ምዕራፍ 25
አምላክ ለእኛ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ሕይወት “አጭርና በመከራ የተሞላ” እንደሆነ ይናገራል። (ኢዮብ 14:1) በእርግጥ አምላክ የፈጠረን እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ነው? ካልሆነስ አምላክ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ነው? አምላክ በሚፈልገው መንገድ የምንኖርበት ጊዜስ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ማወቅህ ያጽናናሃል።
1. ይሖዋ የሚፈልገው ምን ዓይነት ሕይወት እንድንኖር ነው?
ይሖዋ አስደሳች ሕይወት እንድንኖር ይፈልጋል። የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ በኋላ ኤደን ገነት ተብሎ በሚጠራ ውብ የአትክልት ቦታ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። ከዚያም “አምላክ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፦ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም።’” (ዘፍጥረት 1:28) ይሖዋ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱ፣ መላዋን ምድር ገነት እንዲያደርጉና እንስሳቱን እንዲንከባከቡ ይፈልግ ነበር። ዓላማው ሁሉም ሰዎች ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር።
በዛሬው ጊዜ ያለን ሕይወት ከዚህ የተለየ ቢሆንምa የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። (ኢሳይያስ 46:10, 11) አሁንም ቢሆን ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ከችግር ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል።—ራእይ 21:3, 4ን አንብብ።
2. በዛሬው ጊዜ አስደሳች ሕይወት መምራት የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ የፈጠረን ‘መንፈሳዊ ፍላጎት’ ማለትም እሱን የማወቅና የማምለክ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። (ማቴዎስ 5:3-6ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድንመሠርት፣ ‘በመንገዶቹ ሁሉ እንድንሄድ፣ እንድንወደው’ እንዲሁም ‘በሙሉ ልባችን እንድናገለግለው’ ይፈልጋል። (ዘዳግም 10:12፤ መዝሙር 25:14) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን። ይሖዋን ማምለክ ሕይወታችን ትርጉም ያለውና አስደሳች እንዲሆንልን ያደርጋል።
ጠለቅ ያለ ጥናት
ይሖዋ ምድርን ለእኛ ምቹ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ ያዘጋጀበት መንገድ ታላቅ ፍቅሩን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፤ በተጨማሪም የአምላክ ቃል ስለተፈጠርንበት ዓላማ ምን እንደሚል እንመረምራለን።
3. ይሖዋ ሰዎች ደስተኛ ሆነው እንዲኖሩ ይፈልጋል
ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
አምላክ ውብ የሆነችውን ምድራችንን የፈጠረው ለምንድን ነው?
መክብብ 3:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይህ ጥቅስ ይሖዋ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ ምን ያስተምርሃል?
4. የይሖዋ ዓላማ አልተለወጠም
መዝሙር 37:11, 29ን እንዲሁም ኢሳይያስ 55:11ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ለእኛ ያለው ዓላማ እንዳልተለወጠ በምን እናውቃለን?
በአግባቡ ባለመያዙ ምክንያት የፈራረሰ ቤት መልሶ ሊታደስ እንደሚችል ሁሉ አምላክም የሰው ዘር ያበላሻትን ምድር መልሶ ያድሳታል። ከዚያም እሱን የሚወዱ ሰዎች በምድር ላይ እንዲኖሩ ያደርጋል
5. ይሖዋን ማምለካችን ዓላማ ያለው ሕይወት እንድንመራ ያስችለናል
የተፈጠርንበትን ዓላማ ማወቃችን ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል። ቪዲዮውን ተመልከቱ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ቴሩሚ የተፈጠርንበትን ዓላማ ማወቋ የጠቀማት እንዴት ነው?
መክብብ 12:13ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦
ይሖዋ ብዙ ነገሮችን አድርጎልናል፤ ታዲያ እኛ በምላሹ ምን ልናደርግ ይገባል?
አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢጠይቅህስ? “የተፈጠርንበት ዓላማ ምንድን ነው?”
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ማጠቃለያ
ይሖዋ ከማንኛውም ችግር ነፃ ሆነን በምድር ላይ ለዘላለም እንድንኖር ይፈልጋል። በሙሉ ልባችን እሱን ስናመልከው በዛሬው ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት መምራት እንችላለን።
ክለሳ
ይሖዋ አዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ሕይወት እንዲኖሩ ይፈልግ ነበር?
አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ እንዳልተለወጠ በምን እናውቃለን?
ሕይወትህ አስደሳችና ትርጉም ያለው እንዲሆን ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
ምርምር አድርግ
ምድር እንደማትጠፋ እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርገን ምክንያት ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለተፈጠርንበት ዓላማ ምን ይላል?
ሁሉ ነገር እንዳለው ያስብ የነበረ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የጎደለው ነገር እንዳለ ያወቀው እንዴት ነው?
a ይህ የሆነበትን ምክንያት በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።