መጠመቂያ ቦታዎች—የተረሳ ልማድን የሚያስታውሱ ድምፅ አልባ ምሥክሮች
ፈረንሳይ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በ2001 በአንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ላይ “በካቴድራል ባለው ገንዳ ውስጥ ጠልቆ ተጠመቀ” የሚል ርዕሰ ዜና ወጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ርዕስ ጋር አብሮ የወጣው ሥዕል የካቶሊክን ሃይማኖት የተቀበለው ሰው እስከ ጉልበቱ ድረስ የሚደርስ ውኃ በያዘ አንድ ትልቅ የመጠመቂያ ገንዳ ውስጥ ቆሞ አንድ የካቶሊክ ጳጳስ በራሱ ላይ ውኃ ሲያፈሱበት ያሳያል። በዓለም ዙሪያ በብዙ ቦታዎች የሚፈጸመው ይህ ክንውን፣ ከሁለተኛው የቫቲካን ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየውን አዳዲስ አማኞችን ውኃ ውስጥ በከፊል በማጥለቅ የማጥመቅ ልማድ የሚያንጸባርቅ ነው። አብዛኞቹ ካቶሊኮች የተጠመቁት ሕፃናት ሳሉ ጥቂት ውኃ ራሳቸው ላይ በማፍሰስ እንደሆነ ሲታሰብ፣ ‘አጥማቂው ዮሐንስና የኢየሱስ ሐዋርያት ካከናወኑት ጥምቀት ጋር ተመሳሳይ የሆነው ምን ዓይነት ጥምቀት ነው? በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች መጠመቅ የሚኖርባቸውስ እንዴት ነው?’ የሚሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመጠመቂያ ቦታዎችን ታሪክ መመርመራችን ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይረዳናል።a
የጥምቀት አጀማመርና ትርጉሙ
በመጀመሪያ ክርስቲያናዊ ጥምቀት የሚከናወነው ተጠማቂውን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ነበር። ፊልጶስ ስላጠመቀው ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይህን ሐቅ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይህ ባለ ሥልጣን ስለ ኢየሱስ ማንነት ከተማረ በኋላ ውኃ ያለበት ሥፍራ ሲደርሱ “እንዳልጠመቅ [“ውኃ ውስጥ እንዳልጠልቅ፣” ዚ ኢምፋቲክ ዲያግሎት] የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ብሎ ጠየቀ። (የሐዋርያት ሥራ 8:26-39) እዚህ ላይ “እንዳልጠልቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ባፕቲዞ ነው። ቃሉም ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን ያመለክታል። ጥምቀት ከመቀበር ጋር የተመሳሰለ መሆኑም ይህን ነጥብ ያጎላል። (ሮሜ 6:4፤ ቈላስይስ 2:12) በርካታ የፈረንሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች (ለምሳሌ አንድሬ ሹራኪ እና ኡቤር ፔርኖ) መጥምቁ ዮሐንስን አጥላቂው ዮሐንስ በማለት የሚጠሩት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።—ማቴዎስ 3:1
ክርስትና በተቋቋመባቸው የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት በቂ ውኃ በተገኘበት በማንኛውም ሥፍራ ማለትም በወንዞች፣ በባሕር ወይም በግል መታጠቢያ ገንዳዎች ውስጥ ተጠማቂዎቹን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ጥምቀት ይከናወን ነበር። ይሁን እንጂ ክርስትናን የሚቀበሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ በሮም ግዛት ውስጥ ከድልማጥያ እስከ ጳለስጢና እንዲሁም ከግሪክ እስከ ግብፅ ድረስ ባሉ ብዙ ሥፍራዎች የመጠመቂያ ቦታዎች ተገነቡ። እስካሁን ድረስ በቁፋሮ ከተገኙት ጥንታዊ የመጠመቂያ ቦታዎች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ የሆነው ሶርያ ውስጥ በኤፍራጥስ ወንዝ ዳርቻ የሚገኘው ሲሆን እሱም በ230 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተሠራ ነው።
