የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • hf ክፍል 8 ገጽ 26-28
  • መከራ ሲያጋጥማችሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መከራ ሲያጋጥማችሁ
  • ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • 1 በይሖዋ ታመኑ
  • 2 ራሳችሁንም ሆነ ቤተሰባችሁን ተንከባከቡ
  • 3 እርዳታ ሲያስፈልጋችሁ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ
  • ድንገተኛ የጤና እክል ሲያጋጥም
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
  • ይሖዋ ሕዝቡን በትኩረት ይመለከታል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ተስፋ አስቆራጭ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር በተስፋ መኖር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
ደስተኛ ቤተሰብ ሊኖርህ ይችላል
hf ክፍል 8 ገጽ 26-28
ባልና ሚስት ልጃቸውን በሞት በማጣታቸው ሲያዝኑ

ክፍል 8

መከራ ሲያጋጥማችሁ

“አሁን ለአጭር ጊዜ በልዩ ልዩ ፈተናዎች መጨነቃችሁ የግድ ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ነገሮች የተነሳ እጅግ እየተደሰታችሁ ነው።”—1 ጴጥሮስ 1:6

አስደሳች ትዳርና የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራችሁ የተቻላችሁን ሁሉ ለማድረግ ብትጥሩም እንኳ ደስታችሁን የሚያሳጡ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። (መክብብ 9:11) ችግሮች ሲያጋጥሙን መቋቋም እንድንችል አፍቃሪው አምላካችን እርዳታ ያደርግልናል። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች የምትከተሉ ከሆነ በጣም የከፋ ችግር ቢያጋጥማችሁም እንኳ ልትቋቋሙት ትችላላችሁ።

1 በይሖዋ ታመኑ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።” (1 ጴጥሮስ 5:7) ለደረሱባችሁ መከራዎች ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ ምንጊዜም አትዘንጉ። (ያዕቆብ 1:13) ወደ አምላክ ስትቀርቡ እሱም ከሁሉ በላቀ መንገድ ይረዳችኋል። (ኢሳይያስ 41:10) “ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።”—መዝሙር 62:8

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በየዕለቱ ስታነቡና ስታጠኑ መጽናኛ ታገኛላችሁ። ይህም ይሖዋ ‘በመከራችን ሁሉ የሚያጽናናን’ እንዴት እንደሆነ በራሳችሁ ሕይወት ለማየት ያስችላችኋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ሮም 15:4) ይሖዋ ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ ሊሰጣችሁ ቃል ገብቷል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13

ሆስፒታል የተኛ ሰው ከቤተሰቡ ጋር ሲጸልይ

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • መረጋጋትና አጥርታችሁ ማሰብ እንድትችሉ ይሖዋ እንዲረዳችሁ ጸልዩ

  • ያሏችሁን አማራጮች ከገመገማችሁ በኋላ የተሻለውን አካሄድ ምረጡ

2 ራሳችሁንም ሆነ ቤተሰባችሁን ተንከባከቡ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የአስተዋይ ሰው ልብ እውቀትን ያገኛል፤ የጥበበኛም ጆሮ እውቀትን ለማግኘት ይጥራል።” (ምሳሌ 18:15) የተሟላ መረጃ ለማግኘት ሞክሩ። እያንዳንዱ የቤተሰባችሁ አባል ምን እንደሚያስፈልገው ለማወቅ ጥረት አድርጉ። እርስ በርስ ተነጋገሩ፤ አንዳችሁ ሌላው አዳምጡ።—ምሳሌ 20:5

አንድ የቤተሰባችሁ አባል ቢሞትስ? ሐዘናችሁን ለመግለጽ አትፍሩ። ኢየሱስም እንኳ ‘እንባውን እንዳፈሰሰ’ አስታውሱ። (ዮሐንስ 11:35፤ መክብብ 3:4) በቂ እረፍትና እንቅልፍ ማግኘትም አስፈላጊ ነው። (መክብብ 4:6) እንዲህ ማድረጋችሁ ያጋጠማችሁን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቋቋም ይረዳችኋል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ከቤተሰባችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ልማድ ለማዳበር መከራ እስኪያጋጥማችሁ አትጠብቁ። እንዲህ ዓይነት ልማድ ካላችሁ ችግር በሚያጋጥማችሁ ጊዜ ማውራት ቀላል ይሆንላችኋል

  • ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሌሎች ሰዎችንም አነጋግሩ

3 እርዳታ ሲያስፈልጋችሁ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበሉ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።” (ምሳሌ 17:17) ወዳጆቻችሁ ሊረዷችሁ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ የሚያስፈልጋችሁን ነገር ለእነሱ ከመንገር ወደኋላ አትበሉ። (ምሳሌ 12:25) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ የሚያውቁ ሰዎች መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያደርጉላችሁ ጠይቁ። እነሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚሰጧችሁ ምክር ይጠቅማችኋል።—ያዕቆብ 5:14

በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ካላቸውና እሱ በገባቸው ተስፋዎች ከሚተማመኑ ሰዎች ጋር አዘውትራችሁ በመሰብሰብ፣ የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ማግኘት ትችላላችሁ። ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎች መርዳትም በእጅጉ ያጽናናችኋል። በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ስላላችሁ እምነት ለሌሎች ተናገሩ። የተቸገሩትን በመርዳት ራሳችሁን በሥራ አስጠምዱ፤ እንዲሁም ከሚወዷችሁና ከሚያስቡላችሁ ሰዎች ራሳችሁን አታግልሉ።—ምሳሌ 18:1፤ 1 ቆሮንቶስ 15:58

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ለምትቀርቡት ወዳጃችሁ ስሜታችሁን አውጥታችሁ ንገሩ፤ የሚያደርግላችሁን እርዳታም ተቀበሉ

  • የሚያስፈልጓችሁን ነገሮች በግልጽና በሐቀኝነት ተናገሩ

ትልቁ ጉዳይ

የደረሰባችሁ መከራ ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ቢሰማችሁም እንኳ ትኩረታችሁን በአምላክ ላይ አድርጉ። ኢዮብ መከራ በደረሰበት ጊዜ “የይሖዋ ስም ምንጊዜም ይወደስ” ብሎ ነበር። (ኢዮብ 1:21, 22) እንደ ኢዮብ ሁሉ እናንተም ከሚያስጨንቋችሁ ነገሮች በላይ ለይሖዋ ስምና ለእሱ ፈቃድ ቅድሚያ ስጡ። ነገሮች በምትፈልጉት መንገድ ባይሄዱ እንኳ ተስፋ አትቁረጡ። ሙሉ በሙሉ በአምላክ ታመኑ። “‘ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁና’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።’”—ኤርምያስ 29:11

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  • በትንንሽ ነገሮችም ጭምር ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እተማመናለሁ?

  • ይሖዋን ለጥሩነቱ በየዕለቱ እንዳመሰግነው የሚያነሳሱኝ ምን ምክንያቶች አሉኝ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