የጥናት ርዕስ 9
መዝሙር 51 ራሳችንን ለአምላክ ወስነናል!
ለመጠመቅ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ
“ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ።”—ሥራ 22:16
ዓላማ
የሳምራውያንን፣ የጠርሴሱን ሳኦልን፣ የቆርኔሌዎስንና የቆሮንቶስ ሰዎችን ምሳሌ በመመርመር ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ያለህን ቁርጠኝነት አጠናክር።
1. ለመጠመቅ የሚያነሳሱ ምን ጥሩ ምክንያቶች አሉ?
ይሖዋን ትወደዋለህ? መልካም ስጦታዎችን ሁሉ ሌላው ቀርቶ ሕይወት እንኳ ያገኘኸው ከእሱ ነው። ታዲያ ለእሱ ያለህን ፍቅር ማሳየት አትፈልግም? ይህን ማድረግ የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ራስህን ለእሱ መወሰንና ይህን ውሳኔህን በውኃ በመጠመቅ ማሳየት ነው። እነዚህን እርምጃዎች ስትወስድ በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ትታቀፋለህ። በዚህም ምክንያት፣ አባትህና ወዳጅህ የሆነው ይሖዋ ይመራሃል እንዲሁም ይንከባከብሃል፤ ምክንያቱም አሁን የእሱ ንብረት ነህ። (መዝ. 73:24፤ ኢሳ. 43:1, 2) ራስህን ወስነህ መጠመቅህ ለዘላለም በደስታ መኖር የምትችልበት አጋጣሚም ይከፍትልሃል።—1 ጴጥ. 3:21
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 እንዳትጠመቅ የሚይዝህ ነገር አለ? ይህ ሁኔታ የገጠመህ አንተ ብቻ አይደለህም። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለጥምቀት ብቁ ለመሆን በምግባራቸውና በአስተሳሰባቸው ላይ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች አሁን ይሖዋን በደስታና በቅንዓት እያገለገሉ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለመጠመቅ ከወሰኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች የምትማረው ነገር ይኖር ይሆን? እስቲ ያጋጠሟቸውን እንቅፋቶች እንመልከት፤ ከዚያም ከእነሱ ምሳሌ የምናገኘውን ትምህርት እናያለን።
ሳምራውያን ተጠመቁ
3. አንዳንድ ሳምራውያን ለመጠመቅ ምን እንቅፋት መወጣት አስፈልጓቸው ሊሆን ይችላል?
3 ሳምራውያን በኢየሱስ ዘመን ከይሁዳ በስተ ሰሜን በጥንቷ ሴኬም አቅራቢያና በሰማርያ ይኖሩ የነበሩ ሃይማኖታዊ ቡድን ናቸው። ሳምራውያን ከመጠመቃቸው በፊት ስለ አምላክ ቃል የተሟላ እውቀት ማግኘት ነበረባቸው። የአምላክ ቃል አድርገው የሚቀበሉት ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉትን የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እና ምናልባትም የኢያሱን መጽሐፍ ብቻ ነው። ይሁንና ሳምራውያን ዘዳግም 18:18, 19 ላይ አምላክ በሰጠው ተስፋ መሠረት የመሲሑን መምጣት ይጠባበቁ ነበር። (ዮሐንስ 4:25) ሳምራውያን መጠመቅ ከፈለጉ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን አምነው መቀበል ነበረባቸው። “ብዙ ሳምራውያን” ይህን አድርገዋል። (ዮሐ. 4:39) ሌሎች ሳምራውያን ደግሞ ለአይሁዳውያን የነበራቸውን ሥር የሰደደ ጥላቻ ማስወገድ አስፈልጓቸዋል።—ሉቃስ 9:52-54
4. በሐዋርያት ሥራ 8:5, 6, 14 መሠረት አንዳንድ ሳምራውያን ፊልጶስ ለሰበከው መልእክት ምን ምላሽ ሰጡ?
