ደግነት
ለሌሎች ደኅንነት ከልብ ማሰብን እንዲሁም ወዳጃዊ መሆንንና ሌሎችን ለመርዳት ተግባራዊ እርምጃ መውሰድን ያመለክታል። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ደግነት” ተብሎ የተተረጎመው መሠረታዊ ቃል ክህሬስቶቴስ ነው። ይህን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ይሖዋ ግንባር ቀደም ሲሆን ክፉዎችና የማያመሰግኑ ጭምር ንስሐ እንዲገቡ በማበረታታት፣ በብዙ መንገዶች ለሌሎች ደግነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው። (ሉቃስ 6:35፤ ሮም 2:4፤ 11:22፤ ቲቶ 3:4, 5) በክርስቶስ ልዝብ ቀንበር ሥር (ማቴ 11:30) ያሉ ክርስቲያኖችም ደግነትን እንዲለብሱ (ቆላ 3:12፤ ኤፌ 4:32) እና ደግነትን የሚያካትተውን የአምላክ መንፈስ ፍሬ እንዲያፈሩ ተመክረዋል። (ገላ 5:22) በዚህ መንገድ ራሳቸውን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገው ያቀርባሉ። (2ቆሮ 6:4-6) “ፍቅር . . . ደግ ነው።”—1ቆሮ 13:4
“ደግነት” (ወይም ምክንያታዊነት፤ ቃል በቃል እሺ ባይነት፤ በግሪክኛው ኤፒኤኪአ ) ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታወቅበት ዋነኛ ባሕርይ ነው። (2ቆሮ 10:1) ጳውሎስ የማልታ ደሴት ነዋሪዎች የተለየ “ሰብዓዊ ደግነት” (ቃል በቃል ለሰው ዘር ሊኖር የሚገባ ፍቅር፤ ግሪክኛው ፊላንትሮፒአ) እንዳሳዩት ተናግሯል።—ሥራ 28:2፣ ግርጌ
የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት። እንደ ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይም ስለ ደግነት ብዙ ጊዜ ተጠቅሷል። ሄሴድ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ደግነትን ለማመልከት 245 ጊዜ ተሠርቶበታል። “የታማኝነት ተግባር (ወይም ፍቅራዊ ደግነት) የሚል ትርጉም ያለው ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆነው ሃሳድ የሚለው ግስ በርኅራኄ ማየትን ወይም ከፍቅር የሚመነጭ ደግነት ማሳየትን የሚጨምር ቢሆንም ከዚህ ያለፈ ትርጉም አለው። (መዝ 18:25፣ ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም፣ ግርጌ) ሄሴድ “የአንድነገር ዓላማ ግቡን እስኪመታ ድረስ ከዚያ ነገር ጋር ራስን በፍቅር በማቆራኘት የሚገለጽን ደግነት ያመለክታል። ቲኦሎጂካል ዲክሺነሪ ኦፍ ዚ ኦልድ ቴስታመንት እንደሚገልጸው ሄሴድ “አድራጊ፣ ማኅበራዊና ጽኑ ነው፤ . . . አንድ ሰው ያለውን ዝንባሌ ብቻ የሚገልጽ ሳይሆን በዚህ ዝንባሌ ተነሳስቶ የሚፈጽመውን ተግባርንም ይጨምራል። ሕይወትን ለማቆየት ወይም ለማሻሻል የሚወሰድ እርምጃ ነው። ችግር ላይ ለወደቀ ወይም መከራ ላጋጠመው ሰው መድረስን ያመለክታል። የወዳጅነት ወይም የሃይማኖተኝነት መገለጫም ነው። ክፉውን ሳይሆን ሁልጊዜ ጥሩ የሆነውን ነገር ለማድረግ መጣርን ያመለክታል።” (በጆንስ ቦተርዌክ እና በሄልመር ሪንግሬን የተዘጋጀ 1986፣ ጥራዝ 5 ገጽ 51) በመሆኑም ብዙ ትርጉም ያለው ሄሴድ ጠቅለል ተደርጎ “ፍቅራዊ ደግነት” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፤ አለዚያም ከታማኝነት፣ ከአንድነት እና ተፈትኖ ከተረጋገጠ ታማኝነት ጋር ተዛማጅነት ስላለው “ታማኝ ፍቅር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህ ቃል በብዙ ቁጥር ሲገለጽ “ፍቅራዊ ደግነቶች፣” “የታማኝ ፍቅር ተግባሮች፣” “የተሟላ ፍቅራዊ ደግነት” ወይም “የተሟላ ታማኝ ፍቅር” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል።