የሃይማኖት የወደፊት ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንፃር ሲታይ
ክፍል 18:- ከ15ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ—“ክርስቲያኖች” ከ“አረማውያን” ጋር በተገናኙ ጊዜ
“የሃይማኖት ማደሪያ ልብ እንጂ ጉልበት አይደለም”—ዲ ደብልዩ ጀሮልድ፣ የ19ኛው መቶ ዘመን ጸሐፊ ተውኔት
የጥንቱ ክርስትና መለያ ባሕርይ የሆነው የሚስዮናዊነት ሥራ ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘አሕዛብን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና’ ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ’ ምሥክሮቹ እንዲሆኑ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ያስችላል።— ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8
ሕዝበ ክርስትና በ15ኛው መቶ ዘመን “አረማውያንን” ወደ ክርስትና ለመለወጥ መላውን ምድር ያቀፈ እንቅስቃሴ ጀመረች። እነዚህ “አረማውያን” እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንዴት ባለ ሃይማኖት ይመላለሱ ነበር? ወደ “ክርስትና” በተለወጡ ጊዜስ ልባቸው በአዲሱ እምነት ተነክቷል ወይስ ይህን እምነት እንደተቀበሉ ለማስመሰል ብቻ በጉልበታቸው ተንበረከኩ?
በአፍሪካ ውስጥ ከሳሃራ በስተ ደቡብ በሚገኙት አገሮች 700 የሚደርሱ የተለያዩ ጎሣዎች እንዳሉ ይገመታል። እነዚህ ጎሣዎች በሙሉ የየራሳቸው ሃይማኖት ነበራቸው። እርግጥ፣ ሁሉም ከአንድ ምንጭ የተገኙ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መመሳሰል አላቸው። በአውስትራሊያ፣ በአሜሪካ አገሮችና በፓስፊክ ደሴቶች በደርዘን የሚቆጠሩ የጎሣ ሃይማኖቶች ይገኛሉ።
አብዛኞቹ ከሁሉ በላይ የሆነ አንድ አምላክ እንዳለ ቢያምኑም ቁጥራቸው የበዛ የቤተሰብ፣ የነገድ ወይም የማኅበረሰብ አማልክት እንዳሉ ያምናሉ። ስለ አዝቴኮች ሃይማኖት የተደረገ አንድ ጥናት 60 የሚያክሉ የተለያዩና እርስ በርሳቸው የተዛመዱ አማልክትን ስሞች ዘርዝሯል።
በአፍሪካና በአሜሪካ አገሮች “እጅግ ኋላ ቀር” የሆኑ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሕዝቦች ትሪክስተር በተባለ ከሁሉ በላይ የሆነ አካል ያምናሉ። ይህ አንዳንድ ጊዜ የጠፈር አካላት ፈጣሪ፣ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የፍጥረት አደራጅ እንደሆነ የሚነገርለት አምላክ ሌሎችን በመጉዳት የሚደሰት ባይሆንም ሁልጊዜ መሰሪና አታላይ እንደሆነና እጅግ ከፍተኛ የሆነ የፍትወት ስሜት እንዳለው ይታመናል። የሰሜን አሜሪካ ናቫሆ ሕንዶች ሞትን ያመጣ እርሱ እንደሆነ፣ የኦግላላ ላኮታ ነገዶች ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በሌላ ሥፍራ የተሻለ ሕይወት እንደሚያገኙ በመናገር ከገነት እንዲባረሩ ያደረገ አንድ ዓመፀኛ መልአክ እንደሆነ ያስተምራሉ። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን የተባለው መጽሐፍ ትሪክስተር “ስለ ፍጥረት በሚነገሩ አፈታሪኮች ሁሉ መንፈሳዊ የሆነው ፈጣሪ አምላክ ተቃራኒ እንደሆነ ይነገራል” ይላል።