4 ሳምራውያን እንዲጠመቁ የረዳቸው ምንድን ነው? ወንጌላዊው ፊልጶስ “ስለ ክርስቶስ” ሲሰብክላቸው አንዳንድ ሳምራውያን “የአምላክን ቃል [ተቀበሉ]።” (የሐዋርያት ሥራ 8:5, 6, 14ን አንብብ።) ፊልጶስ አይሁዳዊ መሆኑ ለመልእክቱ ጆሮ እንዳይሰጡ አላገዳቸውም። ምናልባት በአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ላይ የሚገኙ አምላክ እንደማያዳላ የሚገልጹ ጥቅሶች ትዝ ብለዋቸው ሊሆን ይችላል። (ዘዳ. 10:17-19) ያም ሆነ ይህ ‘ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የተናገረውን ነገር በትኩረት ተከታትለዋል’፤ አምላክ ከእሱ ጋር እንደሆነ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃም ተቀብለዋል። ፊልጶስ የታመሙትን መፈወስንና ጋኔን ማስወጣትን ጨምሮ ብዙ ተአምራትን ይፈጽምም ነበር።—ሥራ 8:7
5. ከሳምራውያን ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?
5 እነዚህ ሳምራውያን ለአይሁዳውያን ያላቸው ጥላቻ ወይም ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸው እውቀት የተሟላ አለመሆኑ እንዳይጠመቁ እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችል ነበር። እነሱ ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀዱም። ሳምራውያን ፊልጶስ የሚያስተምረው ነገር እውነት እንደሆነ ባመኑ ጊዜ ለመጠመቅ አላመነቱም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ምሥራች እያወጀ የነበረውን ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ ወንዶችም ሴቶችም ይጠመቁ ጀመር።” (ሥራ 8:12) አንተስ የአምላክ ቃል እውነት እንደሆነ ታምናለህ? የይሖዋ ምሥክሮች ጭፍን ጥላቻን ማሸነፍ እንደቻሉና የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት የሆነውን እውነተኛ ፍቅር አንዳቸው ለሌላው እንደሚያሳዩ እምነት አለህ? ከሆነ ምን ትጠብቃለህ? (ዮሐ. 13:35) ይሖዋ እንደሚባርክህ ተማምነህ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ።
6. ከሩበን ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?
6 በጀርመን የሚኖረው ሩበን ያደገው በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ነው። ሆኖም ወጣት ሳለ ይሖዋ መኖሩን ይጠራጠር ነበር። ታዲያ ጥርጣሬውን ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው? እውቀቱን ማሳደግ እንዳለበት ስለተገነዘበ አንድ እርምጃ ወሰደ። እንዲህ ብሏል፦ “ጥርጣሬ የፈጠሩብኝን ነገሮች በግል ጥናቴ ላይ መመርመር ጀመርኩ። ስለ ዝግመተ ለውጥ በተደጋጋሚ አጠናሁ።” ሩበን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን መጽሐፍም አነበበ። ይህ መጽሐፍ በአመለካከቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ‘ዋው! ይሖዋ በእርግጥ አለ’ ብሎ እንዲያስብ እንዳደረገው ያስታውሳል። በኋላም ዋናውን መሥሪያ ቤት ጎበኘ፤ ጉብኝቱ በዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን ውስጥ ላለው እንደ ተአምር የሚቆጠር አንድነት ያለው አድናቆት እንዲጨምር አደረገ። ወደ ጀርመን ከተመለሰ በኋላ በ17 ዓመቱ ተጠመቀ። አንተስ? ስለተማርካቸው ነገሮች ጥርጣሬ አለህ? ከሆነ በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር በማድረግ ጥርጣሬህን ተጋፈጠው። “ትክክለኛ እውቀት” ጥርጣሬን ማሸነፍ ይችላል። (ኤፌ. 4:13, 14) በሌሎች የዓለም ክፍሎች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ስላለው ፍቅርና አንድነት ስትሰማ እንዲሁም በራስህ ጉባኤ ይህን ፍቅር ስትመለከት ደግሞ ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ያለህ አድናቆት ይጨምራል።
የጠርሴሱ ሳኦል ተጠመቀ
7. ሳኦል የትኛውን አመለካከቱን ማስተካከል ነበረበት?
