የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w23 የካቲት ገጽ 2-7
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስላጻፈው አካል ምን ይነግረናል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ስላጻፈው አካል ምን ይነግረናል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ ያንጸባርቃል
  • መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፍትሕ ያንጸባርቃል
  • መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፍቅር ያንጸባርቃል
  • “መልካም ስጦታ” ለሆነው የአምላክ ቃል አድናቆት ይኑራችሁ
  • መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ ነውን?
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • ምሥራቹ በእርግጥ ከአምላክ የመጣ ነው?
    ከአምላክ የተላከ ምሥራች!
  • ‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተንጸባረቀ ጥበብ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
w23 የካቲት ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 6

መጽሐፍ ቅዱስ ስላጻፈው አካል ምን ይነግረናል?

“የምነግርህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው።”—ኤር. 30:2

መዝሙር 96 የአምላክ መጽሐፍ ውድ ሀብት ነው

ማስተዋወቂያa

1. ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠን አመስጋኝ የሆንከው ለምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን ሰጥቶናል። ስለ ወደፊቱ ጊዜም ግሩም ተስፋ ሰጥቶናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ባሕርያቱን ገልጦልናል። እሱ ባሉት ግሩም ባሕርያት ላይ ስናሰላስል ልባችን በጥልቅ ይነካል፤ በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረት ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንነሳሳለን።—መዝ. 25:14

2. ይሖዋ ራሱን ለሰዎች ለመግለጥ የትኞቹን መንገዶች ተጠቅሟል?

2 ይሖዋ ሰዎች እንዲያውቁት ይፈልጋል። በጥንት ዘመን ሕልሞችን፣ ራእዮችን አልፎ ተርፎም መላእክትን በመጠቀም ራሱን ለሰዎች ገልጧል። (ዘኁ. 12:6፤ ሥራ 10:3, 4) ሆኖም እነዚህ ሕልሞች፣ ራእዮች ወይም በመላእክት በኩል የመጡ መልእክቶች በጽሑፍ ካልሰፈሩ እንዴት ልናጠናቸው እንችላለን? በእርግጥም ይሖዋ፣ እሱ እንድናውቅ የሚፈልገውን መልእክት ሰዎች ‘በመጽሐፍ እንዲጽፉ’ ማድረጉ ተገቢ ነው። (ኤር. 30:2) “የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም” ስለሆነ እሱ ሐሳቡን ለእኛ ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ዘዴ ከሁሉ የተሻለና ጠቃሚ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝ. 18:30

3. ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 40:8)

3 ኢሳይያስ 40:8⁠ን አንብብ። የአምላክ ቃል ታማኝ ለሆኑ ወንዶችና ሴቶች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ጥበብ ያዘለ መመሪያ ሲሰጥ ቆይቷል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። የተጻፉባቸው ነገሮችም ሊበላሹ የሚችሉ ስለሆኑ ከበኩረ ጽሑፉ መካከል እስከ ዘመናችን የዘለቀ አንድም ቅጂ የለም። ሆኖም ይሖዋ ቅዱስ ጽሑፉ በእጅ እንዲገለበጥ አድርጓል። ገልባጮቹ ፍጹማን ባይሆኑም ሥራቸውን ያከናወኑት በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ምሁር የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “መልእክቱ ይህን ያህል ተጠብቆ የቆየ አንድም ጥንታዊ መጽሐፍ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም።” ስለዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ከተጻፉ ረጅም ጊዜ ቢያልፍም፣ የተጻፉበት ነገር ሊበላሽ የሚችል ቢሆንም እንዲሁም ገልባጮቹ ፍጹማን ባይሆኑም በዛሬው ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ የምናነብባቸው ቃላት ያጻፈውን አካል ማለትም የይሖዋን ሐሳብ በትክክል እንደሚያስተላልፉ መተማመን እንችላለን።

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 ይሖዋ ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ ነው። (ያዕ. 1:17) ይሖዋ ከሰጠን ግሩም ስጦታዎች መካከል አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንድ ስጦታ ሰጪው ስለ እኛም ሆነ ስለሚያስፈልገን ነገር ምን ያህል እንደሚያውቅ ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስን ከሰጠን አካል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህን ስጦታ ስንመረምር ስለ ይሖዋ ብዙ እንማራለን። እኛንም ሆነ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ምን ያህል እንደሚያውቅ እንረዳለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚከተሉት ሦስት የይሖዋ ባሕርያት ምን እንደሚያስገነዝበን እንመረምራለን፦ ስለ ጥበቡ፣ ስለ ፍትሑና ስለ ፍቅሩ። በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ጥበብ የሚያንጸባርቀው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ ያንጸባርቃል

5. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቅበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

5 ይሖዋ እሱ የሚሰጠን ጥበብ ያዘለ ምክር እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ስጦታ አድርጎ የሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በእሱ ጥበብ የተሞላ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል። ሙሴ የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በጻፈበት ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ለሆኑት ለእስራኤላውያን “ይህ ቃል ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃል አይደለም” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘዳ. 32:47) ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን መመሪያ የሚታዘዙ ሰዎች ስኬታማና ደስተኛ ሕይወት መምራት ይችላሉ። (መዝ. 1:2, 3) የአምላክ ቃል ከተጻፈ ረጅም ዘመናት ያለፉ ቢሆንም የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይሉን አላጣም። ለምሳሌ jw.org ላይ “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የተባለ ቋሚ ዓምድ አለ፤ ይህ ዓምድ የአምላክ ቃል በዛሬው ጊዜም ‘አማኞች በሆኑት ላይ በእርግጥ እየሠራ’ እንደሆነ የሚያሳዩ ከ50 የሚበልጡ እውነተኛ ታሪኮችን ይዟል።—1 ተሰ. 2:13

6. እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ሌላ መጽሐፍ የለም እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

6 እንደ አምላክ ቃል ያለ ሌላ መጽሐፍ የለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህን መጽሐፍ ያጻፈው ይሖዋ አምላክ ሁሉን ቻይ፣ ዘላለማዊና በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ነው። ብዙ መጻሕፍት ደራሲዎቻቸው ከሞቱ በኋላም እንኳ መነበባቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ፤ ሆኖም በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው ምክር በአብዛኛው ጊዜ የሚሽረው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ግን ጊዜ የሚሽራቸው አይደሉም፤ በየትኛውም ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች ጠቃሚ መሆናቸውም ተረጋግጧል። ይህን ቅዱስ መጽሐፍ ስናነብና ባነበብነው ላይ ስናሰላስል መጽሐፉን ያጻፈው አካል ኃያል የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም ምክሮቹን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድናስተውል ይረዳናል። (መዝ. 119:27፤ ሚል. 3:16፤ ዕብ. 4:12) መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው ምንጊዜም ሕያው የሆነው አምላክ ሊረዳን ዝግጁ ነው። ይህን ማወቃችን አዘውትረን እንድናነብ አያነሳሳንም?

ምስሎች፦ 1. በጥቅልል፣ በኮዴክስ፣ በጥራዝ፣ በኤሌክትሮኒክ ቅጂና በተለያየ መልኩ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ። 2. የተለያየ ዘርና አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች የታተመውንና በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ቤታቸው፣ ሥራ ቦታና ሕዝብ መጓጓዣ ላይ ሆነው ሲያነቡ።

መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን የይሖዋን ሕዝቦች አንድ ያደረገው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 7-8⁠ን ተመልከት)

7. መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ ሕዝቦችን አንድ ያደረጋቸው እንዴት ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቅበት ሌላው አስደናቂ መንገድ የአምላክን ሕዝቦች አንድ ማድረግ መቻሉ ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ የሰፈሩት በጣም ሰፊ የሆነ ቦታ ላይ ነበር። ከዚያም አንዳንዶቹ ዓሣ አጥማጆች፣ ሌሎቹ ደግሞ ከብት አርቢዎች ሆኑ፤ በግብርና ሥራ የተሰማሩም ነበሩ። ይህ ሁኔታ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እስራኤላውያን በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ስለሚኖሩ እስራኤላውያን ሁኔታ ማሰባቸውን እንዲያቆሙ ሊያደርግ የሚችል ነበር። ይሖዋ ግን እስራኤላውያን በተለያዩ አጋጣሚዎች አንድ ላይ ተሰብስበው በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ሲነበብና ሲብራራ የሚያዳምጡበት ዝግጅት አደረገ። (ዘዳ. 31:10-13፤ ነህ. 8:2, 8, 18) አንድ ታማኝ እስራኤላዊ ኢየሩሳሌም ደርሶ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ፣ ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የእምነት ባልንጀሮቹን ሲያይ ምን ሊሰማው እንደሚችል አስቡ! በዚህ መንገድ ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ ሆነው እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። በኋላም የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ጉባኤው የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የተለያየ አስተዳደግና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ወንዶችና ሴቶችን ያቀፈ ሆነ። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች ለቅዱሳን መጻሕፍት ፍቅር ስለነበራቸው እውነተኛውን አንድ አምላክ በአንድነት ማምለክ ችለዋል። በኋላ አማኞች የሆኑ ሰዎች የአምላክን ቃል ለመረዳት የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እርዳታ መቀበልና ከእነሱ ጋር አብረው መሰብሰብ ያስፈልጋቸው ነበር።—ሥራ 2:42፤ 8:30, 31

8. መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችን አንድ ያደረገው እንዴት ነው?

8 ጥበበኛ የሆነው አምላካችን በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሕዝቡን ማስተማሩንና አንድ ማድረጉን ቀጥሏል። የምንመገበው መንፈሳዊ ምግብ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አዘውትረን በምናደርጋቸው የጉባኤ፣ የወረዳና የክልል ስብሰባዎች ላይ ቅዱሳን መጻሕፍት ሲነበቡና ሲብራሩ እንሰማለን። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሕዝቦቹ “እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት” ያለውን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።—ሶፎ. 3:9

9. የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመረዳት የትኛው ባሕርይ ያስፈልጋል? (ሉቃስ 10:21)

9 የይሖዋ ጥበብ የተገለጠበትን ሌላም መንገድ እንመልከት። ይሖዋ አብዛኞቹ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች እንዲጻፉ ያደረገው ትሑት የሆኑ አንባቢዎች ብቻ እንዲረዱት በሚያስችል መንገድ ነው። (ሉቃስ 10:21⁠ን አንብብ።) በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያነብባሉ። አንድ ምሁር እንደተናገሩት መጽሐፍ ቅዱስ “የመጀመሪያውን ቦታ የሚይዘው በዓለም ላይ በስፋት በመነበቡ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ በላይ በጥንቃቄ በመነበቡም ጭምር ነው።” ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ በትክክል መረዳትና ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት ትሑት የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።—2 ቆሮ. 3:15, 16

10. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ጥበብ የሚገልጥበት ሌላ መንገድ ምንድን ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ጥበብ የሚገልጥበት ሌላም መንገድ አለ። ይሖዋ ቅዱሳን መጻሕፍትን እኛን በቡድን ደረጃ ለመምራት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ ለማስተማርና ለማጽናናትም ይጠቀምባቸዋል። ሁላችንም የአምላክን ቃል ስናነብ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ምን ያህል እንደሚያስብልን እንገነዘባለን። (ኢሳ. 30:21) ችግር አጋጥሟችሁ ቅዱሳን መጻሕፍትን ስታነብቡ ልክ ለእናንተ የተጻፈ የሚመስል ጥቅስ ያገኛችሁበት ብዙ አጋጣሚ የለም? እንደዚያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ ይነካል። ታዲያ ለእያንዳንዳችን ሁኔታ የሚሠራ ወቅታዊ መረጃ ሊይዝ የቻለው እንዴት ነው? ይህ ሊሆን የቻለው መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው በጥበቡ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አካል ስለሆነ ብቻ ነው።—2 ጢሞ. 3:16, 17

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፍትሕ ያንጸባርቃል

11. አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈበት መንገድ እንደማያዳላ የሚያሳየው እንዴት ነው?