አንዳንድ የጎሣ ሃይማኖቶች እንደ ባቢሎንና ግብጽ ሃይማኖቶች በሥላሴ ያምናሉ። ዘ ኤስኪሞስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው የአየር መንፈስ፣ የባሕር መንፈስና የጨረቃ መንፈስ አንድ ላይ ተዋህደው ሥላሴ ከሆኑ በኋላ “በኤስኪሞዎች ሕይወት ዙሪያ ያሉትን ነገሮች በሙሉ ይቆጣጠራሉ።”
“ሊጠፋ የማይችል መንፈሳዊ ባሕርይ” ያላቸው የሰው ልጆች
የምዕራብ አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ሮናልድ ኤም በርንት የአውስትራሊያ አቦርጅኖች የሕይወት ኡደት “ከግዑዝነት ወደ መንፈሳዊነት፣ ከመንፈሳዊነት ደግሞ ወደ ግዑዝነት እየተለዋወጠ ከሞት በኋላ ሳያቋርጥ እንደሚቀጥል” ያምናሉ ብለዋል። ይህ ማለት “የሰው ልጆች ሊጠፋ የማይችል መንፈሳዊ ባሕርይ አላቸው” ማለት ነው።
አንዳንድ የአፍሪካ ጎሣዎች ተራ ሰዎች ከሞቱ በኋላ መናፍስት ሲሆኑ እውቅ የሆኑ ታላላቅ ሰዎች ደግሞ ሲሞቱ የማይታዩ የማኅበረሰብ መሪዎች ስለሚሆኑ ክብርና ልመና ሊቀርብላቸው የሚገቡ የአባቶች መናፍስት እንደሚሆኑ ያምናሉ። ማነስ ኦቭ መላኔዥያ እንደሚለው የቅርብ ዘመድ የሆነ ሰው መንፈስ ቤተሰቡን መቆጣጠሩን ይቀጥላል።
አንዳንድ የአሜሪካ ሕንዶች የነፍሳት ቁጥር የተወሰነ ስለሆነ “በመጀመሪያ በሰብዓዊ አካል ውስጥ በኋላም በመንፈሳዊ ወይም በእንስሳ አካል ውስጥ ለማደር ይገደዳሉ” ብለው ያምናሉ። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ ይህንኑ ሲያብራራ “አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ነጻ ወጥታ ወደ እንስሳ አካል ትገባለች ወይም መንፈስ ትሆናለች። በዚህ መንገድ ሰዎች፣ እንስሳትና መናፍስት እርስ በርሳቸው በሚደጋገፉበት ኡደት ውስጥ ይገባሉ” ይላል።
በዚህ ምክንያት ቀደም ያሉ አሳሾች የኤስኪሞ ወላጆች ልጆቻቸውን እንደማይቀጡና እንዲያውም “እናቴ” ወይም “አያቴ” ብለው ሲጠሩ በመመልከታቸው በጣም ተደንቀዋል። ኧርነስት ኤስ ባሩክ ጁንየር የተባሉ ደራሲ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲያስረዱ ልጅየው የሚጠራው በአያቱ ወይም በቅድመ አያቱ ስም ስለሆነ አንድ የኤስኪሞ አባት “አያቱ ምንም እንኳ አሁን በልጁ አካል ውስጥ ያደረች ብትሆንም እርሷን መቆጣት ወይም መቅጣት ይከብደዋል” ብለዋል።
የሰሜን አሜሪካ ሕንድ ጎሣዎች “መጪው ዓለም” ሰዎችም ሆነ እንስሳት ከሞቱ በኋላ የሚሄዱበት አስደሳች የአደን ቦታ እንደሆነ ይገልጻሉ። በዚህ ዓለም ይወዷቸው ከነበሩ ዘመዶቻቸውና ከቀድሞ ጠላቶቻቸው ጋር ይገናኛሉ። አንዳንድ ሕንዶች ጠላቶቻቸው ወደ መንፈሳዊ ዓለም እንዳይገቡ ያግዳቸዋል ብለው ያምኑ ስለነበረ ጠላቶቻቸውን ከገደሉ በኋላ ቆዳቸውን ይገፍፉ ነበር።
ታዲያ በርካታ የጥንት ጎሣዊ ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ የሚኖር ሕይወት አለ ብለው ማመናቸው ሕዝበ ክርስትና የሰው ልጆች የማትሞት ነፍስ አላቸው ብላ የምታስተምረው ትምህርት ትክክል መሆኑን ያረጋግጣልን? በፍጹም አያረጋግጥም። እውነተኛው ሃይማኖት በተቆረቆረበት በኤደን አምላክ ለሰዎች ከሞት ተቃራኒ የሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጠ እንጂ ከሞት በኋላ ስለሚኖር ሕይወት አልተናገረም። ሞት ወደተሻለ ሕይወት የሚያስገባ በር ነው የሚለውን ሐሳብ የጠነሰሰው ሰይጣን ሲሆን በኋላም የተስፋፋው ከባቢሎን ነው።
ቅድሚያ የሚሰጠው የሰው ልጆች ፍላጎት ነው ወይስ የአምላክ?
