የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • nwt ኢዩኤል 1:1-3:21
  • ኢዩኤል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢዩኤል
  • አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ
ኢዩኤል

ኢዩኤል

1 ወደ ፐቱኤል ልጅ፣ ወደ ኢዩኤል* የመጣው የይሖዋ ቃል ይህ ነው፦

 2 “እናንተ ሽማግሌዎች ይህን ስሙ፤

የአገሪቱም* ነዋሪዎች ሁሉ ልብ በሉ።

በእናንተም ዘመን ይሁን በአባቶቻችሁ ዘመን

እንዲህ ያለ ነገር ተከስቶ ያውቃል?+

 3 ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤

ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፣

የእነሱ ልጆች ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ ይናገሩ።

 4 ከአውዳሚ አንበጣ የተረፈውን የአንበጣ መንጋ በላው፤+

ከአንበጣ መንጋ የተረፈውንም ኩብኩባ በላው፤

ከኩብኩባ የተረፈውን ደግሞ የማይጠግብ አንበጣ በላው።+

 5 እናንተ ሰካራሞች ንቁ፤+ ደግሞም አልቅሱ!

እናንተ የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ

ጣፋጩ የወይን ጠጅ ከአፋችሁ ላይ ስለተወሰደ ዋይ ዋይ በሉ።+

 6 ኃያል የሆነና የሕዝቡ ብዛት ስፍር ቁጥር የሌለው ብሔር ምድሬን ወሮታልና።+

ጥርሶቹ የአንበሳ ጥርሶች ናቸው፤+ መንገጭላውም የአንበሳ መንገጭላ ነው።

 7 የወይን ተክሌን አጠፋው፤ የበለስ ዛፌንም ጉቶ አደረገው፤

ቅርፊታቸውን ሙልጭ አድርጎ ልጦ ወዲያ ጣላቸው፤

በቅርንጫፎቻቸው ላይ አንድም ልጥ አልቀረም።

 8 ማቅ ለብሳ ለልጅነት ሙሽራዋ* እንደምታለቅስ ድንግል*

ዋይ ዋይ በዪ።

 9 የእህል መባና+ የመጠጥ መባ+ ከይሖዋ ቤት ተቋርጧል፤

የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑት ካህናቱም ሐዘን ላይ ናቸው።

10 እርሻው ወድሟል፤ ምድሪቱ አዝናለች፤+

እህሉ ወድሟልና፤ አዲሱ የወይን ጠጅ ደርቋል፤ ዘይቱም ተሟጧል።+

11 ገበሬዎች አፍረዋል፤ የወይን አትክልት ሠራተኞች ዋይ ዋይ ይላሉ፤

ይህም የሆነው ከስንዴውና ከገብሱ የተነሳ ነው፤

የእርሻው መከር ጠፍቷልና።

12 ወይኑ ደርቋል፤

የበለስ ዛፉም ጠውልጓል።

ሮማኑ፣ ዘንባባው፣ ፖሙና

በሜዳው ላይ ያለው ዛፍ ሁሉ ደርቋል፤+

በሕዝቡ መካከል የነበረው ደስታ ወደ ኀፍረት ተለውጧልና።

13 እናንተ ካህናት ማቅ ልበሱ፤* ደግሞም ሐዘን ተቀመጡ፤*

እናንተ በመሠዊያው ፊት የምታገለግሉ+ ዋይ ዋይ በሉ።

እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች ኑ፣ ማቅ ለብሳችሁ እደሩ፤

ከአምላካችሁ ቤት የእህል መባና+ የመጠጥ መባ+ ተቋርጧልና።

14 ጾም አውጁ!* የተቀደሰ ጉባኤ ጥሩ።+

ሽማግሌዎቹንና የምድሪቱን ነዋሪዎች ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋ ቤት ሰብስቡ፤+

እርዳታም ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጩኹ።

15 ከቀኑ የተነሳ ወዮላችሁ!

የይሖዋ ቀን ቀርቧልና፤+

ሁሉን ከሚችለው አምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል!

16 ምግብ ከዓይናችን ፊት፣

ሐሴትና ደስታም ከአምላካችን ቤት ጠፍቶ የለም?

