ጦርነት እና ግጭት ሊቆም ያልቻለው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የጦርነትና የግጭት ዋነኛ መንስኤዎች ምን እንደሆኑ እንዲሁም ጦርነት እስካሁን ሊቆም ያልቻለው ለምን እንደሆነ ይገልጽልናል።
ኃጢአት
አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን አዳምንና ሔዋንን የፈጠራቸው በራሱ መልክ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) በመሆኑም ሰላምንና ፍቅርን ጨምሮ የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ተፈጥሯዊ ችሎታ ነበራቸው። (1 ቆሮንቶስ 14:33፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ሆኖም አዳምና ሔዋን አምላክን ሳይታዘዙ ቀሩ፤ እንዲሁም ኃጢአት ሠሩ። በዚህም የተነሳ ሁላችንም ኃጢአትንና ሞትን ወርሰናል። (ሮም 5:12) በዘር የወረስነው ኃጢአት አስተሳሰባችንም ሆነ ድርጊታችን ወደ ዓመፅ ያዘነበለ እንዲሆን አድርጓል።—ዘፍጥረት 6:5፤ ማርቆስ 7:21, 22
የዓለም መንግሥታት
አምላክ ሲፈጥረን ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር ችሎታ አልሰጠንም። መጽሐፍ ቅዱስ “[ሰው] አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም” ይላል። (ኤርምያስ 10:23) በዚህም የተነሳ የዓለም መንግሥታት ጦርነትንና ዓመፅን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አይችሉም።
ሰይጣንና አጋንንቱ
መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው ቁጥጥር ሥር እንደሆነ’ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 5:19) “ክፉው” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው፤ እሱ ነፍሰ ገዳይ ነው። (ዮሐንስ 8:44) ከጦርነትና ከዓመፅ በስተ ጀርባ ያሉት ዋነኛ ጠንሳሾች ሰይጣንና ሌሎች ክፉ መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው።—ራእይ 12:9, 12
እኛ የጦርነትንና የዓመፅን ዋነኛ መንስኤዎች ማስወገድ አንችልም፤ አምላክ ግን ይችላል።