—መዝ 25:6 ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም፣ ግርጌ፤ ኢሳ 55:3 ባለማጣቀሻው አዲስ ዓለም ትርጉም፣ ግርጌ
ፍቅራዊ ደግነት ይሖዋ በጣም የሚደሰትበት ውድ ባሕርይው ሲሆን ከአገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነት ሁሉ ይህን ባሕርይ ያሳያል። (መዝ 36:7፤ 62:12፤ ሚክ 7:18) ይሖዋ ይህን ባሕርይ የሚያሳይ አምላክ ባይሆን ኖሮ አገልጋዮቹ ገና ድሮ ጠፍተው በቀሩ ነበር። (ሰቆ 3:22) በመሆኑም ሙሴ የይሖዋን ታላቅ ስምና የእሱን ፍቅራዊ ደግነት መሠረት በማድረግ ስለ ዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ሲል ይሖዋን ተማጽኗል።—ዘኁ 14:13-19
ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚገልጹት የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ታማኝ ፍቅር በተለያዩ መንገዶችና በተለያዩ ሁኔታዎች ይገለጻል፤ ይኸውም ነፃ ለማውጣትና ሕይወትን ለማትረፍ (መዝ 6:4፤ 119:88, 159)፣ ለመጠበቅና ለመከላከል (መዝ 40:11፤ 61:7፤ 143:12)፣ እንዲሁም ከችግር ለመገላገል ሲል በሚወስዳቸው እርምጃዎች ተገልጿል (ሩት 1:8፤ 2:20፤ መዝ 31:16, 21)። የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት፣ አንድን ሰው የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኝ (መዝ 25:7)፣ ሕይወቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ሊያደርገው አልፎ ተርፎም ደግፎ ሊያቆመው ይችላል። (መዝ 94:18፤ 117:2) አምላክ ምርጦቹን የሚረዳውም በፍቅራዊ ደግነቱ ተነሳስቶ ነው። (መዝ 44:26) የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ለሎጥ (ዘፍ 19:18-22)፣ ለአብርሃም (ሚክ 7:20) እና ለዮሴፍ (ዘፍ 39:21) ባደረጋቸው ነገሮች በጉልህ ታይቷል። በተጨማሪም ለይስሐቅ ሚስት በመምረጥ ረገድ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ሚና እንደተጫወተም እናያለን።—ዘፍ 24:12-14, 27
ከእስራኤል ብሔር መቋቋም ሆነ ከዚያ በኋላ ይሖዋ ከገባላቸው ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ጉልህ ስፍራ ያለው ሆኖ ቀጥሎ ነበር። (ዘፀ 15:13፤ ዘዳ 7:12) ከዳዊት (2ሳሙ 7:15፤ 1ነገ 3:6፤ መዝ 18:50)፣ ከዕዝራና ከእሱ ጋር ከነበሩት ሰዎች (ዕዝራ 7:28፤ 9:9) እንዲሁም ‘በሺዎች’ ከሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ጋር በተያያዘም (ዘፀ 34:7፤ ኤር 32:18) ፍቅራዊ ደግነቱ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ይሖዋ ለዳዊት በገባለት የመንግሥት ቃል ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ከሞተ በኋላም እንኳ ይህን “ታማኝ አገልጋዩን” ከሙታን በማስነሳት ፍቅራዊ ደግነቱን ማሳየቱን ቀጥሏል፤ ይህ ደግሞ “ለዳዊት ቃል የተገባውን የማይከስም [ፍቅራዊ ደግነት] አሳያችኋለሁ” የሚለው ትንቢት ፍጻሜ እንዲያገኝ አድርጓል።—መዝ 16:10፤ ሥራ 13:34፤ ኢሳ 55:3