የስመ ክርስትና እምነት በአራተኛው መቶ ዘመን በሮም ግዛት ውስጥ እውቅና የተሰጠው ሃይማኖት በሆነ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “ክርስቲያኖች” ስለሆኑ መጠመቅ ነበረባቸው። ስለዚህ ለዚህ ዓላማ የሚውሉ መጠመቂያ ቦታዎች በይፋ በየሥፍራው ይገነቡ ጀመር። በስድስተኛው መቶ ዘመን ሮም ውስጥ ብቻ በቅዱስ ዮሐንስ ላቴራን በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ጨምሮ 25 መጠመቂያ ቦታዎች ተሠርተዋል። ጎል በሚባለው አካባቢ የሚገኝ እያንዳንዱ ሃገረ ስብከት የየራሱ መጠመቂያ ቦታ የነበረው ይመስላል። አንድ ምንጭ እንደሚገልጸው ከሆነ የመጠመቂያዎቹ ብዛት እስከ 150 ይደርስ ነበር። በገጠሮች ውስጥ በትንንሽ ቤተ ክርስቲያኖች፣ በመካነ መቃብሮች ወይም በገዳማት አቅራቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ መጠመቂያዎች እንደነበሩ ይገመታል።
የመጠመቂያዎቹ አሠራርና የውኃ አቅርቦት
መጠመቂያ ቦታዎች ብዙውን ጊዜ በክብ ቅርጽ ወይም ባለ ብዙ ማዕዘን ሆነው የሚሠሩ ሲሆን ነጠል ብለው ለብቻቸው አለዚያም ከአንድ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዘው ይገነቡ ነበር። በመሬት ቁፋሮ የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት እነዚህ መጠመቂያ ቦታዎች መጠናቸው ትንሽ ቢሆንም (በአብዛኛው ከ200 ካሬ ሜትር ያነሱ) በተወሰነ ርቀት በተደረደሩ ዓምዶች እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን በሚያሳዩ በእብነ በረድና በጠጠር በተሠሩ ወይም ባልደረቀ ግድግዳ ላይ በተቀረጹ ምስሎች ያጌጡ ነበሩ። እንዲያውም በማሪያና፣ ኮርሲካ እንደሚገኘው ያሉ አንዳንድ መጠመቂያ ቦታዎች ከገንዳው በላይ በሚያምር ጨርቅ የተሠራ ጥላ ወይም አጎበር ይደረግላቸው ነበር። መጠመቂያ የሚለው ስያሜ ገንዳውንም ጭምር የሚያመለክት ሲሆን የገንዳው ቅርጽ ሁሉም ጎኖቹ እኩል የሆኑ አራት ማዕዘን፣ ክብ፣ ባለ ስድስት ማዕዘን፣ ሞለል ያለ አራት ማዕዘን፣ የመስቀል ቅርጽ ያለው ወይም ባለ ስምንት ማዕዘን ሊሆን ይችል ነበር። ከስፋታቸውና ከጥልቀታቸው መመልከት እንደሚቻለው የጥንቶቹ መጠመቂያዎች አዋቂዎች እንዲጠመቁባቸው የተሠሩ ነበሩ። በአብዛኛው በአንድ ጊዜ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን ለማጥመቅ የሚያስችል ስፋት ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በማዕከላዊ ምሥራቅ ፈረንሳይ በሊዮን ከተማ የሚገኘው ገንዳ ስፋቱ 3.25 ሜትር ነው። ብዙዎቹ ገንዳዎች ወደ ውኃው የሚያስወርዱ በአብዛኛው ሰባት ደረጃዎች አሏቸው።
እርግጥ ነው፣ የመጠመቂያ ቦታዎቹን ንድፍ የሚያወጡት ሰዎች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው የውኃ አቅርቦቱ ነበር። በደቡብ ፈረንሳይ በኒስ ከተማ እንደሚገኘው ያሉ ብዙ መጠመቂያዎች የተሠሩት በምንጭ አጠገብ ወይም በፈራረሱ የፍል ውኃ መታጠቢያዎች ውስጥ ነው። ብዙውን ጊዜ ውኃ ወደ ገንዳው የሚገባበትና ከዚያ የሚወጣበት ቱቦ ይሠራለት ነበር። በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ በአካባቢው ከሚገኝ የዝናብ ውኃ ማጠራቀሚያ ተቀድቶ ይወሰድ ነበር።
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን “የክርስቲያኖች” መጠመቂያ ቦታ ምን ይመስል እንደነበረ ለማወቅ በፕዋትዬ፣ ምዕራብ ፈረንሳይ በ350 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ የተገነባው የቅዱስ ዮሐንስ መጠመቂያ ቦታ ጥሩ ምሳሌ ነው። በዚህ ቦታ ዙሪያውን በበርካታ ቅጥያ ሕንፃዎች በተከበበ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ክፍል ውስጥ ወደ ውኃው የሚያስወርዱ ሦስት ደረጃዎች ያሉት አንድ ትልቅ ባለ ስምንት ማዕዘን ገንዳ አለ። ገንዳው ጥልቀቱ 1.41 ሜትር ሲሆን ሰፊ የሆነው ጎኑ ደግሞ 2.15 ሜትር ነው። ይህ መጠመቂያ ገንዳ በአቅራቢያው ከሚገኝ ምንጭ ወደ ከተማው ውኃ ከሚያመጣ ቦይ ጋር ተገናኝቷል።
ጥምቀት የሚከናወነው ሙሉ በሙሉ በማጥለቅ ነው ወይስ በከፊል?