ጎሣዊ ሃይማኖቶች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለግላቸው ወይም ለማኅበረሰባቸው ደህንነት ነበር። በዚህም ምክንያት ሮናልድ በርንት ስለ አውስትራሊያ አቦርጅኖች ሃይማኖት “ሰዎች በዕለታዊ ኑሮአቸው የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ጭንቀቶች ያንጸባርቃል። የሚያተኩረውም በማኅበረሰብ ግንኙነቶች፣ የሰው ልጆች ሕልውና በሚያጋጥሙት ችግሮችና ተግባራዊ በሆኑ የኑሮ ጉዳዮች ላይ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
እንደነዚህ ያሉትን ሰብዓዊ ችግሮች የመቋቋም ዓላማና ግብ ብቻ ያላቸው አኒሚዝም፣ ፈቲሽዝምና ሻማኒዝም በመባል የሚታወቁ የአምልኮ ዓይነቶች በተለያዩ ማኅበረሰቦች በተለያየ ስፋትና መጠን ተስፋፍተው ይገኛሉ።
አኒሚዝም እንደ ዕፀዋትና እንደ ድንጋይ ያሉት ግዑዛን ነገሮች፣ እንደ ምድር መናወጥና መብረቅ የመሰሉት የተፈጥሮ ክስተቶች ሳይቀሩ በውስጣቸው የሚኖር መንፈስ እንዳላቸው ያምናል። በተጨማሪም ከሥጋ የተለዩ መናፍስት እንዳሉና እነዚህም በሕይወት በሚኖሩ ሰዎች ላይ በጎ ወይም መጥፎ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ ያምናል።
ፈቲሽዝም ባለቤታቸውን የመርዳት ወይም የመጠበቅ ምትሐታዊ ኃይል አላቸው የሚባሉ ዕቃዎችን ለመግለጽ ከሚያገለግል የፖርቱጊዝ ቃል የተወሰደ ቃል ነው። ስለዚህ የፖርቱጋል አሳሾች ምዕራብ አፍሪካውያን በሃይማኖታቸው ሲጠቀሙባቸው ያገኟቸውን ክታቦችና የአስማት ዕቃዎች ለመጥራት የተጠቀሙበት ቃል ነበር ማለት ነው። ፈቲሽዝም ከጣዖት አምልኮ ጋር የቀረበ ዝምድና ሲኖረው የተለያዩ መልኮች አሉት። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የአሜሪካ ሕንዶች ላባዎች ጸሎቶችን ወይም መልእክቶችን ወደ ሰማይ የማድረስ ኃይል አላቸው ብለው ስለሚያምኑ ምትሐታዊ ኃይል እንዳላቸው አድርገው ያስባሉ።
ሻማኒዝም ከቱንጉሶ ማንቹሪያ ቃል የተገኘ ስያሜ ሲሆን “አዋቂ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ አምልኮ ሕሙማንን የመፈወስና ከመናፍስት ዓለም ጋር የመገናኘት ችሎታ አለው በሚባለው ሻማን ላይ ያተኩራል። መድኃኒተኛው ወይም አስተማተኛው ወይም የምድር አዋቂው ጤናና የመራባት ኃይል የመስጠት ችሎታ እንዳለው ይናገራል። ሕክምናው የሚሰጠው አንዳንድ በደቡብ አሜሪካ ደኖች የሚኖሩ ጎሣዎች እንደሚያደርጉት ምላስ በመሰንጠቅ፣ አፍንጫ ወይም ጆሮ በመብሳት ወይም ሰውነትን ቀለም በመቀባት ወይም አንዳንድ ጌጦችን በማድረግ ነው። አለበለዚያም እንደ ትንባሆና እንደ ኮካ ቅጠል ያሉትን አደንዛዥ ዕፆች እንድትወስድ ልትጠየቅ ትችላለህ።