ግለሰቦችን ወደ ይሖዋ የሚስባቸው ይሖዋ የሚያሳየው ይህ ፍቅራዊ ደግነት ነው። (ኤር 31:3) በፍቅራዊ ደግነቱ የሳባቸው ሰዎች እንዲህ ባለው ፍቅሩ ይታመናሉ (መዝ 13:5፤ 52:8)፣ ተስፋ ያደርጋሉ (መዝ 33:18, 22)፣ ፍቅራዊ ደግነቱን እንዲያሳያቸው ይጸልያሉ (መዝ 51:1፤ 85:7፤ 90:14፤ 109:26፤ 119:41)፤ እንዲሁም በዚህ ፍቅር ይጽናናሉ (መዝ 119:76)። በተጨማሪም ይሖዋን ስለፍቅራዊ ደግነቱ ያመሰግኑታል (መዝ 107:8, 15, 21, 31)፤ በዚህ ባሕርይው የተነሳ ያወድሱታል እንዲሁም ያከብሩታል (መዝ 66:20፤ 115:1፤ 138:2)፤ ለሌሎችም ስለፍቅራዊ ደግነቱ ይናገራሉ። (መዝ 92:2) የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ጥሩ በመሆኑ (መዝ 69:16፤ 109:21) እና ታላቅ የደስታ ምንጭ ስለሆነ (መዝ 31:7) ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ እነሱም ፈጽሞ ሊሸሽጉት አይፈልጉም። (መዝ 40:10) በእርግጥም ይህ መለኮታዊ ፍቅራዊ ደግነት ሊሄዱበት የሚገባ አስደሳች መንገድ ነው።—መዝ 25:10
በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይም የፍቅራዊ ደግነቱ ብዛት (መዝ 5:7፤ 69:13፤ ዮናስ 4:2)፣ ታላቅነት (ዘኁ 14:19) እና ዘላቂነት (1ነገ 8:23) ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ፍቅራዊ ደግነቱ እስከ ሰማያት እንደሚደርስ (መዝ 36:5፤ 57:10፤ 103:11፤ 108:4)፣ ምድርን እንደሚሞላ (መዝ 33:5፤ 119:64) እንዲሁም እስከ ሺህ ትውልድ እንደሚዘልቅ (ዘዳ 7:9) እና “ለዘላለም ጸንቶ” እንደሚኖር (1ዜና 16:34, 41፤ መዝ 89:2፤ ኢሳ 54:8, 10፤ ኤር 33:11) ተገልጿል። በመዝሙር 136 ውስጥ ባሉት 26 ቁጥሮች ሁሉ ላይ “[ፍቅራዊ ደግነቱ] ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚለው ሐረግ ተደጋግሞ ይገኛል።
የይሖዋ የላቀ ባሕርይ የሆነው ፍቅራዊ ደግነት ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ድንቅ ባሕርያት ማለትም ከአምላክ ምሕረት፣ ርኅራኄ፣ እውነት፣ ይቅር ባይነት፣ ጽድቅ፣ ሰላም፣ ፍርድና ፍትሕ ጋር ተያይዞ ተገልጿል።—ዘፀ 34:6፤ ነህ 9:17፤ መዝ 85:10፤ 89:14፤ ኤር 9:24
ሰዎች የሚያሳዩት ፍቅራዊ ደግነት። ከላይ ከሰፈረው ሐሳብ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ‘ታማኝነትን [ፍቅራዊ ደግነትን] መውደድ’ እና ‘አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ፍቅር [ፍቅራዊ ደግነት] እና ምሕረት ማሳየት’ አለባቸው። (ሚክ 6:8፤ ዘካ 7:9) “የሰው ተወዳጅ ባሕርይ ታማኝ ፍቅሩ [ፍቅራዊ ደግነቱ] ነው” ከሚለው ምሳሌ እንደምንረዳው ይህ ባሕርይ ታላቅ ሽልማት ያስገኛል። (ምሳሌ 19:22፤ 11:17) አምላክ፣ እስራኤል በወጣትነት ዘመኗ ያሳየችውን ፍቅራዊ ደግነት እንደሚያስታውስና ተደስቶበት እንደነበረ ተናግሯል። (ኤር 2:2) ይሁን እንጂ ‘[ፍቅራዊ ደግነታቸው] እንደ ጠዋት ጉም፣ ወዲያው እንደሚጠፋም ጤዛ’ በሆነ ጊዜ ይሖዋ አልተደሰተም፤ ምክንያቱም “ከመሥዋዕት ይልቅ ታማኝ ፍቅር [ፍቅራዊ ደግነት] . . . ያስደስተኛል” ብሏል። (ሆሴዕ 6:4, 6) የእስራኤል ሕዝብ ፍቅራዊ ደግነት ሳያሳይ በመቅረቱ ተገሥጿል፤ ሆኖም ተግሣጹ ራሱ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት መግለጫ ነበር። (ሆሴዕ 4:1፤ መዝ 141:5) በተጨማሪም የእስራኤል ሕዝብ ፍቅራዊ ደግነትና ፍትሕ በማሳየት ወደ አምላክ እንዲመለስ ምክር ተሰጥቶታል። (ሆሴዕ 12:6) አንድ ሰው በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ እንዲያገኝ ከተፈለገ ምንጊዜም እንደዚህ ያሉትን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይኖርበታል።—ኢዮብ 6:14፤ ምሳሌ 3:3, 4
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግለሰቦች ለሌሎች ፍቅራዊ ደግነት ያሳዩባቸው በርካታ ሁኔታዎች ተገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሣራ፣ እሷና አብርሃም በጠላት ክልል ውስጥ ሳሉ እሱን ከጥቃት ለመጠበቅ ስትል ወንድሟ እንደሆነ በመናገር ፍቅራዊ ደግነት አሳይታዋለች። (ዘፍ 20:13) ያዕቆብም ሲሞት በግብፅ እንዳይቀብረው ዮሴፍን ቃል በማስገባት ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳየው ጠይቆታል። (ዘፍ 47:29፤ 50:12, 13) ረዓብ እስራኤላውያን ሰላዮችን በመደበቅ ፍቅራዊ ደግነት እንዳሳየቻቸው ሁሉ እነሱም ከኢያሪኮ ጥፋት የቤተሰቧን ሕይወት በማትረፍ ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳዩአት ተማጽናቸዋለች። (ኢያሱ 2:12, 13) ቦዔዝ ሩትን ፍቅራዊ ደግነት በማሳየቷ አመስግኗታል (ሩት 3:10)፤ እንዲሁም ዮናታን ዳዊትን ለእሱና ለቤተሰቡ ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳየው ጠይቆታል።—1ሳሙ 20:14, 15፤ 2ሳሙ 9:3-7
ሰዎች ደግነት ወይም ፍቅራዊ ደግነት እንዲያሳዩ የሚያነሳሳቸው የልብ ግፊትና ሁኔታ በእጅጉ ይለያያል። በአጋጣሚ የሚደረግ የደግነት ተግባር እንደ ባሕል የሚታይን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ወይም ሰው ወዳድነትን ሊያሳይ ቢችልም ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ላያመለክት ይችላል። (ከሥራ 27:1, 3፤ 28:1, 2 ጋር አወዳድር) የቤቴል ከተማ ነዋሪ የነበረው ሰው ለዮሴፍ ቤት ሰላዮች ደግነት ያሳየው እነሱ በምላሹ ለሚከፍሉት ወሮታ ሲል ነበር። (መሳ 1:22-25) ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ሰው፣ ለተጨነቀ ሌላ ሰው ውለታ በመዋል እሱም ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት ውለታውን እንዲመልስለት የጠየቀበት ጊዜ ነበር። (ዘፍ 40:12-15) ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የተደረገላቸውን