ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም
“ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [“ታማኝነት፣” አዓት] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”—ኤፌሶን 4:24
1. ለይሖዋ አምላክ ታማኝ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
የታማኝነትን ፈተና መቋቋም ብዙ ነገሮችን ያጠቃልላል። ለይሖዋ አምላክ ታማኝ መሆን የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በይበልጥ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ነው። ከይሖዋ ማንነት፣ እርሱ ለእኛ ካደረገልን ነገርና ራሳችንን ለእርሱ ከመወሰናችን አንፃር ሲታይ ለእርሱ ታማኝ የመሆን ግዴታ እንዳለብን የተረጋገጠ ነው። ለይሖዋ አምላክ ታማኝ መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው? አንዱና ዋንኛው መንገድ ለይሖዋ የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶች ታማኝ መሆን ነው።
2, 3. በታማኝነትና በጽድቅ መካከል ምን ግንኙነት አለ?
2 የታማኝነትን ፈተና ለመቋቋም “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” የሚሉትን በ1 ጴጥሮስ 1:15, 16 ላይ የሚገኙትን ቃላት መታዘዝ ይኖርብናል። ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን በማንኛውም ጊዜ ለእርሱ እንድንታዘዝና ሐሳባችንን፣ ቃላችንንና ድርጊቶቻንን ከአምላክ ቅዱስ ፈቃድ ጋር እንድናስማማ ይረዳናል። ይህም ንጹህ ሕሊና ይዞ መመላለስ ማለት ሲሆን በ1 ጢሞቴዎስ 1:3-5 ላይ እንዲህ ተብለን ታዝዘናል፦ “የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው።” እርግጥ ነው ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ ሆኖም የምንችለውን ያህል ለመሥራት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፤ አይደለም እንዴ?
3 ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በራስ ወዳድነት እንዳንጥስ ያደርገናል። ታማኝነት ግብዞች ከመሆን እንድንቆጠብ እንደሚረዳን የተረጋገጠ ነው። መዝሙራዊው “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ። በእውነትህም እመላለሳለሁ። ስምህን እንድፈራ ልቤን አንድ አድርግልኝ” በማለት በዘመረበት ወቅት ታማኝነትን በአእምሮው ይዞ ነበር። (መዝሙር 86:11 አዓት) ታማኝነት “ሰብዓዊ ሕግ አስከባሪዎች ሊያስከብሩ ለማይችሏቸው ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች መገዛት” ተብሎ በሚገባ የተገለጸውን ነገር መፈጸምን ይጠይቃል።
4, 5. ታማኝነት የትኛውን መጥፎ ተግባር ከመፈጸም እንድንጠነቀቅ ይረዳናል?
4 በተጨማሪም ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን በስሙና በመንግሥቱ ላይ ነቀፋ የሚያመጣ ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ሁለት ክርስቲያኖች ተካስሰው ዓለማዊ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ውስጥ ገብተዋል። ዳኛው ‘ሁለታችሁም የይሖዋ ምሥክሮች አይደላችሁምን?’ በማለት ጠየቃቸው። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ዳኛው ለምን ፍርድ ቤት እንደመጡ ሊገባው አልቻለም። ይህ ምንኛ አሳፋሪ ነገር ነበር! እነዚህ ወንድሞች ለይሖዋ ታማኝ ቢሆኑ ኖሮ ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጒድለት ነው። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን?” በማለት የሰጠውን ምክር ይታዘዙ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 6:7) በእርግጥም አንድ ክርስቲያን ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ከሆነ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ነቀፌታ ከማምጣት ይልቅ ራሱ ቢጎዳ ይመርጣል።
5 በተጨማሪም ለይሖዋ ታማኝ መሆን ለሰው ፍርሃት አለመንበርከክን ይጨምራል። “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል።” (ምሳሌ 29:25) ይህም በመሆኑ ስደት በሚያጋጥመን ወቅት አቋማችንን ከማላላት ይልቅ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት፣ በማላዊ፣ በኢትዮጵያና በሌሎች ብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የተዉልንን ምሳሌ እንከተላለን።
6. ታማኝነት ከእነማን ጋር ወዳጅነት እንዳንፈጥር ይጠብቀናል?
