የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ሦስት ነገሥታት ኢየሱስን በቤተ ልሔም ጎብኝተውት ነበርን?
ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ የአይሁድ ንጉሥ እንደሆነ አድርገው በመመልከት አክብሮታቸውን ለመግለጽ ታላላቅ ሰዎች ከምሥራቅ ወደ ቤተ ልሔም መጥተው ነበር። የገናን በዓል የሚያከብሩ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች እስካሁንም ድረስ ይህን ጉብኝት ያስቡታል።
በአንዳንድ ቦታዎች ሰዎች እነዚህ ከምሥራቅ የመጡ ጎብኚዎች ለጨቅላው ሕፃን ለኢየሱስ ስጦታዎች ይዘው የቀረቡ ሦስት ነገሥታት እንደሆኑ አድርገው የሚያሳዩ የኢየሱስን ልደት የሚያንጸባርቁ ምስሎች ይሠራሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ ልጆች የእነዚህን “ቅዱስ ነገሥታት” አልባሳት ለብሰው ሰፈራቸው ውስጥ ይዞራሉ። ይህ ሁኔታ የተፈጸመው ከ20 መቶ ዘመናት በፊት ቢሆንም በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች አሁንም ድረስ እነዚህን ያልተለመዱ ዓይነት ጎብኚዎች ያስታውሷቸዋል። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ?
ነገሥታት ነበሩ?
የዚህ ክንውን ታሪካዊ ዘገባ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ . . . አንድ ቀን ኮከብ ቆጣሪዎች ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡና እንዲህ ሲሉ ጠየቁ:- ‘የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት ነው? ኮከቡን ከመውጫው አይተን አክብሮታችንን ልንገልጽለት መጥተናል።’” (ማቴዎስ 2:1, 2፣ ኒው አሜሪካን ባይብል) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እነዚህን ጎብኚዎች ነገሥታት ሳይሆን ከምሥራቅ የመጡ ኮከብ ቆጣሪዎች ብሎ የሚጠራቸው ለምንድን ነው?
ቅዱሳን ጽሑፎች እዚህ ቦታ ላይ የተጠቀሙት ብዙ ቁጥር የሚያመለክተውን ማጎስ የተባለውን የግሪክኛ ቃል ነው። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ቃል “ጠቢባን፣” “ኮከብ ቆጣሪዎች፣” ወይም “ከዋክብትን የሚከታተሉ ሰዎች፣” ወይም ደግሞ ቃል በቃል “ሰብአ ሰገል” ሲሉ ተርጉመውታል። ይህ ቃል በከዋክብትና በፕላኔቶች ሁኔታ ላይ ተመርኩዘው ምክር የሚሰጡና የሚተነብዩ ሰዎችን ያመለክታል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ወደ ቤተ ልሔም ሄደው የነበሩ ጎብኚዎች በአምላክ የተወገዙ አስማታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ምዋርተኞች እንደሆኑ አድርጎ ይገልጻቸዋል።—ዘዳግም 18:10-12
እነዚህ ሰዎች ነገሥታትም ነበሩ? ቢሆኑ ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ ነገሥታት እንደነበሩ አድርጎ ይገልጻቸው ነበር ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። ማቴዎስ 2:1-12 ላይ “ንጉሥ” የሚለው ቃል አራት ጊዜ ተጠቅሷል። አንዱ ኢየሱስን ለማመልከት ሲሆን ሦስቱ ደግሞ ሄሮድስን ለማመልከት ተሠርቶባቸዋል። ሆኖም አንድ ጊዜም እንኳ ሰብአ ሰገልን ነገሥታት ብሎ አይጠራቸውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “የትኛውም የቤተ ክርስቲያን አባት ሰብአ ሰገል ነገሥታት እንደሆኑ አድርጎ አስቦ አያውቅም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ነገሥታት እንደሆኑ አድርጎ አልገለጻቸውም።
ሦስት ነበሩን?
