የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 5/8 ገጽ 14-15
  • አስደናቂው ኒም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አስደናቂው ኒም
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በዛፍነቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች
  • ተባዮች አይወዱትም
  • “የገጠር መድኃኒት ቤት”
  • ጥርስ መፋቂያ እንጨት
    ንቁ!—2003
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2005
  • ኬሚካላዊ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ተባዮችን በመግደል ብቻ አይወሰኑም
    ንቁ!—1999
  • አስገራሚው የሦስት አፅቄዎች ዓለም
    ንቁ!—2000
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 5/8 ገጽ 14-15

አስደናቂው ኒም

በናይጄርያ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በሕንድ አገር የሚኖሩ ሕዝቦች ኒም የተባለውን ዛፍ “የገጠር መድኃኒት ቤት” ሲሉ ይጠሩታል። በዚህች አገር የሚኖሩ ሰዎች ለበርካታ መቶ ዓመታት ይህንን ዛፍ ለሥቃይ፣ ለትኩሳትና ለሌሎች የተለያዩ በሽታዎች ማስታገሻነት ሲገለገሉበት ቆይተዋል። ኒም ደማቸውን እንደሚያጠራላቸው ስለሚያምኑ ብዙ ሂንዱዎች አንድን አዲስ ዓመት ሲጀምሩ ጥቂት የኒም ቅጠሎችን ያኝካሉ። በተጨማሪም የዚህን ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጠው ጥርሳቸውን ይፍቁበታል፣ ቅጠሉን ጨምቀው ለቆዳ ሕመም መድኃኒትነት ይጠቀሙበታል፣ ሰውነታቸውን እንዲያጠነክርላቸውም እንደ ሻይ አፍልተው ይጠጡታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሳይንቲስቶች ለኒም ዛፍ የተለየ ትኩረት ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ኒም ኤ ትሪ ፎር ሶልቪንግ ግሎባል ፕሮብለምስ የሚል ርዕስ የተሰጠው አንድ ሳይንሳዊ ሪፖርት እንዳስጠነቀቀው “ኒም ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልባቸው መንገዶች በጣም ብዙ ቢሆኑም እስከ አሁን በእርግጠኝነት የታወቀ ነገር የለም። ስለዚህ ተክልና ይህ ተክል ሊኖረው ስለሚችለው አገልግሎት የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ያደረባቸው ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ አሁን ባሉበት ደረጃ ለተስፋቸው ያገኙት ድጋፍና ማስረጃ ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ አለመሆኑን ያምናሉ።” ይሁን እንጂ ሪፖርቱ እንዲህ ሲል አክሎ ይገልጻል:- “ለሁለት አሥርተ ዓመታት የተደረገው ምርምርና ጥናት ይህ ገና በስፋት ያልታወቀ ተክል ለድሆችም ሆነ ለበለጸጉ አገሮች በብዙ መስኮች ከፍተኛ ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችል ስለመሆኑ ተስፋ የሚሰጥ ውጤት አስገኝቷል። በጣም ጠንቃቃ የሆኑ ተመራማሪዎች ሳይቀሩ ‘ኒም ተአምረኛ ተክል ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ዛፍ ነው’ ማለት ጀምረዋል።”

በዛፍነቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች

በሐሩር ክልል የሚገኘው ኒም ከጥቁር እንጨት የዛፍ ዓይነቶች የሚመደብ ነው። ቁመቱ እስከ 30 ሜትር ሊደርስ የሚችል ሲሆን ውፍረቱ እስከ 2.5 ሜትር ሊደርስ ይችላል። ቅጠሉ ከዓመት እስከ ዓመት ስለማይረግፍ ሙሉውን ዓመት በጥላነት ሊያገለግል ይችላል። እድገቱ ፈጣን ከመሆኑም ሌላ ብዙ እንክብካቤ አይፈልግም። በጣም ለም ባልሆነ አፈር ላይ ሳይቀር ሊያድግ ይችላል።

