በአምላክ መኖር የማያምን ሰው ቢያጋጥማችሁ ምን ትሉታላችሁ?
1 ከፖላንድ የመጡ አንዲት ፕሮፌሰር አፍሪካ ውስጥ ለምታገለግል ሚስዮናዊት “በአምላክ መኖር አላምንም” ይሏታል። የሆነ ሆኖ እህት ከሴትዮዋ ጋር ውይይት ማድረግ ስለቻለች ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ሰጠቻቸው። ሚስዮናዊቷ በሚቀጥለው ሳምንት ተመልሳ ስትሄድ ፕሮፌሰሯ “ካሁን በኋላ በአምላክ መኖር አላምንም የሚለውን ሐሳቤን አንስቻለሁ!” አሏት። ፍጥረት የተባለውን መጽሐፍ አንብበው ጨርሰው ነበር። በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠየቁ። በአምላክ እንደማያምኑ ለሚናገሩ ሰዎች ምሥክርነት በመስጠት ረገድ እንዲሳካልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በመጀመሪያ ሰዎች እንዲህ ብለው እንዲናገሩ የሚያደርጓቸውን የተለያዩ ምክንያቶች ተመልከት።
2 ሰዎች እምነት እንዲያጡ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች፦ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ሁሉ ከልጅነታቸው አንስቶ እምነት የለሽ አልነበሩም። አብዛኞቹ አንድ ዓይነት ሃይማኖት ይከተሉ የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት በአምላክ ያምኑ ነበር። ሆኖም በሕይወታቸው የደረሰባቸው ከባድ የጤና እክል ወይም የቤተሰብ ችግር አሊያም አንዳንድ የፍትሕ መጓደል እምነታቸውን አዳክሞባቸዋል። ሌሎች ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቀሰሟቸው ትምህርቶች ስለ አምላክ በነበራቸው አመለካከት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል። በአምላክ መኖር የማያምኑ የነበሩ ኋላ ግን በይሖዋ አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት አሳድረው የእርሱ ምሥክሮች የሆኑ ሰዎችን በሚመለከት ቀጥሎ የቀረቡ ምሳሌዎችን ተመልከት።
3 አንዲት በፓሪስ የምትኖር ሴት ስትወለድ ጀምሮ አጥንት የሚያመነምን በሽታ ይዟት ነበር። ምንም እንኳ ካቶሊክ ሆና የተጠመቀች ቢሆንም እሷ ግን በአምላክ መኖር እንደማታምን ትናገር ነበር። አምላክ እንዲህ ዓይነት እክል ይዛ እንድትወለድ ያደረገው ለምን እንደሆነ ደናግሎቹን ስትጠይቃቸው የሰጧት መልስ ቢኖር “ስለሚወድሽ ነው” የሚል ነበር። ይህ ትርጉም የለሽ ሐሳብ ሊዋጥላት አልቻለም። በተጨማሪም በተደረገለት ምርመራ የማይድን የጡንቻ በሽታ እንደያዘው ተረጋግጦ በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀሰውን የአንድ ፊንላንዳዊ ወጣት ሁኔታ ተመልከት። እናቱ በሽተኞችን አድናለሁ ወደሚል አንድ የጰንጤቆስጤ እምነት ተከታይ ወሰደችው። ሆኖም ተአምራዊ ፈውስ ሳያገኝ ቀረ። ከዚህ የተነሳ ይህ ወጣት በአምላክ ላይ የነበረውን እምነት በማጣቱ አምላክ የለም የሚል ሰው ሆነ።
4 በሆንዱራስ የሚኖር አንድ ሰው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሆኖ ቢያድግም ሶሻሊስታዊ ፍልስፍናንና ስለ አምላክ አለመኖር የሚሰጥን ትምህርት ተከታተለ። የሰው ዘር የአዝጋሚ ለውጥ ውጤት ነው በሚለው የዩኒቨርሲቲው ትምህርት እምነት በማሳደሩ በአምላክ ማመኑን አቆመ። በተመሳሳይ አንዲት በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሴት የሜቶዲስት እምነት ተከታይ ሆና ነበር ያደገችው። ኮሌጅ ውስጥ የሥነ ልቦና ትምህርት ተከታተለች። ትምህርቱ በእምነቷ ላይ ምን ውጤት አስከተለ? እንዲህ ትላለች:- “በጥቂት ወራት ውስጥ በሃይማኖት ላይ የነበረኝን እምነት ሙልጭ አድርገው አጠቡት።”
5 ቅን የሆኑ ሰዎችን ልብ መንካት፦ በአምላክ አናምንም የሚሉ ብዙ ሰዎች የጤና ችግር፣ የቤተሰብ ብጥብጥ፣ የፍትሕ መጓደልና የመሳሰሉት ችግሮች መፍትሄ ያላቸው መሆኑን ማወቅ ሊያስደስታቸው ይችላል። የሚከተሉትን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ የማግኘት ልባዊ ፍላጎት አላቸው:- ‘ክፋት ለምን ኖረ?’ ‘ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገር የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ እና ‘የመኖር ትርጉም ምንድን ነው?’
