እውነተኛው ሃይማኖት የሚሰጠው ተስፋ
በተፈጥሯችን ስለሚያሳስቡን ወይም ስለሚያስደስቱን ነገሮች ማውራት እንወዳለን። የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን ግሩም መልእክት ለሌሎች በማካፈል የሚደሰቱበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ይህ መልእክት የወደፊቱን ጊዜ፣ ደህንነትን፣ ጤናንና ደስታን ስለመሳሰሉ በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን በጣም ስለሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ለሚነሱት ጥያቄዎች መልስ ይዟል።—ሉቃስ 4:43
ይሁን እንጂ በመጀመሪያ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?
አስደሳች ተስፋ
የአምላክ መንግሥት “የሰላም አለቃ” የሆነው ልጁ ገዥ ሆኖ የተሾመበት መስተዳድር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እሱን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ... የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ... አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።”—ኢሳይያስ 9:6, 7
አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ደግሞ ብዙ ዘመናት ወደፊት አሻግሮ በመመልከት በእኛ የታሪክ ዘመን ስለሚኖሩት ገዥዎች ሲናገር እንዲህ ይላል:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ... እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44
በሰላሙ ገዥ በክርስቶስ የሚተዳደረው ይህ የአምላክ መንግሥት ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያስተማረውን የሚከተለውን ጸሎት ይፈጽማል:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ... መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ መንግሥት ሲመጣ ለምድርም ሆነ ለእኛ የሚያደርጋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙትን ይሖዋ አምላክ ራሱ የሰጣቸውን ተስፋዎች ተመልከት። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በእነዚህ ገጾች ላይ ተዘርዝረዋል።
ከአምላክ የመጣ መልእክት
በአምላክ ቃል ውስጥ የሰፈሩት አስደናቂ ተስፋዎች በምሥጢር መያዝ የለባቸውም። ይህ ደግሞ ስለ ሃይማኖት መወያየትን ወደሚመለከተው ርዕሰ ጉዳይ ይመልሰናል። ኢየሱስ ይህ የአሁኑ ሥርዓት ከማክተሙ በፊት ተከታዮቹ ቅድሚያውን በመውሰድ ስለ አምላክ መንግሥት እንደሚሰብኩ አስቀድሞ ተናግሯል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8
የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ እያወጁ ያሉት ይህን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት ነው። ከዚህ መጽሔት ጋር እየታተመ የሚወጣው መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት በ130 ቋንቋዎች የሚታተም ሲሆን በእያንዳንዱ እትም በሚዘጋጁት ከ22 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ቅጂዎች በእያንዳንዳቸው ላይ “የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ” የሚሉ ቃላት ተጽፈው ይገኛሉ።
እንደ ጥበበኛ ሰው መጠን ሕይወትህን በተመለከተ በእውቀት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች መውሰድ ይኖርብሃል። (ምሳሌ 18:13) እንግዲያው ስለ ክብራማው የአምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ለአንተ ምን ሊያስገኝልህ እንደሚችል በግለሰብ ደረጃ ተጨማሪ እውቀት እንድትቀስም እንጋብዝሃለን። ይህን ማድረግ እንድትችል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ውይይት ከማድረግ ወደ ኋላ አትበል። ከእንዲህ ዓይነቱ ውይይት ይበልጥ እውቀት የሚጨምር፣ ስሜት የሚማርክና የሚጠቅም ውይይት ሊኖር አይችልም።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ገነት ስለምትሆነው ምድር የተሰጡ ተስፋዎች
በምድር ላይ ፍጹም ሰላም ይሰፍናል። “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው።”—መዝሙር 72:7, 8
ሙታን እንኳ ሳይቀሩ ዳግመኛ ሕያው ይሆናሉ። “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን [ይነሣሉ]።”—ሥራ 24:15
የሰው ልጆች ፍጹም ጤና አግኝተው ለዘላለም ይኖራሉ። “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።”—ራእይ 21:3,4
ሰዎች የየራሳቸውን ቤቶች ሠርተው ይኖራሉ። “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ።”—ኢሳይያስ 65:21
የተትረፈረፈ ምግብ ይኖራል። “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ።”—መዝሙር 72:16 “የ1980 ትርጉም”