ምድር የአምላክ ስጦታ
“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” በተጨማሪም ስለ ምድር ሲናገር “እጅግ መልካም” ነበረች። (ዘፍጥረት 1:1, 31) ውበቷን የሚያበላሽ የቆሻሻ ክምር ወይም አካባቢዋን የሚበክል የጥራጊ ጥርቅም አልነበረም። የሰው ልጅ እጹብ ድንቅ የሆነች መኖሪያ ተሰጠው። “የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው። ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት።”—መዝሙር 115:16
በኢሳይያስ 45:18 ላይ አምላክ ምድርን የፈጠረበትን ዓላማ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፣ እንዲህ ይላል:- እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።”
ምድርን በሚመለከት የሰው ልጅ የተሰጠው ኃላፊነት ምን እንደሆነ ለይቶ ሲያመለክት “ያበጃትም፣ ይጠብቃትም ዘንድ” ብሏል።—ዘፍጥረት 2:15
በዚህ ረገድ ይሖዋ ራሱ ጥሩ ምሳሌ ሆኗል። ለምድር አስፈላጊውን እንክብካቤ ያደርጋል። ይህን ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ በምድር ላይ ለሚኖሩ ነፍሳት ሕልውና አስፈላጊ የሆኑ ዑደቶች እንዲፈራረቁ በማድረግ ነው። አንድ የሳይንቲፊክ አሜሪካን ልዩ እትም እነዚህን የተለያዩ ዑደቶች የሚገልጽ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ከእነዚህም መካከል የምድር የኢነርጂ ኡደት፣ የባዮስፌር የኢነርጂ ዑደት፣ የውኃ ዑደት፣ የኦክስጂን ዑደት፣ የካርቦን ዑደት፣ የናይትሮጅን ዑደትና የማዕድናት ዑደት ተጠቅሷል።
አስደናቂና ውብ ፍጥረት የሆነችው ምድር
ጽሑፎቻቸው በሰፊው የተሠራጩላቸው የሥነ ሕይወት ሊቅ ለዊስ ቶማስ ዲስከቨር በተባለው የሳይንስ መጽሔት ስለ ምድር የሚከተለውን የውዳሴ ቃል አስፍረዋል:-
“ምድር ዕጹብ ድንቅ የሆነ፣ እስካሁን ድረስ ስለ ጽንፈ ዓለማችን ካወቅነው በጣም የተለየ፣ የጠፈር ምርምር ሳይንስ ሊደርስበት ያልቻለ፣ ለመረዳት ያደረግነውን ጥረት በሙሉ የተፈታተነ መዋቅርና አፈጣጠር አላት። ሰማያዊ በሆነ ከባቢ አየር የተጠቀለለች፣ ራስዋ የሠራችውን ኦክስጂን የምትተነፍስ፣ ከራሷ አየር ናይትሮጂን ወስዳ ከአፈሯ ጋር የምታዋህድ፣ በሞቃታማ የሐሩር ደኖቿ ላይ የራሷ የአየር ሁኔታ መቆጣጠሪያ ያላት፣ የራሷን የቆዳ ሽፋን ከሕያዋን ክፍሎች ማለትም ቀደም ሲል በሕይወት ይኖሩ ከነበሩ ፍጥረታት አንዳቸው በሌላው ላይ በመደራረብ ከፈጠሩት ኖራና ቅሪተ አካል የምትሠራ አስደናቂ፣ በፀሐይ ዙሪያ የምትንሳፈፍ በዓይነቷ ብቸኛና ልዩ የሆነች አካል መሆኗን መገንዘብ የጀመርነው ገና አሁን ነው።”
የተዋበች የሰው ልጆች ስጦታ፣ ለሰውና በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሕያዋን ፍጥረታት መኖሪያ እንድትሆንና ለዘላለም እንድትኖር ሆና በተፈጠረችው በዚች ምድር ላይ ይሖዋ እንዲከናወኑ ካደረጋቸው የተለያዩ ዝግጅቶች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። መዝሙር 104:5 “ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረትዋ ላይ መሠረታት” ይላል። ሌላው በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ የጻፈ ምሥክር ደግሞ ስለምድር ዘላለማዊነት ሲናገር “ትውልድ ይሄዳል፣ ትውልድም ይመጣል፣ ምድር ግን ለዘላለም ነው” ብሏል።—መክብብ 1:4
ምድርን የዞሩ የጠፈር ተጓዦች ይህችን በፀሐይ ዙሪያና በራስዋ ምሕዋር የምትሽከረከር የተዋበችና ረቂቅ የሆነች ዓለም ሲመለከቱ በጣም ከመደነቃቸውም በላይ የሰው ልጅ ውበቷን ተገንዝቦ የሚገባትን እንክብካቤ ሊያደርግላት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ኤድጋር ሚቸል የተባለው ጠፈረተኛ ምድርን ከጠፈር ላይ ሆኖ እንደተመለከተ ሂውስተን ለሚገኘው ጣቢያ የሚከተለውን የራዲዮ መልእክት አስተላልፏል:- “በሰማያዊ ቀለም ያሸበረቀችና እያብረቀረቁ . . . በቀስታ በሚሽከረከሩ ነጭ ሻሾች የተጠመጠመች እንቁ ትመስላለች። . . . ምሥጢራዊ በሆነ ጥቅጥቅ ያለ ጥቁር ባሕር ውስጥ እንዳለች ትንሽ ሉል ነች።” ፍራንክ ቦርማን የተባለ ጠፈረተኛ ደግሞ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “የጋራ ቤታችን የሆነችው ይህች ፕላኔት እጅግ ውብ ናት። . . . በጣም የሚያስደንቀው ነገር ግን ይህን የመሰለውን ውድ ስጦታ ልናደንቅ የማንችልበት ምክንያት ነው።” ከአፖሎ 8 ጠፈረተኞች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል:- “በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ወደየትኛውም አቅጣጫ ብንመለከት፣ ቀለም ያለው ነገር የምናየው በምድር ላይ ብቻ ነው። በምድር ላይ የባሕሮችን ደማቅ ሰማያዊ ቀለም፣ የደረቁን ምድር ቡናማ ቀለም፣ የዳመናትን ነጫጭ ቀለም መመልከት እንችላለን። . . . በመላው ሰማያት ውስጥ በውበቷ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ናት። በዚህች ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች እንዲህ ያለ በጣም ውድ ንብረት እንዳላቸው አይገነዘቡም።”
እነዚህ አስተያየቶች ትክክል መሆናቸውን በአሁኑ ጊዜ የሚታዩ ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ። ሰዎች ውድ የሆነ ንብረት እንዳላቸው አይገነዘቡም። የሰው ልጅ ከአምላክ ያገኘውን ይህን ውድ ስጦታ ተንከባክቦ ከመያዝ ይልቅ ሲያበላሸውና ሲበክለው ይታያል። ጠፈረተኞቹ ይህንንም ተመልክተዋል። ቻሌንጀር የተባለችው የጠፈር መንኮራኩር የመጀመሪያ በረራ አዛዥ የነበሩት ፖል ዊትስ የሰው ልጅ በምድር ከባቢ አየር ላይ ያደረሰው ጉዳት ከጠፈር ሆኖ ሲታይ “በጣም ያስደነግጣል” ብለዋል። “ይህ ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት ወደ አመዳምነት በመለወጥ ላይ ነው።” ቀጥለውም “ታዲያ ይህ ለእኛ የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው? የራሳችንን ጎጆ በገዛ እጃችን እያፈረስን ነን” ብለዋል። በተለይ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ጥፋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በእነዚህ “የመጨረሻ ቀናት” ውስጥ ነው። ይሖዋ ምድርን በሚያጠፉት ላይ የሚያመጣው ፍርድ በግልጽ አስታውቋል። ‘ምድርን የሚያጠፉትን ያጠፋል።’—ራእይ 11:18
የአምላክ ስጦታ የማይገባው ምስጋና ቢስ ኅብረተሰብ
ለቁሳዊ ነገሮች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ይህ ኅብረተሰብ ሥጋዊ ፍላጎቶቹን ስድ ለመልቀቅ ሲል መንፈሳዊ እሴቶችን ረጋግጧል። ይሖዋ ደስታና እርካታ ያስገኛሉ ብሎ ለሰው ልጆች የሰጣቸው የኑሮ መመሪያዎች ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገው የዘመናችን ዋነኛ ባሕርይ የሆነው ስለ ራስ ብቻ የማሰብ ዝንባሌ ቀዳሚ ቦታ አግኝቷል።
ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-5 ይህ የምንኖርበት ዘመን ምን ያህል እንደከፋ ጥሩ አድርጎ ገልጿል። “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”
ንግድና ማስታወቂያ እጅና ጓንት በመሆን የሁሉ አማረሽነት ባሕርይ እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። ተገቢ የሆኑ ብዙ ማስታወቂያዎች እንዳሉ ሁሉ ጥሩ ያልሆኑ ሌሎች ብዙ ማስታወቂያዎችም አሉ። ኤሪክ ክላርክ ጥሩ ያልሆኑ ማስታወቂያዎችን በማስመልከት ዘ ዎንት ሜከር ላይ ካሰፈሩት አስተያየት ጋር የሚስማማ ነው:- “ማስታወቂያ መጥፎ ነገሮችን በቂ ገንዘብ ለሌላቸው ሰዎች እንዲሸጥ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሚገባው በላይ በጣም ውድ በሆነ ዋጋ እንዲሸጥ ለማድረግም ያገለግላል።” የወርልድ ዋች ባልደረባ የሆኑት አልን ደርኒንግ “አስተዋዋቂዎች የሚያሻሽጡት ሸቀጦችን ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ፈሊጦችን፣ ዝንባሌዎችን፣ ምኞቶችን ጭምር ሲሆን ሸቀጦቻቸውን ምንጊዜም በቃኝ የማይል አምሮት ባላቸው ነፍሳት ላይ ያራግፋሉ።” የማስታወቂያዎች ዓላማ ባሉን ነገሮች እንዳንረካና የማያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት እንድንቋምጥ ማድረግ ነው። ሊረካ የማይችል ጥማት ይፈጥሩብናል፤ ወደማያስፈልግ ብክነት ይመራሉ፤ ምድርን የሚበክሉ የቆሻሻ ቁልል እንዲበራከቱ ያደርጋሉ። መሠሪ የሆነው የማሳመን ችሎታቸው በተጎሳቆለ የድህነት ኑሮ የሚማቅቁትን ምስኪኖች ልብ ሳይቀር ያጠምዳል። ብዙ አስተዋዋቂዎች ሰዎችን እንደሚያሳምሙ ወይም እንደሚገድሉ የታወቁ ሸቀጦችን ይሸጣሉ።