የጎሣ ሃይማኖቶች የመሠረተ ትምህርት ድክመት ስላላቸው ስለ ፈጣሪ ማንነት ትክክለኛ እውቀት ለመስጠት አይችሉም። ከመለኮታዊ ፈቃድ ይልቅ ለሰው ልጆች ጉዳዮች ቅድሚያ ስለሚሰጡ አምላክ ከፍጡሮቹ ማግኘት ያለበትን ነገር እንዳያገኝ አድርገዋል። ስለዚህ ሕዝበ ክርስትና ዘመናዊውን የሚስዮናዊነት ሥራ እንቅስቃሴ ስትጀምር “ክርስቲያኖች” “የአረመኔዎችን” ልብ ወደ አምላክ ለመመለስ ይችሉ ይሆን የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር።
በአሥራ አምስተኛው መቶ ዘመን ስፔይንና ፖርቱጋል ምድርን የማሰስና ቅኝ ግዛት የማስፋፋት ፕሮግራም ጀመሩ። እነዚህ ካቶሊክ መንግሥታት አዳዲስ አገሮችን ሲያገኙ ቤተ ክርስቲያን የአገሩ ኗሪዎች አዲሱን “ክርስቲያን” መንግሥት የሚቀበሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ወደ ክርስትና መለወጥ ጀመረች። በካቶሊክ ሊቀ ጳጳሳት ድንጋጌ መሠረት በአፍሪካና በእስያ ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ የማድረግ መብት የተሰጠው ለፖርቱጋል ነበር። በኋላም የአሜሪካ ምድር ከተገኘ በኋላ አሌክሳንደር ስድስተኛ የተባሉ ሊቀ ጳጳስ አትላንቲክን ለሁለት የሚከፍል የግምት መስመር ካሰመሩ በኋላ የምዕራቡን ክፍል ለስፔይን የምሥራቁን ደግሞ ለፖርቱጋል ሰጥተዋል።
በዚህ ጊዜ ፕሮቴስታንቶች ከካቶሊኮች ያገኙትን ነፃነት በማጠናከር ላይ አተኩረው ስለነበረ ሌሎችን ወደ ሃይማኖታቸው ለመለወጥ ብዙም አልሞከሩም ነበር። የሃይማኖታዊ ተሐድሶ መሪዎቻቸውም ቢሆኑ እንዲህ እንዲያደርጉ አላበረታቷቸውም። ሉተርና መላንክተን የዓለም ፍጻሜ በጣም ቀርቧል ብለው ያስቡ ስለነበረ “ለአረማውያን” ለማዳረስ የሚያስችል ጊዜ የለም ብለው ያምኑ ነበር።
ይሁን እንጂ በ17ኛው መቶ ዘመን ፓየትዝም የሚባል የፕሮቴስታንቶች እንቅስቃሴ ተጀመረ። ይህ የተሐድሶ ቅጥያ የሆነ እንቅስቃሴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ሃይማኖትን አጥብቆ ለመያዝ ትልቅ ቦታ ከመስጠቱም በላይ ሃይማኖት ወደ ግለሰቦች ልብ ጠልቆ መግባቱ የተወሰነ የአምልኮ ሥርዓት ከመፈጸም እንደሚበልጥ ያምን ነበር። አንድ ጸሐፊ እንዳሉት “መላው የሰው ልጅ የክርስቶስ ወንጌል እንደሚያስፈልገው መገንዘቡ” የፕሮቴስታንት ሃይማኖት በ18ኛው መቶ ዘመን ሚስዮናዊ እንቅስቃሴ የሚጀምርበትን “መርከብ” እንዲሳፈር አስችሏል።
በመላው ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ቁጥር በ1500 ከዓለም ጠቅላላ ሕዝብ አንድ አምስተኛ ነበር። በ1800 ግን ይህ ቁጥር አድጎ የዓለምን ሕዝብ አንድ አራተኛ ሲያክል በ1900 የዓለምን አንድ ሦስተኛ ሊሆን ችሏል። በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሕዝብ አንድ ሦስተኛ “ክርስቲያን” ነው!