17 ዘሮቹ* ከአካፋዎቻቸው ሥር ጠውልገዋል።

ጎተራዎቹም ተራቁተዋል።

ጎታዎቹ* ፈራርሰዋል፤ እህሉ ደርቋልና።

18 መንጎቹ እንኳ ሳይቀሩ ያቃስታሉ!

ከብቶቹ ግራ ተጋብተው ይቅበዘበዛሉ፤ መሰማሪያ የላቸውምና!

የበጎቹም መንጋ ቅጣቱን ይቀበላል።

19 ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ እጣራለሁ፤+

በምድረ በዳ ያለውን የግጦሽ መሬት እሳት በልቶታልና፤

በሜዳ ያሉትንም ዛፎች ሁሉ ነበልባል አቃጥሏቸዋል።

20 የዱር አራዊትም እንኳ አንተን በጉጉት ይጠባበቃሉ፤

ምክንያቱም የውኃ ጅረቶቹ ደርቀዋል፤

በምድረ በዳ ያለውን የግጦሽ መሬትም እሳት በልቶታል።”

2 “በጽዮን ቀንደ መለከት ንፉ!+

በቅዱሱ ተራራዬ ላይ ቀረርቶ አሰሙ።

የአገሪቱ* ነዋሪዎች በሙሉ ይንቀጥቀጡ፤

የይሖዋ ቀን ቀርቧልና!+ ቀኑ ደፍ ላይ ነው!