6 ለይሖዋ ታማኞች ከሆንን የእርሱ ጠላቶች ከሆኑት ሰዎች ጋር ከመወዳጀት እንቆጠባለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (ያዕቆብ 4:4) ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ የሚጠሉህን እኔ የጠላሁ አይደለሁምን? ስለ ጠላቶችህም የተሰቀቅሁ አይደለሁምን? ፍጹም ጥል ጠላኋቸው፣ ጠላቶችም ሆኑኝ” በማለት በተናገረበት ወቅት ያሳየው ታማኝነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። (መዝሙር 139:21, 22) ሆን ብለው ኃጢአት ከሚሠሩ ሰዎች ጋር አንዳችም ኅብረት ስለሌለን ከእነርሱ ጋር ለመወዳጀት አንፈልግም። ለይሖዋ ታማኞች መሆናችን እንደነዚህ ካሉት የይሖዋ ጠላቶች ጋር በግል ወይም በቴሌቪዥን ከመገናኘት እንድንቆጠብ አያደርገንምን?
ከይሖዋ ጎን መቆም
7. ታማኝነት ለይሖዋ ምን እንድናደርግ ይረዳናል? ኤሊሁ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?
7 ታማኝነት ከይሖዋ አምላክ ጎን እንድንቆም ይገፋፋናል። በዚህ ረገድ ኤሊሁ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነበር! ኢዮብ 32:2, 3 እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “የኤሊሁ ቁጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቆጣው። ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቆጣ።” ከኢዮብ 32 እስከ 37 ባሉት ምዕራፎች ላይ ኤሊሁ ከይሖዋ ጎን ቆሞ ተሟግቷል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና ጥቂት ቆየኝ እኔም አስታውቅሃለሁ። . . . ፈጣሪዬንም፦ ጻድቅ ነው እላለሁ። . . . ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም።”—ኢዮብ 36:2-7
8. ከይሖዋ ጎን መቆም የሚኖርብን ለምንድን ነው?
8 ከይሖዋ ጎን መቆም ያስፈለገው ለምንድን ነው? ዛሬ አምላካችን ይሖዋ ከመቼውም ጊዜ በላይ በብዙ መንገዶች ይሰደባል። አምላክ የለም፣ የሥላሴ ክፍል ነው፣ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ሰዎችን ለዘላለም ያሠቃያል፣ ዓለምን ለመለወጥ ደካማ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፣ ለሰው ልጆች ግድ የለውም እየተባለ ከመሆኑም በተጨማሪ እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ወቀሳዎች ይቀርቡበታል። ከእርሱ ጎን መቆምና ይሖዋ እንዳለ፣ ጥበበኛ፣ ፍትሐዊ፣ ሁሉን ቻይና አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ፣ ሁሉን ነገር የሚፈጽምበት የተወሰነ ጊዜ እንዳለው፣ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ክፋትን ጠራርጎ እንደሚያስወግድና መላውን ምድር ገነት እንደሚያደርግ በመግለጽ ለእርሱ ታማኝ መሆናችንን እናስመሠክራለን። (መክብብ 3:1) ይህም ለይሖዋ ስምና መንግሥት ለመመሥከር እያንዳንዱን አጋጣሚ መጠቀምን ይጠይቃል።
ለይሖዋ ድርጅት ታማኝ መሆን
9. አንዳንዶች ታማኝ ሳይሆኑ የቀሩት በየትኞቹ ሁኔታዎች ምክንያት ነው?