7 አሁን ደግሞ የጠርሴሱን ሳኦልን ምሳሌ እንመልከት። ሳኦል በአይሁዳውያን ሃይማኖት ትልቅ እድገት እያደረገ ነበር፤ አስተዳደጉም በአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዲሰጠው የሚያደርግ ነበር። (ገላ. 1:13, 14፤ ፊልጵ. 3:5) በወቅቱ ብዙ አይሁዳውያን፣ ክርስቲያኖችን እንደ ከሃዲ ይመለከቷቸው ነበር፤ ሳኦልም ክፉኛ ያሳድዳቸው ጀመር። የአምላክን ፈቃድ እያደረገ እንዳለ ተሰምቶት ነበር። (ሥራ 8:3፤ 9:1, 2፤ 26:9-11) ኢየሱስን በመቀበል ተጠምቆ ክርስቲያን ለመሆን ግን እሱ ራሱ የስደት ዒላማ ለመሆን ፈቃደኛ መሆን ነበረበት።
8. (ሀ) ሳኦል እንዲጠመቅ የረዳው ምንድን ነው? (ለ) የሐዋርያት ሥራ 22:12-16 እንደሚገልጸው ሐናንያ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 ሳኦል እንዲጠመቅ የረዳው ምንድን ነው? ክብር የተጎናጸፈው ጌታ ኢየሱስ ሲገለጥለት ሳኦል ዓይኑ ታወረ። (ሥራ 9:3-9) ከዚያ በኋላ ለሦስት ቀናት ፆመ፤ መንገድ ላይ ስላጋጠመው ነገር አሰላስሎ እንደሚሆንም ጥያቄ የለውም። ሳኦል ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነና ተከታዮቹ እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዙ አመነ። በእስጢፋኖስ ሞት እጁን በማስገባቱ ጸጸት ተሰምቶት መሆን አለበት! (ሥራ 22:20) ከሦስት ቀናት በኋላ ሐናንያ የሚባል ደቀ መዝሙር መጥቶ በደግነት አነጋገረው፤ የዓይኑን ብርሃን መለሰለት እንዲሁም ወዲያውኑ እንዲጠመቅ አበረታታው። (የሐዋርያት ሥራ 22:12-16ን አንብብ።) ሳኦል የተደረገለትን እርዳታ በትሕትና የተቀበለ ሲሆን አዲስ የሕይወት መንገድ ጀመረ።—ሥራ 9:17, 18
እንደ ሳኦል የሚሰጥህን ማበረታቻ ተቀብለህ ትጠመቃለህ? (አንቀጽ 8ን ተመልከት)
9. ከሳኦል ምን ትምህርት ታገኛለህ?
9 ከሳኦል የምናገኛቸው ትምህርቶች አሉ። ኩራት ወይም የሰው ፍርሃት እንዳይጠመቅ እንቅፋት ሊሆንበት ይችል ነበር። እሱ ግን እነዚህ ነገሮች እንዲያሰናክሉት አልፈቀደም። ሳኦል ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ሲቀበል በትሕትና አካሄዱን አስተካክሏል። (ሥራ 26:14, 19) ስደት እንደማይቀርለት ቢያውቅም ክርስቲያን ለመሆን ፈቃደኛ ሆኗል። (ሥራ 9:15, 16፤ 20:22, 23) ከተጠመቀ በኋላ በይሖዋ በመታመን የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት መወጣት ችሏል። (2 ቆሮ. 4:7-10) አንተም ተጠምቀህ የይሖዋ ምሥክር በመሆንህ የእምነት ፈተና ወይም መከራ ሊገጥምህ ይችላል። ሆኖም እርዳታ ታገኛለህ፤ የአምላክና የክርስቶስ ድጋፍ እንደማይለይህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ፊልጵ. 4:13
10. የአና ምሳሌ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?