 2 የጨለማና የጭጋግ ቀን፣+

የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ነው፤+

በተራሮች ላይ እንደፈነጠቀ የማለዳ ወጋገን ነው።

ስፍር ቁጥር የሌለውና ኃያል የሆነ ሕዝብ ይመጣል፤+

ከዚህ በፊት እንደ እሱ ያለ ፈጽሞ ታይቶ አያውቅም፤

ወደፊትም ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ

እንደ እሱ ያለ አይኖርም።

 3 ከፊቱ ያለውን እሳት ይበላዋል፤

ከኋላው ያለውንም ነበልባል ያቃጥለዋል።+

ከፊቱ ያለው ምድር እንደ ኤደን የአትክልት ስፍራ ነው፤+

ከኋላው ያለው ግን ወና ምድረ በዳ ነው፤

ከእሱም የሚያመልጥ አይኖርም።

 4 መልካቸው እንደ ፈረስ መልክ ነው፤

እንደ ጦር ፈረሶችም ይጋልባሉ።+

 5 በተራሮች አናት ላይ ሲዘሉ የሚሰማው ድምፅ እንደ ሠረገሎች ድምፅ፣+

ገለባንም እንደሚበላ የሚንጣጣ የእሳት ነበልባል ድምፅ ነው።

ለጦርነት እንደተሰለፈ+ ኃያል ሕዝብ ናቸው።

 6 ከእነሱም የተነሳ ሕዝቦች ይጨነቃሉ።

የሰውም ፊት ሁሉ ይቀላል።

 7 እንደ ተዋጊዎች በፍጥነት ጥቃት ይሰነዝራሉ፤

እንደ ወታደሮች ቅጥር ላይ ይወጣሉ፤

እያንዳንዱም የራሱን መንገድ ይዞ ይሄዳል፤

አቅጣጫቸውንም አይቀይሩም።

 8 እርስ በርሳቸው አይገፋፉም፤

እያንዳንዱ ሰው መንገዱን ይዞ ይገሰግሳል።

አንዳንዶቹ በመሣሪያ* ተመተው ቢወድቁ እንኳ

ሌሎቹ አይፍረከረኩም።

 9 ወደ ከተማዋ እየተጣደፉ ይገባሉ፤ በቅጥርም ላይ ይሮጣሉ።

ቤቶችም ላይ ይወጣሉ፤ እንደ ሌባ በመስኮት ይገባሉ።

10 ምድሪቱ በፊታቸው ትንቀጠቀጣለች፤ ሰማያትም ይናወጣሉ።

ፀሐይና ጨረቃ ጨልመዋል፤+

ከዋክብትም ብርሃናቸውን መስጠት አቁመዋል።

11 ይሖዋ በሠራዊቱ+ ፊት ድምፁን በኃይል ያሰማል፤ ሠራዊቱ ስፍር ቁጥር የለውም።+

ቃሉን የሚፈጽመው ኃያል ነውና፤

የይሖዋ ቀን ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ ነው።+

ማንስ ሊቋቋመው ይችላል?”+

12 “አሁንም ቢሆን” ይላል ይሖዋ፣

“በጾም፣+ በለቅሶና በዋይታ በሙሉ ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ።+

13 ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤+

ወደ አምላካችሁ ወደ ይሖዋም ተመለሱ፤

እሱ ሩኅሩኅና* መሐሪ፣ ለቁጣ የዘገየና+ ታማኝ ፍቅሩ የበዛ ነውና፤+

ሊያመጣ ያሰበውንም ጥፋት መለስ ብሎ ያጤናል።*

14 ደግሞም ተመልሶ ጉዳዩን እንደገና በማጤን፣*+

ለአምላካችሁ ለይሖዋ የእህል መባና የመጠጥ መባ ማቅረብ ትችሉ ዘንድ

በረከት ያስቀርላችሁ እንደሆነ ማን ያውቃል?

15 በጽዮን ቀንደ መለከት ንፉ!

ጾም አውጁ፤* የተቀደሰ ጉባኤ ጥሩ።+

16 ሕዝቡን ሰብስቡ፤ ጉባኤውን ቀድሱ።+

ሽማግሌዎቹን ሰብስቡ፤ ልጆቹንና ጡት የሚጠቡትን ሕፃናት ሰብስቡ።+

ሙሽራው ከውስጠኛው ክፍል፣ ሙሽሪትም ከጫጉላ ቤት ይውጡ።

17 የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑት ካህናቱ

በበረንዳውና በመሠዊያው መካከል+ ሆነው ያልቅሱ፤ እንዲህም ይበሉ፦

‘ይሖዋ ሆይ፣ ለሕዝብህ እዘን፤

ርስትህ መሳለቂያ እንዲሆን አታድርግ፤

ብሔራትም አይግዟቸው።

ሕዝቦች “አምላካቸው የት አለ?” ለምን ይበሉ?’+

18 ያን ጊዜ ይሖዋ ለምድሩ ይቀናል፤

ለሕዝቡም ይራራል።+

19 ይሖዋ ለሕዝቡ መልስ ይሰጣል፦

‘እነሆ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት እልክላችኋለሁ፤

እናንተም በሚገባ ትጠግባላችሁ፤+

ከእንግዲህ በብሔራት መካከል ለነቀፋ አልዳርጋችሁም።+

20 የሰሜኑን ሠራዊት ከእናንተ አርቃለሁ፤

ደረቅና ወና ወደሆነ ጠፍ መሬት እበትነዋለሁ፤

ፊቱ ወደ ምሥራቁ ባሕር፣*

ኋላውም ወደ ምዕራቡ ባሕር* ይሆናል።

ግማቱ ወደ ላይ ይወጣል፤

ክርፋቱም ወደ ላይ መውጣቱን ይቀጥላል፤+

አምላክ ታላላቅ ነገሮች ያደርጋልና።’

21 ምድር ሆይ፣ አትፍሪ።

ደስ ይበልሽ፤ ሐሴትም አድርጊ፤ ይሖዋ ታላላቅ ነገሮች ያደርጋልና።

22 እናንተ የዱር እንስሳት፣ አትፍሩ፤

በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ይለመልማሉና፤+

ዛፎችም ፍሬ ያፈራሉ፤+

የበለስ ዛፉና የወይን ተክሉ ጥሩ ምርት ይሰጣሉ።+

23 እናንተ የጽዮን ልጆች ሆይ፣ በአምላካችሁ በይሖዋ ተደሰቱ፤ ሐሴትም አድርጉ፤+

እሱ የፊተኛውን ዝናብ በተገቢው መጠን ይሰጣችኋልና፤

በእናንተም ላይ ዝናቡን ያዘንባል፤

እንደቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ ይሰጣችኋል።+

24 አውድማዎቹ በእህል ይሞላሉ፤

መጭመቂያዎቹም በአዲስ የወይን ጠጅና በዘይት ተሞልተው ያፈሳሉ።+

25 ደግሞም በመካከላችሁ የሰደድኩት ታላቁ ሠራዊቴ

ይኸውም የአንበጣ መንጋው፣ ኩብኩባው፣ የማይጠግበው አንበጣና አውዳሚው አንበጣ

ሰብላችሁን ለበሉባቸው ዓመታት ማካካሻ እሰጣችኋለሁ።+

26 እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤+

ደግሞም ድንቅ ነገሮችን ያደረገላችሁን

የአምላካችሁን የይሖዋን ስም ታወድሳላችሁ፤+

ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አያፍርም።+

27 እናንተም እኔ በእስራኤል መካከል እንደሆንኩ+

እንዲሁም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ እንደሆንኩ፣+ ከእኔም በቀር ሌላ እንደሌለ ታውቃላችሁ!