እንደዚህ ባሉት መጠመቂያ ቦታዎች ውስጥ ጥምቀት የሚከናወነው ተጠማቂውን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ነበር? አንዳንድ የካቶሊክ ታሪክ ጸሐፊዎች ለዚህ ጥያቄ ‘አይደለም’ በማለት መልስ ይሰጣሉ፤ እንዲህ የሚሉበት ምክንያት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ታሪክ ላይ ውኃ በመርጨት (አናት ላይ በማፍሰስ) ማጥመቅ እንደሚቻል ተጠቅሶ ስለሚገኝ ነው። በተጨማሪም እነዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች ብዙ መጠመቂያ ገንዳዎች ጥልቀታቸው ከ1 ሜትር እምብዛም የማይበልጥ በመሆኑ ትልልቅ ሰዎችን ለማጥለቅ የሚያስችል ጥልቀት እንደሌላቸው ይናገራሉ። አንድ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ በፕዋትዬ ከተማ “ቄሱ በሦስተኛው ደረጃ ላይ ቆሞ ውኃ እንዳይነካው ማድረግ ይችል ነበር” ይላል።
ይሁን እንጂ እስከ 12ኛው መቶ ዘመን ድረስ የነበሩት ጥምቀትን የሚያሳዩ ሥዕሎችም እንኳን የተለመደው ጥምቀት ይከናወን የነበረው ሰውነትን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ እንደነበረ ያሳያሉ፤ የጥምቀት ዕጩው ከመጠመቁ በፊት እስከ ደረቱ አልፎ ተርፎም እስከ አንገቱ በሚደርስ ውኃ ውስጥ እንደቆመ የሚያሳዩ ነበሩ። (ከላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።) የውኃው መጠን መካከለኛ ቁመት ላለው ሰው እስከ ወገቡ ብቻ የሚደርስ ቢሆንም እንኳ ሰውነቱን ሙሉ በሙሉ ውኃው ውስጥ በማጥለቅ ማጥመቅ ይቻላል? በርከክ ወይም ቁጢጥ ያለው የጥምቀት ዕጩ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅ እስኪችል ድረስ የውኃ ማውረጃው ለጊዜው ሊዘጋ ይችል እንደነበረ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ይገልጻል።b በፓሪስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ሥነ ሥርዓት ያጠኑት ፕሮፌሰር ፒየር ዡኔል እንዲህ ይላሉ:- ዕጩው “እስከ ወገቡ በሚደርስ ውኃ ውስጥ ይቆማል። ቄሱ ወይም ዲያቆኑ እጁን በተጠማቂው ራስ ላይ በማኖር ሰውነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲጠልቅ ውኃው ውስጥ እንዲጎነበስ ያደርገዋል።”
መጠመቂያዎቹ እያደር እያነሱ ሄዱ
እያደር፣ በሐዋርያት ዘመን ቀላል የነበረው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት መልኩን ቀይሮ የተለየ ልብስንና የሰውነት እንቅስቃሴን፣ አጋንንት ለማውጣት የሚቀርቡ ጸሎቶችን፣ የጥምቀት ውኃውን መባረክን፣ ጸሎተ ሃይማኖትን መድገምንና ቅብዓ ቅዱስ መቀባትን ያካተተ የተወሳሰበ ሥነ ሥርዓት ሆነ። በከፊል መጥለቅ ሠፊ ተቀባይነት እያገኘ ሄደ። የመጠመቂያ ገንዳዎች መጠናቸው እያነሰ የመጣ ሲሆን አንዳንዶቹ ከመጀመሪያ ስፋታቸውና ጥልቀታቸው በግማሽ ወይም ከዚያም በላይ ያነሱ ሆነው መስተካከል ጀመሩ። ለምሳሌ ያህል በደቡብ ፈረንሳይ፣ ካሴር ውስጥ በፊት 1.13 ሜትር ጥልቀት የነበረው ገንዳ በስድስተኛው መቶ ዘመን 0.48 ሜትር ብቻ ጥልቀት እንዲኖረው ተደርጎ ተገነባ። ቆይቶም በ12ኛው መቶ ዘመን አካባቢ በሮም ካቶሊክ ሃይማኖት ውስጥ ከፊል ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ቀረና አናት ላይ ውኃ በመርጨት በሚከናወን ጥምቀት ተተካ። የፈረንሳዩ ምሑር ፒየር ሾኑ እንደሚሉት ከሆነ ይህ የሆነው “መጥፎ የአየር ጠባይ ባለባቸው አገሮች ውስጥ ሕፃናትን ማጥመቅ እየተለመደ በመምጣቱና ሕፃናትን በቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ አጥልቆ ማጥመቅ የማይቻል ስለሆነ ነው።”