በእርግጥ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት ሊያፈሩ ችለዋልን?
የጎሣ ሃይማኖቶች የነበሯቸው የእውነት ርዝራዦች በባቢሎናዊ ውሸቶች ተውጠው ጠፍተዋል። የክህደት ክርስትናም ቢሆን ከእነዚህ ሃይማኖቶች የተሻለ አልሆነም። ስለዚህም የጎሣ ሃይማኖቶችም ሆኑ የክህደት ክርስትና ከአንድ ምንጭ የተቀዱ በመሆናቸው “አረማውያን” ወደ “ክርስትና” ለመግባት አስቸጋሪ አልሆነባቸውም። ዘ ሚቶሎጂ ኦቭ ኦል ሬስስ የተባለው መጽሐፍ “የማያውያንን ሃይማኖት ያህል ከክርስትና የአምልኮ ሥርዓቶችና ተምሳሊቶች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሃይማኖት በማንኛውም የአሜሪካ ክፍል አይገኝም” ብሏል። መስቀል እንደ ቅዱስ ነገር ተቆጥሮ መከበሩና ሌሎች ተመሳሳይነት ያላቸው የአምልኮ ሥርዓቶች መኖራቸው “አዲሱን ሃይማኖት አለ ብዙ ችግር እንዲቀበሉ አስችሏቸዋል።”
ለ450 ዓመታት በአዲሱ ዓለም በባርነት እንዲያገለግሉ “በክርስቲያኖች” ታፍነው ሲወሰዱ የቆዩት አፍሪካውያንም ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ “አስቸጋሪ አልሆነባቸውም።” “ክርስቲያኖች” በሞት የተለዩአቸውን አውሮፓውያን “ቅዱሳን” ያከብሩ ስለነበረ “አረማውያን ክርስቲያኖች” አፍሪካውያን የሆኑትን የቅድመ አያቶቻቸውን መናፍስት ማምለካቸው ስህተት ሆኖ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን እንዳለው “የምዕራብ አፍሪካ ሃይማኖቶችን፣ ጥንቆላን፣ ክርስትናንና ባሕላዊ ወጎችን የሚያጣምረው የቩዱ ሃይማኖት . . . የአብዛኞቹ የሃይቲ ሕዝቦች፣ ካቶሊክ ነን የሚሉት ጭምር ሃይማኖት ሆነ።”
ዘ ኮንሳይስ ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ወርልድ ሚሽን የተባለው መጽሐፍ የላቲን አሜሪካና የፊሊፒንስ ሕዝቦች ወደ “ክርስትና” መለወጥ ለይስሙላ ብቻ የተደረገ መሆኑን ካመነ በኋላ በመቀጠል “የእነዚህ አካበቢዎች ክርስትና በአጉል እምነቶችና በድንቁርና የተዋጠ ነው” ይላል። ለአዝቴኮች፣ ለማያዎችና ለኢንካዎች “ወደ ክርስትና ‘መለወጥ’ ከነበሯቸው በርካታ አማልክት ሌላ አዲስ አምላክ ከመጨመር የበለጠ ትርጉም አልነበረውም።”
ሚሸል ጊልበርት የተባሉት የፒበዲ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ባልደረባ በጋናና በኮት ዲቩዋር ስለሚኖሩት የአካን ሕዝቦች እንዲህ ብለዋል:- “አብዛኞቹ ሕዝቦች ባሕላዊ ሃይማኖታቸውን አልተዉም። ምክንያቱም ብዙዎቹ ባሕላዊ ሃይማኖታቸውን ይበልጥ ውጤታማና የሚኖሩበት ዓለም ትርጉም ያለው እንዲሆንላቸው የሚያስችል አድርገው ስለሚመለከቱ ነው።”
የዚምባብዌ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ኤም ኤፍ ሲ ቡርዲሎን የሾና ሃይማኖት አባሎች ስላላቸው “ሃይማኖታዊ ዝውውር” ጽፈዋል። ሲያብራሩም “የተለያዩ የክርስትና ዓይነቶችና በርካታ የሆኑ ባሕላዊ ሃይማኖቶች መኖራቸው ማንም ግለሰብ በአንድ የተወሰነ ጊዜ ላጋጠመው ችግርና ፍላጎት የሚበጀውን ሃይማኖት መርጦ ለመያዝ የሚችልበት ሰፊ ምርጫ እንዲኖረው አስችለውታል” ብለዋል።