ሕዝቤ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አያፍርም።

28 ከዚያ በኋላ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤+

ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤

ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ፤

ወጣቶቻችሁም ራእዮችን ያያሉ።+

29 በዚያ ቀን በወንዶች ባሪያዎቼና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ሳይቀር

መንፈሴን አፈሳለሁ።

30 በሰማያትና በምድር ድንቅ ነገሮች አሳያለሁ፤*

ደም፣ እሳትና የጭስ ዓምድ ይታያል።+

31 ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን+ ከመምጣቱ በፊት

ፀሐይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።+

32 የይሖዋን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤+

ይሖዋ እንደተናገረው በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም የሚድኑ+ ይኸውም

ይሖዋ የሚጠራቸው ከጥፋት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ።”

3 “እነሆ፣ በዚያ ዘመንና በዚያ ጊዜ

የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምርኮኞች ስመልስ፣+

 2 ብሔራትን ሁሉ ሰብስቤ

ወደ ኢዮሳፍጥ* ሸለቆ* አወርዳቸዋለሁ።

ለሕዝቤና ርስቴ ለሆነው ለእስራኤል ስል

በዚያ ከእነሱ ጋር እፋረዳለሁ፤+

በብሔራት መካከል በትነዋቸዋልና፤

ደግሞም ምድሬን ተከፋፍለዋታል።+

 3 በሕዝቤ ላይ ዕጣ ይጣጣላሉና፤+

ዝሙት አዳሪ ለማግኘት ሲሉ ወንድ ልጅን አሳልፈው ይሰጣሉ፤

የወይን ጠጅ ለመጠጣት ሲሉም ሴት ልጅን ይሸጣሉ።

 4 ጢሮስ፣ ሲዶና እና የፍልስጤም ግዛቶች ሁሉ፣

ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ?

ላደረግኩባችሁ ነገር ብድራት ልትመልሱልኝ ነው?

ብድራት የምትመልሱልኝ ከሆነ

ብድራታችሁን ወዲያውኑ፣ በፍጥነት በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ።+

 5 ምክንያቱም እናንተ ብሬንና ወርቄን ወስዳችኋል፤+

እጅግ ምርጥ የሆነውን ውድ ንብረቴንም ወደ ቤተ መቅደሶቻችሁ አስገብታችኋል፤

 6 ደግሞም ከምድራቸው ርቀው እንዲሄዱ ለማድረግ ስትሉ

የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ለግሪኮች ሸጣችሁ፤+

 7 እነሆ፣ እነሱን ከሸጣችሁባቸው ቦታዎች እንዲመለሱ አነሳሳቸዋለሁ፤+

ብድራታችሁንም በራሳችሁ ላይ እመልሳለሁ።

 8 ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ለይሁዳ ሕዝብ እሸጣለሁ፤+

እነሱም በሩቅ ላለ ብሔር ይኸውም ለሳባ ሰዎች ይሸጧቸዋል፤

ይሖዋ ራሱ ይህን ተናግሯልና።

 9 በብሔራት መካከል ይህን አውጁ፦+

‘ለጦርነት ተዘጋጁ!* ኃያላን ሰዎችን አነሳሱ!

