-
ማርቆስ 3:1-6አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
3 ዳግመኛ ወደ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+ 2 ኢየሱስን ሊከሱት ይፈልጉ ስለነበር ሰውየውን በሰንበት ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር። 3 እሱም እጁ የሰለለበትን* ሰው “ተነሳና ወደ መሃል ና” አለው። 4 ከዚያም “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት* ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።+ እነሱ ግን ዝም አሉ። 5 በልባቸው ደንዳናነት+ በጣም አዝኖ በዙሪያው ያሉትን በብስጭት ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። እሱም በዘረጋ ጊዜ እጁ ዳነለት። 6 ፈሪሳውያኑ ወጥተው ከሄዱ በኋላ ወዲያው ከሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች+ ጋር በመሰብሰብ እንዴት እንደሚገድሉት መመካከር ጀመሩ።
-
-
ሉቃስ 6:6-11አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
6 በሌላ የሰንበት ቀን+ ወደ ምኩራብ ገብቶ ያስተምር ጀመር። በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለ* አንድ ሰው ነበር።+ 7 ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም ኢየሱስን የሚከሱበት ምክንያት ማግኘት ይፈልጉ ስለነበር በሰንበት ይፈውስ እንደሆነ ለማየት በትኩረት ይከታተሉት ነበር። 8 እሱ ግን ሐሳባቸውን አውቆ+ ስለነበር እጁ የሰለለበትን* ሰው “ተነሳና መሃል ላይ ቁም” አለው። ሰውየውም ተነስቶ በዚያ ቆመ። 9 ከዚያም ኢየሱስ “እስቲ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ፤ በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት* ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው።+ 10 በዙሪያው ያሉትን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ ሰውየውን “እጅህን ዘርጋ” አለው። ሰውየውም እንደተባለው አደረገ፤ እጁም ዳነለት። 11 እነሱ ግን እጅግ ተቆጡ፤ በኢየሱስ ላይ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉም እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር።
-