ይህ ዛፍ በዚህ መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ ምዕራብ አፍሪካ የገባው በጥላነት እንዲያገለግልና የሰሃራ በረሃ ወደ ደቡብ የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲገታ ታስቦ ነበር። በተጨማሪም ደን አልሚዎች ይህን ዛፍ በፊጂ፣ በሞሪሽየስ፣ በሳውዲ አረብያ፣ በማዕከላዊና ደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በካሪቢያን ደሴቶች አስፋፍተዋል። በዩናይትድ ስቴትስ በአሪዞና፣ በካሊፎርንያና በፍሎሪዳ ደቡባዊ ክፍሎች የሙከራ ተክል ጣቢያዎች ተቋቁመዋል።

የኒም ዛፍ በሞቃት የአየር ጠባይ ከዓመት እስከ ዓመት በጥላነት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለማገዶነትም ሊያገለግል ይችላል። ከዚህም በላይ በምስጥ የማይደፈረው እንጨቱ ለግንባታና ለአናጺነት ሥራ በጣም ጠቃሚ ነው። ስለዚህ ኒም በዛፍነቱ በሚሰጠው አገልግሎት ብቻ እንኳን ቢመዘን ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው። ይሁን እንጂ አገልግሎቱ በዚህ ብቻ አይወሰንም።

ተባዮች አይወዱትም

ሕንዳውያን የኒም ቅጠል አስቸጋሪ ነፍሳትን እንደሚያባርር ከብዙ ዘመን በፊት ጀምሮ ስለሚያውቁ በአልጋቸው፣ በመጽሐፎቻቸው፣ በቆሻሻ ማጠራቀሚያዎቻቸውና በቁም ሣጥኖቻቸው ውስጥ የኒም ቅጠሎችን ያስቀምጣሉ። በ1959 አንድ ጀርመናዊ ኤንትሞሎጂስት እና ተማሪዎቻቸው በሱዳን አገር በደረሰ ከፍተኛ የአንበጣ ወረራ ምክንያት ከኒም ቅጠሎች በስተቀር የሁሉም ዛፎች ቅጠሎች ሙልጭ ብለው እንዳለቁ ከተመለከቱ በኋላ በኒም ዛፍ ላይ ምርምር ማድረግ ጀመሩ።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሳይንቲስቶች በኒም ውስጥ የሚገኘው እጅግ የተወሳሰበ ኬሚካላዊ ቅንብር የተለያዩ የምስጥ ዝርያዎችን፣ ጥገኛ ትሎችን፣ ባክቴሪያዎችን፣ ፈንገሶችንና በርካታ ቫይረሶችን ጨምሮ ከ200 የሚበልጡ የነፍሳት ዝርያዎችን የመዋጋት ችሎታ እንዳለው ደርሰውበታል። በአንድ ሙከራ ተመራማሪዎች በአንድ ዕቃ ውስጥ የአኩሪ አተር ቅጠሎችንና ጃፓኒዝ ቢትልስ የተባሉትን የጥንዚዛ ዝርያዎች አንድ ላይ አስቀመጡ። በእያንዳንዱ ቅጠል ግማሽ ላይ የኒም ጭማቂ ተረጭቷል። ጥንዚዛዎቹ ያልተረጨውን የቅጠል ወገን ሙልጭ አድርገው ሲበሉ የተረጨውን ወገን ግን ንክች አላደረጉም። እንዲያውም የተረጨውን የቅጠል ክፍል ከመብላት ይልቅ በረሐብ ሞተዋል።

እንደነዚህ ያሉት ሙከራዎች አንዳንዶቹን ሰው ሠራሽ ፀረ ተባዮች ሊተካ የሚችል፣ ብዙ ወጪ የማይጠይቅና መርዛምነት የሌለው ፀረ ተባይ ማዘጋጀት እንደሚቻል አመልክተዋል። ለምሳሌ ያህል በኒካራጉዋ ገበሬዎች 80 ግራም የሚመዝን የተወቀጠ የኒም ፍሬ በአንድ ሊትር ውኃ ከበጠበጡ በኋላ 12 ሰዓት ያህል እንዲቆይ ያደርጋሉ። ፍሬውን አጥልለው ከለዩ በኋላ ውኃውን በሰብሎቻቸው ላይ ይረጫሉ።

