የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ijwbq ርዕስ 166
  • ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው?
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ ምን ያስተምራል?
  • መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ፍቅርን በተመለከተ የሚያስጠነቅቀን ለምንድን ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ የሚሰጠው ምክር ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራና ስለ ገንዘብ ምን ይላል?
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ijwbq ርዕስ 166
አንድ ሰው ገንዘብ ለማፈስ ሲሞክር።

ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብ መጥፎ ነገር እንደሆነ አይገልጽም፤ ገንዘብ የክፉ ነገሮች ሁሉ መንስኤ እንደሆነም አይናገርም። ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተወሰደ የሚነገርለት “ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው” የሚለው የተለመደ አባባል የጥቅሱን የተሟላ ሐሳብ ያልያዘና የተሳሳተ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው። ትክክለኛው የጥቅሱ ሐሳብ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነው”a የሚል ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:10 የ1954 ትርጉም፤ ጎላ አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ ምን ያስተምራል?

  • መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ፍቅርን በተመለከተ የሚያስጠነቅቀን ለምንድን ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ የሚሰጠው ምክር ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

  • ስለ ገንዘብ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ ምን ያስተምራል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብን በጥበብ እስከተጠቀምንበት ድረስ ሊጠቅመን እንደሚችል እንዲያውም “ጥበቃ” እንደሚያስገኝልን ይገልጻል። (መክብብ 7:12) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገንዘብን ጨምሮ ያላቸውን ነገር ለሌሎች በልግስና የሚሰጡ ሰዎችን ያመሰግናል።—ምሳሌ 11:25

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሕይወታችን ውስጥ ለገንዘብ ትልቅ ቦታ እንዳንሰጥ ያስጠነቅቃል። “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ” ይላል። (ዕብራውያን 13:5) ይህ ጥቅስ ለገንዘብ ከተገቢው ያለፈ ቦታ እንዳንሰጥና ሀብት በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት እንዳንመራ ያሳስበናል። እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን በማግኘት ረክተን መኖር ይገባናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:8

መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ፍቅርን በተመለከተ የሚያስጠነቅቀን ለምንድን ነው?

ስግብግብ ሰዎች የዘላለም ሕይወት አያገኙም። (ኤፌሶን 5:5) ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ ስግብግብነት የጣዖት አምልኮ መሆኑ ነው። (ቆላስይስ 3:5) ሁለተኛ፣ ስግብግብ ሰዎች የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ብዙውን ጊዜ መልካም የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ይጥሳሉ። ምሳሌ 28:20 “ሀብት ለማግኘት የሚጣደፍ [ሰው] ንጽሕናውን ማጉደፉ አይቀርም” ይላል። እንዲህ ያለ ሰው አስፈራርቶ ገንዘብ እንደ መቀበል፣ ዝርፊያ፣ ማጭበርበር፣ አፈና ወይም ነፍስ ግድያ ያሉ ወንጀሎችን ለመፈጸም ሊፈተን ይችላል።

አንድ ሰው በገንዘብ ፍቅር የተነሳ መጥፎ ድርጊት ባይፈጽምም እንኳ ሌሎች ጉዳቶች ሊደርሱበት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ ግን ፈተናና ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ፤ እንዲሁም . . . ከንቱና ጎጂ በሆኑ ብዙ ምኞቶች ይያዛሉ” ይላል።—1 ጢሞቴዎስ 6:9

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገንዘብ የሚሰጠው ምክር ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

ለገንዘብ ስንል ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ እሴቶቻችንን የማንጥስ ከሆነ ለራሳችን አክብሮት ይኖረናል፤ የአምላክን ሞገስና ድጋፍም እናገኛለን። አምላክ፣ እሱን ለማስደሰት ከልቡ የሚጥርን ሰው በተመለከተ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል ገብቷል። (ዕብራውያን 13:5, 6) በተጨማሪም “ታማኝ ሰው ብዙ በረከት ያገኛል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል።—ምሳሌ 28:20

ስለ ገንዘብ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

መክብብ 7:12፦ “ገንዘብ ጥበቃ [ያስገኛል]።”

ትርጉሙ፦ ገንዘብን በጥበብ እስከተጠቀምንበት ድረስ ሊጠቅመን ይችላል፤ ምክንያቱም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የደኅንነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።

ሉቃስ 12:15፦ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም።”

ትርጉሙ፦ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊው ነገር ገንዘብ አይደለም፤ እንዲሁም ገንዘብ መዳን አያስገኝልንም።

1 ጢሞቴዎስ 6:10፦ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነውና፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተሸንፈው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”

ትርጉሙ፦ ገንዘብ በራሱ መጥፎ ነገር አይደለም። ሆኖም ገንዘብን የሚወዱ ይኸውም በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ ለገንዘብ የሚሰጡ ሰዎች በራሳቸው ላይ ችግሮች ያመጣሉ፤ ከእነዚህ ችግሮች መካከል የቤተሰብ መፍረስ እንዲሁም ከልክ በላይ በመሥራት የሚመጣ የጤና መቃወስ ይገኙበታል።

ዕብራውያን 13:5፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።”

ትርጉሙ፦ ሀብት ለማግኘት ስንል ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ከማድረግ ይልቅ በሚያስፈልጉን መሠረታዊ ነገሮች ረክተን መኖራችን ብልህነት ነው።

ማቴዎስ 19:24፦ “ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”

ትርጉሙ፦ ኢየሱስ ይህን ሐሳብ ከመናገሩ በፊት ለአንድ ሀብታም ወጣት እሱን እንዲከተለው ግብዣ አቅርቦለት ነበር። ወጣቱ ግን ንብረቱን በጣም ይወድ ስለነበር ግብዣውን አልተቀበለም። ስለዚህ ኢየሱስ ይህን ማስጠንቀቂያ ሰጠ። ለሀብት ከአምላክ የበለጠ ቦታ የሚሰጥ ሰው የዘላለም ሕይወት ሊያጣ ይችላል።

a ጥቅሱ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው” ተብሎም ተተርጉሟል።

    የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ ጽሑፎች (2011-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • የኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