ዓርብ፣ ነሐሴ 1
የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።—መዝ. 34:19
በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ልብ በል። (1) ጻድቅ የሆኑ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። (2) ይሖዋ ከሚያጋጥመን መከራ ይታደገናል። ይሖዋ የሚታደገን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለንን ሕይወት በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን በመርዳት ነው። ይሖዋ እሱን በማገልገል ደስታ እንደምናገኝ ቃል ቢገባልንም በአሁኑ ዘመን ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምንመራ ዋስትና አልሰጠንም። (ኢሳ. 66:14) እሱ እንድንኖር የሚፈልገውን ሕይወት ለዘላለም በምናጣጥምበት በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) እስከዚያው ግን ለእያንዳንዱ ቀን የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። (ሰቆ. 3:22-24) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ በዘመናችን የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሁላችንም ያልተጠበቁ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ ከታመንን እሱ ምንጊዜም ይደግፈናል።—መዝ. 55:22፤ w23.04 14-15 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2
ለበላይ ባለሥልጣናት [ተገዙ]።—ሮም 13:1
አመቺ ባልሆነ ጊዜ ጭምር ለበላይ ባለሥልጣናት በመታዘዝ ረገድ ከዮሴፍና ከማርያም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 2:1-6) ማርያም የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሳለች እሷና ዮሴፍ የታዛዥነት ፈተና አጋጠማቸው። የሮም ገዢ የሆነው አውግስጦስ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዘዘ። ማርያምና ዮሴፍ ዳገት ቁልቁለት አቋርጠው 150 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ቤተልሔም መሄድ ነበረባቸው። ይህ ጉዞ በተለይ ለማርያም የሚያንገላታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የማርያምና የፅንሱ ደህንነት አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል። መንገድ ላይ ሳለች ምጧ ቢመጣስ? በማህፀኗ የተሸከመችው ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ነው። እነዚህ ነገሮች መንግሥትን ላለመታዘዝ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ? ዮሴፍና ማርያም እነዚህ ምክንያቶች የመንግሥትን ሕግ ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲሉ እንዲያደርጓቸው አልፈቀዱም። ይሖዋም ለታዛዥነታቸው ባርኳቸዋል። ማርያም ወደ ቤተልሔም በሰላም ደረሰች። በዚያም ጤናማ ልጅ ተገላገለች። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጋለች።—ሚክ. 5:2፤ w23.10 8 አን. 9፤ 9 አን. 11-12
እሁድ፣ ነሐሴ 3
እርስ በርስ እንበረታታ።—ዕብ. 10:25
በስብሰባ ላይ ሐሳብ ስለመስጠት ስታስቡ እንኳ በጣም የሚያስፈራችሁ ከሆነስ? በደንብ መዘጋጀታችሁ ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 21:5) ትምህርቱን ከራሳችሁ ጋር ይበልጥ ባዋሃዳችሁት መጠን ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ይቀላችኋል። በተጨማሪም አጭር መልስ ለመመለስ ሞክሩ። (ምሳሌ 15:23፤ 17:27) መልሳችሁ አጭር ከሆነ ያን ያህል አያስፈራችሁም። በራሳችሁ አባባል አጭር መልስ መመለሳችሁ በደንብ እንደተዘጋጃችሁና ትምህርቱን በሚገባ እንደተረዳችሁት ያሳያል። እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ብታደርጉም ከአንዴ ወይም ከሁለቴ በላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈራችሁ ቢሆንስ? አቅማችሁ የፈቀደውን ነገር ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ ሁኑ። (ሉቃስ 21:1-4) ምርጣችንን መስጠት ማለት ከአቅማችን በላይ መጣጣር ማለት አይደለም። (ፊልጵ. 4:5) ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ፤ ግብ አውጡ፤ እንዲሁም መረጋጋት እንድትችሉ ጸልዩ። መጀመሪያ ላይ፣ አንድ አጭር መልስ ብቻ ለመመለስ ግብ ማውጣታችሁ በቂ ሊሆን ይችላል። w23.04 21 አን. 6-8