ድሃ አገሮች የባለጠጋ አገሮች ቆሻሻ መጣያ ሆነዋል
የመርዛማ ቆሻሻው ጭነት አባት እናቱን በሞት አጥቶ ፈላጊ እንዳጣ ሕፃን ማረፊያ ለማግኘት ከመርከብ ወደ መርከብ፣ ከወደብ ወደ ወደብ ሲንከራተት ቆይቷል። መርዛማ ፀረ ተባዮችና ሙጫዎች እንዲሁም ሌሎች አደገኛ ኬሚካሎች የታጨቁባቸው አሥራ አንድ ሺህ በርሜሎች አፍሪካ ከምትገኘው ጂቡቲ ወደ ቬንዝዌላ፣ ከዚያም ወደ ሶርያና ወደ ግሪክ ሲጓጓዙ ቆይተዋል። በመጨረሻም በርሜሎቹ ተበስተው ማፍሰስ በመጀመራቸው ከመርከቡ ሠራተኞች በአንዱ ላይ ጉዳት አደረሱ። አንድ ሰው ሲሞት አብዛኞቹ በጫኑት መርዝ ምክንያት ለቆዳ፣ ለኩላሊትና ለመተንፈሻ አካላት በሽታ ተዳረጉ።
ተመሳሳይ የሆኑ ገዳይ መርዛማ ቆሻሻዎችን ጭነው የሚያራግፉበት ቦታ በመፈለግ መላዋን ምድር የሚያስሱ መርከቦች፣ የጭነት መኪናዎችና ባቡሮች በጣም ብዙ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ በድህነት፣ በረሃብና በበሽታ የተጎሳቆሉት አገሮች የበርካታ ኩንታል መርዞችና የተበከሉ ቆሻሻዎች ማራገፊያ ይሆናሉ። ስለ አካባቢ ደህንነት የሚያጠኑ ሊቃውንት በሥነ ምህዳር መበላሸት ምክንያት ከፍተኛ እልቂት መድረሱ የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።
ጊዜ ያለፈባቸው ቀለሞች፣ መበጥበጫዎች፣ ጎማዎች፣ ባትሪዎች፣ ራድዮ አክቲቭና ሌሎች መርዛም ዝቃጮች አይማርኩህ ይሆናል። በጣም ለደራው ከኢንዱስትሪ ለሚወጡ የቆሻሻ ንግድ ግን ምራቅ የሚያስውጡ ናቸው። አንድ መንግሥት ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ቆሻሻዎችን የሚቆጣጠር ጥብቅ ሕግ ባወጣ መጠን የዚሁ አገር ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጭ አገሮች የሚልኳቸው መርዛማ ቆሻሻዎች ይጨምራሉ። ዘ ኦብዘርቨር የተባለው የለንደን ሳምንታዊ ጋዜጣ እንደገለጸው በበለጸጉ አገሮች የሚገኙ “ለሌላው ደንታ የሌላቸው ኩባንያዎች በየዓመቱ 200 ሚልዮን ኩንታል የሚያክል መርዛማ ኬሚካል በሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ያራግፋሉ።” በሕግ አስከባሪዎች ልል መሆንና በሕጎች ደካማነት ምክንያት በብዙ ሺህ ኩንታል የሚመዘን መርዛማ ቆሻሻ በአፍሪካ በእስያና በላቲን አሜሪካ መሬቶች ይራገፋል።
እነዚህ ኩባንያዎች ቆሻሻዎቻቸውን በእነዚህ አገሮች ለማራገፍ መቋመጣቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ትክክለኛው ቦታ ላይ ማራገፍ ከተቻለ ወጪው በከፍተኛ መጠን ሊቀንስ ይችላል። በአንድ ወቅት የመንገደኞች ማጓጓዣ የነበረችውና የአሜሪካንን ባንዲራ ታውለበልብ የነበረችው ዩናይትድ ስቴትስ የተባለች ፈጣን መርከብ ለዚህ ምሳሌ ትሆናለች። በጣም ምቹ የሆነች የመንገደኞች ማጓጓዣ እንድትሆን የተገዛችው በ1992 ነበር። ከማንኛውም መርከብ ጋር ሊወዳደር የማይችል ብዙ መጠን ያለው አስቤስቶስ ነበረባት። ያን የሚያክል አስቤስቶስ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለማስወገድ ቢፈለግ 100 