9 አሁን ደግሞ ለሚታየው የይሖዋ ድርጅት ታማኝ ስለመሆን እንመለከታለን። ክርስቲያን ጉባኤ መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኝበትን “ታማኝና ልባም ባሪያ”ን ጨምሮ ለድርጅቱ ታማኝ መሆን እንደሚገባን የማያጠራጥር ነው። (ማቴዎስ 24:45-47) በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ አንድ ግልጽ ሊሆንልን ያልቻለ ወይም ለመቀበል የሚያስቸግረን ትምህርት ወጣ እንበል። ምን እናደርጋለን? በዚህ ቅር ተሰኝተን ከድርጅቱ እንወጣለንን? ከበርካታ ዓመታት በፊት መጠበቂያ ግንብ አዲሱ ቃል ኪዳን የሚሠራው በሺው ዓመት ነው የሚል ሐሳብ ይዞ በወጣበት ወቅት አንዳንዶች ከድርጅቱ ወጥተዋል። ሌሎች ደግሞ መጠበቂያ ግንብ በአንድ ወቅት ስለ ገለልተኝነት ጉዳይ የተናገረው ነገር አስቆጥቷቸው ነበር። በእነዚህ ነገሮች የተደናቀፉት ሰዎች ለድርጅቱና ለወንድሞቻቸው ታማኝ ቢሆኑ ኖሮ ይሖዋ እነዚህን ነገሮች ግልጽ እስኪያደርጋቸው ድረስ ይጠብቁ ነበር። ይሖዋ በተገቢው ጊዜ ይህን አድርጓል። ስለዚህ ታማኝነት በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ተጨማሪ እውቀት እስኪገለጽ ድረስ በትዕግሥት መጠባበቅን ይጨምራል።
10. ታማኝነት ስለምን ነገር ለማወቅ ከመጓጓት ይጠብቀናል?
10 ለሚታየው የይሖዋ ድርጅት ታማኝ መሆን ከሃዲዎችን አለመቀበልንም ይጨምራል። ታማኝ ክርስቲያኖች እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት ምን እንደሆነ ለማወቅ አይጓጉም። እርግጥ ይሖዋ አምላክ በምድር ላይ ሥራውን ለመምራት የሚጠቀምባቸው ሰዎች ፍጹማን አይደሉም። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ምን እንድናደርግ ይነግረናል? የአምላክን ድርጅት ተዉ ይለናልን? በፍጹም አይለንም። የወንድማማች መዋደድ ለድርጅቱ ታማኝ መሆናችንን እንድንቀጥል ሊረዳን ይገባል፤ በተጨማሪም ‘እርስ በርሳችን ከልባችን አጥብቀን መዋደዳችንን’ ማቋረጥ የለብንም።—1 ጴጥሮስ 1:22
ለታማኝ ሽማግሌዎች ታማኝ መሆን
11. ታማኝነት ከየትኛው አፍራሽ አስተሳሰብ እንድንርቅ ይረዳናል?
11 በጉባኤ ውስጥ አንድ ለመረዳት የሚያስቸግረን ነገር ከተነገረ ወይም ከተደረገ ታማኝነት የራሳችንን ፍርድ ከመስጠት እንድንቆጠብ ከማድረጉም በላይ እኛ ነገሩን በሌላ መንገድ ተረድተነው ሊሆን ይችላል ብለን እንድናስብ ይረዳናል። በሽማግሌዎችና በሌሎች የእምነት ጓደኞቻችን ጉድለቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ባሏቸው ጥሩ ባሕርያት ላይ ማተኮር በይበልጥ የተሻለ አይደለምን? እንዲህ ዓይነቱ አፍራሽ አስተሳሰብ ታማኝ ካለመሆን ጋር ስለሚዛመድ ከዚህ ለመራቅ እንፈልጋለን! በተጨማሪም ታማኝነት ጳውሎስ “በማንም ላይ ክፉ ነገር እንዳትናገሩ” በማለት የሰጠንን መመሪያ ለመታዘዝ ይረዳናል።—ቲቶ 3:1, 2 የ1980 ትርጉም
12, 13. ሽማግሌዎች ምን ለየት ያሉ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?