ወታደሮቹ ሁሉ ቀርበው ጥቃት ይሰንዝሩ!+

10 ማረሻችሁን ሰይፍ፣ ማጭዳችሁንም ጦር ለማድረግ ቀጥቅጡ።

ደካማው ሰው “እኔ ብርቱ ነኝ” ይበል።

11 እናንተ ዙሪያውን ያላችሁ ብሔራት ሁሉ፣ ኑና ተረዳዱ፤ አንድ ላይም ተሰብሰቡ!’”+

ይሖዋ ሆይ፣ ኃያላንህን* ወደዚያ ቦታ አውርድ።

12 “ብሔራት ይነሱና ወደ ኢዮሳፍጥ ሸለቆ* ይምጡ፤

ዙሪያውን ባሉት ብሔራት ሁሉ ላይ ለመፍረድ በዚያ እቀመጣለሁና።+

13 መከሩ ስለደረሰ ማጭድ ስደዱ።

የወይን መጭመቂያው ስለሞላ ኑ፣ ወርዳችሁ እርገጡ።+

ማጠራቀሚያዎቹ ሞልተው አፍስሰዋል፤ ክፋታቸው እጅግ በዝቷልና።

14 ብዙ ሕዝብ፣ በጣም ብዙ ሕዝብ የፍርድ ውሳኔ በሚሰጥበት ሸለቆ* ተሰብስቧል፤

የፍርድ ውሳኔ በሚሰጥበት ሸለቆ* የይሖዋ ቀን ቀርቧልና።+

15 ፀሐይና ጨረቃ ይጨልማሉ፤

ከዋክብትም ብርሃናቸውን አይሰጡም።

16 ይሖዋም ከጽዮን እንደ አንበሳ ያገሳል፤

ከኢየሩሳሌም ድምፁን በኃይል ያሰማል።

ሰማይና ምድር ይናወጣሉ፤

ይሖዋ ግን ለሕዝቡ መጠጊያ፣+

ለእስራኤል ሕዝብ ምሽግ ይሆናል።

17 እናንተም እኔ በተቀደሰው ተራራዬ+ በጽዮን የምኖር አምላካችሁ ይሖዋ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ።

ኢየሩሳሌም ቅዱስ ስፍራ ትሆናለች፤+

እንግዶችም* ከእንግዲህ በእሷ አያልፉም።+

18 በዚያ ቀን ተራሮቹ ጣፋጭ የወይን ጠጅ ያንጠባጥባሉ፤+

ኮረብቶቹ ወተት ያፈሳሉ፤

የይሁዳ ጅረቶችም ሁሉ በውኃ ይሞላሉ።

ከይሖዋም ቤት ምንጭ ይፈልቃል፤+

የሺቲምንም* ሸለቆ* ያጠጣል።

19 ግብፅ ግን ባድማ ትሆናለች፤+

ኤዶምም በምድራቸው ንጹሕ ደም በማፍሰስ+

በይሁዳ ሕዝብ ላይ ግፍ ስለፈጸመች+

ጠፍ ምድረ በዳ ትሆናለች።+

20 ይሁንና ይሁዳ ምንጊዜም፣

ኢየሩሳሌምም ከትውልድ እስከ ትውልድ የሰው መኖሪያ ትሆናለች።+

21 ንጹሕ አድርጌ ያልቆጠርኩትን ደማቸውን* ንጹሕ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፤+

ይሖዋም በጽዮን ይኖራል።”+

“ይሖዋ አምላክ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “የምድሪቱም።”

ወይም “ባሏ።”

ወይም “ወጣት ሴት።”

ቃል በቃል “ታጠቁ።”

ወይም “ደረታችሁን ምቱ።”

ቃል በቃል “ጾምን ቀድሱ።”

“የደረቁት በለሶች” ማለትም ሊሆን ይችላል።

ከጎተራ አነስ ያለ የእህል ማስቀመጫ።

ወይም “የምድሪቱ።”

ወይም “በተወንጫፊ መሣሪያዎች።”

ወይም “ቸርና።”

ወይም “ሊያመጣ ባሰበውም ጥፋት ይጸጸታል።”

ወይም “በመጸጸት።”

ቃል በቃል “ጾምን ቀድሱ።”

ሙት ባሕርን ያመለክታል።

ሜድትራንያን ባሕርን ያመለክታል።

ወይም “ምልክቶች አሳያለሁ።”

“ይሖዋ ፈራጅ ነው” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ቃል በቃል “ጦርነትን ቀድሱ!”

ወይም “ይሖዋ ሆይ፣ ተዋጊዎችህን።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”

ወይም “ባዕዳንም።”

“የግራር ዛፎች” የሚል ትርጉም አለው።

ወይም “ደረቅ ወንዝ።”

ወይም “የደም ዕዳቸውን።”

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