ይሁን እንጂ “አረመኔ ክርስቲያኖች” ለይስሙላ ብቻ የተለወጡ፣ በድንቁርናና በአጉል እምነት የተዋጡ፣ በበርካታ አማልክት የሚያምኑ፣ ባሕላዊ ሃይማኖታቸው ከክርስትና ይበልጥ ውጤታማ እንደሆነ የሚያምኑ፣ ሃይማኖት እንደ አመቺነቱ የሚቀያየር እንደሆነ ነገር አድርገው የሚመለከቱ ከሆኑ ሕዝበ ክርስትና እውነተኛ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት አፍርታለች ለማለት ይቻላልን?
ታዲያ ደቀ መዛሙርት ካልሆኑ ምንድን ናቸው ሊባል ነው?
የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን መሐይማን የሚማሩባቸው በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች እንዳቋቋሙ አይካድም። በሽተኞች የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎች ሠርተዋል። በተጨማሪም በመጠኑም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከበሬታ እንዲያገኙ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ “አረማውያን” የተመገቡት ጠንካራ የሆነውን የአምላክ ቃል እውነት ነው ወይስ የክህደት ክርስትናን ፍርፋሪዎች? “የአረማውያን” እምነቶችና ልማዶች ፈጽመው ተወግደዋል ወይስ “በክርስትና” ልብስ ብቻ እንዲሸፈኑ ተደርጓል? በአጭሩ የሕዝበ ክርስትና ሚስዮናውያን የሰዎችን ልብ ወደ አምላክ መልሰዋል ወይስ “የአረማውያን” ጉልበት “ለክርስትና” መሠዊያዎች እንዲንበረከክ ከማድረግ ያለፈ ነገር አላደረጉም?
አንድ የክህደት ክርስትናን የተቀበለ ሰው በድንቁርና ይሠራቸው በነበሩት ኃጢአቶች ላይ የግብዝነት ክርስትናን ኃጢአቶች ይጨምራል። ይህን በማድረጉም ከቀድሞው ይበልጥ እጥፍ ድርብ ወንጀለኛ ይሆናል። ስለዚህ የሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት በሕዝበ ክርስትና ላይ ተፈጻሚነት አግኝተዋል:- “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፣ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፣ ወዮላችሁ።”— ማቴዎስ 23:15
ሕዝበ ክርስትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ኃላፊነትዋን በብቃት እንዳልተወጣች ግልጽ ነው። እየተለወጠ የመጣውን የዓለም ሁኔታ በመቋቋም ረገድስ ተሳክቶላት ይሆን? በሚቀጥለው እትማችን “ሕዝበ ክርስትና እየተለወጠ የመጣውን የዓለም ሁኔታ መቋቋም አልቻለችም” በሚል ርዕስ ይህን ርዕሰ ጉዳይ እንመለከታለን።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እነዚህ በዶሚኒካን ሪፓብሊክ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያን ሚስዮናውያን የሰዎችን ጉልበት ብቻ ሳይሆን ልባቸውን ጭምር ይለውጣሉ