“ያደግሁት አምላክ የለሽ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው”
በፕራግ፣ ቻርለስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ፍራንቲሼክ ቪስኮቺል ስለ ነርቭ ሥርዓት አሠራር ባደረጉት ምርምር ታዋቂነትን አትርፈዋል። በአንድ ወቅት አምላክ የለሽ የነበሩት እኚህ ሰው አሁን አምላክ እንዳለ አጥብቀው ያምናሉ። ፕሮፌሰር ቪስኮቺል አመለካከታቸውን የለወጡት ለምን እንደሆነ ከንቁ! መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ገልጸዋል።
በሳይንሱ መስክ ከመሰማራትዎ በፊት ስለ ሃይማኖት ምን አመለካከት ነበርዎት?
ያደግሁት አምላክ የለሽ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን አባቴ ብዙ ጊዜ በቀሳውስት ያሾፍ ነበር። በ1963 በባዮሎጂና በኬሚስትሪ ዲግሪ በመያዝ ከኮሌጅ ተመረቅሁ። በትምህርት ላይ በነበርኩባቸው ዓመታት ሁሉ በምድር ላይ ያሉት የተለያዩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተገኙት በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ አምን ነበር።
በሳይንሱ መስክ ስላከናወኗቸው ነገሮች እስቲ ትንሽ ያጫውቱን።
የዶክትሬት ዲግሪዬን ካገኘሁ በኋላ የነርቭ ሴሎችን ጫፍ ስለሚያገናኙት ሲናፕሶች ኬሚካላዊና ኤሌክትሪካዊ ባሕርይ ጥናት አድርጌ ነበር። በተጨማሪም ስለ ነርቭ ሴሎች፣ ስለ ሜምብሬን ፓምፕስ፣ የአንድን ሰው ጡንቻዎችና ነርቮች ጨምሮ ሕብረ ሕዋሳትን ወደ ሌላው ስለ ማዛወርና አንድ መድኃኒት በሰውነት ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤት ለመቀነስ ወይም ለማስቀረት ስለሚረዱ ዘዴዎች ምርምር አድርጌያለሁ። አብዛኞቹ የጥናቴ ውጤቶች ለኅትመት የበቁ ሲሆን አንዳንዶቹም የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንዲሆኑ ተመርጠዋል። ከጊዜ በኋላ፣ የቼኮዝሎቫኪያ ምሑራን ማኅበር ተብሎ የሚጠራው የሳይንቲስቶች ማኅበረሰብ አባል ሆንኩ። በታኅሣሥ 1989 በቼኮዝሎቫኪያ ከተደረገው “ቬልቬት ሬቮሉሽን” በመባል ከሚታወቀው አብዮት በኋላ በቻርለስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሆንሁ፤ እንዲሁም የሙያ አጋሮቼ ከሆኑ አንዳንድ የኖቤል ተሸላሚዎች ጋር ለመገናኘት ወደ ምዕራባውያን አገሮች እንድሄድ ተፈቀደልኝ።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ስለ አምላክ አስበው ያውቁ ነበር?
አዎን፣ አስብ ነበር ማለት ይቻላል። ያስተማሩኝን አንዳንድ ፕሮፌሰሮች ጨምሮ በጣም የተማሩ ብዙ ሰዎች በአምላክ የሚያምኑት ለምን እንደሆነ ሳስብ አንዳንድ ጊዜ እገረም ነበር፤ እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች በኮሚኒስቱ አገዛዝ ምክንያት ይህን እምነታቸውን በግልጽ አይናገሩም። እኔ ግን አምላክ የሰው አእምሮ የፈጠረው ነገር እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። በተጨማሪም በሃይማኖት ስም የሚፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች በጣም ያበሳጩኝ ነበር።
ታዲያ ስለ ዝግመተ ለውጥ የነበርዎትን አመለካከት እንዲለውጡ ያደረግዎት ምንድን ነው?
የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ መጠራጠር የጀመርኩት የነርቭ ሴሎችን ጫፍ ስለሚያገናኙት ሲናፕሶች በማጥናት ላይ ሳለሁ ነበር። ቀላል እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩት ሲናፕሶች ምን ያህል ውስብስብ እንደሆኑ ሳውቅ እጅግ ተገረምሁ። ‘ሲናፕሶች እንዲሁም የእነሱን አወቃቀርና ባሕርይ የሚወስነው ጄኔቲካዊ መረጃ እንዴት በአጋጣሚ ሊገኙ ይችላሉ?’ የሚለው ጉዳይ ያሳስበኝ ነበር። እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው የሚለው ነገር ፈጽሞ ሊዋጥልኝ አልቻለም።
ከዚያም በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ አንድ ታዋቂ ሩሲያዊ የሳይንስ ሊቅና ፕሮፌሰር የሰጡትን ንግግር አዳመጥሁ። እኚህ ሰው፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጂን ላይ በአጋጣሚ በሚከሰት ለውጥ (ራንደም ሚውቴሽን) እና በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት ሊመጡ እንደማይችሉ ተናገሩ። ከዚያም ከአድማጮች መካከል አንድ ሰው፣ ‘ታዲያ ሕይወት ያላቸው ነገሮች እንዴት ተገኙ?’ በማለት ጠየቀ። ፕሮፌሰሩ ከኪሳቸው አንዲት ትንሽ የሩሲያኛ መጽሐፍ ቅዱስ አውጥተው እያሳዩ “መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያለውን የፍጥረት ዘገባ አንብቡ” ብለው መለሱ።
ከንግግሩ በኋላም ፕሮፌሰሩን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተናገሩት ከልባቸው እንደሆነ ጠየቅኋቸው። የሰጡኝ መልስ ፍሬ ሐሳብ እንዲህ የሚል ነበር፦ “ውስብስብ ያልሆነ አንድ ባክቴሪያ በየ20 ደቂቃ ገደማ ሊከፈል የሚችል ሲሆን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ፕሮቲኖች ይኖሩታል፤ እያንዳንዱ ፕሮቲን ደግሞ በሰንሰለት መልክ የተቆላለፉ 20 ዓይነት አሚኖ አሲዶችን የያዘ ሲሆን እነዚህ በሰንሰለት መልክ የተቆላለፉ አሚኖ አሲዶች በጣም ረጅም ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ባክቴሪያ ጠቃሚ በሆነ ሚውቴሽን (ቤኔፊሺያል ሚውቴሽን) አማካኝነት በጊዜ ሂደት ለውጥ ያድርግ ቢባል ግን ከሦስት ወይም ከአራት ቢሊዮን ዓመታት የሚበልጥ በጣም ረጅም ጊዜ ይፈጅበታል፤ የሳይንስ ሊቃውንት ደግሞ በምድር ላይ ሕይወት ኖረ የሚሉት ለሦስት ወይም ለአራት ቢሊዮን ዓመታት ነው።” ፕሮፌሰሩ ከዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዘፍጥረት ዘገባ አሳማኝ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።
የፕሮፌሰሩ አስተያየት በእርስዎ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል?
ፕሮፌሰሩ የሰጡኝ ሐሳብ እኔ ራሴ ከነበሩኝ ጥርጣሬዎች ጋር ተዳምሮ ሃይማኖተኛ ከሆኑ የተለያዩ የሙያ አጋሮቼና ወዳጆቼ ጋር በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንድወያይ አነሳሳኝ፤ ሆኖም የእነሱም አመለካከት ቢሆን አሳማኝ አልሆነልኝም። ከዚያም የፋርማኮሎጂ ባለሙያ ከሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተነጋገርኩ። ይህ ሰው ለሦስት ዓመታት ያህል እኔንና ባለቤቴን ኤማን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አወያየን። በውይይታችን መሃል ትኩረቴን የሳቡት ሁለት ነገሮች ነበሩ። አንደኛ፣ የተለመደው “ክርስትና” መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው የተለየ መሆኑን አወቅሁ። ሁለተኛ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ ማስተማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር የሚስማማ መሆኑን ተገነዘብሁ።
አመለካከትዎን መለወጥዎ ለሚያደርጉት ሳይንሳዊ ምርምር እንቅፋት ሆኖብዎታል?
በጭራሽ። ማንኛውም ጥሩ የሚባል የሳይንስ ሊቅ እምነቱ ምንም ይሁን ምን በምርምሩ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት አይገባም። ይሁን እንጂ እምነቴ እንደለወጠኝ አልክድም። አንደኛ ነገር፣ ከመጠን በላይ በራሴ የምተማመንና የፉክክር መንፈስ የተጠናወተኝ ብሎም ስለ ሳይንሳዊ ችሎታዎቼ ከልክ ያለፈ ኩራት የሚሰማኝ ሰው ከመሆን ይልቅ አሁን ላለኝ ለማንኛውም ችሎታ አምላክን ማመስገንን ተምሬያለሁ። በተጨማሪም እኔም ሆንኩ ጥቂት የማይባሉ ሌሎች የሳይንስ ሊቃውንት፣ በፍጥረት ውስጥ የተንጸባረቁት ዕጹብ ድንቅ ንድፎች በአጋጣሚ እንደመጡ ከመናገር ይልቅ ‘አምላክ እንዲህ ዓይነት ንድፍ ያወጣው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቃለን።
[ከገጽ 9 የተቀነጨበ ሐሳብ ]
እኔም ሆንኩ ጥቂት የማይባሉ ሌሎች የሳይንስ ሊቃውንት፣ ‘አምላክ እንዲህ ዓይነት ንድፍ ያወጣው እ