ሰኞ፣ ነሐሴ 4
ጥሩር እንልበስ፤ . . . ራስ ቁር እንድፋ።—1 ተሰ. 5:8
ሐዋርያው ጳውሎስ ዝግጁ ከሆኑና የጦር ትጥቅ ከለበሱ ወታደሮች ጋር አመሳስሎናል። አንድ ወታደር በማንኛውም ጊዜ ለጦርነት ዝግጁ እንዲሆን ይጠበቅበታል። የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር በመልበስ እንዲሁም ተስፋን እንደ ራስ ቁር በመድፋት የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ እንችላለን። ጥሩር የአንድን ወታደር ልብ ከጉዳት ይጠብቅለታል። እምነትና ፍቅርም ምሳሌያዊ ልባችንን ይጠብቁልናል። አምላክን ማገልገላችንንና ኢየሱስን መከተላችንን እንድንቀጥል ይረዱናል። እምነት ካለን ይሖዋ እሱን በሙሉ ልባችን በመፈለጋችን ወሮታ እንደሚከፍለን እርግጠኞች እንሆናለን። (ዕብ. 11:6) እምነት፣ መከራ ቢደርስብንም እንኳ ለመሪያችን ለኢየሱስ ምንጊዜም ታማኝ እንድንሆን ያነሳሳናል። ስደት ወይም የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥማቸውም ንጹሕ አቋማቸውን ከጠበቁ በዘመናችን ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በመማር የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል እምነት መገንባት እንችላለን። በተጨማሪም መንግሥቱን ለማስቀደም ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ያደረጉ ክርስቲያኖችን ምሳሌ በመከተል ከፍቅረ ነዋይ ወጥመድ መራቅ እንችላለን። w23.06 10 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 5
ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም።—መክ. 11:4
ራስን መግዛት፣ ስሜትንና ድርጊትን የመቆጣጠር ችሎታ ነው። ግባችን ላይ ለመድረስ ራስን መግዛት ያስፈልገናል። በተለይ እዚያ ግብ ላይ መድረስ ከባድ ከሆነ ወይም ተነሳሽነት ካጣን ራሳችንን መግዛታችን አስፈላጊ ነው። ራስን መግዛት የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ አትዘንጋ። በመሆኑም ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ማዳበር እንድትችል መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው። (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከሉ አትጠብቅ። በዚህ ዓለም ውስጥ ሁሉ ነገር ሊስተካከልልን እንደማይችል የታወቀ ነው። ሁሉ ነገር እስኪስተካከል ከጠበቅን ግባችን ላይ ፈጽሞ ላንደርስ እንችላለን። ግባችን ላይ መድረስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ከተሰማን ተነሳሽነታችን ሊጠፋ ይችላል። የአንተም ሁኔታ እንደዚያ ከሆነ ግብህን በትንሽ በትንሹ ልትከፋፍለው ትችል ይሆን? ለምሳሌ ግብህ አንድ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር ከሆነ መጀመሪያ ላይ ይህን ባሕርይ በትናንሽ መንገዶች ለማንጸባረቅ ለምን አትሞክርም? ግብህ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መጨረስ ከሆነ ደግሞ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በማንበብ ለምን አትጀምርም? w23.05 29 አን. 11-13
ረቡዕ፣ ነሐሴ 6
የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።—ምሳሌ 4:18
በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ድርጅቱን በመጠቀም ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ሁላችንም መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚረዳ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ እያቀረበልን ነው። (ኢሳ. 35:8፤ 48:17፤ 60:17) አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ለመጓዝ አጋጣሚ ተከፈተለት ሊባል ይችላል። አንዳንዶች ጥቂት መንገድ ብቻ ተጉዘው ከአውራ ጎዳናው ይወጣሉ። ሌሎች ደግሞ እስከ መዳረሻቸው ድረስ ከመንገዱ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ይሁንና መዳረሻቸው የት ነው? “የቅድስና ጎዳና” ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች በሰማይ ወዳለው ‘የአምላክ ገነት’ ይወስዳቸዋል። (ራእይ 2:7) ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች ደግሞ ሁሉም ሰው ፍጹም ወደሚሆንበት የክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ያደርሳቸዋል። በዚህ አውራ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምረህ ከሆነ እባክህ ወደ ኋላ አትመልከት። በተጨማሪም አዲሱ ዓለም ውስጥ እስክትገባ ድረስ ከዚህ መንገድ አትውጣ። w23.05 17 አን. 15፤ 19 አን. 16-18