-
ማቴዎስ 14:24-33አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
24 በዚህ ጊዜ ጀልባው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሜትሮች* ከየብስ ርቆ የነበረ ሲሆን ነፋሱ ወደ እነሱ ይነፍስ ስለነበር ማዕበሉ በጣም አስቸገራቸው። 25 ሆኖም ኢየሱስ በአራተኛው ክፍለ ሌሊት* በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ። 26 ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ ደንግጠው “ምትሃት ነው!” አሉ። በፍርሃት ተውጠውም ጮኹ። 27 ሆኖም ኢየሱስ ወዲያውኑ “አይዟችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።+ 28 ጴጥሮስም መልሶ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው። 29 እሱም “ና!” አለው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ ወርዶ በውኃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ። 30 ሆኖም አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ። መስጠም ሲጀምርም “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። 31 ወዲያው ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ! ለምን ተጠራጠርክ?” አለው።+ 32 ጀልባው ላይ ከወጡ በኋላ አውሎ ነፋሱ ጸጥ አለ። 33 ከዚያም በጀልባው ውስጥ ያሉት “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት።*
-
-
ዮሐንስ 6:16-21አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
-
-
16 በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕሩ ወረዱ፤+ 17 በጀልባም ተሳፍረው ባሕሩን በማቋረጥ ወደ ቅፍርናሆም ለመሻገር ተነሱ። በዚያን ሰዓት ጨልሞ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ገና ወደ እነሱ አልመጣም ነበር።+ 18 በተጨማሪም ኃይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለነበረ ባሕሩ ይናወጥ ጀመር።+ 19 ይሁን እንጂ አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ገደማ* እንደቀዘፉ ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲቃረብ ተመልክተው ፈሩ። 20 እሱ ግን “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።+ 21 ከዚያም ወዲያው ጀልባዋ ላይ አሳፈሩት፤ ጀልባዋም ሊሄዱ ወዳሰቡበት ቦታ በፍጥነት ደረሰች።+
-