ዓይነ ሥውር ብሆንም ጠቃሚ ድርሻ ማበርከትና ደስተኛ መሆን ችያለሁ
ፖሊቲሚ ቬኔትስያኖስ እንደተናገረችው
ከሁለት ወንድሞቼና ከአንዲት እህቴ እንዲሁም ከአንዲት የአጎቴ ልጅ ጋር እየተጫወትን ሳለ አንድ አነስተኛ ነገር በመስኮት በኩል ተወርውሮ ገባ። የእጅ ቦምብ ነበር። ቦምቡ ሲፈነዳ ሁለቱ ወንድሞቼና እህቴ ሞቱ። እኔ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ዓይነ ሥውር ሆንኩ።
ዕለቱ ሐምሌ 16, 1942 ሲሆን ገና የአምስት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ለተወሰኑ ቀናት በተደጋጋሚ ራሴን እስት ነበር። ስነቃ ስለ ወንድሞቼና ስለ እህቴ ጠየቅኩ። እንደሞቱ ሲነገረኝ ምነው እኔም ሞቼ ቢሆን ኖሮ ብዬ ተመኘሁ።
እኔ ስወለድ ወላጆቼ ይኖሩ የነበረው በአቴንስ ወደብ በፒሬፍስ አቅራቢያ በምትገኝ ሳላሚስ በተባለች የግሪክ ደሴት ላይ ነበር። ድሆች የነበርን ብንሆንም እንኳ ሕይወታችን ሰላም የሰፈነበት ነበር። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1939 ሲጀምር ይህ ሁሉ አከተመለት። አባቴ በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የሚሠራ መርከበኛ ነበር። ብዙውን ጊዜ ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ከሚጠቀሙባቸው ሰርጓጅ መርከቦች፣ የጦር መርከቦች፣ ቶርፒዶዎችና ቦምቦች ማምለጥ ነበረበት። ግሪክ በፋሺስቶችና በናዚዎች ቁጥጥር ሥር ወድቃ ነበር።
ለአምላክ ጥላቻ አደረብኝ
በጦርነቱ ወቅት በነበሩት አስከፊ ሁኔታዎች ሳቢያ እናቴ አራተኛ ልጅዋንም በሞት አጣች። ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ ከመውደቋም በላይ ሳንባ ነቀርሳ ያዛትና ስድስተኛ ልጅዋን ከወለደች በኋላ በነሐሴ 1945 አረፈች። አጥባቂ ሃይማኖተኛ የሆኑት ጎረቤቶቻችን የአምላክ ቁጣ ነው ማለት ጀመሩ። አንዳንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት እኛን ለማፅናናት ብለው አምላክ ወንድሞቼንና እህቶቼን ወደ ሰማይ የወሰዳቸው ትንንሽ መላእክት እንዲሆኑ ነው አሉን። ሆኖም ይህ ከማጽናናት ይልቅ ሐዘናችንን አባባሰው።
አባቴ በጣም ተበሳጨ። አምላክ በሚልዮን የሚቆጠሩ መላእክት እያሉት አራት ልጆችን ከአንድ ድሃ ቤተሰብ ነጥቆ የሚወስደው ለምንድን ነው? እነዚህ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነቶች ጠንካራ የሆነ ፀረ አምላክና ፀረ ሃይማኖት ስሜት አሳደሩበት። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ራሱን ከሃይማኖት ለማግለል ወሰነ። ለሥቃያችንና ለመከራችን ተጠያቂው አምላክ እንደሆነ በመግለጽ አምላክን እንድጠላውና አቃልዬ እንድመለከተው አደረገኝ።
ከብረት በተሠራ ቤት ውስጥ እንዳለ አውሬ
በ1945 እናቴ ከሞተች በኋላ ብዙም ሳይቆይ አባቴም ሳንባ ነቀርሳ ያዘውና ሆስፒታል ገባ። ትንሿ እህቴ ደግሞ ወደ ሕፃናት ማሳደጊያ ተወሰደች። ከጊዜ በኋላ አባቴ ከሆስፒታል ወጥቶ እህቴን ሊያመጣ ወደ ሕፃናት ማሳደጊያው ሲሄድ እንደሞተች ተነገረው። እኔም ዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት እንድገባ ተደረገና ለስምንት ዓመታት ያህል እዚያው ቆየሁ። መጀመሪያ ላይ ቅስሜ ተሰብሮ ነበር። በተለይ ወዳጅ ዘመዶች ለጥየቃ በሚመጡባቸው ቀኖች በጣም ይከፋኝ ነበር። አብዛኞቹ ዓይነ ሥውር ጓደኞቼ የሚጠይቃቸው ሰው ይመጣ ነበር። እኔ ግን አንድም ጠያቂ አልነበረኝም።
ልክ ከብረት በተሠራ ቤት ውስጥ እንዳለ አውሬ ሆንኩኝ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ቀንደኛ በጥባጭ ሆንኩ። በዚህም ምክንያት ተገረፍኩና ረባሽ ልጆች በሚቀመጡበት ወንበር ላይ እንድቀመጥ ተደረገ። ብዙ ጊዜ የራሴን ሕይወት የማጥፋት ሐሳብ ወደ አእምሮዬ ይመጣ ነበር። ሆኖም እያደር ራሴን መቻልን መማር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ብዙውን ጊዜ ዓይነ ሥውር የትምህርት ቤት ጓደኞቼ ልብሳቸውን ሲለብሱ ወይም አልጋቸውን ሲያነጥፉ በማገዝ ራሴን ማስደሰት ጀመርኩ።