6 በስዊትዘርላንድ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ከልጅነታቸው አንስቶ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሆነው ነበር ያደጉት። ለመጀመሪያ ጊዜ እውነትን ሲሰሙ የሰጡት መልስ አሉታዊ ነበር። ሆኖም ከባድ የቤተሰብ ችግር የነበራቸው ሲሆን ለመፋታትም አስበው ነበር። ምሥክሯ እንደገና ሄዳ ባነጋገረቻቸው ጊዜ ያሉባቸውን ችግሮች እንዴት ማሸነፍ እንደሚችሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳየቻቸው። ባልና ሚስቱ ቅዱሳን ጽሑፎች በያዙት ተግባራዊ ምክር ከመደነቃቸው የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማሙ። ትዳራቸው ተጠናከረ፣ መንፈሳዊ እድገት አደረጉ ከዚያም ተጠመቁ።
7 በአምላክ መኖር የማያምን አንድ ሰው ቢያጋጥምህ ምን ማለት ትችላለህ? አንድ ሰው በአምላክ መኖር እንደማያምን ሲነግርህ እንዲህ ያለበትን ምክንያት ለማወቅ ጥረት አድርግ። እንዲህ ሊል የቻለው በቀሰመው የትምህርት ዓይነት፣ በሕይወቱ በደረሰበት ችግር ወይም ባየው ሃይማኖታዊ ግብዝነትና በሰማቸው የሐሰት ትምህርቶች ምክንያት ነው? “ከድሮም ጀምሮ አመለካከትህ ይኸው ነበር?” ወይም “እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ ያደረገህ ነገር ምንድን ነው?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ሰውዬው የሚሰጠው መልስ ምን ብለህ እንደምትቀጥል ለመወሰን ይረዳሃል። ከበድ ያለ የመከራከሪያ ነጥብ ማቅረብ ካስፈለገ ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ በቂ ሊሆን ይችላል።
8 በአምላክ መኖር ከማያምን ሰው ጋር ውይይቱን ለመቀጠል እንዲህ ብለህ መጠየቅ ትችላለህ:-
◼ “‘አምላክ ካለ በዓለማችን ላይ ይህን ያህል መከራና ግፍ የበዛው ለምንድን ነው?’ ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ፍቀድለት።] መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚል ላሳይዎት?” ኤርምያስ 10:23ን አንብብ። ጥቅሱን ካነበብክ በኋላ ስለ ጥቅሱ ምን ሐሳብ እንዳለው ጠይቀው። ከዚያም ጦርነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆን? (እንግሊዝኛ) ከተባለው ብሮሹር ላይ ገጽ 16 እና 17ን አሳየው። ወይም በዚያ ፋንታ ፈጣሪ በተባለው መጽሐፍ 10ኛ ምዕራፍ መጠቀም ትችላለህ። ጽሑፉን ወስዶ እንዲያነብ ጋብዘው።—ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ማመራመር መጽሐፍ ገጽ 150-1ን ተመልከት።
9 ግልጹን ለመናገር በአምላክ መኖር የማያምኑ ሁሉም ሰዎች እውነትን ይቀበላሉ ብለን መጠበቅ አንችልም። ሆኖም አንድ ለየት ያለ አመለካከት ለመመርመር ፈቃደኛ የሚሆኑ ብዙዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች እውነትን ማስተዋል ይችሉ ዘንድ ምክንያታዊ የሆኑ ነጥቦችን አቅርብ፣ በማሳመን ዘዴ ተጠቀም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክ ቃል ባለው ኃይል ተጠቀም።—ሥራ 28:23, 24፤ ዕብ. 4:12