የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 10/8 ገጽ 12-13
  • የተሳካ ውጤት ያስገኘ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የተሳካ ውጤት ያስገኘ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የሚያስፈልጉ ብቃቶች
  • የትምህርቱ አቀራረብና ሥርዓተ ትምህርት
  • በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይረዳል
  • ከሁሉ ለላቀው ሥራ የሚያስታጥቀን ትምህርት ቤት
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2002
  • ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ ጥቅሞችን ያስገኛል
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመዝገብ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1996
  • ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ምን ጥቅም እናገኛለን?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2004
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1996
g96 10/8 ገጽ 12-13

የተሳካ ውጤት ያስገኘ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት

ይህ ትምህርት ቤት የታደሉ ጥቂት ሰዎች የሚማሩበት ውድ ዋጋ የሚያስከፍል የግል ትምህርት ቤት ወይም ትልቅ ከበሬታ የሚሰጠው ዩኒቨርሲቲ አይደለም። ትምህርት ቤቱ ከተማሪዎቹ የሚጠይቀው ምንም ዓይነት ክፍያ የለም። እንዲያውም በአቅራቢያህ በሚገኝ ቦታ ሳይኖር አይቀርም። ይህ ትምህርት ቤት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የሚካሄደውም የይሖዋ ምሥክሮች በሚሰበሰቡበት ቦታ ነው። በመላው ዓለም አምስት ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በዚህ ትምህርት ቤት ይካፈላሉ።

‘በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ምን ብቃቶች ማሟላት ያስፈልጋል? በትምህርት ቤቱስ ምን ዓይነት ትምህርት ይሰጣል? እንዴትስ ይመራል? በትምህርት ቤቱ የሚካፈሉ ሰዎችስ ምን ጥቅም እያገኙ ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የሚያስፈልጉ ብቃቶች

ማንም ሰው በትምህርት ቤቱ ተገኝቶ ለማዳመጥ የሚችል ቢሆንም ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉት የትምህርት ቤቱ ዋነኛ የመማሪያ መጽሐፍ ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዝዘውን የሥነ ምግባር ብቃት የሚያሟላ አኗኗር ያላቸው መሆን ይገባቸዋል። ስለዚህ ተማሪዎች ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ መንገድ የሚኖሩ መሆን የለባቸውም። ሌቦች፣ ሰካራሞች፣ ሴሰኞች፣ ትንባሆ የሚያጨሱ፣ ወዘተ በትምህርት ቤቱ ሊካፈሉ አይችሉም።— 1 ቆሮንቶስ 6:9-11

በዛሬው ጊዜ ብዙ ትምህርት ቤቶች ምንም ዓይነት የአለባበስ ሕግ የላቸውም። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ግን ልከኛና ንጹሕ የሆነ ልብስ እንዲለብሱ ይፈለግባቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ምንም ዓይነት የዕድሜ ገደብ የለም። ማንበብ የሚችሉ የአራትና የአምስት ዓመት ልጆች በትምህርት ቤቱ ተመድበው ክፍል ይወስዳሉ። በ90ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶችና ሴቶችም ይካፈላሉ።

የትምህርቱ አቀራረብና ሥርዓተ ትምህርት

በትምህርት ቤቱ መገኘት አመቺ እንዲሆን በማሰብ ለ45 ደቂቃ የሚቆየው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት አብዛኛውን ጊዜ የሚደረገው የሳምንቱ አጋማሽ በሆኑ ምሽቶች ነው። የትምህርት ቤቱ አስተማሪ አጭር የአቀባበል ንግግር ካደረገ በኋላ የመጀመሪያው ተናጋሪ ከ10 እስከ 15 ለሚደርሱ ደቂቃዎች ከትምህርት ቤቱ የመማሪያ መጻሕፍት የተዘጋጀ ንግግር ያቀርባል። ከዚያም ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃ ለሚደርስ ጊዜ ያቀረበውን ትምህርት የሚከልስ የቃል ክለሳ ያቀርባል።

ከዚያ ቀጥሎ ብቃት ያለው አስተማሪ ከሁለት እስከ አራት ምዕራፍ የሚደርስ ርዝመት ካለው የሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጎላ ጎላ ያሉ ነጥቦች ያቀርባል። ለዚህ ክለሳ የተመደበው ጊዜ ስድስት ደቂቃ ነው። ይህን ሳምንታዊ የቤት ሥራ ሳያቋርጡ የሚከታተሉ ተማሪዎች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበው ለመጨረስ ይችላሉ።

