በድህነት ሲማቅቁ ኖረው ሳያልፍላቸው የሚሞቱ በጣም ብዙ ናቸው!
ያቲ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከሚገኘው ደሳሳ ጎጆዋ ወጥታ ለጫማ መሥሪያ የሚሆን ቆዳ እየገጣጠመች ወደምትሰፋበት ፋብሪካ አቀናች። በሳምንት 40 ሰዓት፣ በወር ውስጥ 90 ተጨማሪ ሰዓት ሠርታ በወር የምታገኘው ደመወዝ ከ80 የአሜሪካ ዶላር አያልፍም። የቀጠራት የጫማ ፋብሪካ ባልበለጸጉ አገሮች ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አጥብቆ የሚሟገት ድርጅት እንደሆነ በጉራ ይናገራል። ይህ ኩባንያ አንዱን ጥንድ ጫማ ለምዕራባውያን አገሮች በ60 የአሜሪካ ዶላር ይሸጣል። ለሠራተኛ ደመወዝ ያወጣው ገንዘብ ግን ከ1.40 የአሜሪካ ዶላር አይበልጥም።
ቦስተን ግሎብ ሪፖርት እንዳደረገው ያቲ “ንጹሕ ከሆነውና በደማቅ መብራቶች ካሸበረቀው ፋብሪካ ከወጣች በኋላ የምትሄደው 3 ሜትር በ3.6 ሜትር ስፋትና እንሽላሊቶች የሚሽሎከሎኩበት፣ ግድግዳው ወደፈራረሰው ደሳሳ ጎጆዋ ነው። በቤቱ ውስጥ ምንም ዓይነት የቤት ዕቃ ስለሌለ ያቲና ሁለት ደባሎቿ በአፈር ወለል ላይ እጥፍጥፍ ብለው ይተኛሉ።” የያቲን ዓይነት ኑሮ የሚገፉ ሰዎች ቁጥር በጣም በርካታ መሆኑ ያሳዝናል።
አንድ የሞያ ማኅበር መሪ “በእርግጥ ለእነዚህ ሰዎች የፈየድኩት ነገር ይኖር ይሆን? የሚያገኟት አነስተኛ ደመወዝ ደህና ኑሮ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። የተቀናጣ ኑሮ ሊኖሩ ባይችሉም አይራቡም” በማለት በምሬት ይናገራል። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት የማይችሉ ከመሆናቸውም በላይ ልጆቻቸው ምንም እህል ሳይቀምሱ ለማደር የሚገደዱባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። የሥራ ቦታቸው ለአስከፊ አደጋ የተጋለጠ ነው። መርዛማ የሆኑ ኬሚካሎችና ተረፈ ምርቶች በሚያደርሱባቸው የአካል መመረዝ ቀስ በቀስ ማቅቀው የሚሞቱት በርካታ ናቸው። ይኽ ነው “ደህና ኑሮ” የሚባለው?
በደቡብ እስያ የሚኖረው ሃሪ የተባለ የእርሻ ሞያተኛ ስለ ኑሮው ያለው አስተያየት ከዚህ የተለየ ነው። በዙሪያው የከበበውን የሞት-ሽረት ትግል ግሩም በሆነ የአነጋገር ዘይቤ ገልጾታል። እንዲህ አለ:- “በዘነዘና የሚወቀጥ በርበሬ ብዙ ሊቆይ አይችልም። እኛ ድሆች እንደ በርበሬው ነን። በየዓመቱ ስንወቀጥ እንቆይና ብዙም ሳንሰነብት ድምጥማጣችን ይጠፋል።” ሃሪ ‘ደህና የተባለውን ኑሮ’ በዓይኑ እንኳን ለማየት አልታደለም። አሠሪዎቹ ምናልባት ያገኙትን የቅንጦት ኑሮም ቢሆን ምን እንደሚመስል ለማወቅ እንኳ አልቻለም። ከጥቂት ቀናት በኋላ ሃሪ በድህነት ማቅቀው ከሚሞቱት በርካታ ሰዎች መካከል አንዱ ሆነ።
የሃሪን ዓይነት ኑሮ ኖረው የሚሞቱ ሰዎች እጅግ ብዙ ናቸው። የመኖር ኃይላቸው ከውስጣቸው ተሟጥጦ የሚኖሩበትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት አጥተው ማቅቀው ይሞታሉ። ይህን ሁሉ ሰቆቃ የሚያደርሱባቸው እነማን ናቸው? እንዲህ ያለ ድርጊት የሚፈጽሙት እንዴት ያሉ ሰዎች ናቸው? ይህን ሁሉ የሚያደርሱባቸው ሰዎች በጎ አድራጊ እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ። ልጆቻችሁን ሊመግቡላችሁ፣ ብዙ ምርት እንድታገኙ የሚያስችላችሁን እርዳታ ሊሰጧችሁ፣ ኑሯችሁን ሊያሻሽሉላችሁና ባለጠጋ ሊያደርጓችሁ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ራሳቸውን ከማበልጸግ የተለየ አንድም ዓላማ የላቸውም። ሸቀጣቸውን የሚያራግፉበትን፣ ትርፋቸውን የሚያጋብሱበትን አጋጣሚ ይፈላልጋሉ። ስግብግብነታቸው ሕፃናትን ቢያስርብ፣ ሠራተኞችን ቢመርዝ፣ አካባቢን ቢበክል ለነርሱ ጉዳያቸው አይደለም። ኩባንያዎቹ ተስገብግበው ለመክፈል የሚፈልጉት ዋጋ ይሄው ነው። ስለዚህ የሚያገኙት ትርፍ እያሻቀበ በሄደ መጠን የሚደርሰው ቅስም ሰባሪ ጉዳትም በዚያው መጠን ይጨምራል።
[ምንጭ]
U.N. Photo 156200/John Isaac