የኒም ውጤቶች አብዛኞቹን ነፍሳት ወዲያው በቅጽበት አይገድሉም። የኒም ውጤቶችን በመጠቀም የሚካሄደው ርጭት የነፍሳቱን የአኗኗር ሥርዓት ስለሚያናጋ ቀስ በቀስ መመገብ፣ መራባትና እድገት ማድረግ ያቅታቸዋል። ሆኖም የኒም ውጤቶች በተባዮች ላይ ጉዳት ቢያመጡም በአእዋፍ፣ በደመ ሞቃት እንስሳትና በሰዎች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የሚያስከትሉ አይመስልም።

“የገጠር መድኃኒት ቤት”

ለሰዎች የሚሰጠው ጥቅም በዚህ ብቻ አያበቃም። በዘሮቹና በቅጠሎቹ ውስጥ የፀረ ባክቴሪያነት፣ የፀረ ቫይረስነትና የፀረ ፈንገስነት ባሕርይ ያላቸው ውህዶች ተገኝተዋል። ኒም የሰውነት ብግነት፣ ከፍተኛ የደም ግፊትና አልሰር መከላከል ሳይችል አይቀርም የሚሉ ሐሳቦች ቀርበዋል። ከኒም የተጨመቁ መድኃኒቶች የስኳር በሽታንና ወባን እንደሚከላከሉ ይነገራል። ቀጥሎ የተመለከቱት ደግሞ ኒም ይኖረዋል ከሚባሉት ጥቅሞች አንዳንዶቹ ናቸው:-

ለሦስት አፅቄዎች ማባረሪያ። በኒም ውስጥ ከሚገኙት ቅመሞች አንዱ የሆነው ሳላኒን ተብሎ የሚጠራው ቅመም አንዳንድ ተናካሽ ሦስት አፅቄዎችን የማባረር ኃይል አለው። ከኒም ዘይት የሚሠራ የዝንብና የወባ ትንኝ ማባረሪያ ገበያ ላይ ውሏል።

ለጥርስ ንጽሕና መጠበቂያ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕንዳውያን በየጠዋቱ የኒም ቅርንጫፍ ቆረጥ አድርገው ጫፉን አኝከው ካለሰለሱ በኋላ ጥርሳቸውንና ድዳቸውን ይፍቁበታል። በእንጨቱ ቅርፊት ውስጥ የሚገኙ ውህዶች ብክለት የመከላከል ችሎታ እንዳላቸው በጥናት የተረጋገጠ በመሆኑ ይህን ማድረጋቸው በጣም ጠቃሚ ነው።

ለወሊድ መቆጣጠሪያ። የኒም ዘይት የወንዴ ዘር ሴሎችን የመግደል ኃይለኛ ችሎታ ስላለው በቤተ ሙከራ የሚገኙ እንስሳትን የመራባት ችሎታ ቀንሷል። በዝንጀሮዎች ላይ የተደረጉ ሙከራዎች በወንዶች የሚወሰድ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት ከኒም ከሚገኙ ውህዶች ማዘጋጀት እንደሚቻል አመልክተዋል።

በእርግጥ ኒም ተራ ዛፍ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ዛፍ ገና ያልታወቁ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ኒም ተባዮችን በመቆጣጠር፣ ጤንነት በማሻሻል፣ በደን ልማትና ምናልባትም የሕዝብ ብዛትን በመገደብ ረገድ ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ዛፍ ሆኗል። ብዙ ሰዎች ይህን አስደናቂ ዛፍ “አምላክ ለሰዎች የሰጠው ስጦታ” ብለው መጥራታቸው የሚያስደንቅ አይደለም።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የኒም ዛፍ እና ቅጠሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