ጎላ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ነጥቦች ከተከለሱ በኋላ ሦስት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው በአምስት ደቂቃ ውስጥ ክፍላቸውን ያቀርባሉ። አንደኛው ክፍል ለቤት ሥራ ከተሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚቀርብ ንባብ ነው። የቀሩት ሁለት ክፍሎች ተማሪዎች በሙሉ ከሚያነቧቸውና ከሚዘጋጁባቸው የመማሪያ መጻሕፍት የሚቀርቡ ናቸው። ከእያንዳንዱ የተማሪ ንግግር በኋላ የትምህርት ቤቱ አስተማሪ ምስጋናና መሻሻል ስለሚኖርባቸው ነገሮች ሐሳብ ይሰጣል።

የትምህርት ቤቱ አስተማሪ የሚሰጠው ምክር ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ በተባለው ጽሑፍ ላይ የተመሠረተ ነው። እያንዳንዱ ተማሪ ይህን መጽሐፍ በጥንቃቄ እንዲያጠና ይጠበቅበታል። ተማሪው አንድ የተወሰነ የንግግር ባሕርይ እንዲያዳብር ከዚህ መመሪያ መጽሐፍ “ከአድማጮች ጋር ግንኙነት መፍጠርና የማስታወሻ አጠቃቀም፣” “ተስማሚ ምሳሌዎች፣” “መደጋገምና የሰውነት እንቅስቃሴዎች፣” “ማጥበቅና ድምፅን መለዋወጥ” እንደሚሉ ያሉትን የተወሰኑ ምዕራፎች እንዲከልስ ሊጠየቅ ይችላል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተጨማሪ የፊደልና የንባብ ማሻሻያ ክፍል ያካሂዳል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደነዚህ ባሉት የመሠረተ ትምህርት ክፍሎች አማካኝነት ንባብ ተምረዋል፣ ወይም ንባባቸውን ለማሻሻል ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በሜክሲኮ ከ1946 እስከ 1994 ባሉት ዓመታት ከ127,000 የሚበልጡ ሰዎች መጻፍና ማንበብ ለመማር ችለዋል።

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ይረዳል

ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በመላው ዓለም ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛል። የአሥራ ስድስት ዓመቱ ሞራይ “እንዴት ምርምር አድርጌ መረጃ እንደማገኝና የማቀርበውን ንግግር እንዴት እንደምለማመድ ለማወቅ ችዬአለሁ። በዚህም ምክንያት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰጠኝን የቤትና የክፍል ሥራ መሥራት ኬክ እንደመብላት ቀላል ሆኖልኛል” ብሏል።

በሰባት ዓመቱ በአገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል የጀመረው የአሥራ አምስት ዓመቱ ማቲው የሚከተለውን አስተውሏል:- “በትምህርት ቤት ውጤት ረገድ የትምህርት ጓደኞቼ ያላገኙት ብዙ ብልጫ አለኝ። የማጥናትና የማዳመጥ እንዲሁም ንግግር የመስጠት ችሎታ አዳብሬያለሁ።” ፊል የተባለ 17 ዓመት የሆነው ወንድሙ በማከል “ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በራሴ እንድተማመን አስችሎኛል። የተሰጠኝን ሥራ እንደማከናውን አውቃለሁ” ብሏል።

ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በዕድሜ የጎለመሱ ሰዎችንም አስተምሯል። ለመሥሪያ ቤቱ የሥራ አመራር አባላት ገለጻ እስከማድረግ የደረሰው ማይክል እንዲህ ይላል:- “በአገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል በጀመርኩበት ጊዜ በጣም ፈሪ ነበርኩ። አሁን ግን ፍርሃቴን አስወግጃለሁ። ትምህርት ቤቱ የዓይነ አፋርነት ጠባዬን ለማሸነፍ ያስቻለኝን ጤናማ አካባቢ፣ እውቀት፣ ችሎታና ማበረታቻ ሰጥቶኛል።” አንድ ወላጅ ደግሞ “በወጣትነቴ ላገኝ ያልቻልኩትን ትምህርት በማግኘት ላይ እንዳለሁ ይሰማኛል” ብሏል።

በላቲን አሜሪካ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ መንደር የትምህርት መምሪያ አባላት በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተገኝተው የትምህርቱን አሰጣጥ ተመልክተው ነበር። ጎብኚዎቹ አንድ ተናጋሪ የሰጠውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ ከመካከላቸው የአንድ የትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ የሆነው “ይህ መሐይም እንደሆነ የምናውቀው ሰው ለአድማጮች ንግግር ማድረግ ይቅርና [በአፍ መፍቻ ቋንቋው ሳይሆን] በስፓንኛ መናገር መቻሉ በጣም የሚያስደንቅ ነው” ብሏል።

በእርግጥም ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በዓለም ከሚገኙ በጣም ግሩም ትምህርት ቤቶች አንዱ ነው! ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏል። አንድ ወጣት “በትምህርት ቤቱ ለመካፈል የሚያስቡ ሁሉ ሳይውሉ ሳያድሩ እንዲካፈሉ አሳስባለሁ” ብሏል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ በመርዳት ላይ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