ቤትህ ውስጥ አደጋ የሚፈጥሩ ነገሮች አሉን? ልታስብባቸው የሚገቡ 20 ነገሮች
“ዞሮ ዞሮ ከቤት!” ቀኑን ሙሉ በሥራ ተወጥረህ ከዋልክ በኋላ ከአደጋና ከስጋት ነፃ ወደምትሆንበት ቤትህ ስትመለስ እፎይታና የደስታ ስሜት ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቤትህስ አደጋ ከሚፈጥሩ ነገሮች ሙሉ በሙሉ ነፃ ነውን? የሚያስገርመው ነገር አንዳንድ ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ልብ ያላሏቸው አስከፊ አደጋዎች ይገጥሟቸዋል። በተለይ ደግሞ ትንንሽ ልጆች ያሏቸው ሰዎች ቤት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ በሚገባ የታሰበበት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። የሚከተለውን ዝርዝር መግለጫ በመጠቀም ቤትህ ውስጥ መስተካከል የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ይኖሩ እንደሆነና እንዳልሆነ ለምን አትመረምርም?
✔ ዕፅዋት። ትንንሽ ልጆች ካሏችሁ በግቢያችሁ ውስጥ መርዘኛ የሆኑ ዕፅዋት አለመኖራቸውን አረጋግጡ። ሁሉን ነገር የማወቅ ጉጉት ያላቸው ትንንሽ ልጆች ያገኙትን ነገር ሁሉ ወደ አፋቸው እንደሚከቱ አትዘንጉ።
✔ መጋረጃዎች። የመጋረጃ ገመዶች ልጆች በቀላሉ የሚደርሱባቸው መሆን የለባቸውም። ገመዶቹ ትንንሽ ሕፃናትን ሊጠልፏቸው አልፎ ተርፎም ሊያንቋቸው ይችላሉ።
✔ መሳቢያዎችና ቁም ሣጥኖች። በቀላሉ እንዳይከፈቱ መቀርቀሪያዎች ብታበጁላቸው የተሻለ ነው። እንዲህ ማድረጉ ሕፃናት ስለት ያላቸውን ዕቃዎችና አደገኛ የሆኑ የንጽሕና መገልገያዎችን እንዳይነካኩ ለመከላከል ይረዳል።
✔ ደረጃዎች። በቂ ብርሃን ያላቸውና ከሚያደናቅፉ ነገሮች የጠሩ ናቸው? ትንንሽ ልጆች እንዳይወድቁ ደረጃዎቹ ላይ መከላከያ አጥር አበጅታችኋል?
✔ ምድጃ። በተለይ ምግብ በምታበስሉበት ወቅት የድስቶችንና የመጥበሻዎችን እጀታዎች ወደ ምድጃው ጀርባ ማዞር ያስፈልጋል።
✔ መጥበሻ ያላቸው ምድጃዎች። ቶሎ ቶሎ ማጽዳት ያስፈልጋል። ቅባት የተጠራቀመባቸው እንዲህ ዓይነት ምድጃዎች ማዕድ ቤት ውስጥ እሳት ሊያስነሱ ይችላሉ።
✔ እሳት ማጥፊያ። ቤታችሁ ውስጥ ቢያንስ አንድ እሳት ማጥፊያ መሣሪያ እንዲኖር አድርጉ። ኃላፊነት መሸከም የሚችልበት ዕድሜ ላይ የደረሰ ማንኛውም የቤተሰቡ አባል አጠቃቀሙን ማወቅ አለበት።
✔ የሕፃን አልጋ። በአልጋው ዙሪያ ያሉት ዘንጎች የተጠጋጉ መሆን አለባቸው። የሕፃኑ ጭንቅላት እንዳይቀረቀር በፍራሹ ዙሪያ ያለው ክፍተት ጠባብ መሆን አለበት።
✔ መስኮቶች። መስኮቶች ላይ መከላከያ ዘንጎች መግጠሙ ልጆች እንዳይወድቁ የሚከላከሉ ከመሆኑም በላይ እሳት ቢነሳ ዐዋቂ የሆነ ሰው በቀላሉ ሊያነሳቸው ይችላል።
✔ ቫይታሚኖችና መድኃኒቶች። እነዚህን መድኃኒቶች በሚቆለፍ ቁም ሳጥን ውስጥ ወይም ልጆች በማይደርሱበት ቦታ አስቀምጧቸው።
✔ የባኞ ቤት ገንዳ። አንድን ሕፃን በባኞ ቤት ገንዳ ውስጥ ለብቻው ትታችሁት መሄድ የለባችሁም። አንድ ሕፃን በአጭር ጊዜና በትንሽ ውኃ ሰጥሞ ሊሞት ይችላል።
✔ የማይክሮዌቭ ማብሰያዎች። የማይክሮዌቭ ማብሰያዎች ምግቦችን ወዲያው እንደሚያሞቁ አትዘንጉ። ለምሳሌ ያህል የሕፃን ወተት ጡጦው ውስጥ ሲገባ የጡጦው ሙቀት ብዙም የሚያቃጥል ባይሆንም ወተቱ ግን ሊፋጅ ይችላል።
✔ የቤት ማሞቂያ ምድጃዎች። የቤት ማሞቂያ ምድጃችሁ ካርቦን ሞኖክሳይድ እያሾለከ የሚያስወጣ እንዳይሆን ሁልጊዜ መመርመር አለበት።
✔ የሥጋ መጥበሻ። መጥበሻው በሚግልበት ጊዜ ልጆች ወደ አካባቢው እንዳይቀርቡ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
✔ የመኪና ማቆሚያ ጋራዥ በር። የጋራዡ በር በተለይ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ከሆነ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት ልጆች በበሩ ለማለፍ እንዳይሞክሩ ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል።
✔ ጭስ በሚፈጠርበት ጊዜ የማስጠንቀቂያ ድምፅ የሚያሰሙ መሣሪያዎች። በንጽሕና ያዟቸው፤ እንዲሁም ዘወትር በትክክል የሚሠሩ መሆኑን አረጋግጡ። ባትሪዎቻቸውን በየዓመቱ ለውጡ።
✔ የኤሌክትሪክ ገመዶችና ሶኬቶች። ያረጁ ወይም የተላላጡ የኤሌክትሪክ ገሞዶችን አስወግዱ። የማትጠቀሙባቸው ሶኬቶች ክዳን ቢኖራቸው የተሻለ ነው።
✔ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሣሪያዎች። እነዚህን መሣሪያዎች ከመታጠቢያ ገንዳ ወይም ከዕቃ ማጠቢያ አካባቢ ማራቅ አለባችሁ። ግራውንድ ፎልት ሰርኪት ኢንተራፕተር የተባለው መሣሪያ አንድ እክል ሲፈጠር ኤሌክትሪኩን በማጥፋት ከኤሌክትሪክ ንዝረት ሊጠብቅ ይችላል።
✔ የአሻንጉሊት ማስቀመጫ ሳጥኖች። የአሻንጉሊት ማስቀመጫ ሳጥኑ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ የአየር ማስገቢያ ቀዳዳዎችና ክዳኑ በድንገት ራሱ ተመልሶ እንዳይገጠም ደግፎ የሚይዝ ማጠፊያ ሊኖረው ይገባል።
✔ ካውያ። ገመዱን ጨምሮ ካውያችሁን ልጆች በማይደርሱበት ቦታ አስቀምጡ።