የወደፊት ሕይወትህ ስኬታማ እንዲሆን ማድረግ—እንዴት?
በሕይወትህ እውነተኛ ስኬት ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ አሁን የምታደርጋቸው ውሳኔዎች በወደፊት ሕይወትህ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ አርቀህ በማሰብ ነው።
ለወደፊት ሕይወትህ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝልህ ውሳኔ ማድረግ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አብዛኞቹ ሰዎች ‘ያሰብኩትን ነገር ወዲያው ማግኘት አለብኝ’ የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ጠንካራ ቤተሰብ ለመመሥረት እንደሚያስችል ታውቅ ይሆናል። (ኤፌሶን 5:22 እስከ 6:4) ይህን ለማግኘት ግን በሥራህ ወይም በመዝናኛ ከልክ በላይ ላለመጠመድ ራስህን በመግዛት ከቤተሰብህ ጋር አዘውትረህ ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልግሃል። በሕይወታችን ውስጥ በተለያዩ መስኮች እንደምናደርገው ሁሉ በዚህ ረገድም ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝልህን ነገር መምረጥ ይኖርብሃል። ታዲያ ትክክለኛውን አካሄድ ለመምረጥ የሚያስችልህን የመንፈስ ጥንካሬ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን አራት ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።
1 ውሳኔዎችህ የሚያስከትሉትን ውጤት አስቀድመህ አስብ
ውሳኔ ማድረግ በሚኖርብህ ጊዜ እውነታውን ከግምት በማስገባት ውሳኔህ የሚያስከትለውን ውጤት አመዛዝን። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ውሳኔህ የሚያስከትለውን ውጤት በሐቀኝነት ከመረመርክ ጉዳት ሊያስከትልብህ ከሚችል አካሄድ ለመራቅ መወሰንህ አይቀርም። በሌላ በኩል ደግሞ ጥበብ የታከለበት ውሳኔ ማድረግ ለወደፊት ሕይወትህ ምን ጥቅሞች እንደሚያስገኝልህ ማሰብህ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ እንድትቆርጥ ያነሳሳሃል።
ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ያደረግሁት ውሳኔ ከአንድ ዓመት፣ አልፎ ተርፎም ከ10 ወይም ከ20 ዓመት በኋላ ምን ውጤት ይኖረዋል? በጤንነቴም ሆነ በስሜቴ ላይ ምን ተጽዕኖ አለው? ያደረግሁት ምርጫ ቤተሰቤንም ሆነ የምወዳቸውን ሰዎች የሚነካው እንዴት ነው?’ ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘የማደርገው ውሳኔ አምላክን ያስደስተዋል? ከእሱ ጋር ያለኝን ወዳጅነት የሚነካውስ እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንደመሆኑ መጠን አምላክን የሚያስደስተው ምን እንደሆነ እንድታውቅ የሚረዳህ ከመሆኑም ባሻገር ልብ ያላልካቸውን ወጥመዶች እንድታስተውል ያስጠነቅቅሃል።—ምሳሌ 14:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
2 ያሉህን አማራጮች ራስህ መርምር
ብዙዎች የራሳቸውን ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ የሌሎችን አካሄድ ይከተላሉ። ይሁንና በሕይወታችን ውስጥ የምንከተለው አንድ ዓይነት አካሄድ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ስለሆነ ብቻ ስኬት ያስገኛል ማለት አይደለም። ያሉህን አማራጮች ራስህ መርምር። ናታሊን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።a እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ ትዳር እንዲኖረኝ እፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ የምከተለው አኗኗር ይህን ምኞቴን ለማሳካት እንደማያስችለኝ ግልጽ ነበር። ኮሌጅ እያለሁ ጓደኞቼ በሙሉ በትምህርታቸው ጎበዝ ነበሩ። ያም ሆኖ እነዚህ ወጣቶች በግል ሕይወታቸው በተደጋጋሚ መጥፎ ውሳኔዎች ያደርጉ ነበር። የፍቅር ጓደኞቻቸውን በየጊዜው ይለዋውጣሉ። እኔም እንደ እነሱ ብዙ የወንድ ጓደኞች ነበሩኝ። እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ መከተሌ ስሜቴን በጣም ጎድቶታል።”
ከጊዜ በኋላ ናታሊ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። “በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ደስተኛ የሆኑ ወጣቶችና ጠንካራ ትዳር ያላቸው ሰዎች አገኘሁ። ቀላል ባይሆንልኝም ቀስ በቀስ በሥነ ምግባሬና በአኗኗሬ ረገድ ለውጥ አደረግሁ” ብላለች። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘላት? ናታሊ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ሁልጊዜ የምመኘው በጥልቅ የማከብረውን ሰው ለማግባት ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ እንደ እኔ ዓይነት እምነት ያለው ሰው አገባሁ። አምላክ በሕልሜም በእውኔም አስቤው የማላውቀው ዓይነት ትዳር እንደሰጠኝ ይሰማኛል።”
3 አርቀህ አስብ
ስለ ዛሬ ብቻ የማሰብን አዝማሚያ ለማስወገድ ወደፊት ምን እንደምትፈልግና ይህንን ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማሰብም ያስፈልግሃል። (ምሳሌ 21:5) አብዛኛው ሰው የሚኖረው ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ቢሆንም አንተ ግን ከዚያም አልፈህ አስብ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው ተስፋ መሠረት የዘላለም ሕይወት ስታገኝ ይታይህ።
አምላክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበት ዝግጅት እንዳደረገ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴዎስ 20:28፤ ሮም 6:23) አምላክ፣ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ በቅርቡ እንደሚፈጸም ቃል ገብቷል። አምላክን የሚወዱ ሁሉ ውብ በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። (መዝሙር 37:11፤ ራእይ 21:3-5) አንተም አርቀህ የምታስብ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ታገኛለህ።
4 ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት አድርግ
አምላክ ቃል የገባው ይህ ተስፋ ሲፈጸም ለማየት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? በመጀመሪያ ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም ያስፈልግሃል። (ዮሐንስ 17:3) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘትህ አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች እንደሚፈጸሙ እምነት እንድታዳብር ይረዳሃል። እንዲህ ዓይነቱ እምነት ደግሞ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ለውጥ ማድረግ እንድትችል ብርታት ይሰጥሃል።
የማይክልን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ይላል፦ “ከልክ በላይ መጠጣትና ዕፅ መውሰድ የጀመርኩት በ12 ዓመቴ ነው። የወንበዴዎች ቡድን አባል የነበርኩ ሲሆን 30 ዓመት ሳይሞላኝ እንደምሞት ይሰማኝ ነበር። ውስጤ በቁጣ ስለተሞላና በተስፋ መቁረጥ ስለተዋጥኩ ራሴን ለማጥፋት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጌያለሁ። በሕይወት ውስጥ ከዚህ የተሻለ ነገር እንዳለ ተስፋ ባደርግም ላገኘው ግን አልቻልኩም።” ማይክል በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ እሱ ከነበረበት የወንበዴዎች ቡድን አባላት አንዱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ማይክልም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ።
ማይክል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማረው ነገር ስለ ወደፊት ሕይወቱ የነበረውን አመለካከት እንዲለውጥ አደረገው። እንዲህ ብሏል፦ “ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆንና ሰዎች ከጭንቀት ነፃ ሆነው በሰላም እንደሚኖሩ ተማርኩ። እኔም እንዲህ ዓይነት የወደፊት ሕይወት እንዲኖረኝ ፈለግሁ። ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት የመመሥረት ግብ አወጣሁ። ያም ቢሆን እንቅፋቶች አላጋጠሙኝም ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመርኩ በኋላም የሰከርኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንዲሁም ከአንዲት ልጅ ጋር የፆታ ብልግና ፈጽሜያለሁ።”
ታዲያ ማይክል እንቅፋቶችን ተቋቁሞ ሕይወቱን በመለወጥ ረገድ ሊሳካለት የቻለው እንዴት ነው? እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምረኝ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንዳነብና አምላክን ለማስደሰት ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር እንድሆን አበረታታኝ። ከወንበዴዎች ቡድን አባላት ጋር ያለኝ ወዳጅነት ተጽዕኖ እያሳደረብኝ እንደሆነ ተገነዘብኩ። እነዚህ ሰዎች ለእኔ እንደ ቤተሰቤ ቢሆኑም ከእነሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ አቋረጥኩ።”
ማይክል በአምላክ መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር ያወጣው ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉት የአጭር ጊዜ ግቦች አወጣ፤ እንዲሁም ቅድሚያ በሚሰጣቸው ነገሮች ላይ ማስተካከያ አደረገ። አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። የረጅም ጊዜ ግቦችህንና እዚያ ለመድረስ አሁን ልትወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎችን በጽሑፍ አስፍር። ግቦችህ ላይ እንድትደርስ ሊረዱህ ለሚፈልጉ ሰዎች ያወጣሃቸውን ግቦች ንገራቸው፤ እንዲሁም ምን ያህል ለውጥ እንዳደረግህ እንዲከታተሉህ ጠይቃቸው።
ስለ አምላክ ለመማርም ሆነ መመሪያዎቹን በሕይወትህ ተግባራዊ ለማድረግ ዛሬ ነገ አትበል። ለአምላክ እና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ለማዳበር አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ። የአምላክ ቃል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ስለሚያደርግ ሰው ሲናገር “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይላል።—መዝሙር 1:1-3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።