10 በምሥራቅ አውሮፓ የምትኖረው እህታችን አና ያደገችው በኩርድ ቤተሰብ ውስጥ ነው። እናቷ ከተጠመቀች በኋላ አና አባቷን አስፈቅዳ በ9 ዓመቷ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። አብረዋት የሚኖሩት ዘመዶቿ ግን አስቸገሯት። የአና ዘመዶች፣ የአያት የቅድመ አያቶቿን ሃይማኖት መተው ለቤተሰቡ ውርደት እንደሆነ ተሰማቸው። አና 12 ዓመት ሲሆናት ለመጠመቅ አባቷን አስፈቀደች። አባቷ ይህ በግሏ ያደረገችው ውሳኔ እንጂ ሌላ ሰው ተጽዕኖ አድርጎባት እንዳልሆነ ለማረጋገጥ ጠየቃት። “ይሖዋን እወደዋለሁ” በማለት አና መለሰችለት። አባቷ እንድትጠመቅ ፈቀደላት። ከዚያ በኋላም አና ከዘመዶቿ ብዙ ፌዝና በደል ይደርስባት ነበር። አንድ ዘመዷ “የይሖዋ ምሥክር ከምትሆኚ ስድ እና አጫሽ ብትሆኚ ይሻልሽ ነበር” ብሏት ነበር። ታዲያ አና ለመጽናት የረዳት ምንድን ነው? “ይሖዋ ጠንካራ እንድሆን ረድቶኛል፤ እናትና አባቴም በጣም ይደግፉኝ ነበር” ብላለች። አና የይሖዋን እጅ በሕይወቷ ያየችባቸውን አጋጣሚዎች የመጻፍ ልማድ አላት። ይሖዋ እሷን የረዳባቸውን ሁኔታዎች እንዳትረሳ በየጊዜው ይህን ማስታወሻዋን ትመለከታለች። ተቃውሞ የሚያስፈራህ ከሆነ ይሖዋ አንተንም እንደሚረዳህ አትርሳ።—ዕብ. 13:6
ቆርኔሌዎስ ተጠመቀ
11. ቆርኔሌዎስ እንዳይጠመቅ ምን እንቅፋት ሊሆንበት ይችል ነበር?
11 መጽሐፍ ቅዱስ የቆርኔሌዎስን ምሳሌም ይዟል። ቆርኔሌዎስ በሮም ሠራዊት ውስጥ “መቶ አለቃ” ነበር። (ሥራ 10:1 ግርጌ) በዚህም የተነሳ በማኅበረሰቡና በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው ነበር። እንዲሁም “ለሰዎች ምጽዋት [ይሰጥ]” ነበር። (ሥራ 10:2) ይሖዋ ሐዋርያው ጴጥሮስን በመላክ ቆርኔሌዎስ ምሥራቹን እንዲሰማ አደረገ። ታዲያ ቆርኔሌዎስ በሰዎች ዘንድ የነበረው ቦታ እንዳይጠመቅ እንቅፋት ሆኖበት ይሆን?
12. ቆርኔሌዎስ እንዲጠመቅ የረዳው ምንድን ነው?
12 ቆርኔሌዎስ እንዲጠመቅ የረዳው ምንድን ነው? ዘገባው “ከመላው ቤተሰቡ ጋር . . . ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው” እንደነበረ ይናገራል። እንዲሁም ዘወትር ወደ አምላክ የሚማልድ ሰው ነበር። (ሥራ 10:2) ጴጥሮስ ምሥራቹን ሲሰብክላቸው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ክርስቶስን ተቀበሉ፤ ወዲያውኑም ተጠመቁ። (ሥራ 10:47, 48) ቆርኔሌዎስ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ይሖዋን ለማምለክ ሲል የሚጠበቅበትን ማስተካከያ ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ እንደነበረ ጥያቄ የለውም።—ኢያሱ 24:15፤ ሥራ 10:24, 33
13. ከቆርኔሌዎስ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?
13 እንደ ሳኦል ሁሉ ቆርኔሌዎስም በሰዎች ዘንድ የነበረው ከበሬታ ክርስቲያን እንዳይሆን እንቅፋት ሊሆንበት ይችል ነበር። እሱ ግን ይህ እንዲሆን አልፈቀደም። አንተስ እውነትን መቀበልህ በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንድታደርግ ይጠይቅብሃል? ከሆነ ይሖዋ ረዳትህ እንደሆነ አስታውስ። ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን ለማገልገል ያሳየኸውን ቁርጠኝነት ይባርክልሃል።
14. ከሱዮሺ ምሳሌ ምን ጥቅም ማግኘት ትችላለህ?