ቄሶቹ አምላክ ዓይነ ሥውር ያደረጋችሁ ወላጆቻችሁ በፈጸሙት ከባድ ኃጢአት ምክንያት ነው ይሉን ነበር። ይህ ደግሞ አምላክ ክፉና ጨካኝ እንደሆነ አድርጌ በማሰብ ይበልጥ እንድጠላው አደረገኝ። የሙታን መናፍስት በሕያዋን ዙሪያ እያንዣበቡ ያስጨንቃሉ የሚለው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ያስፈራኝና ያበሳጨኝ ነበር። በመሆኑም በሞት የተለዩኝን ወንድሞቼንና እህቶቼን እንዲሁም እናቴን እወዳቸው የነበረ ቢሆንም እንኳ “መንፈሳቸውን” እፈራ ነበር።
ከአባቴ ያገኘሁት እርዳታ
ከጊዜ በኋላ አባቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። የሥቃይና የሞት ምንጭ ይሖዋ ሳይሆን ሰይጣን መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲማር በጣም ተገረመ። (መዝሙር 100:3፤ ያዕቆብ 1:13, 17፤ ራእይ 12:9, 12) ይህ የእውቀት ብርሃን የፈነጠቀለት አባቴ ብዙም ሳይቆይ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ከዚያም መንፈሳዊ ዕድገት አደረገና በ1947 ተጠመቀ። ይህ ከመሆኑ ከጥቂት ወራት በፊት አግብቶ የነበረ ሲሆን አንድ ወንድ ልጅ ወልዷል። ውሎ አድሮ አዲሷ ሚስቱም ይሖዋን ማምለክ ጀመረች።
አሥራ ስድስት ዓመት ሲሞላኝ ከነበርኩበት የዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤት ወጣሁ። ወዳጃዊ መንፈስ ወደሰፈነበት ክርስቲያን ቤተሰብ መመለስ ምንኛ የሚያጽናና ነበር! የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብለው በሚጠሩት ፕሮግራማቸው ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። በትኩረት ባልከታተልም እንኳ ለእነሱ በነበረኝ አክብሮትና በይሉኝታ ስሜት በጥናቱ ላይ እገኝ ነበር። ለአምላክና ለሃይማኖት የነበረኝ ጥላቻ እንዳለ ነበር።
ቤተሰቡ የእግዚአብሔር መንገድ ፍቅር ነው የተባለውን ቡክሌት እያጠና ነበር። መጀመሪያ ላይ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር። በኋላ ግን አባቴ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ ሲያብራራ ሰማሁ። ይህ ትኩረቴን ሳበው። መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ገልጠው መክብብ 9:5, 10ን አነበቡ:- “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።”
የነበረኝ ፍርሃት መሠረተ ቢስ እንደሆነ መገንዘብ ጀመርኩ። በሞት የተለዩኝ እናቴ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ ሊጎዱኝ እንደማይችሉ ተረዳሁ። በኋላ ውይይቱ ወደ ትንሣኤ ርዕስ ተሸጋገረ። ጆሮዬን ተክዬ መስማት ጀመርኩ። በክርስቶስ ግዛት ሥር ሙታን እንደገና ሕያው እንደሚሆኑ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ስሰማ ልቤ በደስታ ተሞላ! (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:12, 13) አሁን ጥናቱ ስሜቴን በጣም ይማርከው ጀመር። የቤተሰብ ጥናቱ የሚካሄድበትን ቀን በጉጉት መጠባበቅ ጀመርኩ። ዓይነ ሥውር ብሆንም እንኳ በደንብ እዘጋጅ ነበር።
መንፈሳዊ ዓይኔ በራ
ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀቴ እየጨመረ ሲሄድ ስለ አምላክና ከሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ቀደም ሲል የነበሩኝ የተሳሳቱ አመለካከቶች ተወገዱ። አምላክ እኔንም ሆነ ማንኛውንም ሰው ዓይነ ሥውር እንደማያደርግና ለክፉ ነገሮች ሁሉ መንሥኤው ባላጋራው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ተረዳሁ። በአላዋቂነቴ የተነሣ አምላክን ተጠያቂ ሳደርግ በመኖሬ እጅግ ተጸጸትኩ! በከፍተኛ ጉጉት ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት መቅሰሜን ቀጠልኩ። ቤታችን ከመንግሥት አዳራሹ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ይርቅ የነበረ ቢሆንም በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ተሳትፎ አደርግ ነበር። በተጨማሪም ማየት ባልችልም እንኳ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት እካፈል ነበር።