ለእኛ ትልቁ አስፈላጊ ነገር በአምላክ ዘንድ ያለን አቋም ነው። መክብብ 12:13 እንደሚለው “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።” ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ንጹሕ በሆነውና ይሖዋ ባዘጋጀው ገነት ውስጥ ለመኖር ብቁ ይሆናሉ። ኢየሱስ የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቷል:- “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”—ዮሐንስ 5:28, 29
የአምላክ ስጦታ አድናቆት የሚያገኝበት ጊዜ
ምድር ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ አስደናቂ ውበት ትላበሳለች! ይሖዋ የሚከተለውን አስደሳች መግለጫ ሰጥቷል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፣ ባሕርም ወደ ፊት የለም። እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 21:1, 4
እንደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ እንደ መርዛማ ዝቃጭና ጥራጊን የትም መዘርገፍን የመሰሉ የቀደሙ ነገሮች በሙሉ ይወገዳሉ። ከዚያም ጎረቤቶቻቸውን እንደ ራሳቸው የሚወዱ፣ ምድርን ስጦታ አድርጎ የሰጠውን ይሖዋን የሚያወድሱ፣ ምድርን መንከባከብና ገነት አድርጎ መያዝ የሚያስደስታቸው ሰዎች ብቻ በምድር ላይ ይኖራሉ።—ማቴዎስ 22:37, 38፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የፍቅረ ንዋይ ከንቱነት
ኢየሱስ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” ሲል በሰጠው ማስጠንቀቂያ በጣም ወሳኝ የሆነ ሐቅ ገልጿል። (ሉቃስ 12:15) ትልቅ ግምት የሚሰጠው ያለን ነገር ሳይሆን ማንነታችን ነው። ገንዘብ በመሰብሰብ፣ ሀብት በማካበት፣ ሥጋችን የሚያምረውን ደስታ ሁሉ ለመጨበጥ በሚደረገው ሩጫ ተውጦ መቅረት በጣም ቀላል ነው። ይህን ስናደርግ ምንም እንዳላጣንና ሕይወትን እያጣጣምን እንዳለን ሆኖ ይሰማን ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከሕይወት የሚገኘው በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር እያመለጠን ነው።
ምን ያህል አስፈላጊ ነገር እንደቀረብን የምንገነዘበው ወደ ሕይወታችን ፍጻሜ በምንቃረብበት ጊዜ ነው። ያን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው በእርግጥ ትክክል እንደሆነ እንገነዘባለን። ሕይወት በጣም አጭር በመሆኑ ወዲያው እልም እንደሚል ጭጋግ፣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠፋ ጭስና ትንፋሽ፣ ታይቶ ወዲያው እንደሚጠፋ ጥላና ወዲያው እንደሚጠወልግ ሣርና አበባ ነው። ዕድሜያችን የት ደረሰ? ምን አደረግንበት? መጀመሪያውንስ ለምን ተፈጠርን? ሕይወት ማለት ይህ ብቻ ነው? ሁሉ ነገር ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ፣ ነፋስን እንደመከተል ነው?—ኢዮብ 14:2፤ መዝሙር 102:3, 11፤ 103:15, 16፤ 144:4፤ ኢሳይያስ 40:7፤ ያዕቆብ 4:14
ሊሞት የሚያጣጥር በሆስፒታል የተኛ አንድ ሰው ከመስኮቱ ውጭ ያለው ኮረብታ ደማቅ የፀሐይ ብርሃን ፈንጥቆበት ሣሩን፣ አረሞቹን፣ እዚያና እዚህ የበቀሉትን ጥቂት አበቦች፣ ጥራጥሬ ለመለቃቀም አፈሩን ጫር ጫር የሚያደርጉትን ድንቢጦች ይመለከታል። እነዚህ ሁሉ የተለመዱ በመሆናቸው እምብዛም ስሜት የሚቀሰቅሱ አይደሉም። ለሚያጣጥረው ሰው ግን በጣም ያማረ ትዕይንት ነው። ቀላል ግን ከፍተኛ ደስታ የሚሰጡ፣ ጥቃቅን ግን ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ነገሮች እንዳመለጡት ሲያስብ ልቡ በሐዘን ይመታል። ሁሉም ነገር ወዲያው ያልፋል!
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ አስቀምጠውታል:- “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል።” (1 ጢሞቴዎስ 6:7, 8) የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ይበልጥ ፍርጥርጥ አድርገው አስቀምጠውታል:- “ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል። ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም።”—መክብብ 5:15
[ምንጭ]
NASA photo