14 በጃፓን የሚኖረው ሱዮሺ ለጥምቀት ብቃቱን ለማሟላት ሲል በሥራው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነበረበት። ኢኬኖቦ በተባለ ታዋቂ የአበባ ዲኮር ትምህርት ቤት ውስጥ የዋና ኃላፊው ረዳት ነበር። ዋና ኃላፊው በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ካልቻለ እሱን ተክቶ በቡድሃ እምነት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ የሚገኘው ሱዮሺ ነበር። ሱዮሺ ስለ ሞት እውነቱን ሲማር ግን መጠመቅ ከፈለገ ይህን ማድረጉን መቀጠል እንደማይችል ተረዳ። በቡድሃ እምነት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ላለመካፈል ውሳኔ አደረገ። (2 ቆሮ. 6:15, 16) ሱዮሺ ስለ ጉዳዩ ዋና ኃላፊውን አነጋገረው። ውጤቱ ምን ሆነ? በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶቹ ላይ ሳይካፈል በሥራው እንዲቀጥል ተፈቀደለት። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ተጠመቀ።a አንተም አምላክን ለማስደሰት ስትል በሥራህ ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልግህ ከሆነ ይሖዋ ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ የሚያስፈልጋችሁን እንደሚያሟላላችሁ እርግጠኛ ሁን።—መዝ. 127:2፤ ማቴ. 6:33
የቆሮንቶስ ሰዎች ተጠመቁ
15. የቆሮንቶስ ሰዎች እንዳይጠመቁ ምን እንቅፋት ሊሆንባቸው ይችል ነበር?
15 የጥንቷ ቆሮንቶስ በነዋሪዎቿ ገንዘብ ወዳድነትና ልቅ ሥነ ምግባር የምትታወቅ ከተማ ነበረች። የብዙዎቹ የከተማዋ ሰዎች አኗኗር አምላክ የሚደሰትበት ዓይነት አልነበረም። እንዲህ ባለ ከተማ ውስጥ እየኖረ ምሥራቹን መቀበል የሚፈልግ ሰው ተፈታታኝ ሁኔታ እንደሚገጥመው ጥያቄ የለውም። ይሁንና ሐዋርያው ጳውሎስ ወደዚህች ከተማ መጥቶ ስለ ክርስቶስ ሲሰብክላቸው “መልእክቱን የሰሙ በርካታ የቆሮንቶስ [ሰዎች] አምነው ይጠመቁ ጀመር።” (ሥራ 18:7-11) ከዚያም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ለጳውሎስ ተገልጦ “በዚህች ከተማ ብዙ ሰዎች አሉኝ” አለው። ስለዚህ ጳውሎስ በዚያ ለአንድ ዓመት ተኩል መስበኩን ቀጠለ።
16. አንዳንድ የቆሮንቶስ ሰዎች እንዳይጠመቁ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ነገር እንዲያስወግዱ የረዳቸው ምንድን ነው? (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5)
16 የቆሮንቶስ ሰዎች እንዲጠመቁ የረዳቸው ምንድን ነው? (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5ን አንብብ።) የአምላክ ቃልና ኃያል የሆነው ቅዱስ መንፈሱ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። (ዕብ. 4:12) ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች የተቀበሉት የቆሮንቶስ ሰዎች እንደ ስካር፣ ስርቆትና ግብረ ሰዶማዊነት ያሉትን ልማዶችና ምግባሮች እርግፍ አድርገው መተው ችለዋል።—1 ቆሮ. 6:9-11b
17. ከቆሮንቶስ ሰዎች ምን መማር ትችላለህ?