ለዓይነ ሥውርነት የዳረገኝ አሳዛኝ ገጠመኝ ከተከሰተ ከ16 ዓመታት በኋላ በሐምሌ 27, 1958 ስጠመቅ የተሰማኝ ደስታ ወሰን አልነበረውም! ሕይወቴ ከመታደሱም በላይ በተስፋና በብሩህ አመለካከት ተሞላ። አፍቃሪ ሰማያዊ አባቴን በማገልገል ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ጀመርኩ። ስለ እሱ ማወቄ ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ ያወጣኝ ከመሆኑም በላይ ዓይነ ሥውርነቴንና ያስከተለብኝን ችግር በቆራጥነትና በተስፋ እንድቋቋመው የሚያስችል ድፍረት እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ክብራማውን ምሥራች ለሌሎች በመስበክ በየወሩ 75 ወይም ከዚያ በላይ ሰዓት አሳልፍ ነበር።
የትዳር መፍረስ
በ1966 የእኔው ዓይነት ግብ ካለው ሰው ጋር ተጋባሁ። ሁለታችንም በስብከቱ ሥራ የምናደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ ለማድረግ እየጣርን ስለነበር ትዳራችን አስደሳች እንደሚሆን ገምተን ነበር። በአንዳንድ ወራት ለዚህ ሕይወት አድን ሥራ ብዙ ሰዓታት እናውል ነበር። በማዕከላዊ ግሪክ በሊቫዲያ አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ ገለልተኛ ሥፍራ ተዛወርን። እዚያ በነበርንባቸው ከ1970 እስከ 1972 ባሉት ዓመታት ምንም እንኳ በወቅቱ ግሪክ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በጨበጠው በጨቋኙ ወታደራዊ አስተዳደር ሥር የነበረች ቢሆንም በርከት ያሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን እንዲማሩና የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ መርዳት ችለናል። በተጨማሪም በዚያ ቦታ የነበረውን አንድ ትንሽ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የመርዳት አጋጣሚ አግኝተን ነበር።
ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ባለቤቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱንና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን ችላ ማለት ጀመረ። በመጨረሻም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከናካቴው እርግፍ አድርጎ ተወ። ይህ ሁኔታ በትዳራችን ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት በመፍጠሩ በ1977 ተፋታን። በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ደረሰብኝ።
አስደሳችና ፍሬያማ ሕይወት
ከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ይዞኝ በነበረበት በዚህ ወቅትም ይሖዋና ድርጅቱ እንደገና ደግፈው አቁመውኛል። አንድ አፍቃሪ ክርስቲያን ወንድም የቀድሞ ባልሽ የፈጠረው ሁኔታ ደስታሽን እንዲሰርቅብሽ ከፈቀድሽ በተዘዋዋሪ መንገድ የእሱ ባሪያ ሆነሻል ማለት ነው ሲል ገለጸልኝ። እንዲህ ከሆነ የደስታዬ ቁልፍ ያለው እርሱ ጋር ነው ማለት ነው። በዚህ ወቅት አንዲት በዕድሜ የገፋች የክርስቲያን ጉባኤ አባል የስብከት ችሎታዋን ማሻሻል ትችል ዘንድ እርዳታ እንዲደረግላት ጠየቀች። ብዙም ሳይቆይ ከሁሉ የላቀ ደስታ ባስገኘልኝ የአገልግሎት ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠመድኩ!
