የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?
በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የጉባኤ ስብሰባዎችን ማድረግ
ሰኔ 26, 2020
በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ መንግሥታት ሰዎች አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁና አንድ ላይ እንዳይሰበሰቡ የሚያዙ ሕጎችን አውጥተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ደንቦች ሳይጥሱ ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ አንድ ላይ መሰብሰባቸውን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ለዚህም ሲባል ጉባኤዎች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ስብሰባ ለማድረግ የሚያስችሉ እንደ ዙም ያሉ አፕሊኬሽኖችን መጠቀም ጀምረዋል።
ቋሚ በሆነና ደህንነትን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ስብሰባ ለማድረግ ሲባል የበላይ አካሉ በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ ለጉባኤዎች የዙም አካውንት ለመግዛት እንዲውል ፈቃድ ሰጥቷል። ይህ ዝግጅት የቪዲዮ ኮንፈረንስ ለማድረግ የሚያስችሉ አካውንቶችን ለመግዛት የሚያስፈልገውን ከ15 እስከ 20 ዶላር ወይም ከዚያ በላይ ገንዘብ መክፈል የማይችሉ ጉባኤዎችን በእጅጉ ጠቅሟል። ከዚህ ቀደም እነዚህ ጉባኤዎች የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ማስተናገድ የሚችሉ ወይም ደህንነታቸው አስተማማኝ ያልሆኑ ነፃ አፕሊኬሽኖችን ለመጠቀም ተገደው ነበር። ድርጅቱ የገዛቸው የዙም አካውንቶች ግን ለአጠቃቀም ቀላል የሆኑ የደህንነት ገጽታዎች ያሏቸው ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ያስችላሉ። እስካሁን ድረስ፣ ከ170 በሚበልጡ አገሮች ያሉ ከ65,000 በላይ የሚሆኑ ጉባኤዎች እነዚህን አካውንቶች እየተጠቀሙ ነው።
በማናዶ፣ ሰሜን ሱላዌሲ፣ ኢንዶኔዥያ ያለው የካይራጊ ጉባኤ ቀደም ሲል ይጠቀምበት የነበረውን ቪዲዮ ኮንፈረንስ ለማድረግ የሚያስችል ነፃ አፕሊኬሽን ትቶ የድርጅቱን የዙም አካውንት መጠቀም ጀመረ። ወንድም ሃዲ ሳንቶሶ እንዲህ ብሏል፦ “የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በደንብ መጠቀም የማይችሉ ወንድሞችና እህቶች እንኳ ስብሰባዎችን በሚገባ መከታተል ችለዋል፤ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት በአንድ ስብሰባ ላይ በተደጋጋሚ እየተቋረጠባቸው እንደገና መግባት የማያስፈልጋቸው መሆኑ ነው።”
በጓያኩዊል፣ ኢኳዶር በሚገኘው የጓያካኔስ ኦኤስቴ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግል ሌስተር ሂሆን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በርካታ ወንድሞችና እህቶች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ስላላቸው አንዳንድ ጉባኤዎች መላው ጉባኤ ስብሰባውን እንዲከታተል የሚያስችለውን የዙም አካውንት ለመግዛት ጨርሶ አቅማቸው አይፈቅድም። አሁን ግን የድርጅቱ የዙም አካውንት ስላለን ቁጥሩ ይሞላብናል ብለን ሳንሰጋ በርካታ ሰዎችን በስብሰባችን ላይ መጋበዝ ችለናል።”
በሉሳካ፣ ዛምቢያ በሚገኘው የንግዌሬሬ ሰሜን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ጆንሰን ምዋንዛ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በርካታ ወንድሞችና እህቶች ‘የድርጅቱ የዙም አካውንት ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር እንደተቀራረብን ብቻ ሳይሆን ይሖዋ እንደሚወደንና እንደሚንከባከበን ጭምር እንዲሰማን አድርጓል’ ሲሉ በተደጋጋሚ ይደመጣሉ።”
እነዚህ የድርጅቱ አካውንቶች የተገዙት ለአደጋ ጊዜ እርዳታ ከተመደበው ገንዘብ ላይ ነው። ይህ ገንዘብ የተገኘው ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት ከተደረገው መዋጮ ነው። ከእነዚህ መዋጮዎች መካከል አብዛኞቹ የሚደረጉት በdonate.jw.org አማካኝነት ነው። በልግስና ለምታደርጉት መዋጮ እናመሰግናለን፤ የምታደርጉት መዋጮ ለዚህ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ሌሎች የእርዳታ ሥራዎችን ለማከናወንም ይውላል።—2 ቆሮንቶስ 8:14