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ይጠይቅ ነበር። መርከቢቱ በ2 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ሊወገድ ወደ ሚቻልበት ወደ ቱርክ አመራች። ሆኖም የቱርክ መንግሥት ከ46,000 ካሬ ሜትር የሚበልጠውን ካንሰር አምጪ አስቤስቶስ በአገሩ ውስጥ እንዲራገፍ አልፈቀደም። በመጨረሻ መርከቢቱ የአካባቢ ደህንነት ቁጥጥር ልል ወደሆነበት ወደ ሌላ አገር ወደብ ተወሰደች።
ቆሻሻዎችን ወደ ሌላ ምርት የመቀየር አደገኛነት
በታዳጊ አገሮች የሚንቀሳቀሱ ምዕራባውያን የንግድ ድርጅቶች ድሆችን የሚታደጉ እንደሆኑ ይናገሩ ይሆናል። የዩናይትድ ስቴትስ ንግድ ምክር ቤት ባልደረባ የሆኑት ሃርቬ ኦልተር “ቆሻሻዎችን ወደ ሌሎች አገሮች መላክና ወደ ሌሎች ምርቶች መለወጥ የእነዚህን አገሮች የኑሮ ደረጃ ከፍ ያደርጋል” ብለዋል። ይሁን እንጂ የእነዚህ ድርጅቶች ምግባር ሲጤን አብዛኛውን ጊዜ የሰዎችን የኑሮ ደረጃ ከፍ ከማድረግ ይልቅ “በአገሩ ከሚታወቀው የመጨረሻ ዝቅተኛ ደመወዝ የበለጠ እንደማይከፍሉ፣ አካባቢውን እንደሚያቆሽሹና አንዳንድ ጊዜ አደገኛና በአጭበርባሪነት የሚሸጡ ምርቶችን እንደሚያመርቱ ለመረዳት ተችሏል።”
ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል ዳግማዊም በታዳጊ አገሮች እየተስፋፋ ስላለው ብክለት አስመልክቶ በተደረገ ስብሰባ ላይ ነገሩ ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳቱ “የበለጸጉ አገሮች የድሃ አገሮችን የኢኮኖሚና የሕጋዊ ቁጥጥር ደካማነት ተጠቅመው የሕዝቡን የመኖሪያ አካባቢና ጤና የሚጎዱ ቆሻሻ ቴክኖሎጂዎችን በመላክ ትርፍ ማጋበሳቸው በጣም የሚያሳዝን በደል ነው” ብለዋል።
በትልቅነቱ ከዓለም አንደኛ የሆነው የሜርኩሪን ዝቃጭ ወደ ሌላ ምርት የሚለውጥ ፋብሪካ በሚገኝበት በደቡባዊ አፍሪካ የደረሰው ሁኔታ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይሆናል። “በአሕጉሪቱ ውስጥ አካባቢን በመበከል ከተፈጸሙት ቅሌቶች ሁሉ በጣም የከፋ ነው” በተባለው በዚህ አደጋ መርዛማው ቆሻሻ አንድ ሠራተኛ ሲገድል፣ ሌላኛውን ደግሞ ራሱን ስቶ እንዲወድቅ አድርጓል። ከጠቅላላ ሠራተኞች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአንድ ዓይነት የሜርኩሪ መመረዝ በመሠቃየት ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል። አንዳንድ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች መንግሥታት አንዳንድ የሜርኩሪ ዝቃጮች በምንም ዓይነት መንገድ እንዳይጣሉ በጥብቅ ይከለክላሉ። ከእነዚህ አገሮች መካከል ቢያንስ በአንዱ የሚገኙ የንግድ ድርጅቶች አደገኛ ዝቃጮቻቸውን በመርከቦቻቸው ጭነው ወደ አፍሪካ የባሕር ጠረፎች ያጓጉዛሉ። አንድ የተቆጣጣሪ ቡድን የሜርኩሪ ዝቃጮች የተሞሉ 10,000 በርሜሎች በሦስት ባዕዳን ኩባንያ ፋብሪካዎች ውስጥ ተከማችተው አግኝቷል።
ወደ ሌላ ምርት የሚለወጥ ዝቃጭ ወደ ታዳጊ አገሮች መላክ ቆሻሻ ወስዶ ከመጣል የተሻለ ተቀባይነት ያገኛል። ጥሩ ዋጋ የሚያስገኙ ምርቶች ማምረት ይቻላል። የሥራ ዕድል ይከፍታል እንዲሁም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ከላይ የተመለከትነው ከደቡባዊ አፍሪካ የተገኘው ሪፖርት እንደሚያመለክተው አስከፊ የሆነ ከባድ ጉዳት ሊከተል ይችላል። ከእነዚህ ዝቃጮች ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለማስገኘት በሚከናወነው ሂደት አካባቢውን የሚበክሉና አንዳንድ ጊዜ በሠራተኞች ላይ በሽታና ሞት የሚያስከትሉ መርዛማ ኬሚካሎች ሊወጡ ይችላሉ። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት “ዝቃጮችን ወደ ሌሎች ምርቶች መቀየር እነዚህን ዝቃጮች ለማራገፍ ሰበብ ሆኖ ያገለገለበት ሁኔታ እንደሚኖር አያጠራጥርም” ብሏል።
ይህ ዘዴ በዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ላይ ተገልጿል። “ታዳጊ አገሮች የሃሰት መግለጫ በያዙ ምልክቶች፣ ደካማ በሆኑ ሕጎችና በባለሞያ እጥረት ምክንያት መርዛማ ዝቃጮችን እንደ ‘ማዳበሪያ’ ወይም ጊዜ ያለፈባቸውን ፀረ ተባዮች እንደ ‘ግብርና ግብዓቶች’ አስመስለው በሚሸጡ የዝቃጭ ቆሻሻ ነጋዴዎች በቀላሉ ይታለላሉ።”
በሜክሲኮ የባዕዳን ንብረት የሆኑ ማኪላዶራዎች ወይም ፋብሪካዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። የባዕዳኑ ኩባንያዎች ዋነኛ ዓላማ የገዛ አገሮቻቸው ከሚጥሉባቸው የአካባቢ መበከል ቁጥጥር ማምለጥና ርካሽ ደመወዝ ከሚከፈላቸው ሠራተኞች ገደብ የሌለው ትርፍ ማጋበስ ነው። በበርካታ አሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሜክሲካውያን የቆሻሻ ውኃ መተላለፊያ ቦዮች በሚያዋስኗቸው ደሳሳ ጎጆዎች ይኖራሉ። አንዲት ሴት “ፍየሎች እንኳን ይህን ውኃ አይጠጡትም” ብለዋል። አንድ የአሜሪካ ሕክምና ማኅበር ይህንን “ውኃ የሚተላለፍበትን የመኖሪያ ቦታ የተላላፊ በሽታዎች መቀፍቀፊያ” ብሎ ጠርቶታል።
የሚገደሉት ተባዮች ብቻ አይደሉም
አሪፍ ጀማል የተባሉት በካርቱም የሚኖሩ የእርሻና የፀረ ተባይ መድኃኒቶች ባለሞያ “አንድ አገር በራሱ አገር እንዲኖር የማይፈልገውን መርዝ እንዴት ለሌላ አገር አምርቶ ይሸጣል? እንዲህ ያለው ድርጊት በምን ዓይነት መንገድ ትክክል ሊሆን ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል። መድኃኒቶች በሚመረቱባቸው በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች “ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለ” የሚል ማኅተም የተደረገባቸውን በርሜሎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ካሳዩ በኋላ በሱዳን አገር በሚገኝ አንድ የዱር አራዊት መጠበቂያ የተገኙ በርሜሎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከበርሜሎቹ አጠገብ የሞቱ እንስሳት ሬሳ ተከምሯል።