ከዚያም አንድ ክርስቲያን “ተጨማሪ አገልጋዮች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ በመሄድ እርዳታ ማበርከትሽን መቀጠል ትችያለሽ። ይሖዋ አምላክ እንደ ምልክት መስጫ መብራት ሊጠቀምብሽ ይችላል” ሲል ሐሳብ አቀረበልኝ። ይሖዋ አምላክ አንድን ዓይነ ሥውር ሰው “እንደ ምልክት መስጫ መብራት” ሊጠቀምበት የሚችል መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው! (ፊልጵስዩስ 2:15) ወዲያውኑ አቴንስን ለቅቄ በጣት የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ባሉባት በደቡባዊ ኤቭያ በምትገኘው በአማሪንቶስ መንደር መኖር ጀመርኩ። እዚያ ባሉት ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ቤት ለመሥራትና የሚያስፈልጉኝን ነገሮች በበቂ ሁኔታ ለማሟላት ቻልኩ።
በአሁኑ ጊዜ በዚህ ቦታ ከ20 ዓመታት በላይ ያሳለፍኩ ሲሆን በየዓመቱ በርከት ላሉ ወራት በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ተሳትፎ ሳደርግ ቆይቻለሁ። ከይሖዋ ባገኘሁት ብርታት ከቤት ወደ ቤት መሄድን፣ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናትንና በመንገድ ላይ ሰዎችን ማነጋገርን ጨምሮ በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች መካፈል ችያለሁ። በአሁኑ ጊዜ ስለ ፈጣሪያችን የመማር ፍላጎት ያደረባቸውን አራት ሰዎች የማስጠናት መብት አግኝቻለሁ። ከ20 ዓመታት በፊት በዚህ ሥፍራ የነበሩት በጣት የሚቆጠሩ ወንድሞች ቁጥር አድጎ በአሁኑ ጊዜ በዚህ አካባቢ ሦስት ጉባኤዎች ተቋቁመው በመመልከቴ የተሰማኝ ደስታ ወደር የለውም!
አንድም ስብሰባ እንዲያመልጠኝ ስለማልፈልግ በሳምንት ሁለት ጊዜ ወደ ስብሰባው ቦታ ለመድረስ ብቻ ከ30 ኪሎ ሜትር በላይ እጓዛለሁ። በስብሰባዎች ላይ ተናጋሪውን ማየት ስለማልችል አእምሮዬ ሽርሽር መሄድ ሲጀምር የብሬል ማስታወሻ ደብተሬን በመጠቀም አጠር አጠር ያሉ ማስታወሻዎች እይዛለሁ። በዚህ መንገድ ጆሮዬም ሆነ አእምሮዬ በንግግሩ ላይ እንዲያተኩር አደርጋለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ከጉባኤ ስብሰባዎቹ መካከል አንዱ የሚካሄደው እኔ ቤት ውስጥ ነው። በአቅራቢያ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት በሚባለው በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ይመጣሉ። ሁልጊዜ ሌሎች እየመጡ እንዲጠይቁኝ ከመጠበቅ ይልቅ ራሴ ቅድሚያውን በመውሰድ ቤታቸው ድረስ ሄጄ እጠይቃቸዋለሁ። ይህም እርስ በርስ ለመበረታታት አስችሎናል።—ሮሜ 1:12
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ከአባቴ ጋር ስኖር እንደ ዓይነ ሥውር ልጅ አድርጎ አይመለከተኝም ነበር። የተለያዩ ነገሮችን እንዴት በእጄ መሥራት እንደምችል ለማስተማር ሲል በትዕግሥትና በጽናት ብዙ ጊዜ ያጠፋ ነበር። ይህ ተግባራዊ ማሠልጠኛ አትክልቶቼንና ያሉኝን ጥቂት ከብቶች በሚገባ መንከባከብ አስችሎኛል። የቤቴን ንጽሕና በመጠበቅና ምግብ በማዘጋጀት የቤት ውስጥ ሥራዎቼን በትጋት አከናውናለሁ። ተራ በሆኑ ነገሮች ማለትም ባሉን ነገሮች ብቻ ደስታና እርካታ ልናገኝ እንደምንችል ተምሬያለሁ። በተቀሩት አራት የስሜት ሕዋሳቴ ይኸውም በመስማት፣ በማሽተት፣ በመቅመስና በመዳሰስ ብዙ ነገሮች ማከናወን ችያለሁ። ይህ ደግሞ ወደር የሌለው ደስታ ይሰጠኛል። ይህ ለሌሎች ሰዎችም ጥሩ ምሥክርነት ሆኖላቸዋል።