ፍቅራዊ ደግነት በመርሳት ውለታቸውን ሳይመልሱ የቀሩበት ጊዜ አለ። (ዘፍ 40:23፤ መሳ 8:35) የምሳሌ መጽሐፍ እንደሚገልጸው ብዙ ሰዎች ፍቅራዊ ደግነት እንደሚያሳዩ ያወራሉ፤ ይሁንና በታማኝነት ይህን የሚፈጽሙት ጥቂቶች ናቸው። (ምሳ 20:6) ሳኦልም ሆነ ዳዊት ሌሎች ያሳዩአቸውን ፍቅራዊ ደግነት አስታውሰዋል (1ሳሙ 15:6, 7፤ 2ሳሙ 2:5, 6)፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት ከአረማውያን ነገሥታት ጋር ሲነፃፀሩ ፍቅራዊ ደግነት በማሳየት ረገድ መልካም ስም ያተረፉ ይመስላል። (1ነገ 20:31) ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት ዳዊት ያሳየው ፍቅራዊ ደግነት ሌላ ዓላማ እንዳለው ተደርጎ በመጥፎ በመተርጎሙ ጥሩ ምላሽ ሳያገኝ ቀርቷል።—2ሳሙ 10:2-4
ጳውሎስ እንደተናገረው ሕግ የሚወጣው ለጻድቃን ሳይሆን መጥፎ ተግባራትን ለሚፈጽሙና ፍቅራዊ ደግነት ለማያሳዩ ሰዎች ነው። (1ጢሞ 1:9 ግርጌ) እዚህ ላይ የገባው ‘ታማኝ ፍቅር [ፍቅራዊ ደግነት] የሌላቸው’ ተብሎ የተተረጎመው አኖሲዮስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ‘ታማኝ ያልሆኑ’ የሚል ትርጉምም አለው።—2ጢሞ 3:2
ጸጋ [ይገባናል የማንለው ደግነት]። ክሃሪስ የተሰኘው የግሪክኛ ቃል በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከ150 ጊዜ በላይ የሚገኝ ሲሆን ዓውዱን መሠረት በማድረግ በተለያየ መንገድ ተተርጉሟል። ክሃሪስ የተባለው ይህ ቃል የሚያስተላልፈው ዋነኛ መልእክት ደስ የሚያሰኝ (1ጴጥ 2:19, 20) እና ማራኪ (ሉቃስ 4:22) የሚል ሲሆን ይህ ሐሳብ በሁሉም ቦታዎች ላይ ተንጸባርቋል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በልግስና የተሰጠን ስጦታ (1ቆሮ 16:3፤ 2ቆሮ 8:19) ወይም ሰጪው ያሳየውን ልግስና ለማመልከት ተሠርቶበታል። (2ቆሮ 8:4, 6) በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ይህ ቃል ለአንድ የደግነት ተግባር ለአድራጊው እውቅና ለመስጠት ወይም እሱን ለማመስገን ተሠርቶበታል።—ሉቃስ 6:32-34፤ ሮም 6:17፤ 1ቆሮ 10:30፤ 15:57፤ 2ቆሮ 2:14፤ 8:16፤ 9:15፤ 1ጢሞ 1:12፤ 2ጢሞ 1:3
በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ክሃሪስ የሚለው ቃል በገባባቸው አብዛኞቹ ቦታዎች ላይ “ጸጋ” (“grace”) ብለው ተርጉመውታል። ይሁን እንጂ 14 የተለያዩ ትርጉሞች ያለው “ጸጋ” (“grace”) የሚለው ቃል ለአብዛኞቹ አንባቢዎች የግሪክኛው ቃል የያዘውን ሐሳብ ሁሉ አያስተላልፍም። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት በዮሐንስ 1:14 ላይ የሚገኘው ኪንግ ጄምስ ቨርዥን “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ . . . ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ” ብሎ በተረጎመው ሐሳብ ላይ ያለው ጸጋ የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው? “ግርማ ሞገስ የተላበሰ” ማለት ነው? ወይስ “ሞገስ” ማለት ነው? ወይስ ሌላ ትርጉም አለው?