አንድ ሀብታም አገር “በየዓመቱ በገዛ አገሩ ውስጥ ሥራ ላይ እንዳይውል የተከለከለ፣ የታገደ ወይም ያልተፈቀደ 227 ሚልዮን ኪሎ ግራም የሚያክል ፀረ ተባይ ወደ ውጭ አገሮች” እንደሚልክ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። ከዲዲቲ ጋር የቅርብ ተዛማጅነት ያለውና ካንሰር አምጪ የሆነው ሄፕታክሎር ለምግብነት በሚያገለግሉ ሰብሎች ላይ እንዳይረጭ የታገደው በ1978 ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ኬሚካል የፈለሰፈው ኩባንያ ኬሚካሉን ማምረቱን አላቆመም።
“በጣም መርዛማ የሆኑ ፀረ ተባይ ኬሚካሎች” ቢያንስ 85 በሚያክሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ በስፋት እንደሚገኙ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት አረጋግጧል። በየዓመቱ በእነዚህ ኬሚካሎች ጠንቅ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ከፍተኛ ሥቃይ የሚደርስባቸው ሲሆን ምናልባት 20,000 የሚያክሉ ሰዎች ሳይሞቱ እንደማይቀሩ ይገመታል።
የትንባሆ ኢንዱስትሪ ስግብግብነት ለሚያስከትለው ቅስፈት ጥሩ ምሳሌ ነው ለማለት ይቻላል። በሳይንቲፊክ አሜሪካን ላይ የወጣ “ምድር አቀፉ የትንባሆ እልቂት” የተሰኘ ጽሑፍ ላይ “ከትንባሆ ጋር ግንኙነት ባላቸው ምክንያቶች የሚደርሰው በሽታና ሞት መጠን ከሚገባው በላይ ተጋኗል ሊባል የሚችል አይደለም” ብሏል። ሰዎች ትንባሆ ማጨስ የሚጀምሩበት አማካይ ዕድሜ በጣም እያሽቆለቆለ ሲሆን የአጫሽ ሴቶች ቁጥርም በከፍተኛ መጠን በመጨመር ላይ ነው። ትላልቅ የትንባሆ ኩባንያዎች መሠሪ ከሆኑ አስተዋዋቂዎች ጋር ግንባር በመፍጠር በጣም ግዙፍ የሆነውን ያልበለጸጉ አገሮች ገበያ በቁጥጥራቸው ሥር በማስገባት ላይ ናቸው። በበሽታ በሚማቅቁ ሰዎችና በአስከሬኖች ላይ እየተረማመዱ ሀብታቸውን ያካብታሉ።a
ይሁን እንጂ ሁሉም ኩባንያዎች ለታዳጊ አገሮች ደህንነት ደንታ ቢስ ናቸው ለማለት አይቻልም። በታዳጊ አገሮች ትክክለኛ የንግድ ሥራ የሚያከናውኑና የኃላፊነት ስሜት የሚሰማቸው አንዳንድ ኩባንያዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ኩባንያ ለሠራተኞቹ የጡረታና የሕክምና አገልግሎት ከመስጠቱም በላይ የአገሩ ሕግ ከሚጠይቀው ደመወዝ በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ደመወዝ ይከፍላል። ሌላ ኩባንያ ደግሞ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጠንካራ አቋም የወሰደ ሲሆን ይህን የሚጋፉ በደርዘን የሚቆጠሩ ኮንትራቶችን ሰርዟል።
የግብዝነት ማፈግፈግ
በ1989 በባዝል፣ ስዊዘርላንድ አደገኛ የሆኑ ዝቃጮች ከአገር ወደ አገር እንዳይዘዋወሩ የሚያግድ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውል ተፈርሞ ነበር። ውሉ ችግሩን ሊያስወግድ አልቻለም። ኒው ሳይንቲስት እነዚሁ ብሔራት ቆየት ብለው በመጋቢት ወር 1994 ስላደረጉት ስብሰባ እንደሚከተለው ዘግቧል:-