አምላኬ ያደረገልኝ ድጋፍ
የአቅም ገደብ ቢኖርብኝም እንኳ አዎንታዊ አመለካከት ያለኝ መሆኑና ራሴን ችዬ መኖሬ ብዙዎችን ያስገርማቸዋል። ከሁሉም በላይ ለዚህ መመስገን ያለበት “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ብርሃኔን ካጣሁ በኋላ ብዙ ጊዜ ራሴን የመግደል ሐሳብ ወደ አእምሮዬ ይመጣ ነበር። በመሆኑም ይሖዋንና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ባላውቅ ኖሮ ዛሬ በሕይወት መኖሬን እጠራጠራለሁ። ፈጣሪያችን የማየት ችሎታን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ ስጦታዎችንም እንደሰጠን ተገንዝቤያለሁ። እናም ውጤታማ በሆነ መንገድ ከተጠቀምንባቸው ደስተኞች መሆን እንችላለን። በአንድ ወቅት ምሥክሮች እኔ ባለሁበት መንደር ውስጥ ሲሰብኩ አንዲት ሴት “ይህን ሁሉ ሥራ እንድታከናውን የሚረዳት አምላኳ ነው!” ብላ ስለ እኔ ነግራቸዋለች።
የገጠሙኝ ፈተናዎች ሁሉ ከአምላክ ጋር ይበልጥ አቀራርበውኛል። ይህ እምነቴን በጣም አጠንክሮታል። ሐዋርያው ጳውሎስም “የሥጋዬ መውጊያ” (የዓይኑን ችግር ማመልከቱ ሳይሆን አይቀርም) ብሎ የጠራው ችግር እንደነበረበት አስብ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:7፤ ገላትያ 4:13) ይህ በምሥራቹ ሥራ ‘ከመትጋት’ አላገደውም። ልክ እንደ እሱ እኔም “እንግዲህ . . . በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። . . . ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና” ማለት እችላለሁ።—ሥራ 18:5፤ 2 ቆሮንቶስ 12:9, 10
ከሁሉም በላይ ደግሞ ውድ እናቴን፣ እህቶቼንና ወንድሞቼን በትንሣኤ አማካኝነት በገዛ ዓይኔ ላያቸው እችላለሁ የሚል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ ያለኝ መሆኔ አዎንታዊና በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረብኝ ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “የዕውሮች ዓይን ይገለጣል” እንዲሁም “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን [ይነሣሉ]” የሚል ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 35:5፤ ሥራ 24:15) እንዲህ ዓይነቶቹ ተስፋዎች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝና በአምላክ መንግሥት አስተዳደር ሥር የሚኖረውን ክብራማ ጊዜ በጉጉት እንድጠባበቅ አድርገውኛል!
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ አባቴ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጥ ቤቴ ውስጥ ሆኜ ስሠራ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአንዲት እህት ጋር ሳገለግል