ሰብአ ሰገል ስንት እንደነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አይገልጽም። ሆኖም የኢየሱስን ልደት የሚያንጸባርቁ ምስሎችና የገና በዓል መዝሙሮች ሰብአ ሰገል ሦስት እንደሆኑ አድርጎ የሚገልጸውን የተለመደ ወግ የሚደግፉ ናቸው። ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ሊያድርባቸው የቻለው ሰብአ ሰገል ሦስት ዓይነት ስጦታዎች ይዘው በመምጣታቸው እንደሆነ መገመት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር “ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም [ለኢየሱስ] አቀረቡለት” ይላል።—ማቴዎስ 2:11
ሰብአ ሰገል ያቀረቧቸው ስጦታዎች ሦስት ዓይነት ስለነበሩ እነሱም ሦስት መሆን አለባቸው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይሆናልን? እስራኤልን ስለጎበኘች አንዲት ሌላ የታወቀች ሴት የሚገልጸውን ታሪክ እስቲ እንመልከት። የሳባ ንግሥት በአንድ ወቅት ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄዳ የነበረ ሲሆን “ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ የከበረም ዕንቁ” በስጦታ መልክ አቅርባለት ነበር። (1 ነገሥት 10:2) ሦስት ዓይነት ስጦታዎች የተጠቀሱ ቢሆንም እንኳ ስጦታውን እንደሰጠች ተደርጋ የተገለጸችው የሳባ ንግሥት ብቻ ነበረች። የስጦታዋ ዓይነት ሦስት መሆኑ በወቅቱ በሰሎሞን ፊት ቀርበው የነበሩት ሰዎች ሦስት ነበሩ ማለት አይደለም። ልክ እንደዚሁም ለኢየሱስ የቀረቡት ስጦታዎች ሦስት መሆናቸው ስጦታውን ካመጡት ሰዎች ቁጥር ጋር የሚዛመድበት ሁኔታ የለም።
ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በወንጌሉ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው ታሪክ ሰብአ ሰገል ስንት እንደነበሩ አይገልጽም። ስለዚህ ጉዳይ በማያሻማ ሁኔታ የሚናገር አፈ ታሪክም የለም። አንዳንድ አባቶች ሰብአ ሰገል ሦስት እንደነበሩ አድርገው ይናገራሉ። እንዲህ ብለው የሚናገሩት በስጦታዎቹ ቁጥር ተመርተው ሊሆን ይችላል።” አክሎም የተለያዩ የሥዕል ሥራዎች ኢየሱስን የጎበኙት ሰዎች ሁለት፣ ሦስት፣ አራት አልፎ ተርፎም ስምንት እንደነበሩ አድርገው እንደሚያሳዩ ይገልጻል። አንዳንዶቹ አፈ ታሪኮች እስከ 12 ያደርሷቸዋል። ሰብአ ሰገል ስንት እንደነበሩ ማረጋገጥ የሚቻልበት ምንም መንገድ የለም።
በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት የተሳሳተ ታሪክ
ሰብአ ሰገል ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ መጀመሪያ የሄዱት በብዙዎች ዘንድ እንደሚታመነው ወደ ቤተ ልሔም ሳይሆን ወደ ኢየሩሳሌም ነበር። ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት በቦታው አልነበሩም። በኋላ ወደ ቤተ ልሔም ሲሄዱ “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን” እንዳዩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ማቴዎስ 2:1, 11) ስለዚህ ሰብአ ሰገል ወደ ኢየሱስ በሄዱበት ወቅት ቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ገብተው እንደነበረ ግልጽ ነው። ኢየሱስን በግርግም ተኝቶ አላገኙትም።
ከቅዱሳን ጽሑፎች አንጻር ሲታይ ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት ሦስት ነገሥታት አክብሮታቸውን ሊገልጹለት እንደሄዱ የሚገልጸው በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ታሪክ የተሳሳተ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን የጎበኙት ሰብአ ሰገል ነገሥታት ሳይሆኑ አስማታዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ኮከብ ቆጣሪዎች እንደሆኑ ይገልጻል። ቅዱስ ጽሑፋዊው ዘገባ ብዛታቸውንም አይገልጽም። በተጨማሪም ኢየሱስን የጎበኙበት ገና እንደተወለደ በግርግም ተኝቶ በነበረበት ወቅት ሳይሆን የተወሰኑ ጊዜያት ካለፉ በኋላ ማለትም ቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመሩ በኋላ ነበር።
በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ስለ ሦስቱ ነገሥታት የሚገልጸው ታሪክና ሌሎች የገና በዓል አፈ ታሪኮች ከቅዱሳን ጽሑፎች አንጻር ሲታዩ ስህተት ቢሆኑም እንኳ በጥቅሉ ምንም ጉዳት እንደሌላቸው የበዓል ታሪኮች ተደርገው ይታያሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ከውሸት ለጠራ ንጹሕ አምልኮ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ኢየሱስም ቢሆን የነበረው አመለካከት ከዚህ የተለየ አልነበረም። በአንድ ወቅት ወደ አባቱ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 17:17) “በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል . . . አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና።”—ዮሐንስ 4:23
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ለሰብአ ሰገል የሚሰጥ ታላቅ ክብር፣” ኢጣሊያ