12 ሽማግሌዎች ታማኝ በመሆን ረገድ ለየት ያሉ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ከእነዚህ ነገሮች አንዱ ምሥጢር መጠበቅ ነው። አንድ የጉባኤ አባል ለአንድ ሽማግሌ ምሥጢር ሊነግረው ይችላል። ሽማግሌው ለዚህ ግለሰብ ታማኝ በመሆን ምሥጢር የመጠበቅ ሥርዓትን ከመጣስ ይቆጠባል። ምሳሌ 25:9 “የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ” የሚለውን ምክር ይሠራበታል። ይህም ለሚስቱም እንኳ ቢሆን ስለ ጉዳዩ አለመንገርን የሚጠይቅ ነው።
13 ሽማግሌዎች ታማኝነታቸውን የሚፈታተኑ ሌሎች ሁኔታዎችንም መቋቋም ይኖርባቸዋል። ሰዎችን ያስደስታሉ ወይስ መታረም የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዘመዶቻቸው ወይም የቅርብ ጓደኞቻቸው ቢሆኑም እንኳ በድፍረትና በየዋህነት ይረዷቸዋል? ሽማግሌዎች የሆንን ለይሖዋ ድርጅት ታማኝ መሆናችን መንፈሳዊ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመርዳት እንድንጥር ይገፋፋናል። (ገላትያ 6:1, 2) ሽማግሌዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ደግ መሆን ቢኖርባቸውም እንኳ ሐዋርያው ጳውሎስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ እውነቱን ሳይሸሽግ እንደነገረው ሁሉ ታማኝነት እርስ በርሳቸው ግልጽ እንዲሆኑ ይገፋፋቸዋል። (ገላትያ 2:11-14) በሌላ በኩል ደግሞ የበላይ ተመልካቾች ጥበብ የጎደለው ተግባር እንዳይፈጽሙ ወይም አድልዎ እንዳያደርጉ ወይም በአንድ በሌላ መንገድ ሥልጣናቸውን አለአግባብ እንዳይጠቀሙ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። እንደዚህ ቢያደርጉ በሥራቸው ያሉት ለአምላክ ድርጅት ታማኝ መሆን እንዲከብዳቸው ያደርጋል።—ፊልጵስዩስ 4:5
14, 15. የክርስቲያን ጉባኤ አባላትን ታማኝነት ሊፈትኑ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
14 ለጉባኤና ለጉባኤ ሽማግሌዎች ታማኝ መሆንን የሚመለከቱ ሌሎች ነገሮችም አሉ። በጉባኤው ውስጥ አንድ የሆነ ችግር ካለ ይህ ሁኔታ ለይሖዋና እርሱን ለሚወክሉት ሰዎች ታማኝነት ለማሳየት አጋጣሚ ሊፈጥር ይችላል። (ሰኔ 15, 1987 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 15-17 ተመልከት።) ታማኝ መሆን ውገዳ በሚደረግበት ወቅት ለተወሰደው እርምጃ በቂ ምክንያቶች መኖራቸውን ወይም አለመኖራቸውን ለማጣራት ከመሞከር ይልቅ የሽማግሌዎችን ውሳኔ መደገፍን ይጠይቃል።
15 በተጨማሪም ለጉባኤው ታማኝ ከሆንን ሁኔታችንና ችሎታችን የሚፈቅድልንን ያህል አምስቱንም ሳምንታዊ ስብሰባዎች እንደግፋለን። ታማኝነት ዘወትር በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ብቻ ሳይሆን ተዘጋጅተን ወደ ስብሰባ እንድንሄድና አጋጣሚው የፈቀደልንን ያህል የሚያንጹ ሐሳቦችን መስጠት ይጠይቃል።—ዕብራውያን 10:24, 25
ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን
16, 17. የተጋቡ ክርስቲያኖች ታማኝነትን የሚጠይቁ ምን ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?