አር ሲ ትሬንች የተባሉት ምሁር ሲኖኒምስ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ላይ ክሃሪስ የሚለው ቃል በተዘዋዋሪ የሚያመለክተው “በምላሹ ምንም ነገር ሳይጠብቁ በነፃ የሚደረግ ችሮታን ሲሆን ቃሉ የተሰጠው አዲስ ትርጉም [ማለትም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተሠራበት መንገድ]. . . አምላክ ሙሉ በሙሉና ፍጹም በሆነ መልኩ ለሰዎች የሚያሳየውን ነፃ የሆነ ፍቅራዊ ደግነት የሚያጎላ ነው። በዚህም ምክንያት አሪስቶትል [ክሃሪስ] ለተሰኘው ቃል ፍቺ ሲሰጥ አጽንኦት የሰጠው ለዚህ ነጥብ፣ ይኸውም ምንም ምላሽ ሳይጠብቁ በነፃ መስጠትን ሲሆን ደግሞም ልግስናውና ቸርነቱ የተመካው በሰጪው ውስጣዊ ግፊት ላይ መሆኑን ያሳያል።” (ለንደን፣ 1961 ገጽ 158) ጆሴፍ ሄች ታየር በቃላት መፍቻቸው ላይ የሚከተለውን ይናገራሉ፦ [ክሃሪስ] የተሰኘው ቃል ምንም ዓይነት ችሮታ ሊደረግለት ለማይገባ ሰው የሚደረግ ደግነትን የሚያመለክት ሐሳብ በውስጡ የያዘ ሲሆን . . . የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች [ክሃሪስ] የሚለውን ቃል በዋነኝነት የተጠቀሙበት አምላክ ፈጽሞ ለማይገባው ሰው ጭምር ሞገስ በማሳየትና ኃጢአተኞች ለፈጸሙት በደል ይቅርታ በማድረግ ብሎም በክርስቶስ በኩል ዘላለማዊ ደኅንነት እንዲያገኙ ግብዣ በማቅረብ የሚያሳየውን ደግነት ለማመልከት ነው።” (ኤ ግሪክ ኢንግሊሽ ሌክሲከን ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት፣ 1889 ገጽ 666) ክሃሪስ የሚለው ቃል ካሪስማ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ጋር የቅርብ ተዛማጅነት ያለው ሲሆን የዊሊያም ባርክሌይ ኒው ቴስታመንት ዎርድቡክ (1956፣ ገጽ 29) እንደገለጸው ከሆነ ደግሞ “[ካሪስማ] የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጉም ተቀባዩ ይገባኛል ሊለው የማይችል ነፃ ስጦታን ያመለክታል፤ ስጦታውን ያገኘው ሰው የድካሜ ወይም የልፋቴ ዋጋ ሊለው የሚችል ነገር አይደለም።”—ከ2ቆሮ 1:11 [ኢንተርሊንየር] ጋር አወዳድር።
ክሃሪስ ከላይ የተገለጸውን ሐሳብ በሚያስተላልፍ መንገድ ሲሠራበት፣ ይኸውም ይሖዋ የሚያሳየውን ደግነት ማለትም ተቀባዩ ይገባኛል ሊለው የማይችለውን ነፃ ስጦታ የሚያመለክት በሚሆንበት ጊዜ ከግሪክኛው ቃል ጋር አቻ የሆነው የእንግሊዝኛ ሐረግ “undeserved kindness” የሚለው ነው።—ሥራ 15:40፤ 18:27፤ 1ጴጥ 4:10፤ 5:10, 12
አንድ ሠራተኛ ለሠራው ሥራ ደሞዝ ይገባዋል፤ ደሞዝ እንዲከፈለው መጠበቁ መብቱ ነው፤ ደሞዙ የሚገባው ነገር እንጂ ስጦታ ወይም ልዩ የሆነ ይገባኛል የማይለው ደግነት አይደለም። (ሮም 4:4) ይሁን እንጂ ሞት ለተፈረደባቸው ኃጢአተኞች (ደግሞም ሁላችንም ስንወለድ ሞት የተፈረደብን ኃጢአተኞች ነን) ከዚህ የሞት ፍርድ ነፃ መውጣትና ጻድቃን ናችሁ መባል ይህ በእርግጥም ፈጽሞ ይገባናል የማይሉት ደግነት ነው። (ሮም 3:23, 24፤ 5:17) በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር የተወለዱት፣ ሕጉ ኃጢአተኞች መሆናቸውን በማሳየት ለበለጠ የሞት ኩነኔ እንዲዳረጉ አድርጓቸዋል፤ ድነት በመጀመሪያ የቀረበው ለአይሁዳውያን በመሆኑ አምላክ ይገባናል የማይሉት ታላቅ ደግነት በመጀመሪያ የዘረጋው ለእነሱ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።—ሮም 5:20, 21፤ 1:16
