የኑሮ ውድነትን መቋቋም
ገንዘብህን በጥበብ ተጠቀም
የዋጋ ንረት ለሁላችንም ተፈታታኝ ነው። ሆኖም ሁኔታው ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥርህ ውጭ እንደሆነ ሊሰማህ አይገባም። ሁኔታህን ለማሻሻል ማድረግ የምትችላቸው ነገሮች አሉ።
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ገንዘብህን በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት ካላደረግህ ያለህበት ሁኔታ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል፤ ይህም ጭንቀትና ስጋት ይጨምርብሃል። ገቢህ የተወሰነ ቢሆንም እንኳ ገንዘብህን አብቃቅተህ ለመኖር ማድረግ የምትችላቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
እንደ አቅምህ ኑር። ይህን ማድረግህ የገንዘብ ሁኔታህ በመጠኑም ቢሆን በቁጥጥርህ ሥር እንደሆነ እንዲሰማህ ያደርጋል፤ ያልተጠበቁ ወጪዎች ቢያጋጥሙህም ያን ያህል አትሰጋም።
እንደ አቅምህ ለመኖር እንዲያግዝህ በጀት አውጣ፤ በጀቱ ላይ ገቢና ወጪዎችህን አስፍር። በጀትህን ስትገመግም የግድ የሚያስፈልጉህን ነገሮች በጥንቃቄ ለይ። ከዚያም ያወጣኸውን በጀት በጥብቅ ለመከተል ጥረት አድርግ። ገቢህ ወይም የሸቀጦች ዋጋ ሲቀየር በጀትህ ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ። ያገባህ ከሆንክ ማንኛውንም ውሳኔ ስታደርግ ከባለቤትህ ጋር ተማከር።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በዱቤ ከመግዛት ይልቅ ከተቻለ በጥሬ ገንዘብ ክፈል። አንዳንዶች እንዲህ ማድረጋቸው በጀታቸውን መከተል ቀላል እንዲሆንላቸው አድርጓል፤ ብሎም ዕዳ ውስጥ ከመግባት ጠብቋቸዋል። በተጨማሪም የባንክ ሒሳብ መግለጫህን ለመገምገም ጊዜ መድብ። ምን ያህል ገንዘብ እንዳለህ ማወቅህ ጭንቀትህን ሊቀንስልህ ይችላል።
እንደ አቅምህ መኖር ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ተግባራዊ ሊሆን የሚችልና በደንብ የታሰበበት በጀት ማውጣትህ ትልቅ እገዛ ያደርግልሃል። ደግሞም ሁኔታው በመጠኑም ቢሆን በቁጥጥርህ ሥር እንደሆነ እንዲሰማህ ያደርጋል።
የገቢ ምንጭህን ላለማጣት የምትችለውን አድርግ። ሥራህን ላለማጣት የሚከተሉትን ማድረግ ትችላለህ፦ ሰዓት አክባሪ ሁን። ለሥራህ አዎንታዊ አመለካከት ይኑርህ። ተነሳሽነት ይኑርህ እንዲሁም ጠንክረህ ሥራ። ሰው አክባሪ ሁን። መመሪያዎችን ተከትለህ ለመሥራትና ክህሎትህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ።
ገንዘብህን አታባክን። ‘ውድ ነገሮች ላይ ገንዘብ የማጥፋት እንዲሁም የአባካኝነት ልማድ አለኝ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ለፍተው ያገኙትን ገንዘብ ዕፅ በመውሰድ፣ በቁማር፣ በማጨስ ወይም ከልክ በላይ በመጠጣት ያጠፉታል። እነዚህ ልማዶች ከጤንነታቸውና ከሥራቸው አንጻርም ዋጋ ሊያስከፍሏቸው ይችላሉ።
ለክፉ ጊዜ የሚሆን ገንዘብ አስቀምጥ። የምትችል ከሆነ ላልተጠበቁ ወይም ለድንገተኛ ወጪዎች በትንሽ በትንሹ ገንዘብ አስቀምጥ። አንተ ወይም አንድ የቤተሰብህ አባል በድንገት ብትታመሙ፣ ሥራህን ብታጣ ወይም ሌላ ያልተጠበቀ ሁኔታ ቢያጋጥምህ እንዲህ ያለው ተቀማጭ በመጠኑም ቢሆን ዋስትና ይሆንሃል።