረስ ጥላቻ ያሳያሉ። ይሖዋ ለሚያሳየው ደግነት ምላሹ ጥላቻ ከሆነ ይህንን አቅልሎ እንደማይመለከተው በአሞናውያን ላይ ከደረሰው ነገር መማር ይቻላል። በጥንት ጊዜያት እንዳደረገው ሁሉ አሁንም በወሰነው ጊዜ እርምጃ ይወስዳል።—ከመዝሙር 2:6–12 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአሞናውያን ዋና ከተማ የሆነችው ረባት ትገኝበት የነበረው አማን ውስጥ የሚገኝ ሮማውያን የሠሯቸው ሕንፃዎች ፍርስራሽ
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሞናውያን እዚህ አካባቢ ኖረዋል
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.