አምላክ በአጠቃላይ ለሰው ዘር ይህን ልዩ የሆነ ይገባናል የማይሉት ደግነት ያሳየው በክርስቶስ ኢየሱስ ደም አማካኝነት ከኃጢአት ኩነኔ ነፃ እንዲሆኑ ዝግጅት በማድረግ ነው። (ኤፌ 1:7፤ 2:4-7) አምላክ የሰው ዘሮች ይገባናል በማይሉት በዚህ ደግነት አማካኝነት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ድነት አምጥቷል (ቲቶ 2:11)፤ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ነቢያት የተናገሩለት ነገር ነው። (1ጴጥ 1:10) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ “የተመረጡት [ይገባናል በማይሉት ደግነት] ከሆነ በሥራ መሆኑ ቀርቷል፤ አለዚያ [ይገባናል የማይሉት ደግነት፣ ይገባናል የማይባል ደግነት] መሆኑ በቀረ ነበር” የሚል አሳማኝ መከራከሪያ አቅርቧል።—ሮም 11:6
ጳውሎስ ይገባናል ስለማንለው የአምላክ ደግነት በ14 ደብዳቤዎቹ ውስጥ ከ90 ጊዜ በላይ ስለጠቀሰ ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ይበልጥ ይህን መግለጫ ተጠቅሞበታል። ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ካሰፈረው የመግቢያ ሰላምታ በስተቀር በሁሉም ደብዳቤዎቹ መክፈቻና መዝጊያ ላይ አምላክ ወይም ኢየሱስ ለሰዎች ስላሳዩት ይገባናል የማይሉት ደግነት ጠቅሷል። ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም በጽሑፋቸው መክፈቻና መዝጊያ ላይ ተመሳሳይ ሐሳብ ጠቅሰዋል።—1ጴጥ 1:2፤ 2ጴጥ 1:2፤ 3:18፤ 2ዮሐ 3፤ ራእይ 1:4፤ 22:21
ጳውሎስ ይሖዋ ላሳየው ይገባኛል የማይለው ደግነት አመስጋኝ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም፤ ምክንያቱም ‘ቀደም ሲል ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ’ ነበር። ይሁን እንጂ “ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል። የጌታችን [ይገባናል የማንለው ደግነትም] ከእምነት እንዲሁም የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ በመሆኔ ምክንያት ካገኘሁት ፍቅር ጋር እጅግ ተትረፍርፎልኛል” ብሏል። (1ጢሞ 1:13, 14፤ 1ቆሮ 15:10) ጳውሎስ፣ አንዳንዶች እንዳደረጉት እንዲህ የመሰለውን ይገባናል የማንለውን ደግነት (ይሁዳ 4) አላቃለለም፤ ከዚህ ይልቅ በደስታና በአመስጋኝነት የተቀበለው ሲሆን ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ እንዲሁም ይገባናል የማንለውን ይህን ደግነት የተቀበሉ ደግሞ ‘ዓላማውን እንዳይስቱ’ መክሯቸዋል።—ሥራ 20:24፤ ገላ 2:21፤ 2ቆሮ 6:1