ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2
ለበላይ ባለሥልጣናት [ተገዙ]።—ሮም 13:1
አመቺ ባልሆነ ጊዜ ጭምር ለበላይ ባለሥልጣናት በመታዘዝ ረገድ ከዮሴፍና ከማርያም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 2:1-6) ማርያም የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሳለች እሷና ዮሴፍ የታዛዥነት ፈተና አጋጠማቸው። የሮም ገዢ የሆነው አውግስጦስ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዘዘ። ማርያምና ዮሴፍ ዳገት ቁልቁለት አቋርጠው 150 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ቤተልሔም መሄድ ነበረባቸው። ይህ ጉዞ በተለይ ለማርያም የሚያንገላታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የማርያምና የፅንሱ ደህንነት አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል። መንገድ ላይ ሳለች ምጧ ቢመጣስ? በማህፀኗ የተሸከመችው ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ነው። እነዚህ ነገሮች መንግሥትን ላለመታዘዝ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ? ዮሴፍና ማርያም እነዚህ ምክንያቶች የመንግሥትን ሕግ ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲሉ እንዲያደርጓቸው አልፈቀዱም። ይሖዋም ለታዛዥነታቸው ባርኳቸዋል። ማርያም ወደ ቤተልሔም በሰላም ደረሰች። በዚያም ጤናማ ልጅ ተገላገለች። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጋለች።—ሚክ. 5:2፤ w23.10 8 አን. 9፤ 9 አን. 11-12
እሁድ፣ ነሐሴ 3
እርስ በርስ እንበረታታ።—ዕብ. 10:25
በስብሰባ ላይ ሐሳብ ስለመስጠት ስታስቡ እንኳ በጣም የሚያስፈራችሁ ከሆነስ? በደንብ መዘጋጀታችሁ ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 21:5) ትምህርቱን ከራሳችሁ ጋር ይበልጥ ባዋሃዳችሁት መጠን ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ይቀላችኋል። በተጨማሪም አጭር መልስ ለመመለስ ሞክሩ። (ምሳሌ 15:23፤ 17:27) መልሳችሁ አጭር ከሆነ ያን ያህል አያስፈራችሁም። በራሳችሁ አባባል አጭር መልስ መመለሳችሁ በደንብ እንደተዘጋጃችሁና ትምህርቱን በሚገባ እንደተረዳችሁት ያሳያል። እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ብታደርጉም ከአንዴ ወይም ከሁለቴ በላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈራችሁ ቢሆንስ? አቅማችሁ የፈቀደውን ነገር ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ ሁኑ። (ሉቃስ 21:1-4) ምርጣችንን መስጠት ማለት ከአቅማችን በላይ መጣጣር ማለት አይደለም። (ፊልጵ. 4:5) ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ፤ ግብ አውጡ፤ እንዲሁም መረጋጋት እንድትችሉ ጸልዩ። መጀመሪያ ላይ፣ አንድ አጭር መልስ ብቻ ለመመለስ ግብ ማውጣታችሁ በቂ ሊሆን ይችላል። w23.04 21 አን. 6-8
ሰኞ፣ ነሐሴ 4
ጥሩር እንልበስ፤ . . . ራስ ቁር እንድፋ።—1 ተሰ. 5:8
ሐዋርያው ጳውሎስ ዝግጁ ከሆኑና የጦር ትጥቅ ከለበሱ ወታደሮች ጋር አመሳስሎናል። አንድ ወታደር በማንኛውም ጊዜ ለጦርነት ዝግጁ እንዲሆን ይጠበቅበታል። የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር በመልበስ እንዲሁም ተስፋን እንደ ራስ ቁር በመድፋት የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ እንችላለን። ጥሩር የአንድን ወታደር ልብ ከጉዳት ይጠብቅለታል። እምነትና ፍቅርም ምሳሌያዊ ልባችንን ይጠብቁልናል። አምላክን ማገልገላችንንና ኢየሱስን መከተላችንን እንድንቀጥል ይረዱናል። እምነት ካለን ይሖዋ እሱን በሙሉ ልባችን በመፈለጋችን ወሮታ እንደሚከፍለን እርግጠኞች እንሆናለን። (ዕብ. 11:6) እምነት፣ መከራ ቢደርስብንም እንኳ ለመሪያችን ለኢየሱስ ምንጊዜም ታማኝ እንድንሆን ያነሳሳናል። ስደት ወይም የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥማቸውም ንጹሕ አቋማቸውን ከጠበቁ በዘመናችን ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በመማር የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል እምነት መገንባት እንችላለን። በተጨማሪም መንግሥቱን ለማስቀደም ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ያደረጉ ክርስቲያኖችን ምሳሌ በመከተል ከፍቅረ ነዋይ ወጥመድ መራቅ እንችላለን። w23.06 10 አን. 8-9