ከአንባቢዎቻችን
በጣም በጣም አመሰግናችኋለሁ። እኔ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም፤ ነገር ግን ይህን ደብዳቤ የጻፍኩላችሁ ስለ መጽሔቶቻችሁ አስተያየት ለመስጠት ነው። ሕሊናዬ ዘወትር ለሚያነሳቸው መሠረታዊ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎች እስረኛ ሆኜ እኖር ነበር። መልሶቹን ከየት ማግኘት እንደምችል ስለማላውቅ ግራ ተጋብቼ ቆይቻለሁ።
ይሁንና ነገሮችን ከሩቅ እንድንጠራጠር ያደርገን የነበረውን ጠባብ አመለካከት በእግዚአብሔር ፈቃድ መስበር ችያለሁ። ብዙውን ጊዜ ገና ምንም ነገር የመመርመር አጋጣሚ ሳናገኝ ‘አትጠጋ’ ‘አታንብብ’ ተብሎ ይነገረን ነበር። ይህን ከጥላቻ የመነጨ አስተያየት በመስበር በሥራዬ አካባቢ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር አነጋገርኩ። ይህ ሰው መጽሔቶቻችሁን ሰጠኝ። እነዚህ መጽሔቶች ደግሞ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት ይተነትናሉ። ለማንበብም ሆነ ለመረዳት የማያስቸግሩ ናቸው። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በማመሳከር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ይሰጣሉ። እነዚህ መጽሔቶች መንፈሳዊ እምነቴን እንዳጠናከሩልኝ ይሰማኛል። ከዚህም በላይ ለሃይማኖታዊ ጥያቄዎቼ መልስ እንዳገኝ እገዛ አድርገውልኛል።
ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በብዥታና በጥርጣሬ መንገድ እንደምጓዝ ፈጽሞ አይሰማኝም። ከዚህ ይልቅ በጽኑ መሠረት ላይ የተመሠረተ እምነት እንዳለኝ ይሰማኛል። ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት እመራለሁ። የሚያጋጠሙኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት መቋቋም እችላለሁ። መጽሔቶቻችሁ እነዚህን ባሕርያት እንዳዳብር በመርዳት ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል። ለዚህም በእግዚአብሔር ስም በጣም በጣም አመሰግናችኋለሁ።
ኤም. ቲ.፣ ኢትዮጵያ
የወጣቶች ጥያቄ . . . ያለብኝን የጤና ችግር መቋቋም የምችለው እንዴት ነው? (የካቲት 2008) ይህ ጽሑፍ የደረሰኝ በሚያስፈልገኝ ሰዓት በመሆኑ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልነግራችሁ አልችልም! ታምሜ ለሦስት ሳምንታት ሆስፒታል ገብቼ ነበር። ይህ መጽሔት የደረሰኝ ገና ከሆስፒታል እንደወጣሁ ነበር። ሁኔታዬ በጽሑፉ ላይ ከተጠቀሱት ወጣቶች ሁኔታ ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላል። ወጣቶቹ ስለሰጡት ሐሳብና ስለቀረቡት ምክሮች አመሰግናችኋለሁ።
ኬ. ፒ.፣ ካናዳ
ይሖዋ አምላክ እንደ እኔ የአካል ጉዳተኛ የሆኑትንም እንኳ እንደሚያጽናና ማወቄ ልቤን ነክቶታል። ሴረብረል ፖልዚ የተባለው በሽታ የያዘኝ ገና ትንሽ ልጅ ሳለሁ ነበር። መራመድ ባልችልም እንኳ ረዳት አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ ነው። በቅርቡ ምድር ገነት ስትሆን የአካል ጉዳት ያለባቸው ሁሉ ‘እንደ ሚዳቋ’ የሚዘሉበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ።—ኢሳይያስ 35:5, 6
ጄ. ጄ.፣ ኮሪያ ሪፑብሊክ
ይህን ጽሑፍ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ። የይሖዋን ፍቅራዊ አሳቢነት ስገነዘብ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። ይሖዋ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳያገኘን በሚሞቅ ብርድ ልብስ ጠቅልሎ የያዘን ያህል ሆኖ ይሰማኛል። በጣም አመሰግናችኋለሁ።
ኤም. ቲ.፣ ጃፓን
ሞት የሰው ልጆች መጨረሻ ነው? (ታኅሣሥ 2007) እናቴን በሞት ያጣሁት ከጥቂት ወራት በፊት ሲሆን በዚህ ተከታታይ ርዕስ ውስጥ የተሰጠው ማብራሪያ በተለይ ደግሞ የትንሣኤ ተስፋን አስመልክቶ የቀረበው ሐሳብ ልቤን በጣም ነክቶታል። በጣም አመሰግናችኋለሁ። ጽሑፉ እውነተኛ ማጽናኛና ማበረታቻ አስገኝቶልኛል።
ኤም. አር.፣ ማዳጋስካር