11 ሌላው የይሖዋ ባሕርይ ፍትሕ ነው። (ዘዳ. 32:4) ፍትሕ ከአድልዎ ነፃ ከመሆን ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፤ ይሖዋ ደግሞ ከአድልዎ ነፃ ነው። (ሥራ 10:34, 35፤ ሮም 2:11) መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች ይሖዋ የማያዳላ መሆኑን ያሳያሉ። የመጀመሪያዎቹ 39 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት በአብዛኛው በዕብራይስጥ ነው፤ ዕብራይስጥ በወቅቱ የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች በቀላሉ የሚረዱት ቋንቋ ነበር። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የግሪክ ቋንቋ በስፋት መነገር ጀመረ፤ ስለዚህ የቀሩት 27 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በዋነኝነት የተጻፉት በዚህ ቋንቋ ነው። ይሖዋ ቃሉ በአንድ ቋንቋ ብቻ እንዲጻፍ አላደረገም። በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚኖሩ ወደ ስምንት ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ብዙ ቋንቋዎችን ይናገራሉ። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ስለ ይሖዋ ሊማሩ የሚችሉት እንዴት ነው?

12. ዳንኤል 12:4 በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት ፍጻሜውን ያገኘበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

12 ይሖዋ በፍጻሜው ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ‘እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ በነቢዩ ዳንኤል በኩል ቃል ገብቷል። ብዙዎች ይህን እውነት ይረዱታል። (ዳንኤል 12:4⁠ን አንብብ።) የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲበዛ አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ነገር መጽሐፍ ቅዱሶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በስፋት መተርጎማቸው፣ መዘጋጀታቸውና መሰራጨታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት በመተርጎምና በመሰራጨት ረገድ በዓለም ላይ የመጀመሪያውን ቦታ ይዟል። የንግድ ድርጅቶች የሚያዘጋጇቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንዳንዴ በጣም ውድ ይሆናሉ። የይሖዋ ሕዝቦች እስካሁን ድረስ የአምላክን ቃል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከ240 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተርጉመዋል፤ ማንም ሰው እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሶች በነፃ ማግኘት ይችላል። ይህም በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ የሚሰሙበት አጋጣሚ ፈጥሯል። (ማቴ. 24:14) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ቃሉን በማንበብ እሱን የሚያውቁበት አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። ምክንያቱም ሁላችንንም በጣም ይወደናል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ፍቅር ያንጸባርቃል

13. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ፍቅር ያንጸባርቃል የምንለው ለምንድን ነው? (ዮሐንስ 21:25)

13 መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የላቀውን የይሖዋን ባሕርይ ማለትም ፍቅሩን ይገልጣል። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተቱ ያደረጋቸውንና ያላደረጋቸውን ነገሮች ለማሰብ ሞክሩ። በቃሉ ውስጥ ያካተተልን ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት፣ በአሁኑ ጊዜ ደስተኛ ለመሆንና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስፈልጉንን መረጃዎች ነው። ይሖዋ ስለሚወደን ከአቅማችን በላይ የሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን በማዥጎድጎድ አላስጨነቀንም።—ዮሐንስ 21:25⁠ን አንብብ።

14. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ የአምላክን ፍቅር የሚያሳይበት ሌላ መንገድ ምንድን ነው?

14 ይሖዋ እኛን እንደሚያከብረን በሚያሳይ መንገድ ሐሳቡን መግለጹም የእሱን ፍቅር ያንጸባርቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ዝርዝር ሕጎችን በማስፈር እያንዳንዱን የሕይወታችንን ክፍል ለመቆጣጠር አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ታሪኮችን፣ ስሜት ቀስቃሽ ትንቢቶችንና ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት የማሰብ ችሎታችንን ተጠቅመን እንድንወስን አበረታቶናል። በዚህ መንገድ የአምላክ ቃል ይሖዋን ከልባችን እንድንወደውና እንድንታዘዘው ያነሳሳናል።

ፎቶግራፎች፦ 1. አንዲት ትንሽ ልጅ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?” የተባለውን መጽሐፍ እያነበበች እመቤቷን ስላነጋገረችው እስራኤላዊት ልጅ በሚናገረው ዘገባ ላይ ስታሰላስል። 2. አንድ ወጣት ወንድም መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበ ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት እንደሸሸ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ሲያሰላስል። 3. አንዲት በዕድሜ የገፉ እህት መጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ነብይቷ ሐና ሕፃኑን ኢየሱስን እንዳየች በሚገልጸው ዘገባ ላይ ሲያሰላስሉ

ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ አገልጋዮቹን ስለያዘበት መንገድ ማሰላሰላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሥዕሉ ላይ ትንሿ ልጅ፣ ወጣቱ ወንድምና በዕድሜ የገፉት እህት በየትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ላይ እያሰላሰሉ ነው? (ዘፍ. 39:1, 10-12፤ 2 ነገ. 5:1-3፤ ሉቃስ 2:25-38)

15 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን ያሳያል። እንዴት? ቃሉ እኛ የሰው ልጆች የሚሰሙንን ስሜቶች በሚያንጸባርቁ ዘገባዎች የተሞላ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ያላቸው ስለሆኑ ስሜታቸውን መረዳት አይከብደንም። (ያዕ. 5:17) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ እንደ እኛው ያሉ ሰዎችን በምን ዓይነት መንገድ እንደያዛቸው ማንበባችን እሱ “እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ” በግልጽ ለማየት ያስችለናል።—ያዕ. 5:11

16. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስህተት ስለሠሩ ሰዎች ታሪክ ስናነብ ስለ ይሖዋ ምን እንማራለን? (ኢሳይያስ 55:7)

16 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት ሌላም መንገድ አለ። ቅዱሳን መጻሕፍት አምላካችን ስህተት ስንሠራ እርግፍ አድርጎ እንደማይተወን ማረጋገጫ ይሰጡናል። እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜ በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተዋል፤ ከልባቸው ንስሐ ሲገቡ ግን አምላክ ይቅር ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 55:7⁠ን አንብብ።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም አምላክ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ የሚያዩበት አጋጣሚ ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከባድ ኃጢአት የሠራን በኋላ ግን ንስሐ የገባን ሰው የእምነት ባልንጀሮቹ ‘ይቅር ሊሉትና ሊያጽናኑት’ እንደሚገባ በመንፈስ መሪነት ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር። (2 ቆሮ. 2:6, 7፤ 1 ቆሮ. 5:1-5) ይሖዋ በጥንት ጊዜ የነበሩ አገልጋዮቹን ኃጢአት ስለሠሩ ብቻ እንዳልተዋቸው ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ይረዳቸው፣ ያስተካክላቸውና ወደ እሱ እንዲመለሱ ግብዣ ያቀርብላቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ ላሉ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችም እንዲሁ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።—ያዕ. 4:8-10

“መልካም ስጦታ” ለሆነው የአምላክ ቃል አድናቆት ይኑራችሁ

17. መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ስጦታ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ በጣም ልዩ ስጦታ ሰጥቶናል። ቃሉን ልዩ ስጦታ የሚያደርገው ምንድን ነው? እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ይገልጣል። ይህ መጽሐፍ ይሖዋ እንድናውቀው እንደሚፈልግ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ ወዳጆቹ እንድንሆን ይፈልጋል።

18. የይሖዋ “መልካም ስጦታ” ለሆነው ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 “መልካም ስጦታ” የሆነውን የአምላክን ቃል አቅልለን መመልከት አንፈልግም። (ያዕ. 1:17) እንግዲያው ለዚህ ስጦታ ሁሌም አመስጋኞች እንሁን። ይህን ማድረግ የምንችለው በውስጡ የሰፈሩትን ቅዱስ ቃላት በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ነው። እንዲህ ስናደርግ ይህን መጽሐፍ ያጻፈው ታላቁ አምላካችን ጥረታችንን እንደሚባርክልንና “ስለ አምላክ እውቀት [እንደምንቀስም]” መተማመን እንችላለን።—ምሳሌ 2:5

መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተሉትን የይሖዋን ባሕርያት የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

  • ጥበቡን

  • ፍትሑን

  • ፍቅሩን

መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው

a መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ይረዳናል። ይህ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ አምላክ ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ምን ያስተምረናል? በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንማረው ነገር ለአምላክ ቃል ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ይረዳናል፤ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከሰማዩ አባታችን የተሰጠ ስጦታ እንደሆነ እንድንገነዘብ ያደርገናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