16 ከዚህ ሌላ ታማኝነት ልናሳየው የሚገባው ማን ነው? ያገባን ከሆንን ከጋብቻ መሐላችን አንፃር ሲታይ ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ መሆን የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም ይኖርብናል። ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ መሆናችን ከራሳችን ባል ወይም ሚስት ይበልጥ ሌሎች ሴቶችን ወይም ወንዶችን ከማስደሰት እንድንቆጠብ ይረዳናል። በተጨማሪም ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ መሆናችን የትዳር ጓደኛችንን ጉደለት ለሌሎች ሰዎች እንዳንገልጽ ያደርገናል። ከወርቃማው ሕግ ጋር በመስማማት ከትዳር ጓደኛችን ጋር ያለንን የግንኙነት መስመር ክፍት ከማድረግ ይልቅ ቅሬታን ለሌሎች ሰዎች መግለጽ ቀላል ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 7:12) በእርግጥም የጋብቻ ሁኔታ በክርስቲያናዊ ታማኝነት ረገድ ፈተና ያመጣል።
17 ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና ለመቋቋም ከባድ የሥነ ምግባር ብልግና ከመፈጸም መራቅ ብቻ ሳይሆን አሳባችንንና ስሜቶቻችንን ጭምር መጠበቅ ይኖርብናል። (መዝሙር 19:14) ለምሳሌ ያህል አታላይ በሆነው ልባችን ውስጥ ከፍተኛ የጾታ ፍላጎት ካደረ አንድን ነገር ከማድነቅ አልፈን ጭራሽ ያንን ነገር በራስ ወዳድነት ወደ መመኘት ደረጃ ልንደርስ እንችላለን። ንጉሥ ሰሎሞን ለትዳር ታማኝ ስለመሆን ለባሎች ምክር ሲሰጥ “ከምንጭህ የሚፈልቀውን ውኃ ጠጣ” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 5:15) ኢየሱስ ደግሞ “ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል” ብሏል። (ማቴዎስ 5:28) የጾታ ስሜት ለመቀስቀስ ተብለው በሚዘጋጁ ሥዕሎችና ጽሑፎች የሚደሰቱ ባሎች ምንዝር በመፈጸም ሚስቶቻቸውን የማታለልና ለእነርሱ ታማኝ ሳይሆኑ የመቅረት አደጋ ላይ ይወድቃሉ። በተመሳሳይ ምክንያት የምንዝር ይዘት ባላቸው ተከታታይ ድራማዎች የተማረከች ሚስት ለባልዋ ታማኝ እንዳትሆን ልትፈተን ትችላለች። ሆኖም ለትዳር ጓደኛችን ከልባችን ታማኝ መሆናችን የጋብቻ አንድነታችንን ከማጠናከሩም በላይ ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት እርስ በርሳችን እንድንረዳዳ ያስችለናል።
ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል የሚረዱ ነገሮች
18. ታማኝ ለመሆን የሚረዳን ለምን ነገር ያለን አድናቆት ነው?
18 በእነዚህ አራት መስኮች ማለትም ለይሖዋ፣ ለድርጅቱ፣ ለጉባኤና ለትዳር ጓደኛችን ታማኝ በመሆን ረገድ የሚያጋጥመንን ፈተና ለመቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው? ለዚህ የሚረዳን አንዱ ነገር ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋማችን የይሖዋን ሉዓላዊነት ከስድብ ነፃ ከማድረግ ጋር የተያያዘ መሆኑን ማወቃችን ነው። አዎን፣ ታማኝ ሆነን በመቀጠል ይሖዋን የአጽናፈ ዓለም የበላይ ገዢ እንደሆነ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳያለን። በዚህ መንገድ ለራሳችን አክብሮት ከማትረፋችንም በተጨማሪ በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖረናል። በዓመት መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ጨምሮ በመጽሐፍ ቅዱስና በመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ላይ ከይሖዋ ጀምሮ የተጠቀሱትን ግሩም የሆኑ የታማኝነት ምሳሌዎች መመርመር ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ሊጠቅመን ይችላል።
19. እምነት ታማኝ በመሆናችን ረገድ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?