17 ወደ ክርስትና የመጡት የቆሮንቶስ ሰዎች ሊያስወግዷቸው የሚገቡ ሥር የሰደዱ ልማዶች ነበሯቸው፤ ሆኖም ክርስቲያን ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ አልተሰማቸውም። ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ ለመጓዝ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል። (ማቴ. 7:13, 14) አንተስ ለመጠመቅ ስትል ልታስወግደው የሚገባህ መጥፎ ልማድ ወይም ምግባር አለህ? ትግሉ ከባድ ቢሆንም ፈጽሞ እጅ አትስጥ! የተሳሳተ ነገር እንድትፈጽም የሚፈትንህን ስሜት ለመቋቋም እንዲያግዝህ ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው።
18. ከሞኒካ ምሳሌ ምን ጥቅም ማግኘት ትችላለህ?
18 በጆርጂያ የምትኖረው ሞኒካ ለመጠመቅ፣ ጸያፍ አነጋገርንና ተገቢ ያልሆነ መዝናኛን ማስወገድ አስፈልጓት ነበር፤ እነዚህን ልማዶች ለማሸነፍ ብርቱ ጥረት አድርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “የአሥራዎቹን ዕድሜ የተወጣሁት በጸሎት ብርታት ነው። ይሖዋ ትክክለኛውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንዳለኝ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ሁልጊዜ ይረዳኝና ይመራኝ ነበር።” ሞኒካ በ16 ዓመቷ ተጠመቀች። አንተስ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል ልታስወግዳቸው የሚገቡ ልማዶች አሉ? ለውጥ ለማድረግ የሚያስፈልግህን ኃይል እንዲሰጥህ እሱን መለመንህን አታቋርጥ፤ ይሖዋ ለሚለምኑት ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ይሰጣል።—ዮሐ. 3:34
ተራራ የሚያንቀሳቅስ እምነት ማዳበር ትችላለህ
19. እንደ ተራራ የሆኑ እንቅፋቶችን ለመወጣት ምን ሊረዳህ ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
19 አንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፦ ይሖዋ ይወድሃል እንዲሁም የቤተሰቡ ክፍል እንድትሆን ይፈልጋል። ለመጠመቅ ስትል የምትታገለው ነገር ምንም ይሁን ምን ይህ እውነታ አይቀየርም። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት ካላችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደዚያ ሂድ’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ነገር አይኖርም።” (ማቴ. 17:20) ኢየሱስ ይህን ሲል የሰሙት ሰዎች እሱን ካወቁት ገና ጥቂት ዓመታቸው ነው፤ በመሆኑም እምነታቸው ገና በእንጭጩ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ ጠንካራ እምነት ማዳበር ከቻሉ ይሖዋ እንደ ተራራ ያሉ እንቅፋቶችን ለመወጣት እንደሚረዳቸው እያረጋገጠላቸው ነው። ይሖዋ አንተንም እንዲህ እንድታደርግ ይረዳሃል!
ይሖዋ እንደሚወድህ እንዲሁም በእሱ ቤተሰብ ውስጥ እንድትታቀፍ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ሁን (አንቀጽ 19ን ተመልከት)c
20. በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩና ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ምሳሌ ምን ለማድረግ አነሳስቶሃል?
20 እንዳትጠመቅ እንቅፋት የሆነብህን ነገር ለይተህ አውቀሃል? ከሆነ ዛሬ ነገ ሳትል እንቅፋቱን ለማስወገድ እርምጃ ውሰድ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትም ሆነ ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ምሳሌ መጽናኛና ብርታት ይሆንሃል። በእነሱ ምሳሌ ተበረታተህ ራስህን ለይሖዋ ወስነህ ለመጠመቅ እንድትነሳሳ እንመኛለን። ይህ ፈጽሞ የማትቆጭበት ውሳኔ ነው!
መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል
a የወንድም ሱዮሺ ፉጂ የሕይወት ታሪክ በነሐሴ 8, 2005 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ከገጽ 20-23 ላይ ይገኛል።
b ‘ከመጠመቅ ወደኋላ የምትለው ለምንድን ነው?’ የሚለውን ቪዲዮ jw.org ላይ ተመልከት።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ወንድሞችና እህቶች አዳዲስ ተጠማቂዎችን ሞቅ አድርገው ሲቀበሉ