እነዚህ ለውጦች፣ እያደር ይበልጥ ያነሱ የመጠመቂያ ቦታዎችን መሥራት እየተለመደ እንዲመጣ አድርገዋል። ታሪክ ጸሐፊው ፍሬዴሪክ ቡህሌ ስለ ጥምቀት ታሪክ ባደረጉት ጥናት ላይ እንደሚከተለው በማለት ተናግረዋል:- “የመሬት ቁፋሮ ጥናት፣ የጽሑፍ ሰነዶች እንዲሁም በቀለም ቅብና በቅርጻ ቅርጽ ሥራ የተሠሩ ሥዕሎች እንደሚያመለክቱት በጥቅሉ ሲታይ፣ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በኖሩባቸው የቀድሞዎቹ መቶ ዘመናት ተጠማቂውን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ይከናወን የነበረው ጥምቀት መልኩን ለውጦ ትልልቅ ሰዎችን በከፊል ሕፃናትን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ሲከናወን ቆይቷል፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሕፃናት አናት ላይ ውኃ በመርጨት ወደሚደረግ ሥነ ሥርዓት ተቀይሯል።”
በዛሬው ጊዜ ትልልቅ ሰዎችን ውኃ ውስጥ በከፊል እያጠለቁ ማጥመቅ እያደር እየተለመደ የመጣ ይመስላል፤ ዘመናዊዎቹ መጠመቂያዎች ከበፊቶቹ የሚበልጡ ሆነው እየተሠሩ ነው። ቡህሌ ሰውነትን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ ይደረግ የነበረው የጥንቱ ጥምቀት ትዝታ ብለው ከጠሩት ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ፣ ዘመናዊው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ እንዲከናወን ከምንጊዜውም ይበልጥ እያሳሰበ ነው። ቀድሞውንም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያኖች ጥምቀት የሚከናወንበት ትክክለኛ መንገድ ሰውነትን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ እንደሆነ የሚገልጽ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “መጠመቂያ ቦታ” የሚለው ስያሜ በአብዛኛው የሚያመለክተው የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች የሚከናወኑበትን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ወይም የቤተ ክርስቲያኑ አካል የሆነ ቦታ ነው።
b በዘመናችን ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በትናንሽ የመዋኛ ገንዳዎች ሌላው ቀርቶ በገላ መታጠቢያ ገንዳዎች ውስጥም እንኳ ሳይቀር ሰውነታቸው ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ጠልቆ ተጠምቀዋል።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፕዋትዬ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ መጠመቂያ ቦታ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምስተኛው መቶ ዘመን በኮርሲካ የነበረው የማሪያና መጠመቂያ ቦታ እንደገና ተገንብቶ
[ምንጭ]
© J.-B. Héron pour “Le Monde de la Bible”/Restitution: J. Guyon and J.-F. Reynaud, after G. Moracchini-Mazel
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ክርስቶስ ሲጠመቅ የሚያሳዩ ምስሎች
የዮርዳኖስ ወንዝ እስከ ኢየሱስ ደረት የሚደርስ ሲሆን መላእክት ሰውነቱን ለማድረቅ ፎጣ ይዘው ሲመጡ፣ ዘጠነኛው መቶ ዘመን
[ምንጭ]
Cristal de roche carolingien - Le baptême du Christ © Musée des Antiquités, Rouen, France/Yohann Deslandes
ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ እስከ አንገቱ በሚደርስ ውኃ ውስጥ። በስተ ግራ ሁለት መላእክት ሰውነቱን ለማድረቅ ተዘጋጅተው ጨርቅ ይዘው ቆመው፣ 12ኛው መቶ ዘመን
[ምንጭ]
© Musée d’Unterlinden - F 68000 COLMAR/Photo O. Zimmermann