“የባዝል ስምምነት ተፈራራሚ የሆኑት 65 አገሮች ታዳጊ አገሮች ላሰሙት እሮሮ ትክክለኛ እርምጃ በመውሰድ አደገኛ የሆኑ ዝቃጮች ከኦ ኢ ሲ ዲ (የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት) አባል አገሮች የዚህ ድርጅት አባል ወዳልሆኑ አገሮች እንዳይላኩ የሚያግድ ውሳኔ በማስተላለፍ ስምምነቱ እንዲራዘም ወስኗል።”
ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ለበለጸጉት አገሮች የሚዋጥላቸው መስሎ አልታየም። ኒው ሳይንቲስት በዚህ ረገድ ያደረበትን ሥጋት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመንና አውስትራሊያ ውሳኔውን ለማዳከም እንደሚጥሩ መሰማቱ ትልቅ ሥጋት ፈጥሯል። ከዩ ኤስ መንግሥት ሾልከው የወጡ ሰነዶች ይህች አገር ስምምነቱን ከመፈረምዋ በፊት ስምምነቱን ለመበረዝና ለማዳከም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን አጋልጠዋል።”
ስግብግቦች ብድራታቸውን የሚቀበሉበት ቀን ቀርቦአል
መጽሐፍ ቅዱስ በያዕቆብ 5:1 ላይ “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፣ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ” በማለት ያስጠነቅቃል። ፍርዱን የሚያስተላልፈው ሁሉንም ነገሮች የሚያስተካክለው አምላክ ነው። “እግዚአብሔር . . . ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል።”—መዝሙር 103:6
በአሁኑ ጊዜ በማያፈናፍን ድህነት የሚማቅቁ ሁሉ “ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል” የሚለው የመዝሙር 72:12, 13 ተስፋ የሚፈጸመው በቅርብ ጊዜ መሆኑን ማወቃቸው ሊያጽናናቸው ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ግንቦት 22, 1995 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ሚልዮን ለማግኘት ሚልዮኖችን መግደል” የሚለውን ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አልወገድም ያለ አደገኛ ዝቃጭ
“መፍትሄ የታጣለት እጅግ አደገኛ የሆነ የኑክሊየር ዝቃጭ ክምር እየጨመረ መጥቷል።” በ1995 መጋቢት ወር ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በሳይንስ አምዱ ላይ ያሰፈረው ርዕስ ነበር። ይኸው ጽሑፍ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ከሁሉ የሚቀልለው መፍትሔ በምድር ከርስ ውስጥ መቅበር ነበር። ይሁን እንጂ ይህ መፍትሔ ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል። እንደታሰበው በኔቫዳ ምድረ በዳ ቢቀበር በየጊዜው የሚጨመረው የፕሉቶንየም ዝቃጭ ውሎ አድሮ የኑክሊየር ፍንዳታ ሊያስነሳ የሚችል ስለመሆኑ ሳይንቲስቶች እየተነጋገሩ ሲሆን ፌዴራላዊ ድርጅቶችም ጥናት እያደረጉ ነው።”