19 በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት ማሳደራችንና እርሱን ላለማሳዘን መፍራታችን የታማኝነት ፈተናን እንድንቋቋም ይረዳናል። የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና በክርስቲያናዊ አገልግሎት በመካፈል በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከርና ለእርሱ ያለንን ፍርሃት ለመኮትኮት እንችላለን። ይህም በኤፌሶን 4:23, 24 ላይ “በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና [“ታማኝነት፣” አዓት] እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” በማለት ከተመዘገበው የጳውሎስ ምክር ጋር የሚስማማ ነገር እንድናደርግ ይረዳናል።
20. ከሁሉም በላይ ለይሖዋና ታማኝነት ልናሳያቸው ለሚገባቸው ለሌሎች ሰዎች ታማኝ እንድንሆን የሚረዳን የትኛው ባሕርይ ነው?
20 የይሖዋን ባሕርያት ማድነቃችን ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል። ከሁሉም በላይ ለሰማያዊው አባታችን ያለን ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅርና እርሱ ለእኛ ሲል ላደረገው ነገር አመስጋኝ መሆናችን እንዲሁም እርሱን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም አሳባችንና በፍጹም ኃይላችን መውደዳችን ታማኝ እንድንሆን ያስችለናል። በተጨማሪም ኢየሱስ ተከታዮቹ ተለይተው እንደሚታወቁበት የገለጸውን ፍቅር ማሳየታችን በጉባኤያችን ለሚገኙት ክርስቲያኖች በሙሉና ለቤተሰባችን ታማኝ እንድንሆን ይረዳናል። ነገሩን በሌላ መንገድ ለመግለጽ ታማኝነት ራስ ወዳድ የመሆን ወይም ራስ ወዳድ ያለመሆን ጉዳይ ነው። ታማኝ አለመሆን ራስ ወዳድ መሆን ነው። ታማኝ መሆን ራስ ወዳድ አለመሆን ነው።—ማርቆስ 12:30, 31፤ ዮሐንስ 13:34, 35
21. ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋምን በተመለከተ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች መከለስ የሚቻለው እንዴት ነው?
21 ለመከለስ ያህል፦ ታማኝነት ይሖዋ አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስና እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ያሳዩት ከፍተኛ ደረጃ ያለው ባሕርይ ነው። ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን የጽድቅ ብቃቶቹን በማክበር፣ ከጠላቶቹ ጋር አንዳችም ግንኙነት ባለመፍጠርና መደበኛ በሆነ መንገድም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከር ከእርሱ ጎን በመቆም ታማኝ እንዳንሆን የሚያጋጥመንን ፈተና መቋቋም ይኖርብናል። በተጨማሪም ለሚታየው የይሖዋ ድርጅት ታማኝ የመሆንን ፈተና መቋቋም ያስፈልገናል። ለጉባኤዎቻችንና ለትዳር ጓደኞቻችን ታማኞች መሆን አለብን። የታማኝነትን ፈተና በተሳካ ሁኔታ በመቋቋም የይሖዋን ሉዓላዊነት በማረጋገጡ ተግባር ድርሻ ይኖረናል። በተነሣው አከራካሪ ጉዳይም ከእርሱ ጎን እንሰለፋለን። ይህን በማድረጋችን የእርሱን ሞገስ ከማግኘታችንም በተጨማሪ ወደፊት የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንቀበላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክ ያደሩ ስለመሆን የተናገረው ነገር የታማኝነት ፈተና ስለ መቋቋምም ሊሠራ ይችላል። ታማኝ መሆናችን ለአሁኑና ለሚመጣው ሕይወት ጠቃሚ ነው።—መዝሙር 18:25፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:8
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ለአምላክ ታማኝ የመሆንን ፈተና መቋቋም የምንችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ ለይሖዋ ድርጅት ታማኝ መሆን ምን ይጠይቅብናል?
◻ ሽማግሌዎች ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ የተጋቡ ክርስቲያኖች ታማኝነትን በተመለከተ የትኛውን ፈተና መቋቋም ይኖርባቸዋል?
◻ ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና እንድንቋቋም የሚረዱን የትኞቹ ባሕርያት ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ለጉባኤው አባላት ታማኞች መሆናቸው ምሥጢር ከማውጣት እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆን የጋብቻን አንድነት ያጠናክራል