ሳይንቲስቶች በትርፍነት የተከማቸውን ፕሉቶንየም ከዓለም ማስወገድ የሚቻልባቸውን በርካታ መንገዶች ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም ዘዴዎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ፣ ውዝግብ የሚያስነሱና ሌላ ሥጋት የሚፈጥሩ በመሆናቸው ከእቅድነት ደረጃ እልፍ አላሉም። ባሕር ውስጥ መቅበር የሚለው ሐሳብ ግን ብዙዎችን አስከፍቷል። ወደ ፀሐይ መተኮስ የሚለው ሐሳብ ደግሞ ባዶ ሐሳብ ሆኖ ቀርቷል። ሌላው የመፍትሔ ሐሳብ በማብለያ ተጠቅሞ አቃጥሎ ማውደም ነው። በዚህ መንገድ አቃጥሎ ለመጨረስ ግን “በመቶ እንዲያውም በሺህ የሚቆጠር ዓመት ስለሚጠይቅ” ተቀባይነት አላገኘም።
የኃይልና የአካባቢ ሁኔታ ጥናት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማኪጃኒ እንዲህ ብለዋል:- “በቴክኒክ ረገድ ጥሩ ሆኖ የተገኘው ዘዴ ተቀባይነት ሊያገኝ የማይችል ፖለቲካዊ ገጽታ ሲኖረው በፖለቲካ ረገድ ጥሩ ሆኖ የተገኘው መፍትሔ ደግሞ ከቴክኒካዊ አንጻር ችግር ያለበት ይሆናል። ለዚህ ምስቅልቅሉ ለወጣ ጉዳይ አጠቃላይ የሆነ መፍትሔ ሊሰጥ የሚችል፣ እኛንም ጨምሮ ማንም ሰው የለም።”
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት 107 የሚያክሉ የኑክሊየር ኃይል ማመንጫዎች 60 ሚልዮን የሚያክሉ ቤቶች የሚያስፈልጋቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከአገሪቱ የኢነርጂ ፍጆታ 20 በመቶ የሚሆነውን ማለት ነው፣ ለማመንጨት በየዓመቱ 20,000 ኩንታል የሚያክል የነዳጅ ዝቃጭ ያወጣሉ። ይህ የነዳጅ ዝቃጭ ከ1957 ጀምሮ በማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ በጊዜያዊነት ሲከማች ቆይቷል። ሰዎች፣ መንግሥት ዝቃጩን የሚያስወግድበትን መንገድ እንዲፈልግ ለአሥርተ ዓመታት በከንቱ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዘጠኝ ፕሬዚዳንቶች በሥልጣን ላይ ተፈራርቀዋል። 18 ምክር ቤቶች እነዚህ ራዲዮ አክቲቭ ዝቃጮች በከርሰ ምድር ውስጥ በተዘጋጁ ቦታዎች የሚቀበሩበትን የመጨረሻ ጊዜ ወስነው ነበር። ይሁን እንጂ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተወግደው በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት ምንም ዓይነት አደጋ ሳያስከትሉ የሚጠበቁበት ዘዴ አሁንም አልተገኘም።
ነገሩን ለማነጻጸር ያህል፣ ይሖዋ አምላክ ከእኛ በጣም ርቀው በጠፈር ውስጥ የሚገኙት በትሪልዮን በሚቆጠሩ ከዋክብት ዘንድ እንዲፈጠር የሚያደርገው ከፍተኛ የሙቀት ኃይል ምንም ዓይነት ስጋት አይፈጥርም። እንዲያውም በፀሐይ ላይ እንዲካሄድ የሚያደርገው የኃይል ማመንጫ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር አስችሏል።
[ምንጭ]
UNITED NATIONS/IAEA
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መርዛማ ኬሚካሎች የመጠጥና የመታጠቢያ ውኃዎችን ይበክላሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆች አደገኛና ቀሳፊ በሆነ የቆሻሻ መጣያ አካባቢ ይጫወታሉ